መንግሥት በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 መሰረት ስድስተኛውን ዙር ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ነው። ለዚህም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል መሰራት ያለባቸውን ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ ሲሆን በአንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን ዘንድ በሀገሪቷ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ በመነጨ ይካሄድ አይካሄድ በሚሉ ሁለት የተለያዩ ሃሳቦች ቢሟገቱም ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅመው የትኛው ነው?
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር ፈረደ እንደሚሉት ጉዳዩ ምርጫ ማካሄድና የማራዘም ጉዳይ አይደለም። በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር እንዲሰድ እና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ስትኖር በመሆኑ ሀገራዊ መተማመኑ ሊቀድም ይገባል ይላሉ።
‹‹አሁን ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በላይ የሆነ ችግር እየታየ ነው። ክልሎች የራሳቸውን መንግሥት ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ፤ ሀገሪቱን የሚመራውም የራሱን ሪፐብሊክ የመመስረት አዝማሚያ እያሳየ ነው። አክራሪ የሆነ ብሄርተኝነት እየተፈጠረ፤ ምርጫ ማካሄድ ወይም ማራዘም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። መፍትሄው የሽግግር ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ በቅድመ ምርጫው መሰራት ያለባቸውን ነገሮች ለመፍታት እና አቅጣጫ ማስያዝ ይበጃል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ መኮንን ፍሰሐ የተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር ሀሳብን ይቃወማሉ። ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል አቋማቸውም የሚመጨው ከህገ መንግስቱ በመነሳት ነው። ምርጫ ማካሄድና አለማካሄድ በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 ላይ በግልጽ ድንጋጌ በመቀመጡ የማማረጥ ጉዳይ መሆን የለበትም ይላሉ አቶ መኮንን።
‹‹የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከአምስት አመት በኋላ የስልጣን ዘመናቸው ያበቃል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሌለ መንግሥትም አይኖርም፤ የስልጣን ቆይታውም ያበቃል። የክልል መንግሥታትም በተመሳሳይ ከአምስት አመታት በላይ ህጋዊ ስልጣን አይኖራቸውም። ምርጫው በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ካልተካሄደ ይሄ ሁሉ ይፈርሳል።›› ሲሉ ህገመንግስታዊ አመክንዮ በማቅረብ ይከራከራሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ቃል መግባታቸውን አስታውሰው ሀገሪቷ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የተገባውን ቃል ለመፈጸም አያስችልም፤ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫን መጠበቅ የዋህነት ነው የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ጽንፈኛ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸው፣የምርጫ ህጉ በትክክል አለመቀመጡ፣ የምርጫ ቦርዱ እስከታች አለመዋቀሩ፣የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት የሚያደርሱበት ሁኔታ ለምርጫ አለመካሄድ ገፊ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ በማሳያ ይጠቅሳሉ።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ፍልስፍና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አስምሬ፣ መንግሥት ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጁነቱን ሲገልጽ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ፈትሿል የሚል እምነት የላቸውም፤ መንግስት በፖለቲካ፣ በብሄርና በተለያየ ቡድን በተደራጁ አካላት ጫና ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጥ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ምርጫ ይካሄድ የሚሉ አካላት አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚሞክሩ ናቸው ሲሉ ይበይናሉ። በመሆኑም ምርጫው ቢካሄድ አንድን ፓርቲ ወይንም ቡድን የሚጠቅም ካልሆነ በስተቀር ሀገራዊ ፋይዳ የለውም ሲሉ ሁኔታው ምርጫ ለማካሄድ ምቹ አይደለም በማለት ነው።
‹‹በአገሪቱ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄዳል የሚል እምነት የለኝም። በሀገሪቷ አስተማማኝ የሆነ ሰላም አልተረጋገጠም። በብሄር፣በፖለቲካና በተለያዩ መንስኤዎች ግጭቶች እና አለመረጋጋት የተንሰራፋባት እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የተፈናቀሉባት ሀገር ሆናለች። እንዲህ ባለ ሁኔታ ምርጫ ማካሄዱ ደግሞ የተፈናቀሉ ዜጎችን መብት መጋፋት ይሆናል። ቅድሚያ ዜጎች ተረጋግተው መኖር መቻላቸው መረጋገጥ አለበት፤›› ሲሉ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
በእርግጥ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ሀገሪቷ ውስጥ መረጋጋት መኖር አለበት የሚለው ስጋት ተገቢ ነው። ግን ደግሞ በሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋት የሌለው በሁሉም የሀገሪቷ ክልሎች ነው ወይ? ምርጫንስ ለስንት አመት ነው ማራዘም የሚቻለው ብሎ ቁርጥ ያለ መልስ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ሲሉ የህግ መምህሩ ይጠይቃሉ።
ክልሎች ምርጫ ማካሄድ አለመቻላቸውን ለምክር ቤት ማቅረባቸው፣ ምርጫን ማራዘም የሰላምና ያለመረጋጋት ችግር ወይንስ የዝግጅት ችግር ነው? እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ምርጫው መካሄድ የለበትም ከማለት በፊት ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ባይ ናቸው አቶ መኮንን።
ይልቁንም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ህጋዊ ካልሆነና ተቀባይነት ከሌለው የሚፈራው ግርግርና ስጋት ይብሳል የሚሉት መምህሩ መንግሥት ስልጣን ላይ ሆኖ ማረጋገጥ ያልቻለውን ሰላም የስልጣን ዘመኑ ሲያልቅ የሚያረጋግጠው ሰላም እንደማይኖር ይገልጻሉ።
በቅድመ ምርጫ ያልተሰሩ ስራዎች ለብጥብጥና ለአላስፈላጊ ግጭት ሊዳርጉ ይችላሉ ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፤ የብዙ አፍሪካ ሀገሮች ተሞክሮም ይህንኑ ስለሚያሳይ ምርጫ ሁለተኛ ጉዳይ መሆን አለበት፤ ህግ፣ሥርአት፣ደህንነትና ሰላም ቅድሚያ የሚሰጣቸው የመንግሥት ተግባራት ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የሀገሪቷ ትልቁ ፈተና የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
‹‹ኢትዮጵያ የውስጥ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ሀገር ናት ለማለት የማያስደፍሩ ሁኔታዎች አሉ፤ የመንግሥትን ስልጣንና ኃላፊነት የሚጋፉ የተለያዩ ቡድኖች በሀገሪቱ ውስጥ ተፈጥረዋል፤ በመሆኑም ይህ ሳይረጋገጥ ምርጫ ቢካሄድ የሚፈጠረውን ነገር መገመት አያድግትም›› ሲሉ አመልክተዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ የመንግሥት ተ ግባር ህግን ማስከበርና ሰላምና ደህንነት በሀገሪቷ ውስጥ እንዲረጋገጥና የዜጎችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ሆኖ ነገር ግን ይህ እየሆነ ባለመሆኑ ከዴሞክራሲ አኳያም ቢሆን ምርጫ ማካሄዱ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ይሆናሉ በማለት ያለፉት የምርጫ ተሞክሮዎች ተአማኒነት የጎደላቸው በመሆኑ ቀጣዩን ምርጫ መካሄዱን ይቃወማሉ።
