በሕይወቴ የምቆጭባቸው ሁለት ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው በነሶቅራጠስ ዘመን አለመወለዴ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በእኔ ዘመን ሶቅራጠስን መሳይ ሰው አለመፈጠሩ ነው። የኦሾና የሶቅራጠስ ስለሕይወት እይታ ይማርከኛል። ከእየሱስ ጋር አብረው ሕይወትን የፈጠሩ ይመስል «ሕይወት ማለት እንዲህ ናት»፣ «መኖር ማለት ይሄ ነው» ሲሉ በሰሚ ልቦና ውስጥ ጉጉት ይፈጥራሉ። ግን እንዴት ሕይወት ገብቶኝ ሱሰኛ ሆንኩ? ግን እንዴት ራሴን ማፍቀር አቃተኝ? ያልመላለስኩት ጥያቄዬ ነው።
አሁን አሁን ቁጭቴ ወደ ሦስት ከፍ እያለ መጥቷል። እየሱስ ምድር ላይ ሳለ ብኖር እላለሁ። በከብቶች በረት ሲወለድ፣ ውሃ ቀድቶና እንጨት ለቅሞ እናቱ ማርያምን ሲያገለግል፣ በጭቃ ህያው ወፍ ሲሠራ ባየሁት እላለሁ። ወደ ገሊላ ሲያቀና፣ በዶኪማስ ቤት ውሃውን ወደ ወይን ሲቀይር ብታደም እላለሁ። የቢታኒያ ድንጋዮች ሲያመሰግኑት፣ በበርሀ ውሃ ሲያፈልቅ፣ በደብረታቦር በብርሃን ባየው እመኛለሁ። መካኗን ሳራን ሲያስቅ፣ ፈርኦንን ሲቀጣ፣ ለአብረሃም ቃል ሲገባ፣ ኖህን ከጥፋት ውሃ ሲያድን ጎኑ ብሆን እላለሁ።
በጌቴሴማንያ በአትክልቱ ስፍራ፣ በጥብሪያዶስ በባህሩ ዳር፣ በዳናው ጥላ በጌርጌሴኖን አብሬው ቆሜ ቢሆን፣ ጣሊታን ከሞት ሲያስነሳ፣ መቅደላዊት በእንባዋ እግሩን ስታጥብ፣ የሴራብታዋን ሴት ሲያነጋግር ሰምቼ ቢሆን። በአህያ ውርንጭላ ሲጓዝ፣ የማርያም እህት ማርታ መልካም እድልን መርጣ እግሩ ስር ስታርፍ፣ ዘኪዮስ ሊያየው ዛፍ ላይ ሲወጣ፣ ከተከተሉት ከአምስት የገበያ ሕዝብ አንዱን ብሆን። በዕለተ አርብ ዓሣ ካበላቸው አምስት ሺህ እንግዶች አንዱን ሆኜ ብሆን ያምረኛል። እንደዛች ለአስራ ሁለት አመት ደም እንደሚፈሰሳት ሴት ቀሚሱን ዳስሼው ቢሆን፣ እንደ ጰርጠሚዮስ የናዝሬቱ እየሱስ ሆይ ብለው፣ እንደ ሀር ሻጪዋ ሊዲያ በድምጹ ልቦናዬ ቢከፈት አስባለሁ።
እያሱ ፀሐይን ሲያቆም፣ ኤሊያስ ዝናብን ሲገስጽ፣ ሙሴ ባህር ሲከፍል፣ ዳዊት ጎልያድን ሲጥል፣ ደሊላ ሳምሶምን ስትረታ፣ ቤርሳቤህ ከኦርዮን ስትሸሽ፣ ሄሮዲያዳ አንገት ስታስቆርጥ፣ አስቴር ሀማስን ስትሰቅል፣ ሜልኮል ስትዘባበት፣ ኦዚያ ሲቀሰፍ፣ ሩት ስትቃርም፣ ሶስና ከእደረበና ስትድን፣ አፎሚያ ሲከብር፣ እስቂያስ ሲያነባ፣ አጋር ስትሰደድ፣ አናኒያና ሰጲራ ሲዋሹ፣ አክአብ ሲዝት፣ ኤልዛቤል ሲያቅራራ፣ ዮሴፍ ሲሸጥ፣ አዳም ሲያንቀላፋ ሰው ሆኜ ኖሮ ስል እመኛለሁ። ቃየል በወንድሙ ላይ ሲነሳ፣ ሄዋን ሉድ እና ቅሌማን ስትወልድ፣ ታራ ጣኦት ሲያመልክ፣ ስምኦን ዓይኑን በወስፌ ሲያፈስ፣ ፌቨን ወደ ቆረንቶስ ስትላክ፣ ሀናና ፍናና ሲነቋቆሩ ባይና ብሰማ። ጴጥሮስ ሲክድ፣ ይሁዳ ሲያስመስል፣ በርባን ሲፈታ፣ ቬሮኒካ የጌታን ደም ስትጠርግ ሕይወት ኖሮኝ ቢሆን እላለሁ።
