“ከስጋ ደዌ በሽታ መዳን ይቻላል” -ዶክተር ሽመልስ ንጉሴ

 ስጋ ደዌ በሽታ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰት ነው፡፡ በሽታውን ቶሎ ካልታከሙት ከፍተኛ አካል ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን፤ በተለይም ዓይን፣ እጅ እና እግር ላይ ጉዳት በማድረስ ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግር የሚዳርግ ነው፡፡ ለዚህም ነው በበሽታው የታየዙ ሰዎች ከጤናቸው ባሻገር በሥነ ልቦና፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ችግር ሲያጋጥማቸው የሚስተዋለው፡፡

በሽታው ለረዥም ዓመታት ከሰዎች ጋር የኖረ ሲሆን፤ የበሽታው ዋና መንስኤ ማይክሮ ባክቴሪየም ይባላል፡፡ ባክቴሪያው የተገኘው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1873 አርማወር ሃንሰን በተባለ ሳይንቲስ ነበር፡፡ ከዛ በፊት የሥጋ ደዌ በሽታ ‹‹በዘር ይተላለፋል፤ የፈጣሪ ቁጣ ነው፤ እርግማን ነው።›› በማለት ከአምልኮ ጋር የማያያዝ ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህን ምክንያት በማድረግ በታማሚዎች ላይ ከፍተኛ መገለል ይደርስባቸው ነበር፡፡ እድሜ ለሳይንቲስቱ በባክቴሪያ አማካኝነት እንደሚተላለፍ አረጋግጦ ዛሬ ላይ ብዙዎች ታክመው ለመዳን በቅተዋል፡፡

በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳ እና አባላዘር ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶክተር ሽመልስ ንጉሴ እንደሚሉት፤ በሽታው በጀርም እንደመተላለፉ መጠን በፍጥነት ካልታከሙት ወደ ሌሎች ሊተላለፍ ይችላል። ሌላው በበሽታው የተያዘ ሰው ህክምናውን ሳይከታተል ቀርቶ ለረዥም ዓመታ ከቆየ ሌሎች ሰዎች በዚህ በሽታ የመያዝ ዕድላቸው የሰፋ ነው። በተጨማሪም የተያዘው ሰው በሚያስነጥስበት እና በሚያስልበት ወቅት ከአፍ እና ከአንፍጫው የሚወጡ ፈሳሾች ይኖራሉ፡፡ እነዛ ፈሳሾች በአየር ቧንቧዎች አማካኝነት ወደ ጤነኛ ሰው ሰውነት ከገቡ በሽታው የመተላለፍ ዕድል አለው፡፡

ባክቴሪያው በጣም ደካማ የሚባል ሲሆን፤ ለምሳሌ አንድ መቶ ሰዎች ለባክቴሪያው ተጋላጭ ቢሆኑ እንኳን ከአምስት በላይ ሰዎች የመያዝ ዕድ እንደሌላቸው የሚያስረዱት ዶክተር ሽመልስ፤ ባክቴሪያው ወደ ሰውነታችን ቢገባ እንኳን በሽታን የመከላከል አቅማችን ጠንካራ ሆኖ ከተገኘ ባክቴሪያውን በመግደል በበሽታ የመያዙ ዕድላችን እንዲቀንስ ያደርገዋል ይላሉ፡፡

እንደ ዶክተር ሽመልስ ማብራሪያ በስጋ ደዌ በሽታ የተያዘ ሰው የተለያዩ ምልክቶች ሊታዩበት ይችላል። ቆዳን እና ነርቭን የሚያጠቃ እንደመሆኑም የእጅ ጣት ጫፍ እና የእግር መረገጫ አካባቢ፤ የመደንዘዝ፣ በደንብ ያለመሰማት፣ በድን የመሆን ስሜት፣ እንደ እሳት የማቃጠል (መለብለብ)፣ እንደ ኤሌክትሪክ ያለ ንዝረት ያሉ ስሜቶች ምልክቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጣም የነርቭ ጉዳት ሲያጋጥም የእጅ እና የእግር አለመታዘዝ፣ ዓይን እንዳይጨፈን ማድረግ እና የዕይታ ችግር መኖር፤ እቃ ለማንሳት መቸገር፣ መድከም፣ መስነፍ እና ቁስለት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በተጨማሪም፣ እጅ እና እግርን የመውረር ስሜትን ያስተናግዳሉ፡፡

ቆዳ ላይ ነጣ ነጣ፣ ገርጣ ገርጣ ያሉ ምልክቶች ሊታይ እንደሚችል የሚገልጹት የቆዳ እና አባላዘር ስፔሻሊስቱ ዶክተር ሽመልስ፤ አፍንጫ፣ ፊት እና ጆሮ አካባቢ ህመም የሌላቸው ጉብታዎች እንዲሁም እጅ እና እግር የመጣመም (የመበላሸት) ነገር ሊስተዋልባቸው እንደሚችል ጨምረው ይናገራሉ፡፡

ለስጋ ደዌ በሽታ አጋላጭ ምክንያቶቹ የተለያዩ ናቸው፡፡ ማንኛውም ሰው እና በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ያለ ሰው በበሽታው ሊጠቃ ይችላል፡ ፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በአንድ ቤት ለረዥም ጊዜ ተፋፍጎ አብሮ መኖር (Overcrowding) ከአጋላጭ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም ከፍተኛ ከሆነ በበሽታ ላይያዝ ይችላል፡፡ በተቃራኒው ሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም አነስተኛ ከሆነ ለበሽታው የመጋለጥ ዕድል እንደሚኖር እየተሠሩ ያሉ ጥናቶች መኖራቸውን በመጥቀስ ዶክተር ሽመልስ ያስረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ የግል እና የአካባቢን ንፅህና አለመጠበቅ፣ የተበከለ ውሃ እና ምግብ መጠቀም ለበሽታ ሊያጋልጡ እንደሚችል ይገለፃል፡፡ ይህም ለስጋ ደዌ በሽታ ብቻ ሳይሆን ለሌላ በሽታ እንደሚያጋልጥ ዶክተር ሽመልስ ያስረዳሉ። ስለዚህም እጅን በውሃ እና በሳሙና በመታጠብ፣ የግል ንጽህናን እንዲሁም የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣ ንጽህናው የተጠበቀ ውሃ እና ምግብ በመጠቀም ሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅም እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡ ፡ በዋነኛነት ግን በበሽታው ለረዥም ጊዜ ተይዞ ካልታከመ ሰው ጋር በጋራ መኖር አጋላጭ ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ፤ ስጋ ደዌ በሀገራችን የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ተሰራጭቶ ይገኛል፡፡ ሁሉም አካባቢ ላይ ሊኖር እንደሚችል ቢጠበቅም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ብቻ የመገኘቱ ነገር ላይም ‹‹ለምን ይሆን?›› ተብሎ ጥናቶች እየተካሄዱ እንደሆነ ዶክተር ሽመልስ ይናገራሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከስጋ ደዌ በሽታ ጋር በተያያዘ አዳዲስ ኬዞች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ምክንያት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ወደ ጤና ተቋም በፍጥነት አለመሄዳቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ስለዚህም ብዙዎች በበሽታው ተጠቅተው ከፍተኛ አካል ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ወደ ህክምና ተቋማት መምጣታቸው እና በቂ ግንዛቤ አለመኖሩ አዳዲስ ኬዞች እንዲመዘገቡ አድርጓል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት በስጋ ደዌ የሚያዙ ሕፃናት ከአምስት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ይመክራል። የእኛን ሀገር የተመለከትን እንደሆነ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ 10 በመቶ ሕፃናት በስጋ ደዌ በሽታ እንደተያዙ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ዶክተር ሽመልስ ያስረዳሉ። ሕፃናቱ ከቦታ ቦታ (ከሚኖሩበት መንደር) የመንቀሳቀሳቸው ነገር አናሳ እንደመሆኑ መጠን እነርሱ በሚኖሩበት አካባቢ በስጋ ደዌ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አመላካች በመሆኑ ብዙ ሥራ እንድንሠራ ያደርገናል ይላሉ፡፡

ዶክተር ሽመልስ እንዳሉት ከሆነም፤ የስጋ ደዌ በሽታ ሕፃናት ላይ ተመሳሳይ ምልክት ያሳይ እንጂ እነርሱ የበሽታውን ምልክት ለመግለጽ ይቸገራሉ።በዚህ መሠረት ምልክቶቹ በሚገባ ሲታዩ በሽታው የሚታወቅላቸው ሲሆን፤ መለስተኛ ደረጃ ላይ እያሉ ወደ ህክምና የማምጣቱ ነገር አናሳ መሆን እና ከላይ የተገለጸው ምክንያት በስጋ ደዌ የታያዙ ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ከስጋ ደዌ ጋር በተያያዘ ላለፉት 10 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ሦስት ሺህ አዳዲስ ኬዞች ይመዘገባሉ። ከአጠቃላይ የህዝቡ ቁጥር ከተነሳን ግን በሽታውን ተቆጣጥረነዋል ያሉት ዶክተሩ፤ የተያዘውም ሰው ቁጥር ትንሽ ነው ሊባል ይችላል፡፡ የዓለም የጤና ደርጅት መስፈርት መሠረት ብናደርግ የኢትዮጵያ ወደ 0 ነጥብ 2 ሲሆን፣ ከአንድ በመቶ በታች መሆኑ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ እንደ ሀገር ትልቅ ለውጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁን አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የሚታዩት አዳዲስ ኬዞች በመሆናቸው ብዙ መሥራትን ይጠይቃል ባይ ናቸው፡፡

