ሀገራችን በሚልክዌይስ ውስጥ የሚገኙትን ኮከብና ፕላኔት እንድትሰይም የተሰጣትን እድል በመላው ሕዝብና ተቋማት ተሳትፎ ለማከናወን የመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደጠቀሰው አሰያየሙ የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚ ህብረት /IAU/ ያወጣውን ደንብ እና መመሪያ ተከትሎ ይከናወናል።
የሚሰጡት ስያሜዎች የኢትዮጵያን ታላቅነትና የህዝቦቿን ሁሉ ጥንታዊ ስልጣኔና ትስስር የሚያሳዩ፣ ማንንም የማያስከፉ፣ በመላው የዓለም ህዝብ ዘንድ በቀላሉ ሊታወሱና ሊያዙ የሚችሉ ሊሆኑ ይገባል ያለው መግለጫው ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚ ህብረት መስፈርትን ሙሉ በሙሉ ሊያሟሉም ይገባል ብሏል።
ሁለቱም ስሞች የጋራ የሆነ የአሰያየም ስርዓት ይኖራቸዋል ያለው መግለጫው የአሰያየሙ መንገድም ሁለቱን የህዋ አካላት እንዴት እንደሚያዛምድ የሚያመላክት አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር መግለጫ ያስፈልገዋል ብሏል። በስርኣቱ ውስጥም ወደፊት ሌላ አካላት ቢገኙ ተጨማሪ ስያሜን ለመስጠት እንዲመች ስሞቹ ሲወጡ ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርባቸውም አመልክቷል።
በዚህም መሰረት የሚወጡት ስሞች ሊያሟሏቸው የሚገቡ መስፈርቶች ክፍት ቦታዎችንና ስርዓተ ነጥቦችን ጨምሮ ፊደሎቹ ከ4 እስከ 16 የሆነ፤ አንድ ቃል (ይመረጣል)፤ በቀላሉ የሚነበብ፣ ሰዎችን የማያስቆጣ እና ከዚህ በፊት ከተሰየሙ ሰማያዊ አካላት ስያሜ ጋር ያልተቀራረበና የተለየ መሆን እንዳለበት ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር ከንግድ ስያሜ ጋር የተያያዙ፣ ከፖለቲካ፣ ውትድርና ወይም ከሃይማኖት ጋር የሚታወስ የግለሰብ ወይም የቦታ እንዲሁም የክስተት ስም፣ ባለፉት መቶ አመታት ውስጥ በህይወት ያለፈ ሰው ስም፣ በህይወት ያለ ሰው ስም፣ የቤት እንስሳ ስም፣ አዲስ የተፈጠረ ስም፣ በምህጻረ ቃል የተቀመጡ ስሞች እና ቁጥርና ስርዓተ ነጥብ ያላቸው ስሞች መሆን እደሌለባቸው ጠቅሷል።
ስሞቹ በሳይንስ የተሰጡትን የቁጥር ስሜዎች የሚተኩ ሳይሆን በአለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ለህዋ አካላቱ በህዝብ የተሰየሙ ተብለው እውቅና እንደሚያገኙና ከስያሜዎቹ ጋር እውቅና በመስጠት ለህትመት እንደሚበቁም ታውቋል።
የኮከቡ መለያ HD 16175 ሲሆን ከፀሃይ ተለቅ ያለ እንደሆነ መግለጫ ጠቅሷል፤ በኮከቡ ዙሪያ የምትዞረው ፕላኔት ደግሞ HD 16175 b የምትባል ሲሆን መጠነ ቁሷ ጁፒተር ከምትባለው ፕላኔት 4ነጥብ8 እጅ ከፍ ያለች እንደሆነ ታውቋል።
ጥቆማውን በhttp://naminghd16175. essti.gov.et/ ፤ በ920 የስልክ መስመር አጭር የፅሁፍ መልዕክት፣ በፖስታ ሳጥን ቁጥር 8412 (የኢ.ስ.ሳ.ሶ) እና 33679 (የኢ.ስ.ሳ.ቴ.ኢ) እና በኢሜይል “ namehd16175@gmail. com” ዘዴዎች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ማስገባት እንደሚቻልም በመግለጫው ተጠቅሷል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር