ሕግ እና የሕግ የበላይነት

 በዚሁ አምድ ህገ ወጥ ንግድን ወይም ኮንትሮባንድን በተመለከተ ለመጫጫር ሳወጣ ሳወርድ፣ ችግሩ እንዲህ ሊስፋፋ የቻለው በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም ዋናው ግን የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ አለመረጋገጡ ነው ብዬ አሰብሁ።እንደ ሀገር ያለንበት አጠቃላይ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥም ያልተከበረ ያልተረጋገጠ የሕግ የበላይነት ክፍተት እንዳለ ተረዳሁ።እንደ ዜጋ በሁሉም ተቋሞቻችን የሕግ የበላይነት ቢረጋገጥ ኖሮ ዛሬ ሀገራችን መስቀለኛ መንገድ ላይ አትገኝም ነበር የሚል ቁጭትም ፈጠረብኝ።

በዚህ ቁጭት ላይ ሆኜ ስለ የህግ የበላይነት ምንነት ይበልጥ ለመረዳት በድረ ገጽ ሳስስና በጎግል “ስጎለጉል” ኃይለማርያም ይርጋ የተባሉ የህግ ሊቃውንት ጋር ልክ በእውን የተገናኘሁ ያህል ”ቨርቹዋ” ተገጣጠምሁ። በማስከተልም በምናብ ለመሆኑ የሕግ የበላይነት ማለት ምን ማለት ነው ስል ጠየቅኋቸው።በነገራችን ላይ የምናብ ቃለ መጠይቅ የማድረግ ሀሳብ የመጣልኝ ተወዳጁ የCNN የGPS አዘጋጅና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሊቅ ፋሪድ ዘካሪያ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር በአካል ተገናኝቶ ፊት ለፊት ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንደማይችል ሲያውቅ ምናባዊ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ተነሳ።

ጥያቄዎቹን ካወጣ በኋላ ለእያንዳንዱ ጥያቄ ኪም ምን ብሎ ሊመልስለት እንደሚችል በምናብ እያሰበ መልሱን ዘረዘረ።ጠያቂም መላሺም ሆነ።እንደ ሀገራችን ጋዜጠኞች ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል ከሚለው የጨረተ ”Clichy” አባባል ይሻላል። እኔም ከአቶ ኃይለማርያም ጋር እንዲህ በምናብ ለቃለ መጠይቅ ተቀመጥሁ። የኔው ከፋሪድ የሚለየው ጠያቂ እንጂ መላሽ አለመሆኔ ነው።ጥያቄዎቹን የሚመልሱት ሊቅ ሲኖሩ በአካል መገኘት ያልቻልሁት እኔ ስለሆንሁ ከፋሪዱ በፍጹም ይለያል።መልሶችም ከእኔ ምናብ የፈለቁ ሳይሆኑ የአቶ ኃይለማርያም ናቸው።

የሕግ የበላይነት ሲባል

በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት መግቢያ ላይ“ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን…..በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ አንድ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት..” በሚል የሕግ የበላይነት ለሀገራችን ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሆኖም ግን የሕግ የበላይነት የሚለው ቃል በህገ መንግሥቱም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ የቃል ኪዳን ሰነዶች ቢጠቀስም ስምምነት ላይ የተደረሰበት አንዳች ትርጉም ሲሰጠው አይስተዋልም፡፡

ከመዝገበ ቃላት ትርጉም ይልቅ የተሟላ ግንዛቤ ይረዳን ዘንድ ዊሊያም ጋርድነር የተባለ የህግ ምሁር “THE HISTORY AND ELE­MENTS OF THE RULE OF LAW” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ያስቀመጠውን ትርጉም እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በ2014 እኤአ ለፀጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ለህግ የበላይነት የተሰጠውን ትርጉም እናያለን፡፡

ዊሊያም የህግ በላይነትን አጭር እና ግልፅ በሆነ አገላለፅ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል፤

“የህግ የበላይነት ማለት የመንግሥት አካላት፣ ባለስልጣናት(ሰራተኛውን ጭምሮ) እና ዜጎች በሕግ ጥላ ስር ሲወሰኑና ሲያከብሩ ነው“ የሚል ነው፡፡በአንድ ማህበረሰብ የመንግሥት ባለስልጣናትና ዜጎች የእለት- ተለት ስራቸውን የሚፈፅሙት በህግ ጥላ ስር ሆነው ህግን በማክበር ከሆነ በህግ የበላይነት የሚመራ ማህበረሰብ ይባላል፡፡ በዚህ ትርጉም ውስጥ የተገለፀው ህግ ለውጥን ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ በጠቅላላ አገላለፅ የተረቀቀና በቀላሉ የሚረዱት፣ ተደራሽ የሆነ፣ ሊፈፀም የሚችል፣ ሁሉም በህግ ፊት እኩል የሆነበት እንዲሁም ህጉ በማይከበርበት ወቅት የማስፈፀሚያ ሥርዓትና ተቋማት ሊኖረው ይገባል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ የሕግ የበላይነት ሊኖር አይችልም ይላል ዊሊያም፡፡

