በመጤው የእንቦጭ አረምና በተለያዩ በካይ ነገሮች ምክንያት የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ለከፍተኛ አደጋ እየተጋለጡ መሆናቸውን ጥናቶችና የዘርፉ ምሑራን ይገልጻሉ። ችግሩም ወደማይቀለበስበትና ገንዘብ ወጥቶም መፍትሄ ወደማይገኝለት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠውና አገራዊ ጉዳይ ተደርጎ ሊሰራበት እንደሚገባ ምሑራን ይናገራሉ።
ዶክተር ግርማ ጥላሁን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ሕይወት ትምህርት ክፍል የውሃ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ፣ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የስምጥ ሸለቆ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በ6ሺ400 ኪሎ ሜትር ርዝመቱ በዓለም ከፍተኛ የሆነው የአፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ 20 በመቶው በኢትዮጵያ ያለ ነው። በሰሜን፣ በመካከለኛውና በደቡብ ተከፍሎ የሚታየው ይህ ክፍልም ከአፋር ጀምሮ ዝዋይ፣ አቢጃታ፣ ላንጋኖ፣ ሐዋሳ፣ አባያና ጫሞ ሐይቆችን የሚያካትት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእንቦጭ አረም መስፋፋትና የበካይ ነገሮች መበራከት በሐይቆቹ ላይ ትልቅ አደጋን ደቅኗል።
እንደ ዶክተር ግርማ ገለጻ፤ በጣና ሐይቅ ላይ ሰፊ ጉዳት እያደረሰ ያለው እንቦጭ አረም አሁን ላይ በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች እየተዛመተ ነው። አረሙ በቆቃ ላይ ተወስኖ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓትም በዝዋይ ታይቷል፤ አባያም በከፋ ሁኔታ ላይ ነው። ጫሞ ሐይቅ ላይም አደጋው ተደቅኗል።
የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ከወራሪው አረም እንቦጭ ባሻገር፤ በአርሶ አደሩ ማሳ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ማዳበሪያዎች፣ የአረምና ተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ጀምሮ፣ ከአበባ እርሻዎችና ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ በካይ ኬሚካሎችን ብሎም ከየከተማ የሚለቀቁ ቆሻሻዎች ምክንያት በደለልና መርዛማ ኬሚካሎች የሚጠቁ ናቸው። ይሄም ከሐይቆቹ ባሻገር በሐይቆቹ ውስጥ ላሉና በሐይቆቹ ላይ ኑሯቸውን ለመሰረቱ ሁሉ ትልቅ አደጋን ደቅነዋል። ለምሳሌ፣ ቆቃ ለሞጆ ቅርብ ነው፣ ፋብሪካዎችም በብዛት አሉ፤ ዝዋይ ከባቱ ከተማ ጥግ ነው፣ በአካባቢውም የአበባ እርሻ አለ፣ ሙሉውን በሚባል መልኩም የመስኖ እርሻ ይከናወናል። ለመስኖ ስራ ደግሞ ከፍተኛ የግብርና ኬሚካሎችን ነው የሚጠቀሙት።
በዝዋይና አቢያታ ሐይቆች ማሳያነት በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ኢኮሎጂያዊ ሁኔታ ላይ በማተኮር እኤአ በ2016 የተከናወነ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ደግሞ፤ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች የሰፊ ብዝሃ ሕይወት ባለቤት ናቸው። ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የመስኖ ልማት አገልግሎት የሚውሉ፤ ሰፊ የዓሣ ሃብታቸውንም ሳይሰስቱ የሚለግሱ፤ ለኢንዱስትሪዎችም ሆነ ለከተሞች የውሃ አቅርቦት የሚውሉ፤ ለቱሪዝምም በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ናቸው።
ይሁን እንጂ ባልተገባ የመሬት አጠቃቀም፣ በደን መጨፍጨፍ፣ ከከተማ ብሎም ከፋብሪካና እርሻ መሬቶች በሚወጡ በኬሚካሎችና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰፊው እየተበከሉና አደጋ ላይ እየወደቁ ይገኛል። ይህ ሂደትም በዝዋይና አቢያታ ሐይቆች አንጻር ሲታይም ለሐይቆቹ መጠን መቀነስ ብቻ ሳይሆን ሰፊ ስነሕይወታዊ ጉዳት እያደረሱ ይገኛል።
ይሄንን ሀሳብ የሚጋሩት ዶክተር ግርማ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ችግሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣ ነው። ይሄም ሰዎች በሚሰሩት ነገር ላይ ቁጥጥር ያለማድረጋቸውና ዓይናቸውን ጨፍነው የሚፈልጉትን ጥቅም ባቋራጭ ማግኘት እንጂ አካባቢውን እየተንከባከቡና እየጠበቁ ቀጣይነት ያለው ስራ ባለመስራታቸው ነው። በዚህ መልኩ ኃላፊነት የጎደላቸው እንቅስቃሴዎች በየቦታው ሲካሄዱም የሚመለከታቸው ይሄን መከላከል አልቻሉም።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ላይ እንቦጭ አረም ትልቅ ስጋት ብቻ ሳይሆን ጉዳትም እያደረሰ ይገኛል። ለምሳሌ፣ አባያ ባለፈው አመት ከ200 እስከ 300 ሄክታር ይገመት የነበረው፣ በቅርብ ቀን በወጣ መረጃ መሰረት ወደ 570 ሄክታር ደርሷል። የሐዋሳ ሐይቅም በዓይነ ቁራኛ መጠበቅ ካልቻለ በቀላሉ የተጋለጠ ነው። ጫሞም ቢሆን የመጠቃት እድሉ የሰፋ ሲሆን፤ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረቀው የጊዳቦ ግድብም የዚሁ ስጋት ተጋላጭ ነው። እናም አንድም አረሙ በገባባቸው ቦታዎች እንዳይስፋፋ የመግታት፤ ሁለተኛም ባልገባባቸው አካባቢዎች እንዳይገባ የመከላከል ስራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል።
አረሙ ከቁጥጥር በላይ በሆነ ፍጥነት ስለሚራባና የውሃ አካላትንም ስለሚሸፍን ውሃን ያተናል፤ ዓሳ ማስገር አይቻልም፤ ጀልባ ማንቀሳቀስ አያስችልም። በቀጣይም በሰዎች እንቅስቃሴ ከቦታ ቦታ ሊሄድ ይችላል። በገጠር ባሉ ትናንሽ ውሃዎች ሁሉ መታየቱ ስጋቱን የጎላ ያደርገዋል።
ለምሳሌ፣ አባያ 570 ሄክታር ተወርሯል። የሚወረረው ደግሞ የሐይቁ ዳርቻ ነው። የሐይቁ ዳርቻ ደግሞ “ናይል ኮሮኮዳይል” የምንለው ዓዞ የሚኖርበት፣ የሚመገብበትና የሚራባበት ቦታ ነው። ይህ ዓዞ ደግሞ ለቱሪዝምና ሌላም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ነው። በዚህ ሁኔታ እንቦጭን ለመቆጣጠር ቢፈለግ ይህ ዓዞ በጣም ቁጡ በመሆኑ እንደ ጣና ነጻ ሆኖ አረሙን ለመቆጣጠር በጣም ይከብዳል። በዚህ መልኩ አረሙ እየተስፋፋ ሲሄድ ደግሞ አየር ወደ ውሃው በበቂ ሁኔታ ስለማይደርስ ዓሳዎች ስለሚታፈኑ የዓሳ ሀብቱን ይጎዳዋል፤ አረሙ እስከ 90 በመቶ ውሃ ስለሚይዝም ከፍተኛ የውሃ ትነትን ያስከትላል።
