እኔ አይደለሁም፤ አርዕስቱ ነው ያለው። እኔም ‘’አሜን!!” ብያለሁ። ታዲያ አርዕስቱ ማን ነው፤ የማን ነው? ብሎ ለጠየቀ፤ ጥያቄው አግባብ ነውና ልመልስ ግድ ይለኛል። ይህን ያለውም፤ ለዘመናት ሲገፋ ለኖረው የኪነ ጥበብ ባለሙያ፤ “የተሰበረውን ልቡን ለመጠገን እሻለሁ” በማለት ከሦስት ዓመታት በፊት የተነሳው አንድ ለ´ናቱ ነው። እሱም የ”ክብር ለጥበብ” ዓመታዊ የዕውቅናና የሽልማት ሥነ ሥርዓት ነው። አንድ ለናቱ ማለቴ፤ እንደ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት ለሀገራችን የኪነ ጥበብ ባለውለታዎች ዕውቅና ለመስጠት ብቸኛው ዓውደ ሽልማት በመሆኑ ነው።
መሸለሙን፤ ያየ የሰማ ሁሉ ይሸልም ይሆናል። ዕውቅና ለመስጠቱ ግን ዕውቅና ያስፈልጋል። መቼም የደረሰና ደስ ያለው ሁሉ እያነሳ ፊት ላይ የሚመርገው ባለመሆኑ ነው። ስለዚህ አንድ ለ´ናቱ ካልኳችሁ ከክብር ለጥበብ ዕውቅና በስተጀርባ አንድ እውቅ አካል አለ ማለት ነው። አዎን፤ እርሱም የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ነው። ይህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ካሉበት ኃላፊነቶች አንዱ በኪነ ጥበብ ዘርፍ በሚከናወኑ ተግባራት እጅ ከማስገባቱም በዘለለ ትልቅ የሆነ የባለቤትነት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
የሆነው ሆነና በአሁኑ ሰዓት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጀመረው የ”ክብር ለጥበብ” ዓመታዊ የዕውቅና ዝግጅት፣ ከባዶ አንድ ይሻላል “እሰየው!″ የሚያስብል ነው። ከምንም ደግሞ አንድ ለናቱ ይበጃል። ታዲያ ባሳለፍነው ሳምንት ይህን በተመለከተ ተቋሙ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። በዛሬው የዘመን ጥበብ አምዳችንም ከዚሁ መግለጫ ላይ እየዘገንን፤ ማወራረጃ ይሆነን ዘንድም ከማይጎድለው የጥበብ ውሀ ምንጭ ጨለፍ እያደረግን መጎንጨታችን እንቀጥላለን።
“ክብር ለሚገባው ክብርን እንሰጣለን!” አሉ፤ ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ። መግለጫውን በሰጡበት መድረክ ላይ ነበር ይህን ያሉት። ክብርት ወ/ሮ ነፊሳ አልማህዲ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብ ስነ-ጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው። ለዛሬው የመነሻ ሀሳብ የሆነንን፣ ሙሉውን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡትም እኚሁ ሴት ነበሩ። ተቋሙ በ”ክብር ለጥበብ” የሽልማትና ዕውቅና መንገድ መጓዝ ከጀመረ የዘንድሮው ለሦስተኛ ጊዜ ቢሆንም የዘንድሮው ግን ለየት ያለ ስለመሆኑ አስቀድመው ጠቆም አድርገው ነበር። ድግሱም በብዙ ባለሙያዎች የተሰናዳ በመሆኑ፣ የጥበብን ጣት የሚያስቆረጥም እንደሚሆንም የመግለጫው ሽታ ያሳብቃል። ለመሆኑ “ክብር ለጥበብ” ምንድነው? አላማውስ? ነገሩ እንግዳ አይደለም። በዕድሜ፤ የሦስት ዓመት ጨቅላ ቢመስልም፤ ሥራና ግብሩ ግን ገዘፍ ያለ ነው። የዝግጅቱ ዋና ዓላማ በኪነ ጥበብ ዘርፍ የሀገር ባለውለታ ሆነው ያለፉትንም ሆነ የተረሱትን ማስታወስ፤ ያሉትንም “ከጎናችሁ ነን″ ብሎ ማበርታት ነው።