ለምሳሌ ህጉን የማስፈፀሚያ ሥርዓት እና ተቋማት ከሌሉ ወይም ስራቸውን በአግባቡ ካልተወጡ የህግ የበላይነት እንደሌለ ይቆጠራል። ባለስልጣኑም ሆነ ዜጋው ልጓም እንደሌለው ፈረስ እንዳሻው ይሰግራል ማለት ነው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዊሊያም ከሰጠው ትርጉም በሰፋ መልኩ እንደሚከተለው ይተረጉመዋል። “የህግ የበላይነት የአስተዳደር መርህ ሲሆን ሁሉም ሰው፣ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በግልፅ በፀደቀ፣ ያለአድሎ በእኩል በሚፈፀም፣ በገለልተኛ ፍርድ ቤት በሚተረጎም እና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነዶች ጋር በተጣጣመ ህግ ተጠያቂ መሆንን የሚያመለክት ሲሆን ተጠያቂነትን፣ ርትዕን፣ ተገማችነትን፣ የስልጣን ክፍፍልን፣ በውሳኔ ሰጪነት ተሳታፊነትን፣ የዘፈቀደ አሰራርን ለማስወገድ እና የህግና የሥነ ሥርዓት ግልፀኝነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ሂደትና ጥረት ይጨምራል” በማለት።

ፅንሰ ሃሳቡን የሚያጠኑ የህግ ሊቃውንት ከላይ ከተመለከቱት ትርጉሞች አንፃር እይታቸው በሁለት የሚከፈል ሲሆን ሕጋዊነትን መሰረት ያደረገ ዝቀተኛው (formal or procedur­al conception) እይታ እና መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን ያካተተ (substantive conception) የህግ የበላይነት በሚል ይከፈላል፡፡ ህጋዊነትን መሰረት ያደረገው ዝቅተኛው የህግ የበላይነት እይታ ዊሊያም ከሰጠው ትርጉም ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ህግ መሰረታዊ የአስተዳደር መሳሪያ ሲሆን አግባብ ባለው ባለስልጣን ይመነጫል፣ ግልፅ፣ ተደራሽ፣ ተገማች፣ የረጋ እና ወደ ፊት የሚፈፀም መሆን እንደሚገባው ይገልፃሉ። መሰረታዊ

 ፍሬ ነገሮችን መሰረት ያደረገው የህግ የበላይነት እይታ አንድ ህግ ቅቡል ለመሆን ከሥነ ሥርዓታዊ መስፈርቶች በተጨማሪ የሞራል ቅቡልነት ያለው፣ ርትዕንና ሰብዓዊ መብቶችን እና ሌሎች ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ያከበረ መሆን ይገባዋል የሚል ነው።

የኢፌዴሪ ህገ መንግት በአንቀፅ 9 ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሌለው በመደንገግ በመንግስት ስልጣን ላይ ገደብ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው መንግሥት ምንም እንኳ ህጋዊ መስፈርቶችን ያሟላ ህግ ቢያወጣም ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ካላከበረ ህጉ ተፈፃሚነት የለውም። መንግሥት አላማውን ለማስፈፀም ወይም ለአገዛዝ እንዲመቸው መሰረታዊ ፍሬ ነገሮችን ያላከበረና መደበኛ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትን የተከተለ ህግ ሊያወጣ ይችላል፡፡

ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ሥርዓት በህግ የተደገፈ ነበር፡፡ በሀገራችንም ፀረ ሽብር አዋጅ፣ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ እና የምርጫ አዋጅ የገዥውን መንግሥት ስልጣን ለማራዘም ሲባል የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚገድቡ በመሆናቸው መንግስት የህግ የባላይነትን በሚያስከብር መልኩ እያሻሻላቸው ይገኛል፡፡ በመሆኑም የህግ የበላይነት ሲባል በህግ አውጪው አካል መደበኛ የህግ አወጣጥ ስነ ስርዓትን ተከትሎ በወጣ ህግ መተዳደር ብቻ ሳይሆን ህጉ ባስገዳጅ ሁኔታ ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ባከበረ መልኩ ስለመፅደቁ ትኩረት ይሻል ማለት ነው።

የህግ የበላይነት ፋይዳ እና አላባውያን

ምንምን ናቸው?