እንደ ዶክተር ሽመልሽ ገለፃ፣ በየዓመቱ ከአንድ ሺህ በላይ አዳዲስ ኬዞች ከሚመዘገብባቸው 13 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ከአፍሪካ ደግሞ አምስት ሀገራት ሲሆኑ ናይጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሞዛምቢክ ናቸው፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት እ.አ.አ በ2030 የስጋ ደዌ ስርጭትን ዜሮ የማድረስ እቅድ አለው፡፡ ይህንን ለማሳካት ግን እንደ ሀገር ብዙ መሥራትን ይጠይቃል የሚለት ዶክተር ሽመልስ፣ ግቡን ለማሳካት አዳዲስ ኬዞች ሲያጋጥሙ እና ስርጭቱ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ቶሎ ቶሎ ማከም፣ ታካሚዎችን መለየት፣ ህክምናውን በአግባቡ እንዲወስዱ ማድረግ እና ኅብረተሰቡን ማስተማር ይገባል፡፡

ህክምናውን በተመለከተ ዶክተር ሽመልስ እንደሰጡት ማብራሪያ፤ በስጋ ደዌ ለሚታመሙ ሰዎች በሁሉም የጤና ተቋም ህክምናው በነፃ ይሰጣል፡፡ ለታካሚዎች የነርቭ እንዲሁም የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው ‹‹ባክቴሪያው መጠኑ ምን ያህል ነው?›› ለሚለው ናሙና በመውሰድ ያለበት ደረጃ ይለያል። በዚህም መሠረት የባክቴያው ቁጥር አናሳ ከሆነ መድኃኒቶችን እስከ ስድስት ወር እንዲወስዱ ይደረጋል። የባክቴሪያው መጠን ከፍተኛ ከሆነ እና የበሽታው ደረጃ ከፍ ያለ ከሆነ ግን መድኃኒቶችን ለአንድ ዓመት እንዲወስዱ ይደረጋል።

በሽታው የሚድን ሲሆን ባክቴሪያውም ቀላል የሚባል አይነት ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ የበሽታው ደረጃ ከፍ የሚያደርገው ቶሎ የመገኘቱ እና ያለመገኘቱ ነገር እንደሆነ በተደጋጋሚ አጽንኦት ሰጥጠው የሚናገሩት ዶክተር ሽመልስ፣ ስጋ ደዌ የሚድን በሽታ በመሆኑ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ የጤና ባለሙያዎች ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ስልጠና መስጠት ይገባል። ኅብረተሰቡም በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ መሥራት ያስፈልጋል በማለት ያስረዳሉ፡፡

ስጋ ደዌን ለመከላከል ክትባት የለውም። ማንኛውም ሰው ቆዳው አካባቢ የመቆጣት፣ የመደንዘዝ እና የተለየ ምልክት ካየ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም በማምራት ራሱን እንደሁም ሌሎችን ሰዎች ከአካል ጉዳተኛነት፤ እንዲሁም ከስነ ልቦናዊ ችግር መከላከል እንደሚኖርበት ያሳስባሉ፡፡

በቀጣይም ስጋ ደዌን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሠራ ሲሆን፤ በሽታው ያለበት ሰው በጉርብትና፣ አብሮት የሚኖረው ሰው እና በአካባቢው ያሉትን ሰዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ አንድ እንክብል በመውሰድ ለመከላከል ጅምር ሥራዎች አሉ፡፡ በዚህም እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በበሽታ እንዳይያዙ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን በሀገራችን ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ዶክተር ሽመልስ ይጠቁማሉ። በአጠቃላይ ስጋ ደዌን ለማጥፋት በዚህ ዙሪያ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ከሆኑ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቂ በጀት በመበጀት፣ በትብብር እና በድጋፍ፤ እንዲሁም ማኅበረሰቡን በማንቃት በሰፊው መሥራትን ይጠይቃል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You