ከምስጋና ይልቅ ለነቀፌታ የሰሉ አንደበቶች

በሰለጠኑት አለማት ከሚታዩ የሚያስቀኑ ባህሎች መካከል መመሰጋገን አንዱና ዋነኛው ነው። በእነዚህ ሀገራት በትንሽ በትልቁ መመሰጋገንና መበረታታት በስፋት ይታያል። ከህጻን እስከ አዋቂው፤ ከሴት እስከ ወንዱ፤ ከተማረው እስካልተማረው ድረስ የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር የምስጋና አጠቃቀማቸው ነው። ይህ ደግሞ የእድገታቸውም አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኛል።

በድንገት በእነዚህ የሰለጠኑ ሀገራት የተገኘ ኢትዮጵያዊ አንዱ ከሚያስገርሙትና ምናልባትም ከሚያስቀኑት ተግባራት መካከል በየአጋጣሚው የሚሰሙ የምስጋና ቃላት ናቸው። እዚህ ኢትዮጵያ እንደዳይኖሰር ሊጠፉ ከተቃረቡት ቃላት ውስጥ አንዱ የሆነው ‹‹አመሰግናለሁ›› የሚለው ቃል በውጭው ዓለም በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉት አንዱ ነው። በየትራንስፖርቱ፤ በየሆቴሉ፤ በየመዝናኛ ስፍራው፤ በየመንገዱ ‹‹አመሰግናለሁ›› መባባል የተለመደ ነው።

ኢትዮጵያውያን ጀግኖችና ጨዋዎች ብንሆንም የምስጋና ድሃዎች ነን። በጣም በሳሳ መልኩ ከምንጠቀምባቸውና በሂደትም እንዳይጠፉ ከምፈራላቸው ቃላት መካከል ምስጋና አንዱ ነው። ‹‹አመሰግናለሁ›› የሚለውን ቃል በእጅጉ የምንፈራው ይመስለኛል። ከዚያ ይልቅ መውቀስ፤ መርገም፤ ማጣጣልና ማንቋቋሸሽ ይቀናል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ስራዬ ብሎ የተያዘው እና እንደ ዕውቀትም እየተወሰደ ያለው ከማመስገን ይልቅ መውቀስና መተቸት ይመስለኛል። እነዚህ አሉታዊ ቃላት ምስጋናና ደፍጥጠው መድረኩን የተቆጣጠሩት ይመስለኛል።

ሆኖም ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ምስጋና ነው። ምስጋና የመከባበርና መተባበር መገለጫ ነው። ይህም አንድነትን የሚያጠናክር ትልቅ ኃይልም ነው። ተስፋችን ብዙ መሆኑን በመረዳት ነገን በአዎንታዊ ኃይል የምንገነባው ዛሬ ላይ እርስ በእርሳችን ስንመሰጋገንና አርአያዎቻችንን ማመስገን ስንችል ነው። ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ተቋቁማ በአሸናፊነት ያለፈች ሀገር መሆኗን በመናገር፤ ከሆነባት ይልቅ የሆነላት ይበልጣልና ፈጣሪንም ጀግኖች ልጆቿንም ማክበርና ማመስገን የግድ የሚል ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ፈጣሪን ከመፍራት፣ ከማክበር እና ከማመስገን ወደኋላ ያለችበት ጊዜ የለም። ይህ በመሆኑ ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ቆይታለች። በአድዋ ጦርነትም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ጦርነቶች ጀግኖች እርስ በእርሳቸው በመመሰጋገናቸውና በመከባበራቸው ይሸነፋሉ የማይባሉ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ማሸነፍ ተችሏል።

በተለይም የሀገር ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ ልዩነትን አቻችሎና ለሌላ ጊዜ አሸጋግሮ ለሀገርና ለወገን የተሰጠን ክብር አብሮ ማጣጣም ያስፈልጋል። ሀገር ስትሸለም የሚሸለመው መሪዋ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ ነው። የሀገር ስኬትም ሆነ ውድቀት የጋራ መገለጫዎቻችን ስለሆኑ ለጠላቶች አሳልፎ በሚሰጥ መልኩ የሚሰጡ ሽልማቶችንና ዕውቅናዎችን ማጣጣልና ማሳነስ ከአንድ ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝም ሰሞኑን ኢትዮጵያና መሪዋ በውጭው ዓለም በስፋት ሲመሰገኑ እኛ ለጉዳዩ ሩቅ ሆነን ከመገኘታችንም በላይ አንዳንዶቻችን ለትችት የቀደመን አለመኖሩ ነው። በተለይ አንቂዎችና ፖለቲከኞች ነን ባዮች ቀድመን ማመስገን ቢያቅተን እንኳን በውጭው ዓለም ለሀገርና ለመሪ የተሰጠውን ምስጋና ለመተቸት መሯሯጣችን ምን ያህል ከምስጋና ጋር እየተራራቅን እንደመጣን ማሳያ ነው።

የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እና አመራር በሚል ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ሸልሟል። እንደ መንግስታቱ ድርጅት መረጃ ከሆነ ሽልማቱ የሚሰጠው የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ልዩ አበርክቶ ላበረከቱ ታዋቂ እና የተከበረ ስብዕና ላላቸው ሰዎች ነው።

ሽልማቱ በጣሊያን ሮም ከተቀበሉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሽልማቱን ያበረከተላቸውን የመንግስታቱ ድርጅትን በማመስገን “ከፍ ያለ ጠቀሜታ ባላቸው እና የኢንዱስትሪ ግብዓት በሆኑ የግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት መደረጉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እያስገኘ” እንደሚገኝም ገልጸዋል፤ “የምግብ ሉዓላዊነት ጉዟችንን በፅናት እናስቀጥላለን” ብለዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ ይገባቸዋል ከሚል አስተያየት ጀምሮ ሽልማቱ በጠ/ሚኒስትሩ ደጋፊዎች ዘንድ ውዳሴ ተችሮታል። የጠ/ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት እና በመንግስታቱ ድርጅት የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታየ አስቀስላሴ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ሽልማት ማበርከቱን አወድሰው “እርግጥ ነው የገበሬዎች ህይወት ሲሻሻል የሀገሪቱም እንዲሁ ይሻሻላል” የሚል አስተያየት በኤክስ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል። ከዚሁ ምስጋና ጊን ለጎን ደግሞ ትችት ብቻ አንደበታቸው የለመዱ ሰዎች ነቀፌታ አዘል አስተያየት ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፋኦ ሽልማት ያገኙት ባለፉት ዓመታት በጠንካራ አመራራቸው በተለይ በግብርናው ዘርፍ ባስመዘገቡት ውጤት ነው።

ኢትዮጵያ በግጭቶች፣ መከራዎችና ረሃብ ስትፈተን የቆየች ሀገር ብትሆንም አሁን ላይ ግን ካለፈው ትምህርት ወስዳ ሁኔታዎቹን ወደ ዕድል እየቀየረች ያለች ሀገር ነች። ቀደም ሲል በጦርነት፤ በርሃብና ድርቅ የሚታወቀውን ስሟን የሚለውጡ ስራዎችንም በማከናወን ላይ ትገኛለች። በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በግብርና፤ በአረንጓዴ አሻራ፤ በኃይል አቅርቦት እና በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የሀገሪቱ መጻኢ ዕድል ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የሚያመላክቱ ናቸው። ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች በምግብ ሰብል እራሷን ከመቻል አልፎ ስንዴን እና አቦካቶን የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ትገኛለች።

ግብርና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና 120 ሚሊዮን የሚጠጋውን ሕዝብ የሚመግብ ዘርፍ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ 96 ሚሊዮን ወይም 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ኑሮው ቀጥታ ከግብርና ስራ ጋር የተያያዘ ነው። ከውጭ ምንዛሬ አንጻርም ብንመለከተው አብዛኛው ድርሻ የሚገኘው ከዚሁ ዘርፍ ነው። ይህንኑ ሃቅ በመገንዘብ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል። የሀገሪቱን መልክዓምድርና የአየር ጻባይን መሰረት ያደረጉ ስራዎች በመሰራታቸው ጤፍን የመሳሰሉ ምርቶች ምርታማነት ከመጨመሩም ባሻገር ኢትዮጵያ በታሪኳ አምርታቸው የማታቃቸው የበጋ ስንዴና ሩዝን የመሳሰሉ ሰብሎች ከራስ ፍጆታ አልፈው ለውጭ ገበያም ለመቅረብ ችለዋል።

ጤፍ በርካታ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ የሚመገበው እና አብዛኛውን የእርሻ መሬት የሚሸፍን ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ይሄ ነው የሚባል የምርት ዕድገት ሳያሳይ ቆይቷል። የለውጡ መንግስት እውን እስከ ሆነበት ጊዜ ድረስ በአጠቃላይ የነበረው ዓመታዊ ምርት ከ300ሚሊዮን ኩንታል ብዙም የዘለለ አልነበረም። ባለፉት አምስት ዓመታት ጤፍን በክላስተር ማረስ በመቻሉ ምርቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ ምርቱ 639 ሚሊዮን ኩንታል ሊደርስ ችሏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በአዲስ የልማት ጎዳና እንድትራመድ ካደረጓት የግብርና እንቅስቃሴ አንዱ የስንዴ ልማት ነው። ቀደም ሲል በጥቂት መጠን፤ በተወሰኑ አካባቢዎች፤ በክረምት ብቻ ይመረት የነበረውን የስንዴ ልማት ወደ በጋም በማሸጋገር የስንዴ ምርትን ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያም የማቅረብ አቅም ላይ ተደርሷል። የስንዴ ምርት በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማሳደግ የተቻለ ሲሆን በሄክታር ሁለት ቶን ይገኝ የነበረው የስንዴ ምርትም ወደ አራት ቶን ማሳደግ ተችሏል።

በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በ2016 ምርት ዘመን ወደ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 117 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማምረት እየተሠራ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ቀዳሚ ስንዴ አምራች ለመሆን በቅታለች። በ2015 ዓመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ እንደ ስንዴው ሁሉ ለሩዝ ምርት ትኩረት በመስጠት ከሀገራዊ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ለመላክ በትኩረት በመስራት ላይ ትገኛለች። በተለይም ሀገሪቱ ለሩዝ ምርት ተስማሚ የሆነ የአየር ጸባይና ምቹ መሬት ያላት መሆኑ ያቀደችውን ወደ ተግባር ለመለወጥ እንደማያዳግታት የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለከተውም በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በሩዝ መልማት የሚችል መሬት ቢኖርም በየዓመቱ ከ200 ሺህ ቶን በላይ ሩዝ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት በየዓመቱ 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች። ሆኖም በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት መተግበር ከጀመረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ፊቱን ወደ ሩዝ ምርት በማዞር በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል። በተለይ በአማራ ፎገራና በጅማ አካባቢ እየተከናወነ ያለው የሩዝ ምርት ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይ ሀገርነት ወደ ላኪነት የሚያሸጋግራት ነው።

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከ35-40 በመቶ የሚሸፍነው ቡናም ምርታማነቱ ጨምሯል። 500ሺ የነበረው ዓመታዊ ምርትን ወደ 800ሺ ማሳደግ ተችሏል። በዚህም 700ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ገቢ ወደ 1ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ ችሏል። የሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍን ምርታማነት ማሳደግ በመቻሉ ለሀገሪቱ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የማምጣት አቅም ላይ ደርሷል።

ከዚህ ባሻገርም በሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በሁሉም ክልሎች ከፍተኛ ምርታማነት ታይቷል። በማር፤ በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽዖ፣ በጓሮ አትክልትና በፍራፍሬ ምርት ላይ የጎላ ለውጥ መጥቷል። በዚህም ዜጎች እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ግሽበት እንዲቋቋሙ፣ ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ብሎም ከራሳቸው ተርፎ ለገበያ እንዲያቀርቡ አስችሏል። በአጠቃላይ በግብርናው ዘርፍ ያለው መሻሻል ስንዴን፤ ሩዝንና አቦካቶን የመሳሰሉ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያም እንዲቀርብ ያደረገ ነው። ይህ ደግሞ በውጭ ታዛቢዎች ጭምር የተመሰከረለትና ኢትዮጵያም በግብርናው ዘርፍ እምርታ እያሳየች መምጣቷን ያሳየ ነው።

አሊ ሴሮ

 አዲስ ዘመን ጥር 23/2016

Recommended For You