የህግ የበላይነት የአስተዳደር መርህ ሲሆን ለሰላም ግንባታ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሁም ውጤታማና ተአማኒነት ያለው የፍትህ አስተዳደር ተቋማት ለመገንባት በመሰረታዊነት የሚወሰድ ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በዋነኛነት ግን ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮችን ለማሳካት የተወጠነ ሃሳብ ነው፡፡ እነሱም፡-የመንግሥትን የዘፈቀደ የስልጣን አጠቃቀምን ለመገደብ፣ የዜጎችን የንብረት፣ የነፃነት እና የሕይወት መብት በሌሎች እንዳይጣስ ጥበቃ ማድረግ ነው፡፡

በአንድ ሀገር መንግሥት ውስጥ የህግ የበላይነት ስለመኖሩ ማረጋገጭ የሚሆኑ መገለጫ አላባውያን የተለያዩ ቢሆኑም በአለም አቀፍ ደረጃ የህግ የበላይነትን የሚያከብሩ ሀገራትን ደረጃ(rule of law index) የሚያወጣው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፕሮጅክት(world justice project) የሚጠቀምባቸውን መለኪያዎች ከህገ መንግሥታችን አኳያ የሚከተሉትን አምስት አላባውያን እናያለን፡፡

1.በህግ የተገደበ የመንግሥት ስልጣ

2.ህጋዊነት

3.ገለልተኛና ነፃ የዳኝነት አካል

4.ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር

5.ሰላምና ደህነት

በህግ የተገደበ የመንግሥት ስልጣን፦

የመንግሥት፣ የባለስልጣናቱና እንደራሴዎቹ ሥልጣን መገደብ ወይም መወሰን አለበት የሚለው የህግ የበላይነት መለኪያ መስፈርት ከሁለት ሺ ዓመት በፊት ጀምሮ ሲያቀነቅኑት የነበረ ሲሆን ዋና አላማውም መንግሥት በዘፈቀደ ያለገደብ ልጓም እንደሌለው ፈረስ የሚፈነጭ ከሆነ የዜጎችን መብት በመጨፍለቅ ጨቋኝና አምባገነነ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ መንግሥት መጠቀም ያለበት የስልጣን መጠን የሀገርን እና የዜጎችን ሰላም፣ ደህንነት እና መብት አክብሮ ለማስከበር በሚያስችል መልኩ መሆን ይገባዋል። መንግስት በህግ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት በሚፈፅምበት ወቅት በህግ በተቀመጡ አሰራሮች አግባብ መሆን ይገባዋል፡፡

ይህን ከተቃረነ በህግ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም ህጉን ለመቀየር ወይም ለማሻሻል ፍላጎት ቢያድርባቸው ህግ የማውጣት ስልጣንን የሚገድቡ ወሰኖችን(constraints) በመጣስ ሊሆን አይገባም፡፡ የኢፌድሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 9 ማንኛም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ የመንግሥት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ህግ አውጪው የሚያወጣው ህግ ወይም ሕግ አስፈፃሚው የሚወስነው ውሳኔ ወይም ህግ ተርጓሚው አካል ህግ ሲተረጉም ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ማክበር እንዳለበት በስልጣናቸው ላይ ገደብ አስቀምጧል፡፡

ይህን ገደብ የጣሰ ህግ፣ ውሳኔ እና የህግ ትርጉም ተፈፃሚነት የለውም፡፡ የመንግሥት አካላት በህግ በተሰጣቸው ስልጣን( separation of power) ብቻ እየሰሩ ስለመሆኑ ግልፅነትና ተያቂነት የሚያሰፍን የቁጥጥር ማድረጊያ መንገድ ሊኖር ይገባል፡፡ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 12 ማንኛውም ሃላፊና የህዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን ይደነግጋል። ቁጥጥርና ተጠያቂ ከሚደረግባቸው መንገዶች መካከል የሶስቱ የመንግሰት አካላት የእርስ በርስ ቁጥጥር መኖር( ለምሳሌ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 55(17-18) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈፃሚውን አካል የሚቆጣጠሩበትን አግባብ ደንግጓል) ፣ ለሲቨል ማህበራትና ለሚዲያ ተጠያቂ በመሆን፣ የመንግስት ስልጣን በህግ አግባብ ብቻ እንዲተላለፍ በማድረግ(ህገ መንግስት አንቀጽ 9(3) ይመለከቷል) ወ.ዘተረፈ ይገኝበታል፡፡

