አዲስ አበባ፡- ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በሁሉም ክልሎች በ704 ሚሊዮን 832 ሺህ 244 ብር ወጪ 21 ትምህርት ቤቶች እያስገነቡ እንደሚገኙ ተገለጸ።
ከቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ወደሥራ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል ከተማሪዎች ምገባ በተጨማሪ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች አንደኛ ደረጃ ላይ የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ለማስቀጠል እንዲቻል በመላው አገሪቱ በ304 ሚሊዮን 832 ሺህ 244 ብር 20 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንና በ400 ሚሊዮን ብር ወጪ ደግሞ አንድ ማየት ለተሳናቸው ተማሪዎች የአዳሪ ትምህረት ቤት እያስገነቡ ይገኛል።
አራቱን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመጪው ዓመት ትምህርት ለማስጀመር፤ 16 ቱን ደግሞ በመጪው ዓመት አጋማሽ ለማጠናቀቅ ግንባታቸው እየተካሄደ ነው።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡት በሁሉም ክልሎች ሆኖ፤ በተለይም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ በኢኮኖሚ እና በቦታ ርቀት ተወስነው የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ለማዳረስ በሚቻልባቸው ቦታዎች ላይ መሆኑ ተመልክቷል።
ጸህፈት ቤቱ በተጨማሪም፤ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች የድጋፍና ክብካቤ ሥራዎችን መድረግ እንዲቻል በ12 ሚሊዮን ብር አንድ የሕፃናት ማሳደጊያ ሕንፃ ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛል። ከአዳዲስ ግንባታዎች ጎን ለጎንም የሰበታ መርሐ ዓይነ-ስውራን ትምህርት ቤት እድሳት በመከናወን ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።
የቁስቋም ሕፃናት ማሳደጊያ የተጀመረው በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ሲሆን፤ ግንባታውም ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ተገልጸል። በተመሳሳይ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገነባው FBM ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ የተጀመረ ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም ይጠናቀቃል ተብሏል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ከክልል ትምህርት ቢሮዎችና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ማለትም ፕሮጀክቱን ለማስፈፀም ከተወከሉ ድርጅቶች ጋር በመሆን እየተሠራ እንደሚገኝ የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ አስታውቋል። የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ ወጪ የሚሸፈነው የቀዳሚዊት እመቤት ጸህፈት ቤት ከለጋሽ አካላት ባገኘው ዕርዳታ ሲሆን፤ ለሁሉም የግንባታ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 716 ሚሊዮን 832 ሺህ 244 ብር ወጪ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
ጌትነት ምህረቴ