ጴጥሮስን ከቀራጭነት፣ ስሞንን ከዓሣ አጥማጅነት፣ ማቲያስን ከውንብድና ወዳጁ እንዳደረገ እኔንም ከሱሰኝኔ አውጥቶ ደቀመዛሙሩ ቢያደርገኝ ስል አይሆኑ እመኛለሁ። በዚህ ዓለም ላይ እየሱስን እንደመከተል ምን ጥበብ አለ? ግን እኮ በራሴ ዘመን ላይም እየሱስን መፍጠር እችላለሁ። ያን ማድረግ ለምን አቃተኝ? ያኔ ብቻ አይደለም እየሱስ ዛሬም ጌታ ነው። ለምን በራሴ ውስጥ እሱን መፍጠር ተሳነኝ? ሰው ከምኞት ወጥቶ ላመል ፈቀቅ እስካላለ ድረስ የትናንት ምርኮኛ ነው። ቅርቡ እየሱስ ርቆኝ በማይሞትበት ዓለም ላይ እየኖርኩ የተወለደበትን ዘመን እናፍቃለሁ። እሱ እኮ ዛሬም አዲስ . . ዛሬም ስለ እኛ ጎለጎታ ነው ብሎ የሚነግረኝ አማኝ አጣሁ። ለነገሩ ቢነግሩኝስ መች ሰምቼ። ክርስትና የተነሳሁበት የአርባ ቀን አጥቢያዬ አጠገቤ አይደል። ቄሱን ሳልሰማቸው መቼ ቀርቼ አውቅና። ያን በስብከቱ ጉድ የተባለለት ሰው ጆሮ ግንዴ ላይ አይደል? መች ከእውነቴ አራቁኝ። መች ከምኞቴ አሸሹኝ። መች ወደ እየሱስ አደረሱኝ። አውቆ የተኛን አሉ . .
መርፌ ሲለግም መች ቅቤ ይወጋና?
እንደልማዴ የማጨሰውን ሲጋራ በመሀል ጣቴ ሰክቼ፣ እንደ እኔ ግራ የገባት የምትመስለውን የከሰዓት ጀምበር ተከትዬ እግሬ ወደ ወሰደኝ ወደ ሆነ ቦታ ተራመድኩ። ሰው ግን ሃሳብ ይጠፋዋል? ድንገት መጥቶ ሃሳብ ይጠፋኛል። ሃሳብ ቢኖረኝ ኖሮ እግሬ እንደመራኝ አልሄድም ነበር። እየሱስን ያልደረስኩበት ያለ ሃሳብ እግሬ እንደመራኝ እየተጓዝኩ ይሆን? አዎ፣ እንደዛ ቢሆን ነው። እንደዚህ ካልሆነ ሌላ ምንም አይሆንም። አንዳንድ ልማዶች የአለመርባት አዲስ አመቶች ናቸው። ሰው በሃሳብ እግሮቹን ካልመተረ መድረሻው የለውም አልኩ።
ብቻ እግሬን ተከትዬ ራቅ ብዬ ሄድኩ። የሲጋራዬ ዕድሜ አልቆ የመጨረሻ ጭሴን ወደ ሆዴ ስቤ ሌላ አቀጣጠልኩ። እየሱስን በእንደ እኔ ዓይነቱ ወንበዴ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ፓስፊክ ውቅያኖስን በማንኪያ ጨልፎ ማጉደል መስሎ ታየኝ። ማን ነበር ያ በትንሽ ጽድቅ ከማንም ቀድሞ ገነት የገባው? ማን ነበረች ያቺ ስትዘሙት ኖራ በእግዜር ጻድቅ ዓይኖች የታየችው? ገድለ ኦሪት . . ገድለ ሀዲሴን እንዳላበላሽ በሃሳቤ መሀል እየተሰነቀረ . . አንተ እኮ ማለት እያለ ያመጻድቀኝ ጀመር።
ያለሃሳብ መጓዝ በመኖር ውስጥ ያለ የሰው ልጅ ያልደረሰበት ምቹ የነፃነት ስፍራ መስሎ ታየኝ። ግን አይደለም እንደማሰብ ጉልበታምና ሞገሳም ነፃ ዓለም አላየሁም። ገብቶኝ እንኳን ልወዳጀው አቅም አጣሁ። አለማሰብ አለማወቅ ነው። ዝም ብሎ መኖር . . ዝም ብሎ መሞት። ሕይወትን የምናምርባት በማሰብ ውስጥ ነው። ሞትን የምንንቀው በስልሳሌ ውስጥ ነው።