ህጋዊነት፦

የህግ የባላይነት ማረጋገጫ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የህጋዊነት መርህ መኖር ሲሆን አንድ ህግ ከረቂቅ ጀምሮ ፀድቆ ተግባር ላይ በሚውልበት ወቅት ተደራሽ መሆኑ፣ ህጉ ግልፅና በቀላሉ የሚረዱት መሆኑ፣ ለውጥን የሚያስተናግድ፣ ተገማች የሆነ፣ ሊፈፀም የሚችል፣ በሁሉም ላይ በእኩል ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ እና ማስፈፀሚ ሥርዓትና ተቋም ሊኖር ይገባል የሚል ነው፡፡ አንድ የህግ ሥርዓት እነዚህን መስፈርቶች የማያሟላ ከሆነ መንግሥት እና ዜጎች ለህጉ ይገዛሉ ተብሎ አይጠበቀም፡፡ ይህ መርህ መከበሩ ዜጎች ባልወጣ ህግ እንዳይቀጡና የወጡትንም ህጎች አክብረው የእለተ ተለት ህይወታቸውን እንዲመሩ ይደረጋል። ህጉም ተገማች በመሆኑ ግብይት እንዲሳለጥ ያደርጋል፡፡

ምክንያቱም ትርፍና ኪሳራቸውን አስልተው እንዲገበያዩ ያስችላቸዋል፡፡ ለምሳሌ የውል ህግ በመኖሩ ዜጎች ያለ ስጋት በነፃነት እንዲገበያዩ ዋስትና ይሰጣቸዋል። ውሉን ያላከበረ ተገዶ እንዲፈፅም ወይም ካሳ እንዲከፍል ስለሚደረግ ለሌላኛው ወገን ዋስትና ይሆናል፡፡ የንብረት ህግ ዜጎች ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን አውጥተው ያፈሩትን ንብረት በነፃነት እንዲጠቀሙ ጥበቃ ያደርጋል። የዚህ መርህ መስፈርቶች ህገ መንግሥቱ ውስጥ ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ ስለመንግስት አሰራር ግልፅነት እና ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል መሆን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 12(1) እና 25 እንደቅደም ተከተላቸው ተደንግገዋል፡፡

ገለልተኛና ነፃ የዳኝነት አካል፦

ነጻ የሆነ ፍ/ቤት የህግ በላይነት መሰረታዊ ገፅታና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መኖር ቅድመ ሁኔታ ነው። የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛው ባሕሪ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች መከበርና መረጋገጥ ነው። መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በሕገ-መንግሥት ወይም በሌላ ሕግ መደንገጋቸው ብቻ በራሱ ለመብቶች መረጋገጥ ዋስትና ሊሆን አይችልም። እነዚህ መብቶች እውን ይሆኑ ዘንድ ነፃ ፍ/ቤት መኖር አለበት፡፡ ነፃነት የሌለው ፍ/ ቤት የሰዎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲረጋገጥ ሊያደርግ አይችልም፡፡

በዜጎችና በመንግሥት እንዲሁም በሰዎች መካከል ባሉ ግንኙነቶች ሳቢያ የሚነሱ የፍትሐብሔር ወይም ወንጀል ክርክሮችን ገለልተኛና ነፃ ሆኖ እልባት ሊሰጥ የሚችል ፍ/ቤት በሌለበት የሕግ በላይነት ሊረጋገጥ አይችልም። የህግ በላይነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና መልካም አስተዳደር እውን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ሰላምና ዘለቄታ ያለው ልማትም ዋስትና አይኖረውም። የዳኝነት ነፃነት ለኢንቨስትመንትና ለኢኮኖሚ እድገት መሰረት ነው። ባለሀብቱ በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት እንዲኖረው በአንድ ሀገር ውስጥ የዳኝነት ነፃነት መስፈንና መረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡

ስለዚህ ስለዳኝነት ነፃነት አስፈላጊነት ላይ ምንም ክርክር የለውም፡፡ የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት በአንቀጽ 78 እና 79 ነፃ የዳኝነት አካል እንደተቋቋመ እና በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለስልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተፅእኖ ነፃ መሆናቸው እና ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት በህግ በመመራት እንደሚያከናውኑ ተደንግጓል፡፡ ጥያቄው ያለው የዳኝነት ነፃነት ስፋትና እና ተግባራዊ አፈፃፀሙ ላይ ነው፡፡

