ከእሳት ጋር ግብ ግብ

አደጋ በየትኛውም ቦታና ጊዜ እንዲሁም በማንኛውም ሰው ላይ ሳያማክር በዚህ ቀን እደርሳለሁ ብሎ ሳያሳውቅ ድንገት የሚከሰት በመሆኑ ጥሎት የሚያልፈውም ጠባሳ እጅግ ከባድ ነው። እነዚህ አደጋዎች ደግሞ የከፋ ጉዳት ሳያደርሱ መከላከል መቻል ደግሞ ከግለሰብ አልፎ ተቋማትን ጭምር የሚመለከት ነው።

ከእነዚህ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አንዱ ነው። ኮሚሽኑ የሰውን ልጆች ሕይወት ከአደጋ ለመከላከል የሀገርና የሕዝብ ሀብትን ከውድመት ለማዳንም ብቁና ምስጉን በሆኑ ባለሙያዎቹ አማካይነት ሃያ አራት ሰዓት ሰባቱንም ቀናት በዓልን ሳይመርጥ ሁሌም አገልግሎት ላይ ያለ ተቋም ነው።

እኛም ለዛሬ የሕይወት ገጽታ አምዳችን በዚሁ ተቋም ለበርካታ አመታት የአደጋ መከላከል ሥራን በውጤታማነት በማከናወን ላይ ስላለችው ወይዘሮ ትዕግሰት ተክለዓብ የሕይወት ተሞክሮ ይዘን ቀርበናል። በአሁኑ ወቅት ትዕግስት በአዲስ አበባ ከተማ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ምላሽ ቡድን መሪ ናት።

ወይዘሮ ትዕግስት ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ችሎት መድኃኔዓለም በሚባለው ሰፈር ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷንም የተማረችው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነው።

«…..ተወልጄ ያደኩበት ችሎት መድኃኔዓለም ወይም ቀጨኔ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ለቤተሰቦቼ ሦስተኛ ልጅ ነኝ። እናትና አባቴ ከአካባቢው ልጆች እንዲሁም ከእህትና ወንድሞቼ ጋር በመሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን እማር ዘንድ የላኩኝ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በዚያም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርት አጠናቅቄያለሁ» ትላለች።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ሚኒስትሪ ፈተናዋን ተፈትና ጥሩ ውጤት በማምጣት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመማር ያቀናቸው ወደ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ቤቱም አስረኛ ክፍል ይሰጥ የነበረውን የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ወሰደች። ከዚያ በኋላ ግን በትምህርቷ እንዳትቀጥል የሚያደርጋት አጋጣሚ ተፈጠረ።

«……ትምህርት በጣም እወድ ነበር። የሚኒስትሪ ውጤቴም በጣም አሪፍ ነው። በትምህርት ቤት መምህራን የሚያስተምሩትን ነገር በቀላሉ የመረዳት ችሎታ ነበረኝ። ብቻ በጠቅላላው ለትምህርት የነበረኝ ፍቅር በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም» በማለት የተማሪነት ጊዜዋን ታስታውሳለች።

ትዕግስት የልጅነት ገጽታዋ (መልኳ ) የሚያምር ሳቢ ስለነበረ ትምህርት ቤት ደርሳ እስክትመለስ ድረስ በየመንገዱ የሚገጥሟት ጾታዊ ትንኮሳዎች አለፍ ሲልም የጓደኝነት ጥያቄው በጣም አስቸጋሪ ሆኑባት፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ እሷን ከማሳሰቡም አልፎ ለቤተሰቦቿ ትልቅ ጭንቀት ነበር፤ ልጃችን ትሰናከልብን ይሆን የሚለውም ስጋታቸው ከፍ ያለ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ የተነሳ ዘወትር ለሚጠብቃትና ለሚከታተላት አንድ ወጣት ተዳረች። በትዳሯ ደስተኛ ብትሆንም በልጅነቷ በማግባቷ እንደ እኩዮቿ እንደ ልቧ መዝናናት እንዳልቻለች ትናገራለች፡፡

