አዲስ አበባ:- መንግሥት እየተከተለ ያለውን የልማት እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተከትለው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ከግንባታ ጀምሮ እስከ ማምረት ድረስ የሚያከናውኗቸው ተግባራት የአካባቢ ደህንነት፣ ጥበቃ እና የአየር ለውጥን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲያከናውኑ ተጠየቀ።
የኦሮሚያ የደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ቦና ያደሴ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት እስከ ዛሬ በግሉ ዘርፍ የሚደረገው ልማት ለአካባቢ ሁኔታ ትኩረት የሰጠ አልነበረም። ዛፍን ቆራርጦ ጥሎ የመገንባት፣ የፋብሪካ ውጤቶች ስለሚያስከትሉት የውሀ፣ የአየርና ሌሎች ብክለቶችና ብክነቶች ያለመጨነቅ እና የመሳሰሉት ሁኔታዎች እንደነበሩም ሃላፊው ጠቁመዋል።
ይህን ለማስቀረት ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውንና አሁንም እየተሰሩ ያሉ በርካታ ስራዎች መኖራቸውን የገለፁት ምክትል ሀላፊው ህጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በመከለስ እንደገና ከማዘጋጀት ጀምሮ ከባለ ሀብቶች ጋርም የጋራ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት የጋራ ግንዛቤ እስከመፍጠርና መግባባት ድረስ መዝለቃቸውንም ተናግረዋል።
ቁጥጥር (ኢንቬንተሪ) በማድረግ ሁሉንም ባለሀብቶችና ስራዎቻቸውን ለማወቅ ጥረት እየተደረገ ነው የሚሉት አቶ ቦና ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግም በአካባቢው ላይ ተፅእኖ የፈጠሩትን ለመለየት በተደረገ ጥረትም በአካባቢ ጥበቃና አየር ለውጥ ላይ ተፅእኖ የፈጠሩ በርካታ የግል ባለሀብቶች መገኘታቸውንና የማምረት ሂደቱን እንዲያቆሙ የተደረጉ መኖራቸውንም አመልክተዋል።
በአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በልስቲ በለጠ እንደሚሉት ይህንን ችግር ከፍተኛ ቁጥጥር (ኢንቬንተሪ) በማድረግና ማን ምን፣ የት፣ ለምን፣ እንዴት እንደሚሰራ በመለየት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ጥሩ ውጤት ማምጣት ቢቻልም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ማለት ግን አይቻልም፤ ብዙ ስራ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ።
የኦሮሚያ የደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ እንዳሉት በግል ኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ ስርዓት አልበኝነት የሚታይበት ነው። እንደ እሳቸው አባባል ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጡ ሲጠየቁ ሁሉ ዶላር እያመጣንላችሁ ነው፣ የስራ እድል ፈጥረንላችኋል፣ ልማታዊ ባለሀብት ነን እና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ምክንያቶችን እስከመስጠት የደረሱ እንዳሉም ለአብነት አንስተዋል።
ቀደም ሲል ሲከናወን የነበረው የግሉ ዘርፍ የልማት እንቅስቃሴ እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ያገናዘበ ነበር ለማለት አይቻልም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቻችን ቢያንስ ከዚህ በኋላ ይህ ስህተት መደገም እንደሌለበትና ሀይ ሊባል እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ሀላፊው አቶ ቦና ያደሴ ደግሞ ይህ ሁኔታ በ2012 አ.ም አይቀጥልም። አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሁሉ የተደረገ በመሆኑም ባለሀብቱ ወደዚህ ስህተት የሚገባበት እድልም ሆነ መንገድ የለውም። ለዚህ ደግሞ በምክር ቤት ደረጃ አቋም ተይዟል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
ግርማ መንግሥቴ