የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅና የነፃነት አባቱ ማህተመ ጋንዲ

የጠቅላላ ዕውቀት ጥያቄና መልስ ውድድሮች ላይ ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ማን ናት?›› ተብሎ ሲጠየቅ እንሰማለን። የሴቶችን ተሳትፎ ታሪክ በሚዘክሩ መድረኮችና የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ስሟ ይነሳል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ ካሳሁን። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 52 ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም ሕይወቷ ያለፈውን፣ ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ ካሳሁንን እና የነፃነት ታጋዩን ማህተመ ጋንዲን ዘርዘር አድርገን እናስታውሳለን። ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸውን የታሪክ ክስተቶች እናስታውስ፡።

ከ103 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 20 ቀን 1913 ዓ.ም ጀግናው ፀረ ፋሺስት አርበኛ ሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ (የበጋው መብረቅ) ተወለዱ። ጃጋማ ኬሎ ሙት ዓመታቸው በሚታሰብበት የመጋቢት ወር ውስጥ በዝርዝር እናስታውሳቸዋለን።

ከ116 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 22 ቀን 1900 ዓ.ም ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የፖስታ ኅብረት (Universal Postal Union) አባል እንድትሆን ለኅብረቱ ደብዳቤ ፃፉ።

ከ131 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 25 ቀን 1885 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አልጋ ወራሽ የነበሩትና ኢትዮጵያን ከ1903 ዓ.ም እስከ 1909 ዓ.ም ያስተዳደሩት ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ተወለዱ።

ከ47 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በዛሬዋ ቀን ጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም የደርግ ሊቀ መንበር የነበሩትን ብርጋዴር ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ጨምሮ በኢ.ሕ.አ.ፓ ሰርጎ ገብነት የተጠረጠሩ የደርግ አባላትና የወዝአደር ሊግ (ወዝ ሊግ) ሊቀ መንበር የነበሩት ዶክተር ሰናይ ልኬ ተገደሉ። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ከድርጊቱ መፈፀም በኋላ ‹‹ለምሳ ሲያስቡን ለቁርስ አደረግናቸው›› አሉ።

አሁን በዝርዝር ወደምናያቸው የዛሬ ሳምንቱ በታሪክ ጀግኖችና ክስተቶች እንሂድ። የጋዜጠኛ ፍፁም ወልደማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› መጽሐፍ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣና የተለያዩ ድረ ገጾችን በዋቢነት ተጠቅመናል።

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ትውኔት ሮማነወርቅ ካሳሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሣሁን እንግዳሸት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አለሙሽ ዓለም በ1914 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በመማር ዳዊት ደገሙ። ከዚያም ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ተማሩ። በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የወቅቱን ‹‹ሴት ለትምህርት አልተፃፈችም›› የሚለውን ልማድ በጥረታቸውና በትጋታቸው በመቋቋም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የአንደኛነት ደረጃን በመያዝ በአውሮፓውያን አስተማሪዎቻቸው ይሸለሙ ነበር።

በወቅቱ በነበረው ልማድም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ትዳር ይዘው የአንዲት ሴት ልጅ እናት ሆነዋል።

ሮማነወርቅ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ይማሩ በነበረበት ወቅት ከአውሮፓውያን መምህራን ያገኙት ዘመናዊ ትምህርት ከተፈጥሮ ችሎታቸው ጋር ተደምሮ በጥናትና ንባብ ያዳበሩትን እውቀታቸውን ወደ አደባባይ ማውጣት ስለፈለጉ በጥር ወር 1939 ዓ.ም በወቅቱ ‹‹የማስታወቂያና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር›› ተብሎ ይጠራ በነበረው መሥሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመሆን ተቀጠሩ።

በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በተሰጣቸው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሥራቸው የተለያዩ ጽሑፎችንና ዜናዎችን በማዘጋጀት በማራኪ አንደበታቸው ሲያንቆረቁሩት በዜና አቀራረባቸውና በፕሮግራም ዝግጅታቸው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትንና አድናቆትን ለማግኘት ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር።

ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሬዲዮ ዜና አጠናቃሪነት፣ በዜና አንባቢነት፣ በሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅነት ሠርተዋል። በወቅቱም ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመው በዝግጅቶቻቸው ላይ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሥራዎችን በማቅረብ ሕዝቡን ሲያገለግሉ በትምህርት ገበታ ላይ ለነበሩት ሴቶች ልጆች እንደብርቅዬና የበጎ ተግባር ምሳሌ በመሆን ይታዩ ነበር። በዝግጅቶቻቸው የተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በወቅቱ በሴቶች ዘንድ ጫና የሚፈጥሩ አመለካከቶችን ለመፋቅ በመገናኛ ብዙኃን የራሳቸውንና የብዙ ሴቶችን ድምፅ አሰምተዋል።