«……ልጅነቴን ተዝናንቼ ተጫውቼ የማሳለፍ ዕድልን አላገኘሁም፤ ከትዳር በፊት በጓደኝነት ያሉ መዝናናቶችም እኔ ጋር አልነበሩም፤ መዝናናት ይሉትን የወጣትነት ክፍል ሳላውቀው አልፌዋለሁ። በዚህም ከትምህርት ወደ ሕይወት߹ ከሕይወት ወደመተዳደሪያ ሥራ ነው ያመራሁት » ትላለች።

ትዕግስት ትዳር ወይንም ደግሞ ልጅ ወልዶ ማሳደግ ከምትወደው ትምህርት ማስቆም እንደሌለበት ወሰነች። ልጇን ወልዳ ለታላላቅ እህቶቿ እንዲሁም ለእናቷ በመስጠት በአስረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያቋረጠችው ትምህርት ለመቀጠል ወደ ትምህርት ቤት ሄደች።

«……በወቅቱ ልጅ ሆኜ ልጅ አቅፌ መታየት ያስከፋኝ ነበር፤ እናቴና እህቶቼ እንዲይዙልኝ ነበር የማደርገው። ትምህርት ቤት ለመሄድ ደግሞ እሷን ማጥባት ካለቀሰች መቅረት ብዙ ነገሮች ነበሩ ትምህርት ቤት ቁጭ ብዬ ጡቴ ይወጠራል ይህንን ያዩ ጓደኞቼ ደግሞ እንዴ ወልደሽ ነው? አግብተሽ ? የሚሉ ጥያቄዎችን አዘውትረው ይጠይቁኝ ነበር። በጥያቄዎቹ ብከፋም በተቻለ መጠን ራሴን ተቆጣጥሬ ነው የተማርኩት፤» በማለት ሁኔታውን ትገልጻለች።

ባለቤቷ ከሷ በዕድሜም በአቅምም የሚሻል ነበርና ይህንን የልጅነት ድካሟን በጣም እንደሚረዳት ትናገራለች ። ልጅነቷን ተረድቶ በተቻለ መጠን ከሃሳብና ከብስጭት የምትርቀበትን መንገድ በማመቻቸት ቤተሰቧን የምትረዳበትን መንገድ ያመቻችላት ነበር። ራሱን በትምህርት አሻሽሎ የተሻለ ሥራን በመሥራት እሷም በትምህርት ዝቅ እንዳትልበት ልጅ እየያዘላት ትምህርት ቤት እንድትሄድ እንድታጠና ሁኔታዎችን በማመቻቸት የተወጣው ሚና ላቅ ያለ ስለመሆኑና ለዛሬ እዚህ መድረሷም ምክንያቱ እሱ መሆኑን ትናገራለች።

የአራስነት ጊዜዋን ጨርሳ ወደተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤት በመግባት በኮምፒዩተር ሳይንስ የዲፕሎማ ትምህርቷን ጀመረች። በዚህም ከአይቲ ድጋፍ ሰጪነት እስከ ጥገና ድረስ ያሉትን ትምህርቶች ተምራም ዲፕሎማዋን አግኝታለች።

ትዕግስት የዲፕሎማ ትምህርቷን ከተማረች በኋላ ሁለተኛ ልጇን ነፍሰጡር ሆነች። ከመጀመሪያው በተሻለ ሥነ ልቦናና አቅም የሁለተኛ ልጇን የእርግዝና ጊዜ በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅና በሰላም በመገላገል አራስ ቤት ተኛች። በዚህ ጊዜ ግን ታስብ የነበረው ከአራስ ቤት ወጥታ የምትማረውን ትምህርት ነበርና ልክ አራስ ቤቷን አጠናቃ እንደወጣች በቀጥታ የሰው ሀብት አስተዳደር ትምህርት ለመማር ወደ ኮሌጅ ገባች።

የኮሌጅ ትምህርቷንም በተገቢው ሁኔታ አጠናቃ በዲፕሎማ ተመረቀች። ይህም ቢሆን ግን እርካታ ላይ አልደረሰችምና የማኔጅመንት ትምህርቷን በዲግሪ ደረጃ ለማሳደግ ወደ ትምህርት ቤት ሄደች ይህንንም ትምህርት እየተማረች የመጨረሻ ልጇን አርግዛ ስለመውለዷም ነው የምትናገረው።

