ሀገሪቱ ግንባታ በስፋት የሚካሄድበት በመባል ስትጠቀስ ቆይታለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግንባታው ዘርፍ መቀዛቀዝ ቢታይበትም፣ በአሥር አመቱ መሪ አቅድ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። በዚህ እቅድ በመንግሥት ብቻ በርካታ የመንገድ፣ የባቡር፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ የኃይል ማመንጫ፣ ወዘተ ፕሮጀክቶች ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
የግንባታው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት መቀዛቀዝ ውስጥ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ዓለምን ጭምር ቀውስ ውስጥ የከተተው ኮቪድ 19፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትና ያንን ተከትሎ በሀገሪቱ ላይ የተደረገው ጫና፣ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ግጭቶች፣ የግንባታ ግብአት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ዘርፉ እንዲቀዛዝ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፤ ይህን ተከትሎም በርካታ ፕሮጀክቶች ተጓትተው ይታያሉ፤ መንግሥት ትኩረቱን የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን መጨረሻ ላይ ማድረጉን ተከትሎ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መጀመር ላይ ብዙም አልተሰራም።
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም በግሉ ዘርፍ እየተካሄደ ያለው ግንባታ እንዳለ ሆኖ በመንግሥት በኩል የህዝቡን መሰረታዊ ችግር የሚፈቱ፣ በቀጣይ የልማት አቅም መሆን የሚችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ይገኛሉ። ለእዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት በከተማዋም በመላ ሀገሪቱም እየተካሄዱ የሚገኙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በአብነት ይጠቀሳሉ።
ሀገሪቱ ግንባታ የሚጓተትባት ብቻም ሳትሆን ግንባታዎች የዲዛይን ችግር የሚታይባቸው መሆናቸውም ይታወቃል። ግንባታዎች ከጥራት፣ ከዲዛይን፣ ከጊዜ አኳያም ሰፊ ክፍተት እንደሚታይባቸው ይገለጻል። አካል ጉዳተኞችንና አካባቢን ታሳቢ ያላደረጉ ህንጻዎች በስፋት መታየታቸውም ይህንኑ ያመለክታል።
በመዲናችን አዲስ አበባ እና በክልል የተገነቡና እየተገነቡ የሚገኙ አንዳንድ ህንፃዎችን ስንመለከት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረጉ ሆነው ይታያሉ፤ ከእነዚህ ግንባታዎች አንዳንዶቹ ከጅምሩም የዲዛይን ከፍተት እንዳለባቸው ይታወቃል። አንዳንዶቹ የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎች ቢያደርጉም በቅጡ ታስቦበት የተከናወነ ሥራ ግን አይስተዋልባቸውም። ለ45 ዲግሪ የቀረቡና ከባድ ቁልቁለት ያለባቸው የአካል ጉዳተኛ መወጣጫዎች በአንዳንድ ህንጻዎች ይታያሉ፤ ይህ ብቻም አይደለም፤ መወጣጫዎቹ አንሸራታች ሆነው የተገነቡበት ሁኔታም ያጋጥማል። ከዚህም ግንባታዎቹ አካል ጉዳተኞቹን ሊጠቅሙ ቀርቶ ለበለጠ አደጋ የሚያጋለጡ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል። የአደጋ ጊዜ መውጫ የሌላቸው ህንጻዎች እንዳሉም ይገለጻል።
የግንባታዎች በታቀደላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ የከተማዋ ብቻም ሳይሆን የሀገሪቱ መሰረታዊ ችግር ሆኖ ቆይቷል። በሀገራችን ከለውጡ በፊት ከነበረው የፕሮጀክቶች መጓተት በተጨማሪ ባለፉት አመታት በተከሰተው ጦርነት እና የፀጥታ ችግር የተነሳም ግንባታቸው የተጓተተ ፕሮጀክቶች ጥቂት የሚባሉ ስለ አለመሆናቸው በግልጽ የሚታይ ሀቅ ነው፤ ችግሩ ስለመኖሩ የዘርፉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎችም ያረጋግጣሉ። ይህን ተከትሎም የግንባታ ዲዛይን እና የዋጋ ማስተካከያዎችን ማድረግ በእጅጉ የተለመደ ሆኖ ቆይቷል፡፡
በኢትዮጵያ ኮንስትራክሸን ባለሥልጣን የኮንስትራከሽን ግብአቶች ቁጥጥር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ በረከት ተዘራ እንደሚናገሩት፤ ከ2013 ዓ-ም ጀምሮ አገሪቱ ከነበረችበት ጦርነት፣ ከሰላምና ጸጥታ ችግሮች እና ከሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የግንባታ ሥራዎችን በሚፈለገው ፍጥነት እና በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ያለመፈጸም ችግሮች ታይተዋል። ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ያለው በጀት ውስን መሆንም ሌላው ተግዳሮት ሆኗል።
ከግብርና ቀጥሎ ብዙውን የሰው ኃይል የሚያቅፈው የግንባታው ዘርፉ መሆኑን አቶ በረከት ጠቅሰው፣ ዘርፉ ብዙ የስራ እድል መፍጠር የሚችለው ፕሮጀክቶች ሲንቀሳቀሱ መሆኑን ይናገራሉ። አሁን በፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ላይ መቀዛቀዝ መታየቱን ተከትሎ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ብዙም እንደማይጀመሩም ይገልጻሉ። ነባሮቹን ባለው በጀት ቅድሚያ በመስጠት ለማጠናቀቅ ግን ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ይጠቁማሉ።
በተለይ በመንግሥት በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደም ይመደብላቸው ከነበረው በ2016 በጀት ዓመት ቢያንስ ከ50 እስከ 75 በመቶ ያላቸውን መጠን በመቀነስ እየተጠቀሙ እንደሚገኙም መሪ ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል። የበጀት እጥረቱ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው መንገድ እንዳይንቀሳቀሱ ካደረገ ደግሞ በዘርፉ የተሰማራው የሰው ኃይል ቁጥር በዚያው ያህል የሚቀንስ መሆኑንም ይገልፃሉ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የታየውን ይህን ተግዳሮት በምን መልኩ መሻገር እንደሚገባም በመንግስት በኩል እየታሰበበት መሆኑንም ጠቅሰው፣ በቀጣይ ሀገርን ከማረጋጋት አኳያ በሚኖረው እንቅስቃሴ ጥሩ ለውጦች እንንደሚኖሩም ነው ያመለከቱት። በሙሉ አቅም መስራት ውስጥ ባይገባም፣ ከነባሮቹ ፕሮጀክቶች ቀድመው ማለቅ የሚገባቸውን በማየት እና ቅደም ተከተላቸውን በመጠበቅ የማንቀሳቀስ ስራዎችን ለመስራት የሚፈለገውን የሰው ኃይል በማሰማራት እየተሰራ ነው ይላሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ነባር ፕሮጀክቶች ከሚባሉት መካከል በዋናነት በመደበኛ የመንግስት በጀት የሚገነቡ የዩኒቨርሲቲዎች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። በአዲስ አበባና በሸገር ሲቲም በጤና ሚኒስቴር የሚገነቡ ፕሮጀክቶች፣ በአለርት ሆስፒታል ግቢ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች፣ የኢትዮጵያ ሚትሮሎጂ ግንባታዎች ነባር ተብለው የተያዙ ናቸው። በክልሎች ደግሞ በዩኒቨርሲቲ፣ በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚካሄዱ ግንባታዎችም አሉ።
መንግሥት የእነዚህን ፕሮጀክቶች አጠቃላይ በጀት መቶ በመቶ እንዳላሟላላቸው መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፤ ከሚፈለገው አገልግሎት አኳያ የትኛው መቅደም አለበት በሚል መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ በጀታቸውንም መቶ በመቶ ባሟላላቸው ፕሮጀክቶች መጠን ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑን ያስረዳሉ።
በተለይ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ተማሪን ከመቀበልም አኳያ በተወሰነ መልኩ ለተማሪዎች ማደሪያ፣ ለመማር ማስተማር ሂደቱ አጋዥ የሆነ ግንባታ በግቢው የሚገኝ ከሆነ የትኛው ቅድሚያ ይሰጠዋል በሚል እየተለየ የማጠናቀቅ ስራው እንደሚካሄድ ገልጸዋል። ቅድሚያ ከሚሰጣቸውም መካከል የመኖሪያ፣ የምግብ ማብሰያ በሚል ቅደም ተከተል ወጥቶላቸው እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ በረከት እንዳብራሩት፤ በተመሳሳይ መልኩም ከዋጋ ግሽበቱ ጋር በተገናኘ መንግስት ለሁሉም መንግስታዊ ፕሮጀክቶች ባስተላለፈው የዋጋ ማስተካከያ መሰረት እየተሰራ አለመሆኑን ይገልጻሉ። ይሁንና ከውጭ የሚገቡ ግብአቶች ከኤልሲ ጋር በተገናኘ በሚቀመጥላቸው ስኬጁል (ፕሮግራም) መሰረት እየሄዱ አለመሆናቸውንም ተናግረዋል።
ይሄንንም ባለሥልጣኑ ቀደም ሲል ባደረገው ቁጥጥር ባገኘው ግኝት መሰረት ከሚወስዱት የተጨማሪ ክፍያ አኳያ መሰራት ያለባቸው ስራዎች እንዲሰሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገርም በአብዛኛው የግንባታ ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ ውስን የማጠናቀቂያ ቀሪ ስራዎች እንዳሉም ይጠቁማሉ።
ቀደም ሲል በተካሄደው የተካሄደውን ቁጥጥር ተከትሎ በተከናወኑ ተግባሮች መሰረትም ከውጭ መግባት የነበረባቸው እቃዎች ሙሉ በሙሉ መግባታቸውንና መከማቸታቸውን ገልጸው፤ በማጠናቀቂያ /የፊኒሺንግ/ እቃዎች ላይ ጤና ሚኒስቴር ካለው የበጀት ጉድለት አኳያ የዋጋ ማስተካከያ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
እነዚህ ሁኔታዎችን ማስማማት ከተቻለም ፕሮጀክቶቹ በ2016 መጨረሻ ላይ በተቀመጠላቸው ፕሮግራም መሰረት የሚያልቁበት እድል ከፍተኛ መሆኑንም መሪ ሥራ አስፈጻሚ አስታውቀዋል። ይህ ባይሳካ እንኳን በ2017 መጀመሪያ እና ሩብ ዓመት የማጠናቀቅ እድሉ ከፍ ያለ መሆኑንም ይገልፃሉ። ከፕሮጀክቱ ውስበስብነትና ሆስፒታል ከመሆኑም አኳያ ጥንቃቄ እንደሚፈልግ ጠቅሰው፣ የፕሮጀከቱ ግንባታ ሥራ ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱንም ነው ያመለከቱት።
አቶ በረከት በግንባታ ስራዎች ቁጥጥር ላይም በዋናነት በግንባታዎቹ ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይነት ደግሞ ዋጋ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም አስታውቀዋል። ሶስተኛው ጊዜ፣ አራተኛው ደግሞ የደህንነት እና ከአካባቢ ጋር ያለው ተስማሚነት በመመርኮዝ የቁጥጥር ስራው እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ የግንባታ ፕሮጀክት ዲዛይኖች እነዚህን መስፈርቶች ከግንዛቤ ውስጥ ያካተቱ ስለመሆናቸው በቀዳሚነት ይታያል። እነዚህን ያገናዘቡ ከሆነ ወደ መሬት ወርደው መስፈርቶቹን ባገናዘበ መልኩ እንዲገነቡ የማድረግ ተግባር እና ኃላፊነቱ በ524 ደንብ ቀጥር ጸድቆ ለባለስልጣኑ ተሰጥቷል። በመሆኑም ባለስልጣኑ ይሄንን ተግባር የመወጣት ግዴታ አለበት። ግንባታዎች በአጠቃላይ ጥራትን ብቻ ሳይሆን ጊዜን፣ ዋጋን፣ ለአካባቢና ሰራተኛ ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ባለስልጣኑ እየሰራ ይገኛል።
በፌዴራል መንግሥት በጀት ተደግፈው የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ ኮንስትራከሸን ባለሥልጣን በኩል ማለፍ እንዳለባቸው ለሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በ2013 ከገንዘብ ሚኒስቴር ባተላለፈላቸው የውስጥ አሰራር (ሰርኩላር) መሰረት አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ወደ ተቋሙ በመምጣት ዲዛይኖቻቸውን እያፀደቁ ወደ ተግባር እንዲገቡ ይደረጋል።
ዲዛይኑም ጥራትን፣ ዋጋን፣ ጊዜን እና የአካባቢና የማህበረሰብ የሥራ ቦታ ደህንነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲዘጋጅ ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል። ከጥራት አኳያ የሚፈጠሩ ግድፈቶችም ወዲያውኑ እርምት እንዲደረግባቸው እንደሚደረግ ጠቅሰው፣ በቀጣይም ለአካባቢውም ለማህበረሰቡም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሆናቸው እንደሚታይም ተናግረዋል። አደጋ ያመጣሉ ተብለው በሚታሰቡት ላይም በፍተሻ መሳሪያዎች ተጨማሪ የማስተካከያ ስራዎች እንዲደረግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቶች በተለይ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረጉ ከሆነ ዲዛይን አይሰጣቸውም ሲሉ ገልጸው፤ የ2003 ህንፃ አዋጅ መመሪያን መነሻ በማድረግ የዲዛይን ቁጥጥር ስራው ሲሰራ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ስለማድረጉ በቼክ ሊስት እንደሚታይታም ገልጸዋል።