‹‹ለዜጎች ደህንነትና ለሀገር ሰላም ሲባል ምርጫው አለመካሄዱ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል። ህጋዊ በሆነ አግባብ ማራዘሙ ይበጃል። ህገመንግሥቱም ላይ ነጻና ፍትሐዊ ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ ይካሄድ ሲባል ህጋዊ በሆነ መንገድ ምርጫውን ማራዘምን አይከለክልም። ምርጫው መራዘሙ የሚያስከትለው ነገር የለም። መንግሥት በህጋዊ መንገድ ያራዘመውን ምርጫ በህግ ማስከበር አለበት›› የሚለው የረዳት ፕሮፌሰሩ አቋም ነው።
አቶ መኮንን የምርጫ ፍኖተ ካርታ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ይቃወማሉ። ምርጫ በማራዘም ሰበብ ሌላ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ወይም ደግሞ ከህገመንግሥት ውጭ በሆነ መልክ ለመንቀሳቀስ እድል እንዳይፈጠር ስጋት አለኝ ሲሉ የሚገልፁት የህግ መምህሩ፤ ምርጫውን ማራዘም ህገ መንግስቱ አይፈቅድም፤ ቢራዘምም ተግባሩ ኢ-ህገመንግሥታዊ እንደሆነ እና ምርጫን ለማራዘም ደግሞ ህገመንግሥት የማይሻሻል ስራ ስለሚጠይቅ ከእነችግሮቹም ቢሆን ምርጫውን ማካሄድ ግድ ነው የሚል ፅኑ አቋም አላቸው፤ አቶ መኮንን።
ከምርጫ በፊት ሰላም ይቅደም ከሚሉት ወገኖች መካከል እንደሆኑ የሚናገሩት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ከማል አብዱራሂም መንግሥት ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ምንን መሰረት አድርጎ እንደሆነ ለህዝብ ማብራራት ወይም ግልጽ ማድረግ ይኖርበታል።
ህዝቡ ነጻ ሆኖ የሚፈልገውን ለመምረጥ ደህንነቱና ሰላሙ መረጋገጡን መንግሥት ማሳወቅ አለበት። ከፍተኛው ሚና የመንግሥት ነው። ሆኖም ግን መፈናቀል፣ በህዝቦች መካከል መቃቃር፣ በህዝብና በመንግሥት መካከል አለመ ተማመን ባለበት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መብዛት፣ በገዥው ፓርቲ መካከል ያለው አለመግባባት፣ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል የሚያስብሉ አለመሆና ቸውን በአፅንኦት ተናግረዋል።
‹ህዝብ እንደ ህዝብ ችግር የለበትም› የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሰላም ሳይኖር ምርጫ ማካሄዱ ያለውን ፋይዳ፣ባይካሄድ ሊያስከትል የሚችለውን አንድምታ ከምሁራን እና በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። ህዝብ ያመነበት ምርጫ ነው ተቀባይነት ያለው። የአንድን ሀገር ደህንነትና ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑም መዘንጋት እንደሌለበትና አንድ በሚያደርጉና ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎሉ ጉዳዮች ላይ መስራት አለበት ሲሉ መክረዋል።
ምርጫው ቢካሄድ ሊከሰት ይችላል ያሉትን ስጋት አስቀምጠዋል፤ የሀገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ ሳይፈተሽ መንግሥት የያዘውን ምራጫ የማካሄድ አቋም ከቀጠለበት ህዝብ ውጤቱ ላይ ተአማኒነት አይኖረውም። ጥያቄ ከማስከተሉ በተጨማሪ ያልተፈለጉ ሁከትና ግርግሮች ሊከሰት ይችላል ብለዋል። በመሆኑም አምባገነናዊ ሥርዓት እንዲፈጠርም መንገድ ይጠርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ምርጫው ይካሄድ የሚሉት ምሁራን በበኩላ ቸው ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ምርጫው የማይካሄድ ከሆነ አሁን እንደስጋት እየተነሳ ያለው ግርግርና ሁከት እንዲሁም የሰላም ደህንነት የባሰ ይሆናል። አሁን ያለው መንግሥት የስልጣን ዘመኑን ስለሚጨርስ መንግሥት የለም ወደሚል አካሄድ ሊገባም ይችላል። በዚህም ሳቢያ መንግሥት ወደ ኃይል እርምጃ ሊገባ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
ለምለም መንግሥቱ