አዲስ አበባ፡- ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግስት ሰራተኞች በዝቅተኛ ኪራይ ለማስተላለፍ ታስቦ በሁለት ሳይት እየተገነቡ ያሉ 1ሺ717 ቤቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ተገለጸ። ቤቶቹ ለከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች ብቻ ወይም የፌዴራል መንግስት ሰራተኞችን ባካተተ መልኩ ስለመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መሆኑም ተጠቁሟል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ሰርካለም ንጋቱ፣ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የመንግስት ሰራተኛውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት በአሁኑ ሰዓት በባሻ ወልዴ እና ገላን ሳይቶች የቤት ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። በሁለቱ ሳይቶች በድምሩ 1ሺ717 ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን፤ ግንባታቸውም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
እንደ ወይዘሮ ሰርካለም ገለጻ፤ እነዚህ ቤቶች ከኮንዶሚኒዬን የቤት ፕሮግራም የተለዩ ሲሆን፤ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግስት ሰራተኞች በዝቅተኛ ኪራይ የሚተላለፉ ናቸው። ሆኖም ቤቶቹ ለሰራተኞቹ ከተላለፉ በኋላ ምን ያክል ግዜ ከሰሩ የእነርሱ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውና መሰል ጥያቄዎች በአዋጅ የሚወሰን ሲሆን፤ ጥያቄው አዋጁ ከጸደቀ በኋላ በራሱ መመሪያ የሚመለስ ይሆናል።
እነዚህ ቤቶች በከተማ አስተዳደሩ በ2010 ዓ.ም ላይ 335 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞላቸው በ2011ዓ.ም ግንባታቸው የተጀመረ ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ባለው አፈጻጸምም ግንባታቸው ከ91 በመቶ በላይ ደርሷል።
ከዚህ በፊት በእጣ ከሚተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ውስጥ የመንግስት ሰራተኛው 20 በመቶ ድርሻ እንደተሰጠው የሚናገሩት ወይዘሮ ሰርካለም፤ ለመምህራንም አምስት ሺ ቤቶች መሰጠታቸውን እና ከ10/90 የቤት ልማት መርሃ ግብር ከተመዝጋቢዎች የተረፉ ቤቶችን በተመሳሳይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰራተኞች እንዲተላለፉ መደረጉን አስታውሰዋል።
እነዚህ ቤቶች ለሰራተኛው ከተላለፉ በኋላ ሌሎች የቤት አማራጮች ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። የሚገነቡት ቤቶች ግን ለከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች ብቻ ይሁን ወይም የፌዴራል ሰራተኞችን ባካተተ መልኩ ነው የሚለው የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
ወንድወሰን ሽመልስ