በተለያዩ ዘመናት በዓለም እግር ኳስ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደሩ በርካታ አፍሪካውያን ኮከቦች ተፈጥረዋል። ጥቂት የማይባሉ አፍሪካውያን በተለይም በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ከሊግ ዋንጫዎች እስከ ቻምፒዮንስ ሊግ ድረስ በርካታ ክብሮችን ማሳካት ችለዋል። በክለቦቻቸው ስኬትም ቁልፍ ሚና ነበራቸው። እነዚህ ከዋክብት ከክለቦቻቸው ጋር ያላቸውን ስኬት ወደ ሀገራቸው ብሔራዊ ቡድን ተመልሰው በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ ድግስ በድል መድመቅ የዘወትር ምኞታቸው ነው። ነገር ግን የብቃታቸው ጥግ ላይ በነበሩበት ዘመን ከክለቦቻቸው ጋር ያጣጣሙትን ስኬት ከብሔራዊ ቡድናቸውም ጋር የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት ስኬታማ የመሆናቸውን ያህል ያልተሳካላቸው ጥቂት አይደሉም። ከነዚህ መካከል በዘመናቸው ከአፍሪካ አልፈው ከዓለም ከዋክብት መካከል የሚጠቀሱ ነገር ግን የአፍሪካ ዋንጫን ማሳካት ሳይችሉ ጫማ የሰቀሉ ተጫዋቾችን እንመልከት።
ዲዲየር ድሮግባ
ኮትዲቯራዊው ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ ዓለም ከማይረሳቸው ድንቅ አፍሪካውያን አጥቂዎች አንዱ ነው። ይህ ግብ አዳኝ ኮከብ በተለይም ከምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ጋር ይህ ቀረህ የማይባሉ ስኬቶችን ማጣጣም ሲችል ለክለቡ ስኬታማ ዘመን ቁልፉ ተጫዋችም ነበር። ያም ሆኖ ቼልሲን ለተለያዩ ክብሮች ያበቃው ኮከብ ሀገሩ ኮትዲቯርን ለአፍሪካ ዋንጫ ክብር ለማብቃት እንደጓጓ ሳይሳካለት ነው ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ለማግለል የተገደደው። ድሮግባ ከዝሆኖቹ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ህልሙን ለማሳካት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ እአአ 2012 ላይ በፍጻሜ ፍልሚያ በዛምቢያ ተሸንፎ በሚያስቆጭ ሁኔታ ዋንጫ ሳያነሳ ቀርቷል። የሁለት ጊዜ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሽልማት አሸናፊው ድሮግባ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ካገለለ ከሁለት ዓመት በኋላ (እአአ 2014) ግን ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ችላለች።
ንዋንኮ ካኑ
ከማይዘነጉ አፍሪካውያን ኮከቦች አንዱ የሆነው ናይጄሪያዊው ንዋንኮ ካኑ ድንቅ ተሰጥኦ ካላቸው ታሪካዊ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል። የአረንጓዴ ንስሮቹ ወርቃማ ትውልድ አካል የሆነው ካኑ በተለይም በሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ያሳለፈው ድንቅ ዘመን ሁሌም አይረሳም። በአያክስ አምስተርዳም፣ በኢንተር ሚላን፣ በዌስት ብሮም እና ፖርትስማውዝ ባሳየው አስደናቂ ችሎታም በርካታ ክብሮችን አሳክቷል። እአአ በ1996 እና 1999 የአፍሪካ ኮከብ ሆኖ የተመረጠው ካኑ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ካልቻሉ የሚያስቆጩ ተጫዋቾች አንዱ ነው። ካኑ በአፍሪካ ዋንጫ ሀገሩ ናይጄሪያን 2000 ላይ ለፍጻሜ ከማብቃት የዘለለ ታሪክ መሥራት አልቻለም።
አል-ሀጂ ዲዩፍ
