ስፖርት ለጤንነት፤ ደግሞ ለኢኮኖሚም ዋልታ ስለመሆኑ ዓለም ከተረዳው ውሎ አድሯል። በቱሪዝም ላይ አይኑን ለጣለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ የስፖርቱን ዘርፍ በመጠቀም ተፈጥሮአዊ የቱሪስት መስህቦች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚደረጉ ውድድሮች ያላቸው ስፖርታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በእጅጉ ከፍ ያለ ነው። ከዚህም ባለፈ ለተወዳዳሪዎች አመቺና ተመራጭ የውድድር ስፍራን በማዘጋጀት በሁሉም ረገድ ስኬታማ መሆን ይቻላል። ይህን መነሻ በማድረግም ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ በወንጪ ሀይቅ ዙሪያ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የብስክሌት አትሌቲክስ ውድድር ተካሂዷል፡፡ ውድድሩ በወንጪ እንዲካሄድ የታሰበበት ትልቁ ዓላማም በሀይቁና በዙሪያው እየተሰራ ያለውን ግዙፍ የኢኮቱሪዝምና የልማት ፕሮጀክት መሠረት በማድረግ ነው፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሲሆን፣ ከብስክሌት ውድድሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ፣ ከዚሁ ስፍራ ላይ የሩጫ ውድድር ማካሄዱም የሚታወስ ሲሆን፤ የብስክሌት ውድድሩም የዚሁ ዓላማ አንድ አካል ነው። እሁድ፣ ጥር 25/2016 ዓ∙ም ረፋድ ላይ በተጀመረው የብስክሌት ውድድር ከመላው ሀገሪቱ፣ ከሰባት ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ ብስክሌተኞችና 12 ክለቦች፤ በድምሩ 200 ያህል ተወዳዳሪዎች ተሳትፈውበታል። ውድድሩም በወንዶችና በሴቶች፤ በማውንቴንና በኮርስ በአራት የምድብ ዙሮች ተከፋፈሎ ተካሂዷል፡፡
በማውንቴን ወንዶች 24 ኪሎ ሜትር፤ ሴቶች 5 ኪሎ ሜትር እና በኮርስ ወንዶች 64 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በሴቶች 24 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የነበረ ሲሆን፤ መነሻና መዳረሻውም በዚያው የወንጪ ሀይቅ ዙሪያ ነበር፡፡ ከተራራማው ስፍራ አናት ትንቅንቅና ከፍተኛ ፉክክር በታየበት በዚህ የብስክሌት ውድድር፤ አዲስ የተመሰረተው የሸገር ስፖርት ክለብና የአዲስ አበባ ፖሊስ የበላይነቱን ይዘዋል። በማውንቴን ወንድና ሴት አሸናፊዎችም የወርቅ፣ የብርና የነሀስ ሜዳሊያም ወስደዋል። በኮርስ በሁለቱም ጾታዎች በአንደኝነት ላጠናቀቁ የ50ሺህ ብር የገንዘብ፤ የወርቅና የዋንጫ ሽልማት ሲቀበሉ፤ በተጨማሪም ብስክሌት ተበርክቶላቸዋል። 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው ላጠናቀቁ አሸናፊዎች ደግሞ፤ የብርና ነሀስ፤ እንዲሁም የ40 እና 30ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነዋል። አስደናቂ ፉክክር በተንጸባረቀበት የወንጪ ብስክሌት ውድድር፤ ነገ ሀገርን ወክለው በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች እንዳሉ ያሳየና ተስፋ ሰጪም ነበር፡፡ ሀገር አቀፍና የክልል ብስክሌት ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች እንዲሁም ባለ ድርሻ አካላትም ትኩረታቸውን በታዳጊ ወጣቶችና በፕሮጀክቶች ላይ አድርገው ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ጭምር በውድድሩ ላይ የታዩት አሸናፊዎችና ውጤቶቻቸው ጠቋሚ ነው።
ውድድሩ ወንጪ ላይ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የገለጹት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ሰቦቃ፣ የወንጪ 10 ኪሎ ሜትር ሩጫን ዓመታዊ የስፖርት ውድድር በማድረግ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አስታውቀዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የተደረገው ውድድር አንደኛ ዙር እንደመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ፤ የተሳታፊዎችንም ሆነ የውድድር ደረጃውን ከፍ በማድረግ ትልቅ የውድድር መድረክ ለማድረግም ታስቧል። ውድድሩ እንደ ስፖርት ካለው አላማ በተጨማሪ፤ በመልክአ ምድር በታደለችው ወንጪ እየተሰራ ያለውን የልማት ፕሮጀክት ለመደገፍና ለማስተዋወቅም ጭምር መሆኑም ተወስቷል።
ወንጪ በመልክአ ምድርም ሆነ ባላት የአየር ጸባይ ለስፖርቱ በተለይም ለአትሌቲክሱ በእጅጉ አመቺ ናት። ሀገራዊና ትልልቅ ውድድሮችን በስፍራው በማድረግ አንድም ለስፖርቱ፤ ሁለትም ለኢኮ ቱሪዝም፤ በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ ለመጣል የሚያስችል ነው፡፡ ይህን ጥምር ዓላማ ይዞ የተነሳው የወንጪ አትሌቲክስ ውድድር፤ ግቦቹን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን የመጀመሪያ ዙር ውድድር የተደረገውም በዚሁ እሳቤ መሆኑንም ቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የወንጪ የአትሌቲክስ ውድድሮች ስፖርቱን ከቱሪዝም እንዲሁም ከኢኮኖሚው ጋር አጣምረው የያዙና በሁሉም ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ እንደመሆናቸው፤ ከክልል እስከ ፌዴራል ያሉ የስፖርቱም ሆኑ ሌሎች ተቋማት በቀጥታ ሊሳተፍበት የግድ ነው። በክልሉ የተጀመረው ይህ ውድድር አለፍ ሲልም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሳይወሰን ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድሮች የሚካሄዱበትና የሚስተናገዱበት እንዲሆን ተደርጎ ይሰራል የሚለውም በውድድሩ ወቅት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲንጸባረቅ የነበረ ሀሳብ ነው፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም