«የባሕር በር ለማግኘት ወሳኙ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ነው» – ኮሞዶር ጥላሁን መኮንን የቀድሞ የባሕር ኃይል መኮንን

ጊዜው 1950ዎቹ ውስጥ ነው፡፡ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ የባሕር ኃይል ዩኒፎርም (የደንብ ልብስ) ለብሰው አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ መኮንኖችን ሲያዩ ከእነርሱ እንደ አንዱ የመሆን ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሲኒማ ቤት ገብተው በሚያዩት ፊልም የባሕር ኃይል ዩኒፎርም የለበሰን መኮንን ማየት ለእርሳቸው ሕልማቸውን ለማሳካት የተቃረቡ ያህል ደስታ ይሰጣቸዋል፡፡ ብቻ መኮንኖቹን ሲመለከቷቸው ልባቸው የበለጠ ይነሳሳል፡፡ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ኮሞዶር ጥላሁን መኮንን፡፡

አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ኮሞዶር ጥላሁን፣ የባሕር ኃይል መኮንኖች አልፎ አልፎ በከተማዋ ውስጥ ለብሰው የሚያዩትን የደንብ ልብስ ‹‹ልክ እንደእነርሱ መልበስ ነበር!›› በሚል ብቻ ተመኝተው አልቀሩም፡፡ በደንብ ልብሱ ከመሳብ ባለፈ አባል መሆን ችለዋል፡፡

በተቋሙ በዕጩ መኮንንነት ተቀጥረው ሕልማቸውን እውን ያደረጉት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በ1954 ዓ.ም ነው፡፡ ትልቁን ተቋም ከተቀላቀሉ በኋላ በባሕር ኃይል ኮሌጅ ውስጥ ሦስት ዓመት ተምረው ዲፕሎማ አገኙ፡፡ እርሳቸው በተማሩበት ጊዜ በዲፕሎማ ለመመረቅ የሚወስደው ሦስት ዓመት ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ ኮሞዶር ጥላሁን፣ ከኮሌጅ የተመረቁት በምክትል መቶ አለቅነት ደረጃ ነው፡፡ ከዚያም ወደተለያዩ ሀገሮች በመጓዝ አጫጭር ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ስልጠና ከወሰዱባቸው ሀገራት አንዱ እንግሊዝ ሀገር ነበር፣ እዚያም ስድስት ወር ያህል ተጨማሪ ኮርሶችን በመውሰድ ሙያቸውን ማዳበር ችለዋል፡፡

እንግዳችን፣ ከእንግሊዝ ሀገር ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ የኢትዮጵያ መርከቦች ላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ ለአብነትም የኢትዮጵያ ጦር መርከብ ላይ ሠርተዋል፡፡ ይህች መርከብ በወቅቱ በነበሩት በኢትዮጵያ ንጉሥ በአጼ ኃይለሥላሴ ስምም በኢትዮጵያ ስምም የምትጠራ እንደሆነች ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ አጼ ኃይለሥላሴ ወደዚያች መርከብ አብዝተው ይመላለሱ ስለነበር በመርከቧ ውስጥ በልዩ ሁኔታ የሚያርፉበት ክፍል ተዘጋጅቶላቸውም ነበር፤ እርሳቸው ሲመጡ የሚያርፉባት ያች ክፍል በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀች መሆኗን ኮሞዶር ጥላሁን ያስረዳሉ፡፡

እንግዳችን መርከብ ላይ በምክትልና በዋና አዛዥነት ነው የሠሩት፡፡ ሚሳይል የሚጭኑ መርከቦች ላይም ሠርተዋል፡፡ ከመርከብ ወርደውም በተለያየ የባሕር ኃይል መደቦች ላይ አገልግለዋል፡፡ ለምሳሌ ምጽዋ ላይ የሰው ኃይል መምሪያ ኃላፊነት፣ በአሰብ ባሕር ኃይል የደቡብ ዕዝ ላይ ደግሞ በምክትል አዛዥነት አገልግለዋል፡፡