የሴቶች ማኅበራዊ ሕይወት መሻሻል ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችንም ይጽፉ ነበር። ከሥራዎቻቸው መካል የበኩር ሥራቸው የተጠናቀቀው በ1940 ዓ.ም ቢሆንም መጽሐፋቸውን ይዘው ወደ ሕትመት የሄዱት ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ በ1942 ዓ.ም ነበር። ይህንን ጉዳይ አስመልክተውም በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ በማለት ስለሕትመቱ ጉዳይ በትህትና ገልፀዋል።

‹‹ … መጽሐፌን ጽፌ የጨረስኩት በ1940 ዓ.ም ነበር። ከዚያ ወዲህ ሁለት ዓመታት ቆይቼ ሳነበው ከእርሱ የተሻለ ለመፃፍ የምችል ሆኖ ተሰማኝ። በዚህ ምክንያት ተሳንፌ ማሳተሙን ለማቆየት ከቆረጥሁ በኋላ የሰው እውቀት የዕድሜ ደረጃን ተከትሎ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ አዋቂ አለመሆንን በማሰብ ዛሬ የተሻለ መስሎኝ ብሠራም ነገ መናቄ እንደማይቀር ተረዳሁት። ይህም የሰው አዕምሮ ያለማቋረጥ የሚሻሻል ለመሆኑ ዋና ማስረጃ ነው በማለት ይህን ሁሉ ካወጣሁና ካወረድሁ በኋላ ማመንታን ትቼ አሳተምሁት። … ››

የመጀመሪያ ሥራቸውን ለአንባቢ ያቀረቡት ወይዘሮ ሮማነወርቅ ለመጽሐፋቸው የመረጡት ርዕስ ‹‹ትዳር በዘዴ›› የሚል ነበር። መጽሐፉ የገጠሩንና የከተማውን ትዳርና ኑሮ የሚያነፃፅር ሲሆን በውስጡም በገጠር ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ዘርዝሮ ያቀርባል። ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹ለትዳር ፈላጊዎች ምክር አለኝ›› በማለት ስለትዳር የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ሞክረዋል። ሴቶች በማኅበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ያለባቸው ጫናም በመጽሐፉ ተዳስሷል። ከዚያ በኋላም በርካታ ጋዜጣ መጣጥፎችንና መጻሕፍትን ጽፈዋል። በሥራዎቻቸውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ትውኔት ሮማነወርቅ የጤና እክል አጋጥሟቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንትና ሠራተኞች እንዲሁም እጅግ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

ጋዜጠኛዋ ሞት ቀደማቸው እንጂ ‹‹ሔዋን››፣ ‹‹መልካም እመቤት››፣ ‹‹የቤተሰብ አቋም››፣ ‹‹የባልትና ትምህርት››፣ ‹‹የሕፃናት ይዞታ››፣ ‹‹ዘመናዊ ኑሮ››፣ ‹‹የኑሮ መስታወት››፣ ‹‹ጋብቻና ወጣቶች››፣ እና ‹‹የባልና የሚስት ጠብ›› በሚሉ ርዕሶች መጻሕፍትን አዘጋጅተው ለሕትመት ለማብቃት እየጠበቁ እንደነበር ታሪካቸው ያሳያል።

የነፃነት ታጋዩ ማህተመ ጋንዲ

የሕንዱ ማህተመ ጋንዲ የመብት ተሟጋች ስለነበሩ በየትኛውም የዓለም ጫፍ ይታወቃሉ። በሀገራችን ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ስማቸው ይነሳል። ሆስፒታልም በስማቸው ተሰይሞላቸዋል።

ከ76 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 22 ቀን 1940 ዓ.ም የተገደሉትን ማህተመ ጋንዲን እናስታውሳቸው።

ማህተመ ጋንዲ የተወለዱት መስከረም 23 ቀን 1862 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ ኦክቶበር 2፣ 1869) ነው። ማህተመ ጋንዲ ‹‹የሕንድ አባት›› በመባል የሚታወቁ የሰላማዊ ትግል መሪ እና የፀረ ቅኝ አገዛዝ አብዮተኛ ናቸው።

‹‹ፍልስምና›› በተሰኘው የቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው፤ ጋንዲ እንግሊዞችን ፍጹም ሰላማዊ በሆነና ለእነርሱ ጨርሶ ሊገባቸው በማይችል እምነትና መንገድ የታገላቸው ነው። ከምዕተ ዓመታት ቅኝ ግዛታቸው ለማስወጣት የሕንድን ሕዝብ እያንቀሳቀሰ ስለሚፈታተናቸው ብዙ ጊዜ እስር ቤት ይከቱት ነበር።

