አዲስ አበባ፡- አንድነቱ፤ ሰላሙ፤ መከባበሩ እና መተባበሩ ዘላቂ እንዲሆን ሙስሊሙ ህብረተሰብ የድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። አንድ ሺህ 440 ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ስቴዲየም በድምቀት ተከበረ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ፤ የዘንድሮ ኢድ የተለዩ መርሀ ግብሮች የተከናወኑበት ነው፤ አንድነቱን፣ ሰላሙን፣ መከባበሩ እና መተባበሩ ዘላቂ እንዲሆን ሁሉም አማኝ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። በተግባር ሊታይ፣ ሃይማኖታዊ ሆኖ አገራዊ መልክ ሊይዝም ይገባል ብለዋል።
ኢድ ደስታ ማለት ነው፤ ያሉት ሀጂ ዑመር እድሪስ፤ የዘንድሮ ኢድ የሙስሊሙ አንድነት የተከናወነበት፣ ለሙስሊሙ ህብረተሰብና አገራዊ ሰላም የሰፈነበት ሆኖ በመከበሩ በደስታው ልንረካ ይገባናል ብለዋል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር
አብይ አህመድ የሰላምና የአንድት ኮሚቴ እንዲቋቋምና የተከበረ ኢድ እንዲከበር ላደረጉት አስተዋጽኦ ደስታችን ከፍ ያለ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢፍጣር መርሀ ግብር አዘጋጅተው ሙስሊሙን ማህበረሰብ መጋበዛቸውን በመጠቆምም፤ “ይህ አዲስ ዕድል ነው ልንጠቀምበት ይገባል” ብለዋል።
ለሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያን አማኞች አንድነት የጣሩ ታላቅ መሪ ናቸው በማለት ዶክተር አብይን አመስግነዋቸዋል። ወንድሞችና እህት ክርስቲያኖች የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጥሪ ተቀብለው የስግደት ቦታውን ማጽዳታቸው ዘንድሮ ብቻ የተከሰተ መሆኑን ሀጂ ዑመር እድሪስ አንስተዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ የኢድ በዓላት የሰላም፣ የመከባበር፣ የአንድነት፣ የልማት ጉዞዎች ነበሩ ሲሉ ጠቅሰዋል። ዛሬም ናቸው ከዚህ በተሻለ መልኩም ይቀጥላሉ ሲሉ ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል።
የዘንድሮ ሮመዳን የደመቀ እንዲሆን መስጂዶችን በማጽዳት፣ ስቴዲየምን በማስዋብ የበኩላቸውን ድርሻ ያበረከቱ የከተማውን ህብረተሰብም አመስግነዋል። አዲስ አበባ ከተማ እንደ ስሟ ውብ እንድትሆን ከተማዋን የማስዋብና የማፅዳት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት ቁሳቁስ የማቅረብ ትገበራውን የከተማው ሙስሊም ህብረተሰብ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።
ከተማዋ ንጹህ አየር እንድታገኝ ችግኝ መትከል ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በከተማው ለሚተከሉ ችግኞች ሙስሊሙ ህብረተሰብ የድርሻውን እንዲወጣ አደራ ብለዋል። በበዓሉ ሊታደሙ የቻሉት ማክበር ስላለባቸው እንዳልሆነ የጠቆሙት ኢንጂነር ታከለ፤ ወድደው፣ ፈቅደው፣ ባህላቸው መሆኑን አምነው መሆኑን ጠቁመዋል።
የሙስሊም ቤተሰብ በአገሩ በከተማው ተሰባስቦ ማክበር ሲገባው እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሮ ያሳለፈበትን ታሪክ ለመካስ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። አገራችሁ ነው፣ ከተማችሁ ነው በጋራ አገራችንንና ከተማችንን እናልማ ነው ያሉት። ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ ብለዋል፤ ኢንጂነር ታከለ።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ፕሬዚዳንት ሀጅ አብዱላዚዝ ወጉ፤ አገራዊ ለውጥ የመጣበት፣ በእስላማዊ ተቋም ለውጥ ሂደት ውስጥ በመሆን ህዝበ ሙስሊሙ ለዘመናት ሲመኛቸውና ሲናፍቃቸው የነበሩ ነገሮችን ያገኘበት፣ ጥያቄዎቹ የተመለሱበት፣ ወደ አንድነትና እርቅ የመጣበት፣ በመንግሥት በኩል ስለአንድነት ጎልቶ የተመከረበትና ለዜጎች ክብር የተሰጠበት ኢድ ሆኖ መከበሩንም ጠቅሰዋል።
የተፈናቀሉ ወገኖችን በማቋቋም፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና በመጠየቅ ኢድ ሊከበር እንደሚገባም ነው ሀጅ ብዱላዚዝ ያመለከቱት፤ በሙስሊሞች መካከል እርቅና አንድነት እንዲመጣ ዘጠኝ አባላት ያሉት የተቋማዊ ለውጥ ኮሚቴ በማቋቋም ጥረቱ እንዲሳካ መደረጉ የዘንድሮው ኢድ ልዩ ክስተት ነው ብለዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ካርታ ያልነበራቸው ከ10 በላይ መስጂዶች አዲስ ካርታ ተዘጋጅቶላቸው መረከባቸውንም አንስተዋል። የተዘጋጁ ሰባት አዳዲስ የመስገጃ ቦታዎችንም ለመረከብ ዝግጅት ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቶች መቀመጫ እንደመሆኗ፤ ሰላም፣ ልማት፣ ፅዳትና አጠቃላይ ሁኔታውን መጠበቅ ይገባል ብለዋል። ሙስሊሙ ህብረተሰብ በዶክተር አብይ የቀረበውን የችግኝ ተከላ ጥያቄ፣ የክረምት በጎ ተግባርና ሌሎች መሰል ተግባራትን ለመፈጸም ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሀመድ አብዶ፤ ዑለማዎችና የመስጂድ አመራሮች ሁሉንም ሙስሊም ህብረተሰብ አቃፊና አሳታፊ የሆነ አደረጃጀት ይተገበራል ብለዋል። አዲሱ አመራር ተቋሙን ህዝባዊ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል። መላው የሙስሊም ማህበረሰብ በዕምነቱ ጉዳይ ተሳታፊ የሚሆንበት አሠራር ይተገበራልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
ዘላለም ግዛው