በ2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ አሀዱ ብሎ ጀመረ። የዚያን ጊዜ ታዲያ የሽልማት እንጂ የዕውቅና አልነበረም። ነገሩም በውድድር ነበረ። በዚህም ምክንያት በክብር ለጥበብ የ2013 ገጽ ላይ ሦስት ጥቋቁር ነጠብጣቦች ነበሩበት ለማለት እንችላለን። የመጀመሪያው ጥቁር ነጥብ፤ የውድድር መሆኑ ነው። ኋላና ፊት፤ ግራና ቀኝ አሻግሮ ከማየት ይልቅ በጊዚያዊ የውድድር መንፈስ የታጠረ አድርጎታል። ሁለተኛ ነጠላ እይታ ነው፤ የሚሸለሙ አካላት የሚመዘኑት በወቅቱ ባሳዩት ጊዚያዊ ሥራና ብቃት በመሆኑ ቀደም ሲል ድንቅ ሥራ ላበረከቱ እድሉን ያጠብባል። በሦስተኛ ደረጃ ሁሉን አካታች ካለመሆኑም በላይ በሕይወት የሌሉትን ከጨዋታ ውጭ ማድረጉ ነው።
2ኛው ዙር በ2014 ቀጠለ። ክብር ለጥበብ ማሊያውን ቀይሮ መጣ። ከውድድር ይልቅ የወዳጅነት መንፈስ ይኖረው ዘንድ የሽልማት ሳይሆን የዕውቅና እንዲሆን ተደረገ። ሌላም አለ፤ በ1ኛው ዙር ያልተካተተው የሙዚቃ ዘዋሪ (የዲጄ) ዘርፍ እንዲካተት ተደረገ። ከለውጡ ስር ጥቁሩ ነጥብ እዚህም ነበር። የፍትሀዊነቱ ነገር ከማጠያየቅም የሚያነጋግር ጉዳይ ሆኖ ታየ። በአንዳንድ ነገሮቹ በቂ ጥናትና ዝግጅት የተደረገበትም አይመስልም ነበር። መድረክ ላይ ወጥቶ የነበረ አንድ ሙዚቀኛ፤ ይገባሃል ተብሎ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ እዚያው ከመድረኩ ላይ እንዳለ፤ በስህተት ነው በማለት ተቀይሮ በምትኩ ሌላ እንዲሰጠው ተደርጓል።
በዚህ ብቻም ሳይሆን ዕውቅናው የሚገባው ለማን ነው፤ የሚለው በቅጡ ያልተጠናበት መሆኑም በግልጽ የሚታይ ነበር። እንዲህ ቢሆንም ቅሉ፤ ከጥሩነትና ከምስጋና የሚያጎድለው ግን አልነበረም። ቀጣዩ 2015፤ ጥቁርም ነጭም የሌለበትና ምንም ያልተጻፈበት ባዶ ገጽ ነበር። ሳይካሄድ ቀረና፤ ለ2015 ያሏት ሦስት ዞራ ለ2016 ሆነች። 3ኛው ዙርም በትላንትናው የጥር 22 ላይ አረፈ።
2016 በክብር ለጥበብ ውስጥ ያለፉትን ዓመታት ሁሉ ልታስንቅ ወገቧን ታጥቃ ሸብ ረብ እያለች ስለመሆኗ አስቀድሞ ተነግሯል። “ያለፉት ዙሮች ብዙ ተምረንባቸዋል። የታዩብንን ደካማ ጎኖቻችንን ጥለን፤ መቀጠል ባለባቸው ጠንካራ ጎኖቻችን ላይ አዳዲስ ነገሮችን በማከል፤ 2016ን በተለየ አመጣጥ መጥተናል” ላሉት ነፊሳ አልማህዲ፤ እኛም `እንኳን በደህና መጣችሁ!` በማለት፤ ተቋማቸው ይዞ የመጣውን የዘንድሮውን የክብር ለጥበብ ስጦታ በደስታ መቀበል ጨዋነት ነው። ታዲያስ ክብር ለጥበብ በ2016 ምን ይዞ እንዴትስ መጣ? ይዞት እንደሚመጣቸውና ከተነገሩት አንዱና ትልቁ፤ ዕውቅናው የሕይወት ዘመን ከመሆኑም `ሥራውን ለሠሪው፤ ሙያውን ለባለሙያው` የተወ መሆኑ ነው።
ዕውቅና የሚሰጣቸውን ባለውለታዎች የመምረጡን ኃላፊነት ለየዘርፉ አዋቂዎች ሰጥቷል። ይህ የነበረውን የፍትሀዊነት ጥያቄ ለመመለስ ሁነኛው መንገድ ነው። ለዚህም ሲባል ረዥም ጊዜ የፈጀ ዝግጅት በማድረግ በእያንዳንዱ የኪነ ጥበብ ዘርፍ፤ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተሸላሚዎቹን የሚመርጡ አቢይ ኮሚቴዎች ተዋቅረው በጥናት ላይ ሰንብተዋል። በአዲስ አበባ ቅጥር ላይ ብቻ ሲሽከረከር የነበረው ይህ ዕውቅና፤ ከበባውን ጥሶ ወደ መላው የሀገሪቱ ክፍል በመስፋት ሀገር አቀፍ ሆኖ መጥቷል። ከወጣት እስከ አንጋፋ ያሉ የጥበብ ባለሙያዎች ለክብር ይታጩበታል፤ በዕውቅና ይሞሸሩበታል።
2016 እና ኪነ ጥበብ፤ ዘንድሮና ክብር ለጥበብ፤ 50 ያህል የክብር ኒሻኖች በዕውቅና ሙዳይ ውስጥ ተቀምጠዋል። በዘርፉ ውስጥ የተካተቱ 12 ኪነ ጥበባት ከዚህ ክብር ለመቋደስ ልባቸውን ከፍተው ይጠባበቃሉ። ከእያንዳንዱም እንደ ስፋትና ግዝፈታቸው ከ3 እስከ 5 ያህል ጥበበኞች ይመረጣሉ። በድምሩም እስከ 50 ሰዎች ዕውቅናውን ያገኛሉ። “ይህን ጥሶ የመጣው ማን ይሆን?″ የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችሉትም የኮሚቴው አባላት ብቻ ናቸው።
መነሻችን ወደ ነበረው እለት እንመለስና የክብር ለጥበብ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ጋዜጠኞች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፤ ክብርት ነፊሳ አልማህዲ ያነሷቸው ሌሎች ሀሳቦችም ነበሩ። ከእነዚህም አንደኛው በኪነጥበቡ የማይዘነጋ አሻራ ያሳረፉትን ዕውቅና ከመስጠቱ ባሻገር መንግሥት ፊቱን ወደ ኪነ ጥበቡ አዙሮ ዘርፉንና ባለሙያውን በቋሚነት እንዲያግዝ ስለማድረግ ነበር።
“ኪነ ጥበቡና መንግሥት ፊት ለፊት የሚገናኙበት ድልድይ አለመኖሩ ትልቁ ችግር ሆኗል። ስለ ዘርፉ፤ በሕገመንግስቱ የተቀመጠ ምንም ነገር የለም፤ በመሆኑም አዋጅም ሆነ የተለያዩ ደንቦችን ለማርቀቅ እኛም ፈተና ሆኖብናል። ከዚህ አንጻርም መንግሥትን ለመጠየቅ የሚያስችል አግባብ አለመኖሩ ነው። ቢሆንም ተስፋ ሳንቆርጥ ነገሮችን ለመቀየር በመሥራት ላይ ነን” ሲሉ ነበር የተናገሩት። “እየሠራንበት ነው″ ካሏቸው ጉዳዮችም አንዱ፤ የዘርፉ ባለሙያዎች ስለሚገለገሉባቸውና በውድ ዋጋ ከውጭ ስለሚገቡት ቁሳቁሶች ሲሆን፤ የተጫነባቸው ከባድ የሆነ የቀረጥ ቀንበር እንዲነሳላቸው ከሚመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር በመነጋገር ላይ ስለመሆናቸው ገልጸውታል። በኪነ ጥበቡና በመንግሥት መሀከል ትልቅ ግንብ ስለሆነው ሕጋዊ ጉዳይም እንዲሁ በመፍትሔ ፍለጋ መንገድ ላይ ስለመሆኑ።
“ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም” ቢሉም አበው፤ ክብር ለጥበብን እንደተደገፍን በሀሳብ ጥቂት አሸልበን፤ በሸለብታው ሰመመን አንዳንድ ነገሮችን እንይ።