ወደ መጨረሻው አስከፊ እስር ቤት በወረወሩበት ጊዜ ‹‹እናንተ አውሮፓውያን ወዳጆቼ ሆይ! የሰው ልጅ እኮ በአራት ግድግዳ የሚታሰር ግዑዝ ነገር አለዚያም እንሰሳ አይደለም። የሰው ልጅ መንፈስ ነው። እዚህ በእስር ሳለሁ ጽናቱን እምነቴ ሕንዳውያን ወገኖቼን ያንቀሳቅሳል፤ እስር ቤት ክፉ የሚሆነው በመንፈስ ለታሰሩና በግድግዳ ለሚወሰኑ እውነተኞቹ እስረኞች እንጂ መንፈሳቸውን ከፍርሃትና ከጥላቻ ነፃ ላወጡ መንፈሳውያን እስራት አያስጨንቃቸውም፤ አያሸብራቸውም›› ብሏቸዋል።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ጋንዲን የመጨረሻዎቹ ዱርዬዎችና ነፍሰ ገዳዮች መካከል ይከቱታል። ጋንዲ ወደዚያ ሲገባ ‹‹እነሆ ወንድሞቼ መሃል ገባሁ። ከዛሬ ጀምሮ የዚህ ቤተሰብ አካል ነኝ›› ይላቸው ነበር። ኀዘን ቢሰማው እንኳ ኀዘኑን በተስፋና በፍቅር ሊታገለው ይጀምራል እንጂ ቅሬታና ማጉረምረምን አያሰማም ይሉታል። በእነዚህ የማይጠቅሙ ተብለው በተጣሉ ዱርዬዎች ውስጥ ፍቅርና መልካምነት እንዳሉ ያውቃል ብቻ ሳይሆን ያምናል። እናም ኃላፊነት ይወስዳል። የእስር ቤቱን ቆሻሻ ማጽዳት ይጀምራል። እነዚያን አይጠቅሙም እንደውም ማኅበራዊ አደጋ ናቸው ተብለው የተጣሉ ነፍሰ ገዳዮችን በማክበር አክብሮት ከሚሰጠው መልካም ስሜት ያስተዋውቃቸዋል። ከእግዚአብሔር ያስተዋውቃቸዋል። ጤና አጠባበቅን፣ አብሮ መኖርን ያስተምራቸዋል። ታሪክ የማያውቁትን ታሪክ፣ ማይማኑን ማንበብ መፃፍ ያስተምራቸዋል። እንዲህ በመልካም ተግባር ተጠምዶ ሲውል ስለ እስር የሚያስብበት ጊዜ አልነበረውም። እንግዲህ ስለ ነፃነታቸው ሲል የራሱን ነፃነት ያጣላቸው ሕንዳውያን ማለት እነዚህን ወህኒ የተጣሉትንም እንደሚጨምር ያውቃል። እናም የብርሃን ተስፋውን በወህኒ ጨለማ ውስጥ ሳለ ይበልጡኑ ጸንቶና አምኖ እየታገለለት ነው ማለት ነው።

የትግሉ መንገድ ግን ጥላቻን በጥላቻ ማሸነፍ እንደማይቻል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ጥላቻን በፍቅር መፈተን ነው። ስለዚህ መታሰሩ አስጨንቆ ዓላማውን ጥሎ እጁን እንዲሰጥ አያስገድደውም። ይልቁንም በዚያ ጨለማ ውስጥ ሕይወትን ይጀምራል። እናም መታሰሩን ይረሳዋል። በዚህ ጊዜ እነሱው አሳሪዎቹ ራሳቸው አስታውሰው ነው የሚፈቱት። ‹‹የረገጥኳትን መሬት ለመባረክ ሥልጣን ተሰጥቶኛል›› ነው የሚለው።

ማህተመ ጋንዲ በዚህ የሕይወት መንገዱ ያስተማረኝ ትልቅ እውነት ‹‹በዙሪያህ የሚታይህን ክፋት መቋቋም ካቃተህ ‹እኔን ምን ነካኝ?› እንጂ ‹ዓለም ምን ነካት?› ብለህ አትጠይቅ›› የሚል ትምህርት ነው። እንዲህ ብለህ ብትጠይቅም መልስ አታገኝም። ዓለም ክፉ ናት ብትል ራስህ ክፉ ናት ካልካት ከዓለም በእጥፉ የከፋህ ትሆናለህ። በምትጠላው ነገር ውስጥ ያለውን መልካም ነገር የምታስተውልበት ዓይኖች ቢኖሩህ ክፉውን መልካም ታደርገዋለህ። እርሱን ፈውሰህ አንተም ትፈወሳለህ›› ይላል።

ማህተመ ጋንዲ በዚህ ባህሪው ራሳቸው እንግሊዛውያኑ ቅኝ ግዢዎች፣ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ፣ የሌላ እምነት ተከታዮቹ ሳይቀሩ ይወዱት፤ ይከተሉትና ያምኑት ነበር። እንግሊዞቹ ተብትበው በወጡት መከፋፈልና ጥላቻ ምክንያት በተፈጠረው እርስ በእርስ የመጠፋፋት ጦርነት ውስጥ ሙስሊሞቹ ሂንዱዎቹን እያባረሩ በቆንጨራ በሚጨፈጭፉ ሰዓት እንኳ ማህተመ ጋንዲን ግን ይሰሙት ነበር። ይከተሉት ነበር፤ እርሱ ዘንድ ሲደርሱ በፍቅሩ ጭካኔያቸውንና ቂም በቀላቸውን አሸንፎ ያንበረክካቸው ነበር።

የሁሉንም እምነት መጻሕፍት እየገለጠ በየዕለቱ ከሁሉም ሕንዳውያን ጋር አብሯቸው ይጸልይ ነበር። እናም ጋንዲ የቱንም መጥፎ የተባለን ቦታና ሃሳብ ወደ መልካም የመለወጥ ምሳሌ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በመሸ ጊዜ ንጋትን በማሰብ ተስፋህን አምነህ ጉዞህን ጀምር የሚል እምነት አለው። የክፉ ነገር መጨረሻ ጥፋት ነው። መልካሙን የሚያመጣው የግለሰቦች ጽናት ነው። በመጨረሻው ጨለማ ውስጥ ወደ ብርሃንህ መመልከት የማህተመ ጋንዲ እምነት ነው።

ይህ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ታጋይ ናታሁራም ቪናያክ ጎድሴ በሚባል ግለሰብ በጥይት ተገድሏል። ገዳዩም የሞት ቅጣት ተፈርዶበት በስቅላት ተቀጥቷል። እነሆ የማህተመ ጋንዲ ስምና ሥራ ግን በዓለም ዙሪያ ሲወደስ ይኖራል።

ዘመን የየራሱ ትዝታ አለው። ይዞት የሚመጣው አዳዲስና አስገራሚ ነገሮች አሉት። እንደ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ስልክ … የመሳሰሉ የመገናኛ ዘዴዎች ሲፈጠሩ ‹‹አጃዒብ›› አሰኝተው ነበር። ዛሬ ግን እነዚህ ሁሉ በሌሎች ፈጣን የመገናኛ ዓይነቶች እየተቀደሙ ናቸው። ከእነዚህ አንዱ ኢንተርኔትን መሠረት ያደረገው፣ ‹‹ፌስቡክ›› የተባለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ነው። ፌስቡክ የራሱን አብዮት ፈጥሮ ታሪክ አስቀምጧል። ልክ በዛሬዋ ቀንና 20ኛ ዓመቱ መሆኑን ምክንያት በማድረግ በጥቂቱ እናስታውሰው።

ዓለምን እያሽከረከረ ያለው ‹‹ፌስቡክ›› የተባለው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገና የ20 ዓመት ታሪክ ያለው ነው። ፌስቡክ የተገኘው የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በነበሩት ማርክ ዙከምበርግና ጓደኞቹ ከ20 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን ጥር 26 ቀን 1996 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ፌብርዋሪ 4 ቀን 2004) ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ መተዋወቅ የጀመረው ግን ከ10 ዓመት አካባቢ በኋላ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሲተዋወቅ ጥቂት ሰዎች ይጠቀሙት የነበረ ቢሆንም አብዛኛው ሰው መጠቀም የጀመረው ምናልባትም ከ2004 ዓ.ም አካባቢ በኋላ ነው።

ይህ ገና የ20 ዓመት ዕድሜ ያለው የመገናኛ ዘዴ አሁን ላይ ያሉ ታዳጊዎች ምናልባትም ብዙ ዘመን የቆየ ይመስላቸው ይሆናል። በተለይም በኢትዮጵያ ዓውድ ካየነው ደግሞ መረጃን በፍጥነት ማድረሱ ጥሩ ሆኖ ሳለ ለጥላቻና ለሀሰተኛ መረጃዎች መሰራጨት አሉታዊ ሚና አሳድሯል። ይህ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ፌስቡክ ለብዙ ዘመናት የኖረ ይመስላቸው ይሆናል። ምክንያቱም እነርሱ ማገናዘብ የጀመሩበት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ፌስቡክ የሚባል ነገር አለ።

ከፌስቡክ በኋላ ብዙ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ዓይነቶች (ከመቶ ሰላሳ በላይ?) ቢመጡም የመጀመሪያው ግን ፌስቡክ ነውና እነሆ 20 ዓመታትን በማስቆጠር ታሪክ እያስመዘገበ ይገኛል።

 ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You