ሠላም፣ ሥርዓትና ደህንነት፦

የአንድ ሀገር መንግሥት፣ ህዝብና ነዋሪዎች ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት መብትና ጥቅም መከበር እና መረጋገጥ የህግ የበላይነት ዋነኛ ገፅታ ነው፡፡ ዘላቂ ዋስትና ያለው ሰላም ለማረጋገጥ የሚቻለው በሀገራዊ ደህንነት፣ በመንግሥትና በህዝብ ጥቅም፣ በግለሰቦች ደህንነትና መብት ላይ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊት ዝግጅቶችንና ሴራዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ሲቻልና ወንጀሎቹ ከተፈፀሙ አጥፊዎችን በህግ ሥርዓት ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረብና ለማስቀጣት ሲቻል ነው፡፡

የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራትና ማንኛውም ሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን በህገ መንግሥቱና ሌሎች የህግ ማዕቀፎችና ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ የማከናወን የዳበረ ባህል ሲዳብሩ የምርጫ ውድድሮች ጨምሮ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካውና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ህግና ሥርዓትን መሰረት በማድረግ የሚከናወኑ መሆን ይገባቸዋል፡፡ መንግሥት ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ ጉልበትን የመጠቀም(monopoly of coercive power) ብቸኛ መብት አለው፡፡

በመሆኑም ከህግ ከተፈቀደው ውጭ ዜጎች ወይም ሌሎች አካላት መብታቸውን ለማስከበር ኃይል የመጠቀም መብት የላቸውም፡፡ መንግሥት ሀገረ መንግሥቱ የቆመበትን ሥርዓትና ደህንነት ማስከበር አለበት ሲባል ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት የመከላከል ሥራ መሰራት፣ ፖለቲካዊ ግጭቶችን(ሽብርተኝነት፣ አለመረጋጋትን፣ በታጠቁ ኃይሎች መካከል የሚደረግ ግጭትን) ውጤታማ በሆነ መልኩ መቀነስ እና የግል ችግርን ወይም በደልን ለመወጣት መደበኛውን የህግ ማስከበር ሥርዓት ከመከተል ይልቅ ኃይልን መጠቀም ማህበራዊ ተቀባይነት ያለው አድርጎ አለመፈፀም(ለምሳሌ የደቦ ፍትህ) በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሰብዓዊ መብትና ነፃነቶች መከበር፦

ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡ ሀገራችን ህገ መንግሥት የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩ ስለመሆኑ በመሰረታዊ መርህነት የተደነገገ ከመሆኑም በላይ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ የፌዴራል መንግሥት የክልል ህግ አውጪ፣ አስፈፃሚና የዳኝነት አካል በህገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሶስት በተካተቱ የሰብዓዊ መብትና መሠረታዊ ነፃነቶች ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው ስለመሆኑ በአንቀጽ 13(1) ተደንግጓል። መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታ የሚወጣው አስፈላጊውን የህግ፣ የአስተዳደርና ሌሎች እርምጃዎች በመውሰድ ነው፡፡

መንግሥት ከዜጎቹ ጋር ባለው የቀጥታ ግንኙነት እንዲሁም ዜጎች ባላቸው የእርስ በርስ ግንኙነት አንዱ የሌላውን መብት የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ባለስልጣናትና ሰራተኞች ስልጣንና ኃላፊነታቸውን አላግባብና ከህግ ውጪ በመጠቀም የሚፈፀሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ድርጊቶችን እንዲሁም ሰዎች ባላቸው የጎንዮሽ ግንኙነት አንዱ የሌላውን መብትና ነፃነት የሚጥሱ ድርጊቶች የወንጀል ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚያስከትሉ ድርጊቶች መሆናቸውን በመደንገግ፣ በመከላከል እና ጥሰቱ ተፈፅሞ ሲገኝ በተሟላ ሁኔታ በወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ እንዲፈፀም በማድረግ መንግሥት ሰብዓዊ መብት የማክበርና የማስከበር ግዴታውን በመወጣት የህግ የባለይነትን ማረጋገጥ አለበት፡፡

የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ምን ይደረግ ?

በአንድ ሀገር ውስጥ የህግ የበላይነት መኖር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በአንፃራዊነት ካልሆነ በስተቀረ ከላይ የተመለከቱት የህግ የበላይነት መገለጫዎች ሙሉ በሙሉ የተከበረበት ሀገር የለም። የህግ የበላይነት በጊዜ ሂደት የሚገነባ እና የጋራ ባህል መገለጫ ይሆናል። መንግሥት እና ዜጎች ህጎች የእሴቶቻቸው መገለጫ እና ጥቅማቸውን ለማስከበር የወጡ መሆኑን ማመን አለባቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ህጎች በማክበርም ሆነ በማስከበር የራሳቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል፡፡

ሻሎም ! አሜን።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

 አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You