«……በሕይወቴ ብዙ ብፈተንም በዕድሜዬ ግን ምንም ያባከንኩት ጊዜ ባለመኖሩ ደስተኛ ነኝ፤ ልጆቼን እያሳደኩ ቤቴን እየመራሁ ትምህርቴን እየተማርኩ ሥራዬ ላይም ሳልጎድል እዚህ ደርሻለሁ፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ አልችልም የሚል አስተሳሰብን ከአእምሮ ማውጣት ብቻ ለስኬት ትልቅ መንገድ መሆኑንም ተረድቻለሁ» በማለት ትናገራለች።

ትዕግስት አሁን ያለችበትን ሥራ ከመጀመሯ በፊት ንግድ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተቀጥራም ለመሥራት ሞክራለች። የሕይወት አጋጣሚ ብዙ ነውና እሷ ተቀጥራ በሥራ ላይ እያለች እህቷ ፒያሳ የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ኮሚሽን የሥራ ማስታወቂያ አውጥቶ ትመለከታለች። ይህም ሊያመልጠን አይገባም ብላ እራሷንም እህቷንም እንዳስመዘገበቻት ትናገራለች።

«…..በወቅቱ እኔ አራት ኪሎ አካባቢ ወርቅ ቤት ተቀጥሬ እሠራ ነበር፤ እህቴ ደግሞ እንደ አጋጣሚ ማስታወቂያውን ስታይ እኔንም እሷን አስመዘገበች፤ የትምህርት ማስረጃችሁን አቅርቡ በተባለበት ቀን ደግሞ አብረን ሄድን፤ የዛሬ 16 ዓመት የነበረው የመጀመሪያው ቅጥር የሚጠይቀው መስፈርት 8ተኛ ክፍልን ያጠናቀቀ የሚል ነበር። ያም ቢሆን ግን ለማበላለጫ የተጠቀሙት ውጤታችንን ሆነና የእኔ ውጤት አሳለፈኝ እህቴ ሳይሳካላት ቀረ » በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።

የሥራ መደቡ ጥበቃ በመሆኑም ሥልጠና መውሰድ ያስፈልግ ስለነበር ሥልጠናውን ለመውሰድ ወደሚፈለገው ቦታ በመሄድ ሥልጠናውን በጥሩ ሁኔታ በማጠናቀቅ ወደ ሥራው ስለመግባቷም ነው የምትናገረው።

«…….በወቅቱ ለጥበቃ ሥራ ነው የተመዘገብኩት ስል ብዙ ሰዎች ካለማመናቸውም በላይ እንዴት የሚል ጥያቄ ይመላለስባቸው ነበር። ነገር ግን እኔ በሁኔታው በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ደስተኛ የሆንኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ሥራ በጣም ያስፈልገኝ ስለነበር እንዲሁም ቤት በመቀመጤ የማገኘው ነገር ባለመኖሩ ነው። ውጭ ከሰው ጋር ብውል ነቃ ብዬ ብዙ ነገሮችን የማሰብ አጋጣሚው ይኖረኛል፤ እለወጣለሁ የሚል የጸና አቋም ስለነበረኝ በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው ሥራውን የተቀላቀልኩት» ትላለች።

ትዕግስት በሥራዋ ትጉህ ከመሆኗም በላይ በፍላጎት ትሠራ ስለነበር በቶሎ ነበር ከጥበቃ ሥራ ወደሌላ ክፍል ለመዘዋወር ዕድሉን ያገኘችው። በዚህም ለኦፌሰርነት የወጣውን ውድድር ተወዳድራና በብቃት አልፋ የአደጋ መቆጣጠር ባለሙያ በመሆን ሥራዋን ቀጠለች።