ዓለም ዋንጫን ጨምሮ በታላላቅ ውድድሮች ድንቅ ብቃት ማሳየት የቻለው ሴኔጋላዊ ኮከብ አል-ሀጂ ዲዩፍ አስገራሚ ተሰጥኦ ከታደሉ አፍሪካውያን ኮከቦች አንዱ ነው። ከአንዴም ሁለቴ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ዲዩፍ አስገራሚ የግል ችሎታው ሀገሩን የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ለማድረግ በቂ አልነበረም። 2002 ላይ ግን ቡድኑ ለፍጻሜ ቀርቦ በካሜሩን ተሸንፎ ህልሙን ሳያሳካ ቀርቷል።
ማይክል ኢሴን
ከቼልሲ ጋር ባሳለፋቸው ዓመታት ይበልጥ የሚታወቀው ናይጄሪያዊ ኮከብ ማይክል ኢሴን ከሰማያዊዎቹ ታሪካዊ ኮከቦች አንዱ ነው። 2006 ላይ የቢቢሲ የዓመቱ ኮከብ አፍሪካዊ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ኢሴን ከአረንጓዴ ንስሮቹ ጋር የአፍሪካ ዋንጫን ማሳካት አልቻለም። ሀገሩን በ2010 የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ቢያበቃም በጋና አሸናፊነት ነበር የተጠናቀቀው።
ጆርጅ ዊሃ
ላይቤሪያዊው ታሪካዊ ኮከብ ጆርጅ ዊሃ የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት አለመቻል ከሌሎቹም በተለየ አስገራሚ ነው። በ1995 በኤሲ ሚላን ቆይታው ታላቁን የባሎን ድ ኦር ሽልማት በማሸነፍ ዛሬም ድረስ ብቸኛው ጥቁር ተጫዋች የሆነው ዊሃ ሀገሩን ግን ለአፍሪካ ዋንጫ ክብር ለማብቃት አልታደለም። ሁለት ጊዜ የአፍሪካ የአመቱ ኮከብ ሽልማት አሸናፊ መሆን የቻለው ዊሃ የሀገሩ ብሔራዊ ቡድን እሱ ከነበረበት የእግር ኳስ ከፍታ ጋር አብሮ መጓዝ የሚችል አልነበረም። በዚህም እንኳን የአፍሪካ ዋንጫን ለማንሳት በውድድሩ መሳተፍ የቻለውም በሁለት አጋጣሚ ብቻ ነበር። ይህም በ1996 እና 2002 ሲሆን ቡድኑ በሁለቱም ውድድሮች ከምድብ ጨዋታዎች ማለፍ አልቻለም።
አሳሞሃ ጂያን
ጋናዊው ኮከብ አሳሞሃ ጂያን በተጫወተባቸው የአውሮፓ ክለቦች ድንቅ ብቃት ከማሳየት ባሻገር፣ በዓለም ዋንጫ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ሪከርድ የጨበጠ ቀዳሚው አፍሪካዊ ተጫዋች ነው። 2010 ላይ የቢቢሲ የአመቱ ኮከብ አፍሪካዊ ተጫዋች የተሰኘው ጂያን በአፍሪካ ዋንጫ ዕድለኛ አልነበረም። ከጥቁር ከዋክብቱ ጋር 2010 እና 2015 ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ደርሶ በሁለቱም ሳይሳካለት ቀርቷል።
ኢማኑኤል አዲባዮር
ቶጓዊው ድንቅ ተጫዋች በአውሮፓ እግር ኳስ ከተለያዩ ክለቦች ጋር በርካታ ታሪኮችን መሥራት ቢችልም ከሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአፍሪካ ዋንጫን ለመሳም አልታደለም። 2006 ላይ ሀገሩን ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያበቃ በማጣሪያ ጨዋታዎች 11 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ሆኖ ነበር። ያም ሆኖ በውድድሩ ቶጎ ከምድብ ጨዋታዎች መሻገር ሳትችል ተሰናብታለች።
ሙስጠፋ ሀጂ
አፍሪካ ከማትረሳቸው ድንቅ ከዋክብት አንዱ የሆነው ሞሮኳዊው ሙስጠፋ ሀጂ በወርቃማ የእግር ኳስ ዘመኑ ከአትላስ አናብስቱ ጋር የአፍሪካ ዋንጫን አለማንሳቱ ያስቆጫል። 1998 ላይ የአፍሪካ የዓመቱ ኮከብ ተብሎ በተመረጠበት ዓመት እስከ ሩብ ፍጻሜ ብቻ የመጓዝ ታሪክ አኑሮ ነው ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ያገለለው።
ፍሬድሪክ ካኑቴ
የማሊው ታሪካዊ ተጫዋች ፍሬድሪክ ካኑቴ 2007 ላይ የዓመቱ አፍሪካዊ ኮከብ ሽልማትን ተቀብሏል። ያምሆኖ አስደናቂ የእግር ኳስ ብቃቱን ባሳየባቸው ዓመታት ሀገሩን በ2004 የአፍሪካ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ከማድረስ የተሻገረ ታሪክ መጻፍ ሳይችል ነው የብሔራዊ ቡድን ማለያውን ያወለቀው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም