የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ተስፋዬ ጥራዝ በአቢሲኒያ ጤና ጣቢያ በነበራቸው የሥራ ቆይታ በየዓመቱ በክረምቱ ወቅት ከሠራተኞች ጋር በመሆን በተከሏቸው የዛፍ ችግኞች ግቢው ለሠራተኞችና ለታካሚዎች ውብና ማራኪ እንዲሆን ማስቻላችውን ያስታውሳሉ።
ችግኞቹ እንዲተከሉ ጤና ጣቢያው፣ የወረዳው የከተማ ግብርና ባለሙያዎች አስተዋጽኦ የላቀ እንደነበር የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ፤ ችግኞቹ በጤና ጣቢያው ውስጥ በመተከላቸው ሠራተኞች በቅርብ እንዲንከባከቡ ማስቻሉን ይገልጻሉ። አቶ ተስፋዬ አሁን የጤና ጣቢያው ሠራተኛ ባይሆኑም ለግል ጉዳያቸው ወደስፍራው ሲሄዱ፤ የግቢውን ልምላሜና ውበት ይመለከታሉና በጣሙን ይደሰታሉ።
ከጤና ጣቢያ ከለቀቁ በኋላም አሁን በሚገኙበት የፌዴራል መስሪያ ቤት ከሠራተኞች ጋር በመሆን ቱሉ ዲምቱ አካባቢ የዛፍ ችግኞችን በተደጋጋሚ መትከላቸውን የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ፤ እንደከዚህ ቀደሙ ግን ችግኞቹን በቅርበት መከታታል አልቻሉም። ይህ በመሆኑም ይፅደቁ አይጽደቁ የሚያውቁት ነገር የለም።
ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያየዘ የደን መመናመን የሚያስከትለውን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ የዛፍ ችግኝ ተከላን ዋና ሥራዋ አድርጋ ከያዘች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሚሊኒየም አስመልክቶ ሁለት ችግኝ ለአንድ ሰው በሚል አንድ ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል አገር አቀፍ የተከላ መርሐ ግብር የተጀመረ ሲሆን፤ ከዚያ ወዲህ በየዓመቱ በክረምት ወራት የከተማውም የገጠሩም ህዝብ በችግኝ ተከላ እንደሚሳታፍ ይታወቃል።
በዚህ ዓመት መጪ ክረምትም እንዲሁ አራት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከልና አንድ ሰው 40 ችግኞችን በአቅራቢያው እንዲተክል የታቀደ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የችግኝ ተከላውን ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ በይፋ አስጀምረውታል።
ይህን የደን ተክላ መርሐ ግብር በአካባቢ፣ በደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሬድ ፕላስ አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ “የደን ልማት ጉዳይ በመሪ ደረጃ መነሳቱን ትልቅ ዕርምጃ” ሲሉ አድናቆት ይሰጡታል።
ከዚህ ቀደም ችግኝ ከተተከለ በኋላ በፌዴራል ደረጃ ባለቤት ቢኖረውም ክልል ፣ ወረዳና ቀበሌ አካባቢ የሚንከባከበው ባለቤት እንደሌለውና በተለይ ወረዳ ላይ በቂና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በጀት፣ ተሽከረካሪ አለመኖሩ ይህም የሚፈለገው ለውጥ እንዳይመጣ ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ።
በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የደን ልማትን እንደልብ ትርታ መመልከት እንደሚገባ አፅእኖት የሚሰጡት ዶክተር ይተብቱ፣ “በደን ሽፋን ውድመት እየተጎዳን ነው፤ ደን ዝናባችን ነው፤ ኢትዮጵያ ያለችበት መልክዓ ምድር ደን እንድታለማ ያስገድዳታል” ሲሉ ያስገነዝባሉ።
መሪዎቻችን ሁሉ ይህንን አስበውት አያውቁም፤ እንደኬንያ፣ ሱዳን ማረስ ወይም ከብት ማርባት ነው የሚታየን፤ ሀገራችን በደን ብትዋብ ከውስጧ ብዙ ነገር ይወለዳል፤ ለኃይል ማመንጫ፣ ለመጠጥ፣ ለመስኖ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለጤና እንዲሁም በዙሪያችን ላሉ አረብ ሀገሮች ልንሸጠው የምንችል ውሃ ምንጩ ደን ነው” ሲሉም ያብራራሉ፡፡
“ሀገሪቱ 15 ነጥብ አምስት በመቶ የደን ሽፋን አላት፤ ይህን እንደሀገር መጠበቅ ይገባል። እንደሌሎች ሀገሮችም በመትከል በመንከባከብ የደን ሽፋኑን ማስፋት ያስፈልጋል” የሚሉት ዶክተሩ፤ ቁጥሩን በሚመለከትም “እኔ የሚተከለው የዛፍ ችግኝ ብዛት ሳይሆን በመሪ ደረጃ ለደን ልማት የተሰጠውን ትኩረት ነው የምመለከተው፤ አራት ቢሊዮን የሚለው አዕምሯችንን ሊይዘን አይገባም፤ መሪ የያዘው ሥራ ሁሉንም ተቋማት ኅብረተሰቡንም አነቃንቆ ውጤታማ ሊሆን ይችላል፤ ዋናው ነገር በጋራ መንቀሳቀስ ነው ይላሉ። ተግባሩ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከቀጠለና የተተከለውን መንከባከብ ከተቻለም የደን ልማት እውን እንደሚሆን ጥርጥር የላቸውም።
ከፍተኛ የደን ተመራማሪው ዶክተር ውባለም ታደሰ “የሳሳው የሀገራችን ደን ወደተሻለ ሁኔታ እንዲመጣ በሀገር መሪ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት የደን ልማት ዘመቻ መታቀዱ ትልቅ ነገር ነው” ሲሉ የዶክተር ይተብቱን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
በተለይም የደን ዘርፍ ባለሙያዎች ይህን ያህል የዛፍ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱ አስድስቶናል የሚሉት ዶክተር ውባለም፣ የተፈላው ችግኝ መቼና የት እንደሚተከል፤ በማኅበረሰብ ንቅናቄና በመንግሥት ተቋማት ምን ያህል ችግኞች ይተከላሉ የሚሉት በዝርዝር ቢቀመጡ የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት ዓይነተኛ ፋይዳ እንዳላቸውም ሳይጠቁሙ አላለፉም።
“በሀገራችን ላለፉት 40 ዓመታት የዛፍ ችግኝ በአግባቡ እየተተከለና የደኑ ዘርፍ ትኩረት እያገኘ አይደለም” የሚሉት ዶክተር ውብዓለም፤ በዚህም ምክንያት የሀገሪቱ የደን ሀብት በእጅጉ እየተራቆተ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ሀገሪቱ ጣውላና የጣውላ ውጤቶችን ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ እያወጣች ከውጭ እንደምትገዛ የሚያመላክቱት ዶክተሩ፤ የዛፍ ችግኞች እየተተተከሉ ባለመሆናቸው ተራራዎች እየተራቆቱ፤ ግድቦችም በደለል እየተሞሉና መብራትም በፈረቃ እየሆነ ስለመምጣቱ ይናገራሉ።
ባሳላፍነው ዓመት አራት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ችግኝ ተክለናል ተብሎ ሪፖርት ተደርጓል። ይሁንና፤ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዛፍ ችግኞች የምንተክል ከሆነ ዘንድሮ መትከያ ቦታ አናገኝም ነበር፤ የሚሉት ዶክተሩ፤ መትከል ብቻውን ፋይዳ ቢስ መሆኑን ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የተተከሉ የዛፍ ችግኞች ምስክር ናቸው ይላሉ።
ዛፎች በዘመቻ ይተከላሉ፤ በደን ልማቱ ላይ ግን ተጠያቂ ተቋም የለም፤ በማለት የዶክተር ይተብቱን ሃሳብ ያጠናከሩት የደን ተመራማሪው፤ ከመሰል ችግሮች ለመሻገርም የደን ልማቱ ስትራቴጂክ እቅድ ወጥቶለት ሊሠራበት እንደሚባ ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በደን በኩል የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከተቋቋመ ሐምሌ ሲመጣ ስድስት ዓመት ቢያስቆጥርም፤ በክልል ግን ቢሮ እንደሌለውና በፌዴራል ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ መቅረቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ አፅእኖት ሰጥተውታል።
ከደን ልማቱ የዘመቻ ሥራዎች ስህተት መማር አለብን የሚሉት ዶክተር ውብዓለም፣ ተከላውን ከጨረስን በኋላ የዛሬ ዓመት ምን እንተከል? የት እንትከል? በማለት ቦታውን ለተፋሰስ ልማት ለጣውላና ለጣውላ ውጤቶች፣ ለከብት መኖ ወዘተ. አስቀድሞ እየለዩ ስልታዊ የችግኝ ተከላ ማድረግ እንደሚገባውም ነው ያስገነዘቡት፤ “ከተሞቻችን ዛፍ አልባ እየሆኑ ነው፤ አዲስ አበባን ጨምሮ ለሕንፃውና ለአስፋልቱ ነው ትኩረት እየተሰጠ ያለው” ያሉት ዶክተር ውባለም፣ ይሄም ጉዳም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ መርህ ግብር በአዳማ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ አራት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል አንድ ሰው አርባ ችግኞችን መትከል እንደሚጠበቅበትና እርሳቸውም በዚህ የችግኝ ተከላ በጽህፈት ቤታቸው ግቢ ውስጥ አንድ ሺህ ችግኞችን እንደሚተክሉ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የችግኝ ተከላው ሁሉን አቀፍ ሊሆን እንደሚገባው፤ እንደቀድሞው ሩቅ ተሄዶ የሚከናወን እንዳልሆነና በመኖሪያና በሥራ አካባቢዎች እንደሚካሄድ፤ ይህም ችግኞቹን በቅርበት ለመንከባከብና የታለመላቸውን ግብ እንዲያሳኩ ያስችላል ሲሉም መናገራቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