የአደጋ መቆጣጠር ሥልጠና

«…….ከልጅነቴ ጀምሮ በከባባድ ፈተናዎች ውስጥ ስላለፍኩኝ ሥልጠናውን ተቋቋምኩት እንጂ ሥልጠናውስ ገና ሲገባበት የሚያስፈራ እንዴ እንደዚህ ነው እንዴ? የሚያስብል ነበር፤ ሥልጠናው በእሳት ላይ መዝለል߹ ቱቦ ለቱቦ ሄዶ ሰው ማዳን߹ እሳት ውስጥ እየዘለሉ ገብቶ ማለፍ߹ እንደ ወታደር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት እና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ጭምር ማለፍ ይጠይቅ ነበር። ከሁሉም ከባዱ ደግሞ አመጋገቡ ወታደራዊ መሆኑ ነው። የላመ የጣመ ምግብ ብሎ ነገር የማይታሰብ ነበር» ትላለች።

እነዚህንና ሌሎች በርካታ ፈተናዎችን በብቃት መወጣትን የሚጠይቀውን ሥልጠና ትዕግስት ከፍ ባለ ብቃት ከማጠናቀቋም በላይ ሥልጠናውን በዚህ መልኩ መውሰዷ በጥንካሬ ላይ ጥንካሬን እንድትጨምር እንደረዳትም ትገልጻለች።

ለስድስት ወራት ቤተሰብ ምናልባት በሳምንት አልያም በ15 ቀን አንዴ እየታየ ከሚሠለጠንበት የሥልጠና ማዕከል ውስጥ በመቆየትም ሰዎችን ከገቡበት ችግር እንዴት ማዳን ይቻላል የሚለውን ብቻ ሳይሆን ከራስ ጀምሮ ቤተሰበን ብሎም የሥራ ባልደረቦችን እንዴት መምራትና ማስተዳደር እንደሚቻል እውቀት ገብይታበታለች። በሥራ ላይ ብቁና ተፈላጊ ለመሆን ምን ማድረግ ይገባል የሚሉና ሌሎች የሕይወትና የሥራ ክፍሎች ማዳበሪያ ሥልጠናዎችን ማግኘቷንም ነው የምትናገረው።

«……እኔ ሁሌም በሕይወቴ በሥራዬ በእንቅስቃሴዬ ሁሉ መሸነፍ ይሉት ነገር አልፈልግም፤ ከስህተቴ እማር ይሆናል እንጂ አልችልም ብዬ ለመተው አልቸኩልም፤ በዚህ አቋሜም ያንን ከባድ ጊዜ በድል ለማጠናቀቅ በቅቻለሁ። በነገራችን ላይ ከእኔ ጥንካሬና አልሸነፍ ባይነት ጎን ለጎን የባለቤቴ ቀና ትብብርና ድጋፍ ለውጤቴ ማማር ከፍ ያለ ድርሻውን የሚወስድ ነው» በማለት ታብራራለች።

የመጀመሪያ የአደጋ መከላከል ሥራ

ማንኛውም ሰው በሠለጠነበት ሙያ ግዳጁን ይወጣ ዘንድ ግድ ነውና ትዕግስትም የሠለጠነችውን አደጋን የመከላከል ትምህርት በተግባር የምትቀይርበት ጊዜ ደረሰ በዚህም «ሀ» ብላ ሥራዋን ትጀምር ዘንድ ቀኑ ደረሰ። እሷም የጓጓችለት ቀን ነበርና ስምሪቱ ሲመጣ ከመቅጽበት ነው ተነስታ የሄደችው።

«…..ከሥልጠና በኋላ ከባባድ አደጋዎች ነበር የገጠሙኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ተብዬ የተመደብኩትም እህል በረንዳ ተቃጥሎ እሱን ማጥፋት ላይ ነበር። ስደርስም ከሠለጠንኩበት እሳት የባሰ ነበር። በጣም ደነገጥኩ። እንዴት ነው የማጠፋው? ብዬ እራሴን ጠየቅኩ። ከእሳቱ ጋር ግብ ግብ ገጠምኩ። በመጨረሻም አሸነፍኩት። 40 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሲጠፋ ሳይ እንዴ ለካ እንደዚህ ነው በማለት በራሴ አመኔታን አዳበርኩ» በማለት ትናገራለች።

ልክ እሳቱ መጥፋቱን ወይም በቁጥጥር ስር መዋሉን ስታይ ግን ለካ እንደዚህ ነው ሥራው በማለት ወደውስጧ ማስገባቷን ትነጋራለች። በጣም በሚገርም ሁኔታ እሷን ጓደኞቿ ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደሥራ በገቡበት ጊዜ አንድን ሥራ ሠርተው ልብሳቸው እንኳን ሳይደርቅ ሌላ ጥሪ ይመጣ እንደነበር በማስታወስ የአውቶቡስ ተራውን ሥራ እንዳጠናቀቀች ወዲያው መርካቶ ደግሞ ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሮ በመጠራታቸው እሷና ጓደኞቿ ጉዟቸውን ወደዚያ ስለማድረጋቸው ታብራራለች።

«……እንደዚህ ዓይነት ፈጣን ፈጣን አደጋዎችን መሥራት ስጀምር በቃ አደጋ በሁላችንም እጅ ያለ በመሆኑ ማጥፋት እንኳን ባንችል መቀነስ የምንችልባቸው ዕድሎች ስላሉን እሱም ላይ መሥራት አለብኝ በማለት በሩቁ ታየው የነበረውን አደጋ ጠንቅቃ በማወቅ መንስኤና መፍትሔውን በመረዳት ለሌሎች የግንዛቤ ምንጭ በመሆንም መሥራት መቀጠሏን ነው የምታብራራው።

የአደጋ መከላከል ሥራ የወንድ ብቻ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው። ነገር ግን ሴትም ትሁን ወንድ ብቻቸውን ሊወጡት የሚችሉት ኃላፊነት አይደለም። በመሆኑ ሁለቱም በሙያው እስከሠለጠኑ ድረስ ያንቺ ያንተ ሳይባባሉ ተጋግዘው ነው መሥራት ያለባቸው፤ እኔም እስከ አሁን ያለፍኩት በዚህ መንገድ ነው።

እኔ የማውቀውን ለወንዱ የሥራ ባልደረባዬ እነግረዋለሁ እንዲህ ብታደርገው ውጤቱ ይህ ይሆንልሃል ብዬ መንገድ እጠቁመዋለሁ። እነሱም ለእኔ እንደዚያው ናቸው ይህንን አድርጊው በዚህ በኩል ሁኚ ብቻ ተጋግዘንና ተባብረን የተቸገረን አካል እየረዳን ነው እዚህ የደረስነው በማለት የእርስ በእርስ መረዳዳቱን ታብራራለች።

«…..እኔ በሕይወቴ አልችልም የምለው ሥራ የለም። እስከ አሁን የገጠሙኝ የሥራ ጓደኞቼም የሚያበረታቱ መንገድ የሚያሳዩ ለችግሮቼ መፍትሔ የሚፈልጉ ብዙ የተማርኩባቸው ናቸው፤ አሁን ለደረስኩበት ደረጃም ትልቁን ምስጋና የሚወስዱት ተቋሙና የሥራ ባልደረቦቼ ናቸው» ትላለች።

የተቋሙ ሥራ በማንኛውም ጊዜና ቦታ የሚሠራ ከመሆኑ አንጻር በተለይም በዓላት እንደ ትዕግስት ላሉ የቤተሰብ ኃላፊዎች ፈታኝ ነው። ምን ጊዜም የበዓላት ቀናት በተጠንቀቅ ስለሚሆኑ በዓልን በቤታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተሰብስበው የማክበሩ ዕድልም በጣም የመነመነ ነው፡፡

ትዕግስት በዓልን አላውቀም ልጆቼም እኔን በዓል አይተውኝ አያውቁም ትላለች።

«……መጀመሪያ ላይ በተለይ በዓል ሲሆን ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር፤ የእኔ ጥሩ ዕድል እናቴ በመኖሯ ልጆቼና ባለቤቴ በዓልን እዚያው ሄደው ያሳልፋሉ፤ ይህም ቢሆንም ግን በጣም ከባድ ነው። ምናልባት ዋዜማውን ቤቴ የምሆን ከሆነ ከልጆቼ ጋር ላከብር እችላለሁ። በዓልን ግን በቤት ውስጥ ምን እንደሚመሰል የማየት ዕድሉ አይገጥመኝም » በማለት ታብራራለች።

«የከተማዋ ነዋሪ በሰላም በደስታ ያለምንም አደጋ ማሳለፉን ነው ለእኔ በዓሌ» የምትለው ትዕግስት ይህንን ካወቅኩ በኋላ በዓሉ አልፎም ቢሆን እንኳን ዳግም በዓል አስመስዬ ማክበሬም አይቀርም፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ ትላለች።

«……በዓል ምናልባትም ደስታ ነውና ካለፈም በኋላ ቢሆን ደስታን ማክበር ቀላል ነው። ነገር ግን ከሁሉም የሚከብደው ኀዘን ሲመጣ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባን በሚያጎራብቷት ክልሎች አካባቢ አደጋዎች ሲከሰቱ የምንጠራው እኛ ነን። እዚያ በሄድንበት ወቅት ደግሞ የቅርብ ሰው ሊያልፍ ይችላል። ምናልባት ቀብር ላይ መድረስ ላንችል እንችላለን ፤ ይህ በጣም የሚከብድ ነው» በማለት ትናገራለች።

የማይረሱ የሥራ ገጠመኞች

የአደጋ መልካም የለውም። ሁሉም አደጋዎች አሳርፈው የሚሄዱት የራሳቸው ጠባሳ አላቸው። አንዳንድ ጊዜ አደጋ ከደረሰባቸው ሰዎች አልያም በአደጋ የሚወዱትን ካጡ ሰዎች በላይ የአደጋ መከላከል ሥራውን ሲሠሩ የነበሩ ሰዎችም ልባቸው በኀዘን የሚመታባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ትዕግስትም የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ በሄደችባቸው ቦታዎች ሁሉ የምታያቸው ነገሮች እጅግ ልብ የሚነኩና የሚያሳዝኑ ቢሆኑም አንዳንዶቹን ደግሞ ለመርሳት ሁሉ እስከመቸገር በራሷ ላይም ጤናዋን እስከ ማዛባት የደረሱ እንደነበሩ ትናገራለች።

«…….አንድ ወቅት መነን አካባቢ እሳት ተነስቶ አንድ ቤት ውስጥ ተቃቅፈው ተኝተው የነበሩ እናትና ልጆች እንደተቃቀፉ በእሳቱ ተቃጥለው በጭሱ ታፍነው ሕይወታቸውን ያጡበት ሁኔታ እስከ አሁንም የማልረሳው በጣም የሚያሳዝነኝ አደጋ ነበር። በተመሳሳይም በበዓል ወቅት ቤተሰብ እየተዝናና በአንድ መኪና ተሞልተው የሚሄዱ ቤተሰቦች ላይ የደረሰው አደጋ አልረሳውም» ትላለች።

ትዕግስት ትቀጥላለች ‹‹አንዳንድ ጊዜ በሕይወት አለመመቻቸት በተለያዩ ምክንያቶች እህቶቼ ጽንስ ይፈጠርባቸዋል። ዘጠኝ ወር ተሰቃይተው ከወለዱ በኋላ በማይሆን ቦታ በሽንት ቤት በወንዝ ዳር ብቻ በጣም በሚዘገንኑ ቦታዎች ላይ ሕፃናትን ይጥላሉ። አንዳንዶች ግን በመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ ተጎድተው በአውሬ ተበልተው ስናገኛቸው ልብ ይሰብራል። ›› ትላለች፡፡

በተለይም ላዛሪስት አካባቢ በጎርፍ ተወሰደ ተብሎ እስከአሁንም ድረስ ደብዛው የጠፋውን ሕፃን ልጅ ሌሊቱን ሙሉ ቱቦ ለቱቦ እየዞረች መፈለጓንና ውጤት ማጣቷን ስታስብ በጣም እንደምታዝንም ነው የምትናገረው።