በጥናቱ እንደተመላከተው ደግሞ፤ በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ውስጥና አካባቢ በርካታ ብርቅዬ አዕዋፍና ስነ ሕይወታዊ ሀብቶች አሉ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ካሉ የአዕዋፍ ዝርያዎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ናቸው። ሆኖም በሐይቆቹ ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ ሐይቆቹን ለድርቀትና ብክለት፤ እነዚህን አዕዋፍና ስነ ህይወታዊ ሀብቶችም ለጥፋት እየዳረገ ይገኛል። የተለያዩ መረጃዎችም ይሄንኑ የሚያመላክቱ ብቻ ሳይሆን ተገቢው ትኩረትና መፍትሄ ሊደረግለት እንደሚገባም ይጠቁማሉ። በመሆኑም በእነዚህ ሐይቆች ላይ የሚደርስን ጉዳትና የተጋረጠውን አደጋ መፍታት የወቅቱ ጉዳይ ሊሆን፤ ተገቢው የአስተዳደር ስርዓትም ሊበጅ የግድ ይላል።
ዶክተር ግርማ እንደሚሉት፤ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች እድገት፣ የልማት ስራዎችና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለሐይቆች በቆሻሻ መጎዳት ምክንያት እንደመሆኑ ሁሉ፤ የእንቦጭ አረምም ቢሆን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከሃምሳ ዓመት በፊት የአባ ሳሙኤል ግድብን መሰረት አድርጎ ነው። አመጣጡም አረሙ መርዛማና ቆሻሻ የሆኑ ነገሮችን ስለሚያጣራ ወደግድቡ የሚገባውን ፍሳሽ ለማጣራት ይረዳል በሚል ነበር። ከዚህ ተነስቶም ነው ወደ አዋሽ በመግባት ቆቃ አካባቢ ተወስኖ በመቆየት ወደ አባያና ሌሎቹም ሊዛመት የበቃው።
ባለው ሁኔታ ለቀጣይ የሰው ልጅ ኑሮ ጉልህ ድርሻ ያላቸው በርካታ ብዝሃ ህይወቶች እየጠፉ ነው። በቀጣይም ችግሩን ባለበት ማቆም፤ አዲስ እንዳይከሰት ማድረግ ካልተቻለ በስተቀር፣ አንድ የታመመ የሰው አካል በወቅቱ ካልታከመ በኋላ ለማዳን እንደሚያዳግት ሁሉ በሐይቆች ላይ የሚስተዋለው የእንቦጭና የኬሚካሎች ጉዳት የከፋና ገንዘብም ተከፍሎ ብዙ ነገርም ተደርጎ ሊቀለበስ የማይችል አደጋ ነው የሚሆነው።
በመሆኑም አረሙ የኢትዮጵያን የውሃ አካላት ወርሮ ችግር ላይ የሚጥል ስለሆነ ችግሩን ለመቀልበስ እንኳን ባይቻል ባለበት እንዲቆምና ሌሎቹጋ እንዳይገባ ማድረግ ይገባል። ለዚህም ሀብትን፣ የሰው ሃይልንና የመሳሰሉትን ማደራጀት፣ ለችግሩ ትልቅ ቦታ በመስጠት ከታች ጀምሮም አገር አቀፍ ጉዳይ አድርጎ መስራት ይገባል። የኬሚካሎቹንም ቢሆን አንደኛ በሚፈጠርበት ስፍራ ማቆየት፤ የሚገባውንም ነገር ማስወገድ ነው። ሌላው ደግሞ የኬሚካሎችን አይነትና መጠን ብሎም ጥራት መወሰን ይገባል። ቆሻሻን ከወጣ በኋላ ከመቆጣጠር ይልቅ ሳይወጣ መቆጣጠር፤ ሁሉም የአካባቢ ጥበቃን ማዕከል ያደረገ ስራ በማከናወን ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2011
ወንድወሰን ሽመልስ