ባለማሰብ ብዙ ተጉዤ መድረሻዬን አንድ ስፍራ አደረኩ። ሰፊ ግቢ ውስጥ በቅለው የግቢውን ውጪ አውራ ጎዳናውን ባጠሉ ዛፎች ስር። ጥላው ያምራል . . በተደራረቡና በተቃቀፉ ረጃጅም ዛፎች የተሠራ ጥላ ነው። የአስፓልቱ ግማሽ ድረስ ተወርውረው ጥላማ አድርገውታል። የግንቡን አጥር ተደግፋ አንዲት ሴት ቆማለች። አለማሰቤ ሃሳብ ጀመረ። ምንም እንኳን ተጉዤ ባልደርስበትም ከክርስቶስ ምክረ ሃሳብ ማፈንገጥ አልወድም። እንዲህ ስል ጻድቅ ነኝ እያልኩ ሳይሆን ቢሆንለት ለእውነት ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው ነበርኩ እያልኩ ነው። ከጎለጎታ በፊትም ሆነ በኋላ የእየሱስ ሕገ ሥርዓት መነሻ ያደረገው ፍቅርን ነው። አቅም ኖሮኝ ብችል እንደ እየሱስ ጠላቶቹን ሁሉ በፍቅር የረታ መሆን እፈልግ ነበር። ግን አልቻልኩም . . የምችለው አንድ ነገር ነው አቅም አጥቼ እንዳልጠላ መሆን።
ፊት ለፊቴ አንዲት ጉብል የቆመችበት ጥላ . . ጥላው አማረኝ። ከፀሐይ ወደ ጥላ ልብ ላይ የሚያርፍ የሆነ መንፈስ አለው . .። ያ መንፈስ አረፈብኝ። ሲጋራዬን እያቦነንኩ ከወጣቷ አጠገብ ሄጄ ቆምኩ። ለትዝብት በሰሉ ዓይኖች ፊት ለፊት ጎዳናውን ትቃኛለች። ሃሳብ ብትዘራብኝ ስል ተደናብሬ ሄጄ ከሃሳቧ ላደናቅፋት ፈለኩ።
ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም ስል ከሲጋራዬ አንድ ጊዜ ስቤ «እንኪ» ስል ዘረጋሁላት።
እንደዛ ቀን አልተገላመጥኩም። ለምላሹ ብዙ መልካም ነገሮች ነበሯት። እሷ ግን ግልምጫን አስቀድማ እንዳልነበረ አደረገችኝ።
አልተከፋሁም። «ከሌሎች ጋር ለመኖር ብዙ አማራጮች አሉን። እንደ መልካም አንደበት ግን ጥሩ አማራጭ የለንም» ስል ምንም እንዳልመሰለኝ እንድታውቅ በዚያውም እንድትማር ቃል ወረወርኩላት።
«የሰጠኸው እንደሚሰጥህ አታውቅም?»
«የሰጠሁሽ መጥፎ መሆኑን በምን አወቅሽ?»
«የሚረቡ ወንዶች ጣታቸው መሀል እስክሪፕቶ እንጂ ሲጋራ አይዙም» ብላ ወደ ትዝብቷ ተመለሰች።
ኩምሽሽ አልኩ። «እኔ ያለኝን ነው የሰጠሁሽ» ስል ድንጋጤዬን ለመደበቅ ሞከርኩ።
«ያሉን ነገሮች ሁሉ የማይጠቅሙን እንደሆኑ አታውቅም?»
«አልስማማም። ካጣናቸው እና ከሌሉን ነገሮች እንደሚበልጡ ነው የማውቀው።»
«እንደዛም ማሰብ ትችላለህ። ከሁሉም የሚበልጠው መልካም አንደበት ነው» ስትል የሰማሁ መሰለኝ . . ?
«አዎ ሰምተሀል . .! »
«እንግዲያውስ ከሁሉም የሚበልጥ ሌላ ነፃ አውጪ እውቀት እንዳለም ጨምርበት» ብላኝ ትታኝ ሄደች። ከጥላው ወጥታ ፀሐዩዋ ላይ ስትማገድ የሆነ ነገር ቅር ቅር አለኝ። በወጣችበት ቅጽበት ተሲያቷን ትታ ጀምበር እንደ ጌታ የስቅለት ቀን ጨላለመች።
ወደ እየሱስ ታደርሰኝ እንደሁ ስል ተከተልኳት። አስወጣችን እንጂ ከመች ጀምሮ ነው ሴት ወደ ገነት የምታስገባው? አንዱ ልቤ እንዲህ ይለኛል። ቢሆንም መራመዴን አላቆምኩም።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 24/2016