የዓለም የቤት ውስጥ ክብረወሰኖች፤ እንዲሁም ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብ ከሚታወቁ ውድድሮች መካከል የቦስተኑ ኒው ባላንስ ግራንድ ተጠቃሽ ነው::
በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው የቤት ውስጥ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ሩጫ ዘንድሮም በተለያዩ ርቀቶች ፈጣን ሰዓቶች የተመዘገቡበት ሆኖ ተጠናቋል:: በሜዳ ተግባራትና በመም ሩጫ ስመጥር አትሌቶች በተሰባሰቡበት በዚህ ውድድር ላይ አፍሪካውያን አትሌቶች ጠንካራ ተፎካካሪነታቸውን ያሳዩ ሲሆን፤ አስቀድሞ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ስኬታማ ሆነዋል::
የአዲሱን ውድድር ዘመን መጀመር ተከትሎ በዓመቱ መርሐ ግብር መሠረት ከሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አስቀድሞ በርካታ ፉክክሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ:: በሚቀጥለው ወር የሚደረገውን የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አስቀድሞ የቤት ውስጥ ቱር በተለያዩ ዓለማት መካሄዳቸውን ቀጥለዋል:: ጠንካራ ፉክክር በማካሄድ ከሚታወቁትና በየርቀቱ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ አትሌቶች ከሚመርጧቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ ቦስተን ሲሆን፤ አስቀድሞ እንደተገመተው ፈጣን ሰዓቶች የተመዘገቡበት አስደናቂ ፉክክር ተደርጓል:: እንደተለመደው ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በሮጡባቸው ርቀቶች ከአሸናፊነት ባለፈ የቦታውን ፈጣን ሰዓት ጭምር ማሻሻል ችለዋል:: ከእነዚህም መካከል አንዷ የመካከለኛና ረጅም ርቀት ኮከቧ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ናት::
በኦሊምፒክ፣ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በዳመንድ ሊግ እንዲሁም በቤት ውስጥ ውድድር አስደናቂ ድሎችን በማስመዝገብ የምትታወቀው አትሌቷ፤ የዘንድሮውን የውድድር ዓመትም በስኬት ጀምራለች:: በ1ሺህ 500 ሜትር ውድድር የተሳተፈችው ጉዳፍ በግሏ የተያዘውን የሩቁን ፈጣን ሰዓት ለማሻሻል የሮጠች ቢሆንም በውድድሩ የመጨረሻ ርቀት በጥቂት ሰከንዶች መዘግየቷ ያሰበችውን እንዳታሳካ አድርጓታል:: ሆኖም የገባችበት 3:58.11 የሆነ ሰዓት የቦስተን የቤት ውስጥ ውድድር “ፈጣን″ በሚል ተይዞላታል:: እአአ በ2021 ፈረንሳይ ሌቪን ላይ የሮጠችው ጉዳፍ በወቅቱ ያስመዘገበችው 3:53.09 የሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን መሆኑ ይታወቃል::
በፖርትላንድ እንዲሁም በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮናዎች የነሐስ እና የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌቷ፤ በቅርቡ ግላስኮ ላይ ሃገሯን በቀጥታ መወከል የምትችልበትን ውጤት ማስመዝገብም ጀምራለች:: ከሃገሯ ልጆች ጋር በመሆን የሮጠችው ጉዳፍ በዚህ ርቀት አብራት በመሮጥ የምትታወቀውን ብርቄ ኃየሎምን አስከትላ በመግባትም ነው ውድድሯን የደመደመችው:: ወጣቷ አትሌት ብርቄ 3:58.43 በሆነ ሰዓት የሮጠች ሲሆን፤ ይህም ሰዓት “ከ20 ዓመት በታች የ1ሺህ 500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ክብረወሰን″ በሚል ተመዝግቦላታል::
ሌላኛው የውድድሩ ተጠባቂና አጓጊ ርቀት የወንዶች 3ሺህ ሜትር ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ የቦስተን የቤት ውስጥ ውድድር ክብረወሰን በሆነ ሰዓት ፈጽሟል:: አስተማማኝ በሆነ አሯሯጥ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር የረገጠው ወጣቱ አትሌት ርቀቱን የሸፈነበት ሰዓትም 7:29.09 ሆኗል:: ይህ ሰዓት ለቦስተን ፈጣን ቢሆንም ባለፈው ዓመት ሌቪን ላይ በተደረገው የቤት ውስጥ ቱር የገባበት 7:23.81 ከሆነ ሰዓት ጥቂት መዘግየት የታየበት ነው::
የርቀቱ የቤት ውስጥ ክብረወሰን ባለቤት የሆነው ለሜቻ በተመሳሳይ ዓመት ከቤት 7:52.11 የሆነ ሰዓት በመሮጥ ሁለቱንም ክብረወሰኖች ከእጁ ማስገባቱ አይዘነጋም:: ከሁለት ዓመት በፊት ቤልግሬድ ላይ ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ በሆነችበት የቤት ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ያጠለቀ ሲሆን፤ በዓለም ሻምፒዮና የሦስት ጊዜ እንዲሁም በኦሊምፒክ አንድ ጊዜ የብር ሜዳሊያ ለሃገሩ ያስገኘ ድንቅ አትሌት ነው::
በ3ሺህ ሜትር ሴቶች በተደረገው ውድድር ደግሞ ከ3 እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ተከታትለው የገቡት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተቆጣጥረውታል:: በዓለም ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮና በተለያዩ ርቀቶች ሃገራቸውን ማስጠራት የቻሉት ወጣቶቹ አትሌቶች መልክናት ውዱ፣ መዲና ኢሳ፣ ሠናይት ጌታቸው እና አይናዲስ መብራቱ ደግሞ የተስፋ ሰጪው ውጤት ባለቤቶች ናቸው:: መልክናት የገባችበት 8:32.34 የሆነ ሰዓትም በርቀቱ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ፈጣን መሆኑም ታውቋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም