“እንዲህ አይነት በደል ስለመፈጸሙ መረጃው የለኝም”
– የወረዳው አስተዳደር
ሎካ አባያ፡- ለግብርና ግብዓቶች፣ ለትምህርት ቤትና ፖሊስ ጣቢያ ግንባታ በሚል ገንዘብ ብናዋጣም ለተባለው ዓላማ ሳይውል ከሶስት አመት በላይ ሆኖታል፤ ይህን አቤቱታ ይዘን ክልል ፀረ ሙስና ድረስ ብንሄድም ምላሽ አላገኘንም ሲሉ በሲዳማ ዞን የሎካ አባያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ። የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ አርሶ አደሮቹ ስላቀረቡት ቅሬታ መረጃው የለኝም ብሏል።
በዞኑ በሎካ አባያ ወረዳ የኩታዮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ማቶ ሀንዲሶ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በ2008 ዓ.ም ለትምህርት ቤትና ለፖሊስ ጣቢያ ግንባታ በሚል በየወሩ 40 ብር ከፍለዋል። በ2010 ዓ.ም የአደንጓሬ ዘርና ማዳበሪያ ይመጣላችኋል በሚልም 240 ብር ከፍለዋል።
ለተለያዩ መሰረተ ልማቶችና ለግብዓት በሚልም በሶስት ዓመት ውስጥ 12 ሺህ 420 ብር እንዳዋጡ ይናገራሉ። ነገር ግን ይሰራል የተባለው ትምህርት ቤትም ሆነ ፖሊስ ጣቢያ የውሀ ሽታ ሆኗል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ይቀርባል በተባለው ማዳበሪያ ምትክ 125 ግራም እበትና የፍየል ፍግ ውሰዱ መባላቸውን ተናግረዋል።
የቀድሞ ሰራዊት አባልና የጦር አካል ጉዳተኛ አቶ ማቶ፤ በየጊዜው ለተለያዩ ልማቶችና ግብዓቶች በሚል ሰበብ በሚወሰድ ገንዘብ ምክንያት ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እንደተቸገሩ ገልፀው፤ በዚህም ሳቢያ ልጆቻቸውን በአግባቡ ማስተማር አልቻሉም። ካላቸው አነስተኛ ገቢ ቀንሰው ለልማት ቢሰጡም ልማቱ እውን ሆኖ አለማየታቸው እንዳሳዘናቸውም ነግረውናል።
እንደ አቶ ማቶ ማብራሪያ ለተቋማት ግንባታና ለግብዓት በሚል ከሳቸው ብቻ ሳይሆን በቀበሌው ከሚገኙ ከ254 አርሶ አደሮች በተመሳሳይ መልኩ ብር ተሰብስቧል። ከእነዚህ አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ለወረዳውና ለዞን አስተዳደር እንዲሁም ለክልል አቤቱታ ቢያቀርቡም እስካሁን መፍትሄ አልተሰም ብለዋል። ጥያቄ በማቅረባቸው ከአንዳንድ አመራሮች የተለያዩ ማስፈራሪያዎች ደርሶባቸዋል።
በተመሳሳይ ወረዳ የኩታዮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙንጃ ሙጥሳ የ4 ልጆች አባት እንደሆኑና አነስተኛ ገቢ እንደሚያገኙ አስረድተው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለትምህርት ቤት፣ ለፖሊስ ጣቢያና ለግብዓት በሚል ያለፍላጎታቸው በተለያዩ መንገዶች ብር ቢያዋጡም ገንዘቡ ለተባለው ዓላማ ባለመዋሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
እንደ አቶ ሙንጃ ማብራሪያ፤ ተቋማት መገንባት ያለባቸው በመንግስት ሆኖ እያለ ከአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ለተቋማት ግንባታ በሚል ሰበብ ገንዘብ መሰብሰቡ ተገቢ አይደለም። ከአቅመ ደካማ አርሶ አደሮች ብር ተወስዶባቸው ተቋማቱም ሳይገነቡ፤ ግብዓትም ሳይቀርብ መቅረቱ ደግሞ በደላቸውን ድርብ እንዳደረገው ይናገራሉ።
የወረዳው አስተዳዳሪ ከሆኑ አራት ወራቸው እንደሆነ የተናገሩት አቶ ደረሰ ገብቻ፤ እሳቸው ወደ አመራር ከመጡ ወዲህ ከአርሶ አደሮች ፈቃድ ውጪ ለግብዓትም ሆነ ለተቋማት ግንባታ ብር ተወስዶብን ግብዓት አልቀረበም ወይም ግንባታው አልተከናወነም በሚል ለወረዳው የቀረበ ቅሬታ የለም ብለዋል።
ለቅድመ ትምህርት ቤት ግንባታ ከአርሶ አደሮች በተለያዩ መንገዶች ገንዘብ እንዲሰበሰብ እንደሚደረግ የተናገሩት አቶ ደረሰ፤ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለማቅረብም እንዲሁ ከአርሶ አደሮች ገንዘብ እንደሚወሰድ አንስተዋል። ለተጠቀሙበት ማዳበሪያ ክፍያ መፈጸም ሳይችሉ ሲቀሩም በተመሳሳይ መልኩ በየወሩ በተለያዩ ዘዴዎች ገንዘብ እንዲቆረጥ እንደሚደረግ አንስተዋል። ይህም የሚደረገው ግን ከአርሶ አደሮቹ ጋር በመነጋገር በአርሶ አደሮች በጎ ፈቃድ ላይ በመመርኮዝ ነው ብለዋል።
አቶ ደረሰ እንደሚሉት አርሶ አደሮቹ ስልደረሰባቸው በደል ለአዲስ ዘመን ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ ሊያጣሩ ቢሞክሩም ከአርሶ አደሮች ብር ተወስዶ ያልተገነባ መሰረተ ልማትም ሆነ ያልቀረበ ግብዓት ስለመኖሩ መረጃ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል። የተፈጸሙ በደሎች ካሉ የማጣራት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል። ወደ ፊት በሚደረገው የማጣራት ስራ መሰል በደሎች ስለመፈጸሙ መረጃዎች የሚገኙ ከሆነ ድርጊቱን በፈፀሙት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የዞኑን አስተዳዳሪ ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2011
መላኩ ኤሮሴ