«…..እንደዚህ ዓይነቶቹን አደጋ ሳይ ቤት ያሉትን ልጆቼን ሁሉ በሕይወት የማላገኛቸው ስለሚመስለኝ በጣም እጨነቃለሁ። ይህ ጭንቀቴ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ተባብሶ ወደብቸኝነት፤ ወደመርሳት ችግር እየገፋፋኝ ነው» ትላለች።

ሥራው ይብቃኝ ብዬ አላውቅም

«…….ሥራው በጣም ከባድ ነው። እንደነገርኩሽ አንዳንድ አደጋዎች ከውስጥ አይጠፉም፤ ግን ደግሞ እኔ ሥራዬ በደሜ ውስጥ ያለ ከመሆኑ አንጻር አንድም ቀን ይብቃኝ፤ ልተወውና ሌላ ሥራ ልሥራ ብዬ አላውቅም እንዲያውም እረፍት ስሆን ከተማው እንዴት ዋለ? አደጋ የት ነበር? ምን ዓይነት አደጋ ነው የተከሰተው? የሚሉትን ስጠይቅ እና መገናኛ ብዙኃንን ስከታተል ነው የምውለው» በማለት ለሥራዋ ያላትን ፍቅር ትገልጻለች።

በአደጋ ዙሪያ ቢሠራ የምትለው

አደጋ አማክሮ የማይመጣ ከመሆኑ አንጻር እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሀገር ብዙ ግንዛቤን ሊጨምሩ የሚችሉ ተግባራት መሠራት ያለባቸው ይመስለኛል። አንድ ሱቅ ውስጥ ነዳጅ ዘይት፤ ስፖንጅ፤ ሸቀጣሸቀጥ ሁሉም ይሸጣል። ይህ ሱቅ አይበለውና የእሳት አደጋ ቢያጋጥመው ሁሉም ነገሮች ተቀጣጣይ በመሆናቸው የሚደርሰው ጉዳት ከባድ ነው። በመሆኑ ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች ግንዛቤያቸው ሊያድግ ከድርጊታቸውም ሊቆጠቡ ይገባል።

በተመሳሳይ ከተማችን ላይ አሁን አሁን ሰማይ ጠቀስ የሚባሉ ሕንፃዎች እየተገነቡ ነው። እነዚህ ሕንፃዎች የእሳት አደጋ ቢያጋጥማቸው የሚመጥናቸው ማጥፊያ የለንም። ይህም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ እኛ አደጋን የመከላከል ሥራ የምንሠራው ሰዎች ከአልባሳታችን ጀምሮ ዘመናዊ የሆነና ፈጣን ምላሽን ለመስጠት የሚያግዙ መሣሪያዎችን ልንላበስ ያስፈልጋል። ይህ ግን እየሆነ አይደለም። በመሆኑም ምን ጊዜም አደጋ ዛሬ እንጂ ነገ የሚመጣ ባለመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ትላለች።

«…… ከተማችን አድጋለች፤ ግንባታዎች ጨምረዋል። ከተማዋ ሰፍታለች፤ ነገር ግን ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። ካቶ ክሬንና ሄሊኮፕተር እንኳን ይገዛል ከተባለ ዓመታት ተቆጥረዋል። በመሆኑም እንደ ሌላው ዓለም በዘመናዊ መሣሪያ የተደራጀ ተቋም ማፍራት ቢከብደን መሠረታዊ ነገሮች የተሟሉለት ብሎም በተመሳሳይ ሰዓት ተመሳሳይ አደጋዎች ቢከሰቱ ምላሽ ለመስጠት የማይቸገር ተቋም መመስረት ይገባናል። ኅብረተሰቡም የእሳት አደጋ መኪና እየጮኸ ሲመጣ ከመከተል ይልቅ ቅድሚያ ለመስጠት ቢሞክር» በማለት መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

አሁናዊ ሁኔታ

ትዕግስት አሁን ላይ የአደጋ ምላሽ ቡድን መሪ ናት። የምትወደውን ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየሠራች ቤተሰቧን እየመራችና የአራተኛ ዓመት የዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ጥር 26/2016

Recommended For You