ደጋግመን ስለጉድለቶቻችን ማንሳታችን፤ ለነቀፌታ ሳይሆን እንዲያው የተሻለ ሆኖ ለማየት ካለን ጉጉትና ከዚህ በላይ እዚህ ጋር መቆየት እንደሌለብን በአንክሮ ለማሳሰብ ነው። ካነሳን አይቀርም በሸለብታው ይቺን ለመጠየቅ ወደድኩ፤ የኛ ኪነ ጥበብ ወላጅ አልባ፤ ባለቤት አልባ መስሎ እድሜ ዘመኑን ጉስቁልቁል ማለቱ ለምንድነው? ስል እራሴን ጠይቄ ምላሹንም ከራሴው ጠበቅኩኝ፤ እናም እኚህኑ ምላሾች አገኘሁ። ስለሌለን ሳይሆን ስላልገባን ነው። ባለቤት ሆነን የኔ ነው ማለቱን እንፈራለን።
ግራ ቀኙን ቢመለከት አጥብቆ የሚይዘው አለመኖሩን ስለተረዳም ይሁን ብቻ፤ ኪነ ጥበቡም በሞቀበት ሁሉ እየዞረ ሲሟሟቅ ከርሟል። ወላጅ አልባነት፤ ባለቤት አልባነትም የተሰማው እንደሆነም አንዳንዴ ቁዝም ይላል። ሌላው ቀርቶ፤ እንደ ሀገር ያሉትን የሽልማት ተቋማት ብንመለከት እንኳ በኪነ ጥበቡ ምን አይነቱ ድርቅ ገባ የሚያስብል ነው።
በአብዛኛዎቹ ሀገራት የሚሠራ ሰው ይኑር እንጂ በሰበብ አስባቡ እስኪመስል ድረስ ሽልማቱ በሽበሽ ነው። እንደኛ፣ ወደ መንግሥት ዞረን ብንጠይቅ … ነጥብ ላለመጣል ታህል አንድ ለናቱ የ”ክብር ለጥበብ” አለ። ከዚህ ወጣ ስንል ደግሞ፤ በዋናነት ሁለት ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፤ “ለዛ” እና “ጉማ” አዋርድ የተሰኙት የሽልማት ተቋማት። ካላቸው ጥሩ ነገሮች ጎን የሚነሳባቸው ጥያቄ ቢኖርም ልንጠቅስም ሆነ በቋሚነት “አሉን″ ልንል የምንችለውም እነዚህኑ ነው።
በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ስለ ሀገራቸው ደም እንባ ተፍተው፤ ለነብሳቸው እንኳን ሳይሳሱ እንደ ላንባ በርተው፤ እንደ ሻማ የቀለጡ እጅግ ለቁጥር የሚታክቱትን እረግጠን አልፈናል። ውለታን የምንበላ ውለታ ቢስ ሆነንም አይደለም። ደግሞም ለመስጠት የምንፈራ ንፉጎችም አይደለንም። አብዛኛውን ጊዜ አንዳንዶች ወድቀው የተረሱ መሆናቸውን አይናችን እያየ፤ ልባችንም እያወቀ፤ ታዲያ ለምንድነው ከንፈር መጦ ዝምታን የምንመርጠው? ምክንያቱም፤ “አመሰግናለሁ!” ከማለት ይልቅ “ሙያ በልብ ነው” ብለን፤ ክፉውንም ደጉንም ዋጥ ማድረጉን እንወዳለን።
ብዙውን ጊዜ ደግሞ፤ ባለቤቶቹ እኛው እራሳችን መሆናችንን ስለማናምንበት ከኃላፊነቱ እራሳችንን እናገላለን። ለዚህ፤ ከኛ ውጭ የሚመጣና ማድረግ ያለበት ሌላ አካል አለ ብለን ስለምናስብም፤ አንዱ ለአንዱ እየተዋቸው ባለውለታዎቻችን በመሀል ቤት ተረስተው ይቀራሉ። ጥበበኛ ልጆቿ ሲመቱ የምትደማው ጥበብ ናት። የወደቀውን ልጇን አይዞህ! ብለን ስናነሳው፤ የምናነሳው እራሷኑ ጥበብን ነው። ቀላል ነገር አይደለም ለብዙ ዘመናት ሲጎትተን የኖረው ነገር፤ ለኪነ ጥበብ የሚያዝን ጥሩ ልብ ስለጠፋ ሳይሆን እነዚህን ልበ ደጋጎች፤ ለአንድ ዓላማ የሚሰበስብ መጥፋቱ ነው።
ኪነ ጥበቡ የትልቅ ትንሽ ሆኖ የታየው በግለሰብና ባለሀብቱ ዘንድ ብቻም ሳይሆን በመንግሥትም ጭምር ነው። ሕገ መንግሥቱ እንኳን ይህን ያህሉን ፍሪዳ በሬ፤ እንደ እንቦሳ ጥጃ ከበጎቹ ጋር አስሮት ቆይቷል። የሚሰጠውም መኖ የበጎቹን ያህል ነውና ሳይበላ ቢከርም ጊዜ፤ ዛሬ ላይ ቆርቁዞ ከሰባው ይልቅ ከሲታውን አስመለከተን። ይሄው ዛሬም ድረስ “አንተ የጥበብ እንቦሳ፤ ምነው የማታድግ? ማንስ ነው የረገመህ?” እንዳልን አለን። የሚረግም ይኑር እንጂ እርግማኑስ ብዙ ነው። እያማረሩ ብቻ ከመኖርም እርግማኑን በምርቃት ማርከሱ የተሻለ ነው ባይ ነኝ።
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ክብርት ነፊሳ እንዲህ ነበር ያሉት፤ “በተቋማችን እንደተሰጠን ኃላፊነት፤ ለኪነ ጥበቡ የምንመኘውን ያህል እንዳንሄድ እንቅፋት የሆነብን ነገር አለ። በሕገ መንግስቱ የተቀመጠለት ሕጋዊ ማዕቀፍ አለመኖሩ ነው። ነገሮችን ለማስፈጸም በተንቀሳቀስን ቁጥር የሚገጥመን እክል ብዙ ነው። ያም ሆኖ የጀመርናቸው ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛው የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሥራ የሚጠቀሙባቸውን፤ በከባድ ቀረጥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ቁሳቁሶች ጉዳይ ኪነ ጥበቡን በሚያበረታታ መልኩ እንዲሆን፤ ከሚመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር በመነጋገር ላይ ነን።
ሁለተኛው ደግሞ እንደ ስፖርቱ ሁሉ ኪነ ጥበብም ከመንግሥት ሠራተኞች ወርሀዊ ደመወዝና ከመሳሰሉት፤ ተቆራጭ የሚደረግ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው እየሠራንበት ነው” በምትለዋ ሀሳብ ላይ፤ ዘርፉ በሁለት እግሩ ቆሞ መሄድ እንዲችል ከራሱ በላይ የሚደርስለት የለምና በሌሎች ሀገሮች እንደምንመለከተው እራሱን ችሎ መንግሥትንም መደገፍ የሚችልበትን የገቢ ምንጭ ለማግኘት መሥራት ይኖርበታል፤ የምትለዋን ጣል አድርገውበታል።
ገና ምናቸውም ያልተነካ አንጡራ የባህልና የኪነት ሀብታት አሉን። በዚህ ውስጥ፤ ለመሥራት ሞክሮ ያበላሸውን ሁሉም በገባው ልክ ተጠያቂ ያደርገዋል፤ ግን ስላልተሠሩትና ስለተረሱትስ ማን ይጠየቅ? . . . ዘርፉን በባለቤትነት የሚይዙ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ብዙ ነገሮች ሲበረዙና አይሆኑ ሁነው ሲከስሙ እንመለከታለን፤ እና ማንስ በምን አግባብ ይጠየቃል? ህጋዊ ማዕቀፍ ያስፈልጋል።
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ”ክብር ለሚገባው ክብርን እንሰጣለን!” ብለውም ነበር። በርግጥም በዚሁ ቃል ከእንግዲህ ወዲያ ብዙ ነገሮች እንደሚለወጡ ተስፋ እናደርጋለን። ካነሳናቸው ነገሮች ባሻገርም፤ እየተሠራባቸው ነው የተባሉ ጉዳዮችም እንዲሁ። እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያነሳናቸውም በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫና የሚካሄደውን ዓመታዊውን የ”ክብር ለጥበብ” የዕውቅና ሥነ ሥርዓትን ተንተርሰን እንደመሆኑ፤ ታዲያ ስለ ዕለቱስ የት አለ? ማለታችሁ አይቀርም። ለኛም፤ እንጀራውን አቅርቦ ወጡን መከልከል እንዳይሆንብን፤ ስለ ዕለቱና የዕለቱ አጀቦች፤ በሌላ ጊዜ በሰፊው እናወጋበታለን። ለአሁን፤ ለዛሬው ግን “ክብር ለጥበብ . . . አሜን!!” ብለን እንጨርስ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 23/2016