አዲስ አበባ፡- ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሠራዊት በታላቁ የህዳሴ ግድቡ ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ፀረ ሠላም ሙከራ ከመከላከል በተጓዳኝ ላለፉት ሰባት ዓመታት በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት ከአንድ ቢሊየን 119 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማድረጉ ተገለፀ።
መከላከያ ሠራዊት የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሠላም ዋንጫን ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት ባስረከበበት ሥነ ሥርዓት ላይ የመከላከያ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ሙሉ ሞገስ እንዳስታወቁት፤ ሠራዊቱ የሀገሩን ሉአላዊነት ከማስከበር ባሻገር ከድህነት ለማውጣት በሚያደረገው የልማት እንቅስቃሴ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ ነው።
በተለይ የአገሪቱ አረንጋዴ ልማት መርሐ ግብር እንዲሳካ በሚደረገው ጥረት የታላቁ የህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ለመከላከል በየዓመቱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከልና በመንከባካብ የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ኮሎኔል ሙሉ አስታውቀዋል።
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶም እስከ ባለፈው ዓመት ከአለማቋርጥ መላው ሠራዊትና በተቋሙ የሚሠሩ ሲቪል ሠራተኞች በየዓመቱ ቦንድ በመግዛት ከአንድ ቢሊየን 119 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ በማድረግ የዜጎነት ግዴታቸውን መወጣታቸውን ገልፀዋል።
ኮሎኔል ሙሉ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራትም የ222 ሚሊየን 494 ሺ ብር የቦንድ ሽያጭ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ ከቶምቦላ ሎተሪ ግዥ አንድ ሚሊየን 350 ሺ እንዲሁም ከቲሸርት ሽያጭ ከአንድ ሚሊየን 91 ሺ ብር በላይ ገቢ ማድረጉን አብራርተዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ በሠላም ማስከበር የተሰማራው ሠራዊት በስጦታ 48 ሺ የሱዳን ፓውንድ ለግንባታው ሥራ ማበርከቱንና ቀደም ሲልም ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት 292 ሺ 870 ብር የቦንድ ሽያጭ መፈፀማቸውንም አስታውቀዋል።
ተቋሙ ባለፈው ዓመት በተከበረው የሠ ራዊት ቀን በዓል ጋር ተያይዞ የግድቡን የሠላም ዋንጫ መረከቡን ያስታወሱት ኮሎኔል ሙሉ፤ ዋንጫውንም በግዳጅ ምክንያት ከተወሰኑ የሠ ራዊቱ ክፍሎች በስተቀር በሁሉም ሠራዊቱ በሰፈረባቸው ቀጠናዎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል። በዚህ ሂደት በተካሄደ የቦንድ ግዥና ስጦታም ከ197 ሚሊየን 700 ሺ ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ በማሰባሰብ ገቢ ማድረግ ተችሏልም» ብለዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው፤ «የግድቡ መሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ የወንጀል መከላከያ ሃይላችን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በአካባቢው ያለውን ከባድ የአየር ፀባይ ተቋቁመው፤ ግድቡ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይርስበት ሌት ተቀን ጥበቃ በማድረግ ላይ ይገኛሉ» ብለዋል።
ከደህንነት ጥበቃው በተጓዳኝም የኮሚሽኑ መላው አባላት በሙሉ ፈቃደኝነት ከወር ደመወዛቸው ለተከታታይ ሰባት ዓመታት 248 ሚሊየን 468 ሺ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት በግድቡ ላይ ታሪካዊ የዜግነት አሻራቸውን ማሳረፍ መቻላቸውን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ የተረከበውን የሠላም ዋንጫም በሥሩ በሚገኙ የሥራ ክፍሎች በማዞር ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርገውን ማንኛውንም ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። «ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሠላም ምንጭ ነው» በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን የሠላም ዋንጫ ከመከላከያ ሚኒስቴር ሲረከብም በከፍተኛ ኩራት መሆኑን አስታውቀዋል።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ በበኩላቸው፤ የሠራዊቱ አባላት በታላቁ የህዳሴ ግድቡ ላይ የሚቃጣ ማንኛውም አይነት ኢ ሰላማዊ ሙከራ ከመከላከል በተጓዳኝ ካለማቋረጥ ከወር ደሞዙና ከዕለት ጉርሱ በመቆጠብ ለግድቡ ድጋፍ በማድረግ አገራዊ ተልዕኮውንና ህዝባዊ አደራውን በመወጣት ላይ መሆኑን መስከረዋል። የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የታላቁን የህዳሴ ግድብ የሠላም ዋንጫ ሲረከብም የሠላምና የልማት ሃይል የሆነ አጋርነቱን ይበልጥ የሚያጠናክርበት እንደሚሆን አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
ታምራት ተስፋዬ