በተጨማሪም ባሕር ኃይል ውስጥ ዋናው ጠቅላይ መምሪያ የባሕር ኃይል የሰው ኃይል ዳይሬክተር ሆነውም ሠርተዋል፡፡ በጠቅላላ ከባሕር ኃይል በ1983 ዓ.ም እስከተሰናበቱበት ጊዜ ድረስ ለ25 ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ይህን ሁሉ ልምድ የቀመሩ የዘርፉ ሙያተኛ በመሆናቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ተቋሙ መልሶ እንዲደራጅ ባደረጉበት ወቅት የዛሬውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እንዲያደራጁ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ጉምቱ ባለሙያ አንዱ መሆን ችለዋል፡፡ ከእኚህ አንጋፋ የባሕር ኃይል መኮንን ጋር ነው ቆይታ ያደርግነው፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ከእንግሊዝ መልስ ሲሠሩ የነበረው በአብዛኛው በአጼ ኃይለሥላሴ ስም በምትጠራው እና ንጉሡ ሲመጡ የሚያርፉባት ልዩ ክፍል በያዘች መርከብ ላይ ነው፤ መርከቧንም በመርከቧ ውስጥ ያለችዋንም ክፍል ልዩ የሚያደርገው ምን ይሆን?

ኮሞዶር ጥላሁን፡– አብዛኛው የባሕር ኃይል አባላት ሥልጠና የሚሰለጥኑት በዚህች የጃንሆይ ተብላ በምትታወቀው መርከብ ላይ ነው:: ከዚህ የተነሳ ልዩ ያደርጋታል:: መርከቧ ወደ 250 ሰዎችን ትይዛለች:: በአብዛኛው ሰው የሚገኝባት ለሥልጠና ሲሆን ነው:: እኔ ራሴ እስከ ኃላፊነት ደረጃ የደረስኩት በዚያች መርከብ ሠልጥኜ ነው:: ከዚያ ሥልጠና በኋላ ነው በተለያዩ መርከቦች ላይ በኃላፊነት ተመድቤ ማገልገል የቻልኩት::

በወቅቱ ጃንሆይ (አጼ ኃይለሥላሴ) አብዝተው ወደዚያች መርከብ ይመጡ ስለነበር በመርከቧ ውስጥ እርሳቸው የሚያርፉባት ልዩ ክፍል ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ክፍሏን ልዩ የሚያደርጋት ደግሞ በወርቅ ቅብ የተዘጋጀች መሆኗ ነው::

አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በወቅቱ የነበረው ዋና ተልዕኮው ምን ነበር?

ኮሞዶር ጥላሁን፡– የኢትዮጵያን የባሕር ድንበር እና ጠቅላላ ክልሏን ከጠላት ጥቃት እና ከተለያዩ የውንብድና ተግባር መከላከልና መጠበቅ ነበር:: እንዲሁም ክልክል የሆኑትን እንደ ዓሣ ማሳገር ጭምር መከላከልም ነው:: በአጠቃላይ ባሕር ኃይሉ ያለበት ኃላፊነት ሕገ ወጥ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከል ነው::

ዋና ተግባሩ በሰላሙ ጊዜ ሥልጠና ማከናወን ነው:: የተለያዩ የሰው ኃይሎችን ብቁ ማድረግና ማደራጀትም ጭምር ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ባሕር ላይ የሚካሔዱትን ማንኛውንም ሕገ ወጥ ተግባራትን ሔዶ የመቆጣጠር እና አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል:: ባሕር ኃይሉ እስከ 1983 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ይህንን ተግባር ሲያከናውን የነበረ ነው::

የቀድሞው የኢትዮጵያ የባሕር ክልል በኪሎ ሜትር አንድ ሺ፣ በባሕር ማይልስ 540፣ የባሕር ግዛት ወደጎን Territorial water/ 12 የባሕር ማይል ነው:: የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ይቆጣጠር የነበረው ያንን ሁሉ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በእርስዎ እይታ የሚገለጸው እንዴት ነው?

ኮሞዶር ጥላሁን፡– በእርግጥ ባሕር ኃይሉን ትልቅ ባሕር ኃይል ነው ለማለት ይከብደኛል:: ባሕር ኃይልን ጠንካራ ባሕር ኃይል የሚያደርገው የሰው ኃይሉ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው:: ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚታጠቃቸው መሣሪያዎች ደግሞ ወሳኝ ናቸው:: በተለይ በጃንሆይ (አጼ ኃይለሥላሴ) ጊዜ የተወሰኑ የጦር መርከቦች እንዲሁም ጀልባዎች ነበሩን:: ከአሜሪካ ሀገርም በእርዳታ የተገኙ ነበሩ::

ከዚያም በደርግ ማለትም በወታደራዊ መንግሥት ጊዜ ጥሩ ትጥቅ ነበረ ማለት ይቻላል:: ምክንያቱም በወቅቱ ወታደራዊ መንግሥቱ ከሶቪየት ኅብረት ጋር በነበረው መግባባት የታጠቀው መሣሪያ ቀላል የሚባል አይደለምና ነው:: ምናልባት ባሕር ኃይሉ በቀይ ባሕር አካባቢ አሉ ከሚባሉት መካከል የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ከግብጽ ቀጥሎ ተጠቃሽ ባሕር ኃይል ነው::

በአጠቃላይ ግን በአፍሪካ ውስጥ ደግሞ ምናልባት ቀዳሚው ደቡብ አፍሪካ ይሆን እንጂ ከእኛ የተሻለ አልነበረም:: ስለዚህ በጥቅሉ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በወቅቱ ጠንካራ የሆነ ነበር ማለት ይቻላል:: በውስጡ የነበረው የሰው ኃይልም የተማሩ ስለነበሩ ጥሩ እንቅስቃሴ የነበረው ነው:: በወቅቱ ሲሰጠው የነበረውን ተልዕኮም ሲያከናውን የነበረው በአግባቡ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ወታደራዊው መንግሥት ሥልጣኑን ከተነጠቀ ከ1983 ዓ.ም በኋላ የባሕር ኃይሉ የመዳከም ምስጢር ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?

ኮሞዶር ጥላሁን፡– ባሕር ኃይል ሁለት ኃይል ነበረው:: አንዱ ጦር የታጠቀ መርከብ እና በሌላ በኩል የባሕር ኮማንዶ የሚባል ነው:: ይህ ኮማንዶ እግረኛ እንደሚባለው ዓይነት ሲሆን፣ ይህም የባሕር ኃይል ማሪን ኮማንዶ የሚባለው ነው፤ የሚንቀሳቀሰውም ባሕር ላይ ነው:: ባሕር ጠለቅም ኃይል ነበረው:: ባሕር ኃይል የሚባለው እነዚህ ሁሉ ተዳምረው ነው::

ከዳህላክ እና ከዚያ አካባቢ እስከለቀቅንበት ጊዜ ድረስ ባሕሩን ሙሉ ለሙሉ ስንቆጣጠር ነበር:: የሻዕቢያ ኃይል ምጽዋን ከተቆጣጠረ በኋላ እንኳን ሙሉ በሙሉ እንደልቡ መርከብ ማስገባት አይችልም ነበር:: ምክንያቱም በወቅቱ ባሕሩን እንቆጣጠር የነበርነው እኛ ነን:: በዚያም ተሰጥቶን የነበረውን ግዳጅ በሙሉ አጠናቅቀናል:: የነበሩንን መርከቦች ጠላት አንዳቸውንም ሳይወስደው ያሸሸን ነን::

የነበረብን ድክመት ባሕሩን በኋላ ላይ መቆጣጠር አለመቻል ነው:: ለምሳሌ ጥቃት የደረሰብን ምጽዋ ላይ በባሕር በኩል ሳይሆን በመሬት የመጣብንን ኃይል እግረኛ ያልኩት ኮማንዶ የባሕር ወለድ አንድ ብርጌድ ኃይል ኖሮን ቢሆን ኖሮ በሚገባ እንከላከላለን፤ ምጽዋንም አናስነካም ነበር:: ይሁንና በወቅቱ መንግሥት አልፈቀደልንም:: እኛ ራሳችን ካለን ስጋት የተነሳ ወደ አንድ ሻለቃ የሚሆን በራሳችን ማለትም በ«ሞተ ከዳ» በሚባል በጀት ሁሉ ነበር ስንገለገል የነበረው:: በመሬት በኩል መጥተው ምጽዋን ሊቆጣጠሩ የቻሉት ለዚህ ነው::

የማሪን ኮማንዶ ሙሉ በሙሉ ተጠናክሮ ባለማግኘታችንም ጭምር ነው:: በወቅቱ ሻዕቢያ ሊያጠቃ የመጣው ሁለት ጊዜ ነው:: የመጀመሪያው በ1970 ዓ.ም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ምጽዋን የተቆጣጠረበት በ1982 ዓ.ም ነው:: ምርኮኞቻችን ጀልባዎቻችን ናቸው ማለት ይቻላል:: ሲዋጉ የነበረው እንደ እግረኛ ሆነው ነበር::

አዲስ ዘመን፡- ኤርትራ ነፃ ሀገር መሆኗ ከተረጋገጠ በኋላ ኢትዮጵያ ወደብ ማጣቷ ይታወቃልና ያጣንበትን መንገድ የሚገልጹት እንዴት ነው?

ኮሞዶር ጥላሁን፡- ሻዕቢያ ምጽዋን በ1982 ዓ.ም መጥቶ በመቆጣጠሩ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ አሰብም እንዲሁ ነው ማለት ይቻላል:: እኛ ይዘን የነበረው ሁለት ዕዝ ነው:: አንደኛው የሰሜን ዕዝ ሲሆን፣ ያለው ምጽዋ ነው፤ ደቡብ ዕዝ ደግሞ ያለው አሰብ ነው:: እና የደቡብ ባሕር ኃይሎች አሰብ አካባቢ ያለው እስከመጨረሻው ድረስ በእኛ ቁጥጥር ስር ነበር:: ይህ ማለት እስከ 1986 ዓ.ም መሆኑ ነው:: ለቀን የወጣነው ጦሩ ሲለቅ ብቻችንን ምን እናደርጋለን በሚል ነው እንጂ አሰብ ሙሉ በሙሉ በእኛ ቁጥጥር ስር ነበር:: ትንሽ ሙከራ በጀልባ ሻዕቢያዎች ሞክረው ነበር:: ይሁን እንጂ የዚያን ያህል ኃይል አልነበራቸውም:: እኛ እስከ መጨረሻው እዚያ ነበርን:: እናም ያጣነው ምጽዋን ሙሉ በሙሉ ነው እንጂ አሰብ የእኛው ነበር::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሰብን የለቀቀችበት መንገድ አግባብነት አለው ብለው ያስባሉ? አሰብ በመታጣቱ የሚሰማዎት ስሜት ምንድን ነው?

ኮሞዶር ጥላሁን፡– አሰብን ያጣነው በፖለቲካ ውሳኔ እንጂ በኃይል አይደለም:: አሰብን በኃይል የተቆጣጠረ ማንም የለም:: ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ባሕር ኃይልን አፈረሰ:: ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ አሰብን አስረከበ:: ኤርትራ ምጽዋን ያገኘችው ነፃ በመውጣቷ ነው፤ ይህ ደግሞ ልክ መሆኑን ሁላችንም የምንቀበለው ነው:: አሰብ ግን ከእጃችን ሊወጣ የቻለው እንዳልኩሽ በፖለቲካ ውሳኔ ነው::

አሰብ በመታጣቱ ሁሉንም የሚያስቆጭ ጉዳይ ነው:: አንድ ሀገር መንቀሳቀሻ የሚሆነውን የባሕር በር ማጣት የለበትም የሚል እምነት አለኝ:: እኛ ይህን በማጣታችን የሚሰማን ስሜት አለ:: ምክንያቱም አንድ ሀገር የባሕር በር የለውም ማለት የመታሰር ያህል የሚቆጠር ነው:: መውጫ መግቢያ በሌለው ቦታ እንደመቀመጥም የሚታይ ነው:: በዋናነት የሚያስፈልገን በነፃ መንቀሳቀስ የሚያስችለንን የባሕር በር ማግኘት ነው እንጂ ወደብንማ በተለያየ መንገድ እናገኛለን:: በአሁኑ ወቅትም ምንም እንኳ የራሳችን ባይሆንም በመጠቀም ላይ እንገኛለን::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ዘመናዊ የባሕር ኃይልን ቀድማ ያቋቋመች ሀገር መሆኗ ይነገራል:: ይሁንና በኢህአዴግ ዘመን መፍረሱ ይታወቃል፤ በአሁኑ ወቅት ይህ የለውጡ መንግሥት ደግሞ ተቋሙን መልሶ እያደራጀው ነውና ይህን እንዴት ያዩታል?

ኮሞዶር ጥላሁን፡- በአሁኑ ወቅት እየተደራጀ ያለውን የባሕር ኃይል እኔም በሥራው ውስጥ በአማካሪነት ሠርቻለሁ:: ከቀድሞ የባሕር ኃይል አባላት መካከል አራት ያህላችን በማማከሩ ሥራ ተሳትፈናል:: በተለይ አራታችን ባደረግነው የማማከር ሥራ ባሕር ኃይል ተመልሶ እንዲቋቋም አድርገናል ማለት ይቻላል:: የሚቋቋመውም ልክ እንደ ድሮ እንዲሆን ነው:: እኛ በዚያ መልኩ አማክረናል፤ ተግባራዊ የማድረግ ድርሻ ደግሞ የመንግሥት ነው:: በጥቅሉ ለማለት የምፈልገው የባሕር በር ወሳኝ መሆኑን ነው::

ከዚህ ጋር ተያይዞ አሰብ ቢገኝ ጥሩ ነው:: ያንን የማግኘቱ ጉዳይ የመንግሥት ቁርጠኝነት ይሆናል ብዬ አምናለሁ:: ይህ የሚሆነው ግን በተለያየ መንገድ ሲሆን፣ ለምሳሌ ዋናው ጉዳይ ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ መሔድ የበለጠ ተመራጭ ነው:: እንዲያ ሲሆን ባሕር ኃይልም ይኖረዋል:: ሀገሪቱን በባሕር ኃይል ብቻ ሳይሆን የንግድ መርከብ እንቅስቃሴና የገቢ ወጪ ምርቱንም ሁሉ በራስ የመቆጣጠር ደረጃ ላይ የሚያደርስ ይሆናል:: ስለዚህ በሌሎች ላይ ጥገኛ ሆኖ መኖር ያበቃና በራስ ለመንቀሳቀስ ያስችላል::

አዲስ ዘመን፡- ለባሕር ኃይል መደራጀት የባሕር በር ወሳኝና እሱን ለማግኘት ደግሞ በዲፕሎማሲ መንገድ መንቀሳቀስ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፤ ከዚህ ባሻገር የባሕር በርን መልሶ ማግኘት የሚያስችሉ ሌሎች አማራጮች ይኖሩ ይሆን?

ኮሞዶር ጥላሁን፡– በእርግጥ ባሕሩ ሳይኖር ባሕር ኃይሉ መኖር አይችልም:: እንዳልኩት ነው፤ የባሕር በርን ለማግኘት ዋናውና ወሳኙ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ነው:: ጉርብትና እስካለ ድረስ እና ከጎረቤት ጋር አብሮ በሰላም መኖር እስካልተቻለ ድረስ ችግር መምጣቱ አይቀሬ ነው:: ስለዚህ ከጎረቤት ጋር ሊኖረን የሚችለው ግንኙነት ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ:: ከዚህ የተነሳም ፍላጎታችን በሰላማዊ መንገድ ሊመለስ የሚችል ነው የሚል እምነት አለኝ::

ኢትዮጵያ በኢህአዴግ ጊዜ አሰብን ለኤርትራ መስጠቷን ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው:: ይህ ውሳኔ የተደረሰበት በወቅቱ በነበረው መንግሥት አማካይነት ነው:: በዚያን ወቅት ጉዳዩ ሲከሰት የተቃወመ አካል ያለ አይመስለኝም:: በወቅቱ እኛን አሰናብተውናል፤ ነገር ግን በወቅቱ አሰብ ለኤርትራ ሲሰጥ ሕዝቡ መቃወም ነበረበት:: ይሁንና ተቃውሞ ያሰማ አካል የለም:: ያንን ያላደረገበት ምክንያት ቢጠየቅ ሁሉም የተለያየ ምክንያት ይኖረዋል::

አሁንም የባሕር በርን ለማግኘት በሚደረገው እንቅስቃሴ ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው ዲፕሎማሲ ነው:: ወደብ የማግኘት ጉዳይ ብዙም ከባድ አይደለም:: በዙሪያችን ጂቡቲን ጨምሮ ብዙዎች አሉ:: አሁንም ቢሆን እየተጠቀምንበት እንገኛለን::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ተስፋ ይኖራት ይሆን? በዚህ በኩል የዓለም አቀፍ ሕጉስ ምን ይላል?

ኮሞዶር ጥላሁን፡- ይህ እንኳ ከበድ ያለ ጥያቄ ነው:: በዚህ ጉዳይ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉት ፖለቲከኞች ናቸው ብዬ አስባለሁ:: ከባሕር ጋር በተያያዘ እና ከባሕር ሕግ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ሁኔታ በሌላ ሀገር ገጥሞ የሚያውቅ አይመስለኝም:: ምክንያቱም የራስን መሬት ቆርጦ ለሌላ ሀገር የሰጠ ሀገር ካለ ብዬ መረጃ ለማግኘት ሞክሬ ነበር፤ ግን አላገኘሁም:: በእርግጥ ምናልባት ሊኖር ይችላል:: እኔ ግን ስላላየሁ ነው፡።

ስለዚህ ኢትዮጵያ እንዳላት የሕዝብ ብዛት ታይቶ የባሕር በር ሊኖራት ይገባል:: እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ሀገር ናት:: ይህ ሁሉ ሕዝብ ደግሞ ሊኖረው የሚገባ ነገር አለ:: ከዚህ ውስጥ አንዱ የባሕር በር ሲሆን፣ ሁኔታዎች ደግሞ እንዲኖሩት ያስገድዳል:: በተለይ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትንም ሆነ ከሀገር የሚወጡትን ጉዳዮች ለማሳለጥ የባሕር በር ያስፈልገዋል::

ከፍ ያለ ሕዝብ እንቅስቃሴውም የዚያኑ ያህል ከፍ ይላል:: ስለዚህ ለዚህ ሕዝብ መግቢያ እና መውጫ ያስፈልገዋል:: ከዚህ አኳያ ምናልባት በዓለም አቀፍ ደረጃ ነገሮቹ ሊታዩ ይገባ ይሆናል:: ጉዳዩን እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድረስ በመውሰድ ለስኬታማነቱ መሥራት ይገባል:: ከዚያ አስቀድሞ ግን በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል የዲፕሎማሲ አካሄድ መፈጠር አለበት:: ዲፕሎማሲውን ማጠናከር ነው::

ጉዳዩን በሰጥቶ መቀበል መርህ ማስኬድ ይቻላል:: ይህንንም ሁኔታ ማየት አስፈላጊ ነው:: በዚህ በዲፕሎማሲና በሰጥቶ መቀበል መርህ የምንሔድ ከሆነ የባሕር በር ይገኛል የሚል ተስፋ አለኝ:: ያለን አማራጭ ይህ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ የሆነው ሌላ አማራጭ አዋጭ ነው ብዬ አላስብም:: ውጤት ያስገኝልናል ብዬም አልገምትም::

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባሕር በሯንም ሆነ በወቅቱ ጠንካራ የነበረውን የባሕር ኃይሏን በማጣቷ ምን ይሰማዎታል?

ኮሞዶር ጥላሁን፡- የባሕር ኃይላችንን ማጣታችን ሁላችንንም ቢሆን በጣም የሚያሳምም ነው:: የባሕር ኃይላችንን ብቻ ሳይሆን የባሕር በራችንንም ማጣት የሚያስቆጭ ነው:: ድሮም ቢሆን በአክሱም ዘመነ መንግሥት ጊዜ አጣን፤ በመጨረሻም በጃንሆይ (አጼ ኃይለሥላሴ) ጥረት ደግሞ መልሰን ባሕራችንን ማግኘት ቻልን:: አሁን ደግሞ መልሰን አጥተነዋል:: የባሕር በሩን ምናልባት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር መልሰን እንደምናገኘው ተስፋ አደርጋለሁ:: ይህ የሚሆነው ግን ጉርብትናን እስካሳመርነው ድረስ ነው::

አዲስ ዘመን፡- በሥራ ላይ እያሉ ያጋጠመዎ ፈተና ካለ? አሊያም ደግሞ በሥራዎ ደስ የተሰኙበት ጊዜ ካሳለፉ ቢገልጹልን?

ኮሞዶር ጥላሁን፡- አንዴ በ1960 ዓ.ም በጃንሆይ (አጼ ኃይለሥላሴ) አንድ ተልዕኮ ተሰጥቶኝ ነበር:: ይኸውም የዓባይ ወንዝን የማሰስ ተልዕኮ ነበር:: አሰሳውም የሚደረገው ዓባይን በማቋረጥ ነው:: እርሳቸው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር ተነጋግረው የተወሰነ ኃይል መጥቶ እንዲያይላቸው ጠይቀው ነበር:: የመጡትም የዘርፉ እውቀት ያላቸው ወታደሮች ናቸው:: እኔም ከዚህ ኃይል ጋር ተሳትፌ ነበር:: በወቅቱ የዓባይን ወንዝ አቋርጦ መመለሱ ትልቅ ጀብድ ነበር:: ዓባይን በጀልባ ከጫፍ እስከ ጫፍ በመሔድ ማቋረጡ በጣም ከባድ ጉዞ ነበር:: ልክ እንደ ማንኛውም ወንዝ ወይም ባሕር አይደለም::፡ ጉዞው በጣም ከባድ የነበረ ነው::

ከዚያ በፊት በርካታ የውጭ ሀገር ሰዎች ሞክረውታል:: ይሁንና በወቅቱ ሊሳካላቸው አልቻለም:: ለእኛ ግን ተሳክቶልናል:: አንደኛ ሳይንሳዊ ጥናትም ተካሂዷል:: በወቅቱ አራት የሞተር ጀልባዎች ነበሩን:: በዚያ ላይ ወደ 30 የምንጠጋ ሰዎች ነን ስናስስበት የነበረው:: አሰሳውንም ጀምረን የነበረው ደጀን አካባቢ ከሚገኘው ድልድይ ነው:: መቼም የዓባይ ወንዝ አፈሳሰስ በራሱ ተዓምራዊ የሆነ ነው:: በሁላችንም ዘንድ የሚታወቀው ውሃ መፍሰስ ያለበት ከላይ ወደታች ነው:: የዓባይ ወንዝ ግን በተቃራኒው ሁሉ የሚወርድ ነው::

ዓባይን በምናስስበት ጊዜ የእንግሊዞች የምድር ጦር አባላትና የተወሰኑ ደግሞ ሲቪሎች ነበሩ:: በተጨማሪም ከአየር ኃይል የተካተቱ አሉ:: የምድር ኃይልም ነበር:: እነሱ እኛ በምንንቀሳቀስበት ወቅት ሬሽን የሚያቀርቡልን ነበሩ:: አብዛኛው ጊዜ ግን ሬሽናችን የሚቀርብልን በአየር ላይ ሲሆን፣ ወርደው የሚያቀብሉንም በፓራሹት ነው:: ወንዙን ለማሰስ የወሰደብን ጊዜ ሁለት ወር ያህል ነው:: ይህ በሕይወቴ የማልረሳው ጊዜ ነው::

ከኢትዮጵያ ከእኔ በተጨማሪ የመከላከያ ሰዎች እንዲሳተፉ ተጋብዘው ነበር:: ይሁንና ከእኔ በስተቀር ሌሎቹ አልተላኩም:: ከሲቪል ደግሞ የማዕድን ሰዎች ተጋብዘው ነበር:: እነርሱም አልመጡም፤ ቢመጡ ኖሮ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት እንዳለ የሚነገርለትን ቦታ መለየት ይችሉ ነበር ባይ ነኝ:: በእነርሱ ፈንታ የመጡት እንግሊዞች በተወሰነ መልኩ ማዕድንም ያለበትን ለማጥናት ሞክረዋል:: በጥቅሉ ግን ከተለያዩ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የተጋበዙ ቢኖሩም መምጣት ግን የሆነላቸው አልመሰለኝም:: በመጨረሻም እኔን ጨምሮ አምስት ያህል ኢትዮጵያውያን ለጉዞው ዝግጁ ነበርን:: ይሁንና በውሃው ላይ ለመሄድ የበቃሁት ከኢትዮጵያውያኑ በኩል እኔ ብቻ ነኝ፡። የወንዙን 75 በመቶ የሸፈንኩትም እኔ ብቻዬን ነበር::

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እርስዎ ሥራ እየሠሩ ነው? በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት?

ኮሞዶር ጥላሁን፡– ከስደት ከተመለስኩ ቆየት ብያለሁ:: ማለትም ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በ1991 ዓ.ም ነው:: የነበርኩትም ጅቡቲ ነው:: በኢትዮጵያ በባሕር ኃይሉ የወሰድነው ትምህርትና ሥልጠናው መልካም የሚባል በመሆኑ በእዛም ሆኜ የባሕር ኃይል ውስጥ ለመሥራት በቅቻለሁ:: በመሆኑም ለተወሰኑ ዓመታት በሱማሌ፣ ገልፍ አካባቢ፣ ዱባይና ኢራንም በካፒቴንነት ተንቀሳቅሻለሁ:: ጅቡቲ ብቻ ወደ ስምንት ዓመት ያህል ቆይቻለሁ:: ከዚህ ውስጥ ሁለት ዓመት ያህል ባሕር ላይ ስሠራ ነው የቆየሁት::

በአሁኑ ወቅት እየሠራሁ ያለሁት በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ውስጥ ነው:: በዚያም የኮንስትራክሽን ሥራ ነው የምሠራው::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ ከልብ አመሰግናለሁ::

ኮሞዶር ጥላሁን፡- እግዚአብሔር ይስጥልኝ፤ እኔም አመሰግናለሁ::

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ጥር 18/2016

Recommended For You