በተለይም ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ እንደ ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ያሉ ግንባታዎችን በዚያ ደረጃ እያረጋገጥን እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል። በሜጋ ደረጃ ያሉ ፕሮጀክቶች ወደ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ሲመጡ የዲዛይኑ አንዱ ቼክሊስት አካል ሆነው እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።
አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ያለማዘጋጀት ክፍተት በአብዛኛው የሚታየው በግሉ ዘርፍ በመገንባት ላይ ባሉት ግንባታዎች ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ የግሉ ዘርፍ ፕሮጀክቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎችን በማካሄድ በኩል ዝንባሌኣቸው ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ።
አብዛኛዎቹ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛይኖች በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ ጸድቀው የሚወጡ መሆናቸውን መሪ ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ እነዚህን የመቆጣጠር እና አካል ጉዳተኛን ተደራሽ የማድረግ ሥራ በቀጣይ በትኩረት እንዲሰራበት ለማድረግ ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በግል ዘርፉ እና በሪል ስቴት ግንባታዎች ላይ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ዲዛይኖች ላይ በቀጣይ በመነጋገር እና ሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሚሰራበት አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በሕግ ማዕቀፉ እና በህንፃ አዋጁ ላይ ግንባታዎች አካል ጉዳተኞችን ማካተት እንዳለባቸው በገልጽ ተደንግጓል፤ በህንፃ ቁጥጥር ስራውም አንዱ የጥራት ማረጋገጫ መስፈርት የአካል ጉዳተኞች ተደራሽነት ወይም በህንፃው አገልግሎት ተደራሽ መሆናቸው ላይ ያለው ምቹነት እንደሆነም ይፈተሻል። የአካል ጉዳተኞች መካተት ጉዳይ በአዋጆች ላይ የተቀመጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ማየት እና መፈተሽ የሚፈልግ ሥራ እንዳለም አስታውቀዋል።
የባለሥልጣኑ አንዱ ተግባር በሀገር ደረጃ ያሉት የኮንስትራከሽን ኢንዱስትሪ አዋጆች፣ ኮዶች፣ ስታንዳርዶች በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በአግባቡ መተግበራቸውን ይቆጣጠራል የሚል ተግባር እና ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑንም አስታውቀው፣ የዚህ ምሰሶም የህንፃው ዲዛይን መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ዲዛይን አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ስለማድረጉ እየታየ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ሁሉም አካል “የኔ ችግር ነው”፤ ባለቤት ነኝ ብሎ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። ዛሬ ጤነኛ ሆኖ የሚንቀሳቀስ ነገ የሚገጥመው የማይታወቅ መሆኑን በማሰብ ጭምር ጉዳዩ በግንባታ ፕሮጀክቶች በሚገባ ተካቶ እንዲሰራበት ለማድረግ መስራት ይኖርበታል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2016