• የውሃ መቀነስ ሀገሪቱ ሀይልን በመሸጥ የምታገኘውን ገቢ አሳጥቷል
• የንፋስ ሀይል ማመንጫዎቹ ማምረት አላቆሙም
አዲስ አበባ፡- የኤሌክትሪክ ሀይል ስርጭቱ በፈረቃ በመደረጉ በእጃችን ያለውን አነስተኛ የግድቦች የውሀ መጠን ክፉኛ መቀነስን አስቀርቶ ሀይልን ሙሉ በሙሉ ከማጣት ታድጓል ሲል የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። የንፋስ ሀይል ማመንጫዎቹ አሁንም በማምረት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬ ህይወት ወልደሀና በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስገነዘቡት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ግድቦች የያዙት የውሀ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የሀይል አጠቃቀማችንን በፈረቃ በማድረግ በግድቡ ውስጥ ያለውን የውሀ መጠን ከመጥፋት መታደግ ተችሏል።
ከሰኔ በኋላ የምንጠብቀው የውሀ መጠን እስኪመጣ ድረስ ያለውን ውሀ በአግባቡ የመጠቀም ሁኔታ በትኩረት እየሰራንበት ነው የሚሉት ዶክተር ፍሬህይወት ነገር ግን ‹‹ወደ ውጭ እየተሸጠ አገር ውስጥ ሀይል አጣን የሚለው አሉባልታ ካለው የግድቦች የውሀ መጠን ጋር ፍፁም የማይገናኝና ከእውነታው የራቀ ነው›› ብለዋል።
ሀይል ወደ ውጭ መሸጥን በሚመለከት አገሪቱ የምትፈልገውን ያህል ሀይል እየሸጠች አይደለም የሚሉት ዶክተሩ በዚህም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይልን በመሸጥ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ አጥታለች ብለዋል። በተፈጠረው ምክያትም ጎረቤት አገራት የሚፈልጉትን ያህል መጠን እየተሸጠላቸው ባለመሆኑ ሲሸጥላቸው የነበረው የሀይል መጠን የቀነሰበት ሁኔታ መኖሩን አስረድተዋል።
‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ከጎረቤቶቻችን ጋር ባደረግነው ስምምነት ወደ ውጭ የምንልከውንየሀይል መጠን ቀንሰናል። በመሆኑም ለአገራቱ እየተሸጠ ያለው ሀይል እንደሚፈልጉት አይደለም። በመሆኑም የግድቦቻችን የውሀ መጠን መቀነስ ለእኛ ብቻ ሳይሆን የጎረቤት አገራትንም የሀይል መጠን እንዲቀነስ አድርጓል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ እየተናፈሰ ያለው አሉባልታ ፍፁም መሰረተ ቢስ ነው፤›› ሲሉ ዶክተር ፍሬህይወት ወቅሰዋል።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ ከዚህ ቀደም ወደ ጂቡቲ እንዲላክ የሚፈለገው የሀይል መጠን ከ100 በላይ ቢሆንም ለአገሪቱ እየተሸጠላቸው ያለው የሀይል መጠን ከ50 በመቶ በታች ነው። የኤሌክትሪክ ሀይል ታገኝ የነበረው ሌላዋ አገር ሱዳን ብትሆንም በአሁኑ ወቅት በሌሎች ቴክኒካል ምክንያቶች የሀይል ሽያጩ ለጊዜው መቋረጡን አስታውቀዋል።
ሱዳኖቹ የሀይል ማሰራጫ የጥገና ስራ ላይ በመሆናቸው የኤሌክትሪክ ሀይሉን ለአገር ውስጥ ፍጆታ እየተጠቀምንበት እንጂ ወደ ውጭ እየተሸጠ አለመሆኑን በተጨባጭ መረዳት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በመሆኑም አሁን ባለው ሁኔታ በአጠቃላይ ወደ ውጭ የሚሸጠው የሀይል መጠን ይህን ያህል የተጋነነ ሆኖ ሊነገር አይችልም ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ አሁን ያለው የግድቦቻችን የውሀ መጠኝ ካለፈው የተለየ አይደለም። በአንዳንድ አካባቢዎች የሚዘንበው ዝናብ ግድቦቹ ላይ ሊኖር የሚገባው የውሀ መጠን ሊያካክስ አልቻለም፤ በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት በነበሩ ወራት ግድቦቹ መያዝ የሚገባቸውን የውሀ መጠን ባለመያዛቸው የኤሌክትሪክ ሀይል ስርጭቱን በፈረቃ ለማድረግ አስገዳጅ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊረዳ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የንፋስ ሀይል ማመንጫዎቻችን ሀይል ማምረት አላቋረጡም የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው ማምረት አቁመዋል የሚለው አስተያየት ስህተት መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ዶክተር ፍሬህይወት ማብራሪያ የንፋስ ሀይል ሁልጊዜ በስፋት የሚገኝ ሀይል አይደለም ሲሉ ሶስት ምክንያቶችን አስቀምጠው ነው። አንደኛ ንፋስ ከሌለ ሊቆም ይችላል፤ ሁለተኛ በብልሽት ምክንያትም ማመንጫዎቹ ሊቆሙ ይችላሉ፤ ሶስተኛ የሀይል ማመንጫው ከማሰራጫ መስመሮች ጋር የተያያዘ በመሆኑ ማሰራጫዎቹ በሚገናኙበት ወቅት በቂ ወይም ተመጣጣኝ ሀይል ከሌለ ማመንጫዎቹን ለማቆም የምንገደድበት የራሱ ምክንያት አለ ሲሉ አብራርተዋል።
‹‹የንፋስ ሀይል ማመንጫዎቻችን ቆመዋል ተብሎ የሚነገርለቸው አይደሉም። የማምረት ሂደቱ የሚዋዥቅበት ባህሪያቸው ደግሞ አሁን የመጣ ሳይሆን ከጅምሩም የነበረ ነው። በመሆኑም የንፋስ ሀይል ማመንጫ ሊስተጓጎል የሚችልባቸው የራሱ ባህሪ በመኖሩ ሀይል ማመንጨት አቁመዋል ብሎ መደምደም አይቻልም፤›› ሲሉም አስረድተዋል።
ከንፋስ ሀይል የሚገኘው ሀይል 324 ሜጋ ዋት ነው፤ ይህም ከሶስት ማመንጫዎች የሚገኝ መሆኑን አስታውሰው ነገር ግን እንደ ንፋሱ መጠን በየጊዜው እየተፈራረቀ እስከ 200 ወይም 150 ዝቅ ብሎ ሊመረት ይችላል።
አሸጎዳ የሀይል ማመንጫ በአንድ ወቅት ብልሽት እና ከኮንትራክተሩ ከጥገና ጋር ተያይዞ ለተወሰነ ጊዜ ማመንጨት አቁሞ ነበር፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወደ ስራ መግባቱን ዶክተሩ ገልፀዋል። የአዳማውን ጨምሮ በማመንጨት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ሀብታሙ ስጦታው