በሀገራችን የሥጋ ደዌ በሽታ ታማሚዎች ከጤና እክል ባሻገር ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግሮች ከሚገጥሟቸው መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። ሥጋ ደዌ በእርግማን የሚመጣ እና በዘር የሚተላለፍ በሽታ አይደለም። ይልቁንም ማይኮ ባክትሪየም በሚል በሽታ አምጪ ህዋስ የሚመጣ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ህመሙ እንደማንኛውም በሽታ ታክሞ የሚድን ሲሆን፤ ነርቭን ቆዳን የሚያጠቃ በመሆኑ በወቅቱ ተገቢ ህክምና በአግባቡ ካልተወሰደ የእጅ እና የእግርን ስሜት በማደንዘዝ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶች ይዳርጋል።
የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ከተመሠረተ 27 ዓመት ሆኖታል። ማህበሩ ‹‹የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች እንደ ሌላው ማህበረሰብ እኩል ተጠቃሚ መሆን አለባቸው።›› የሚል ዓላማን አንግቦ ነው የተቋቋመው። በተጨማሪም፣ የግንዛቤ ሥራዎችን መሥራት፣ ታማሚዎቹን እና ቤተሰቦቻቸውን የሙያ ባለቤቶች እንዲሆኑ ማስቻልም ከኃላፊነቶቹ መካከል የሚመደቡ ናቸው።
አቶ ዐቢይ አባተ የብሔራዊ ማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ስለ ሥጋ ደዌ እና ታማሚዎች በሕብረተሰቡ በኩል ያለው አመለካከት የተሳሳተ እና የተዛባ መሆኑ በስፋት የሚታይ ነው። ችግሩ በመኖሩ ሳቢያ በርካታ ታማሚዎች እና ቤተሰቦቻቸው አድሎ፣ እንዲሁም መገለል ይደርስባቸዋል። በዚህም ምክንያት ለከፋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጫናዎች ይዳረጋሉ።
ብሔራዊ ማህበሩ በእስከ ዛሬ ጉዞው ብዙ ሥራዎችን ሰርቷል። ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት አብዛኛው ሕብረተሰብ ስለ ሥጋ ደዌ ግንዛቤው አልነበረውም። ባስ ሲልም ታማሚዎችን የሚያገል እንደነበር የሚያወሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ችግሩን ለመቅረፍም የሥጋ ደዌ ቀንን ታሳቢ በማድረግ ስለ በሽታው አመጣጥ እና እንዴት መከላከል እንደሚቻል በተለያዩ አማራጮች የግንዛቤ ሥራ ተሠርቷል። በተለይም በቴሌቪዥን በድራማ መልክ የሚተላለፉ መልዕክቶች ውጤት ማምጣታቸውን ይጠቅሳሉ። ምንም እንኳን መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፣ ዛሬም ድረስ ብዙ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ በመግለፅ፤ መንግሥት ግንዛቤን ከመፍጠር አኳያ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ይናገራሉ።
ማህበሩ በተለያዩ መድረኮች ችግሩን ለመቅረፍ የግንዛቤ ሥራዎች ይሠራል። የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሥጋ ደዌ ቀን ምክንያት በማድረግ የችግሩን አሳሳቢት ለማሳየት ይሞከራል። ‹‹የሥጋ ደዌ በሽታን አንዘንጋው›› በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ25ተኛ ጊዜ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ70ኛ ጊዜ ይከበራል። ጥር 18 እና 19 ቀን 2016 ዓ.ም በሀረር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን፤ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የፓናል ውይይት ይደረጋል። በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የህመሙ ይዞታ ምን እንደሚመስል ዝርዝር መረጃዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ።
አቶ ዐቢይ እንደሚገልጹት፤ ቀኑን ማክበር ያስፈለገው ሕብረተሰቡ ሥጋ ደዌ ላይ ያለውን የተሳሳተ እና የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል እንደሚያግዝ በማመን ነው። በህመሙ የታያዙ ሰዎችን ‹‹በሽታው የአምላክ ቁጣ ነው። በዘር ይመጣል።›› በሚል የተሳሳተ አመለካከት ከማህበረሰቡ ተገልለው ይገኛሉ። በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎችም ታማሚዎች በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ ተወስነው የሚኖሩ ሲሆን፤ ከሕብረተሰቡ ጋር ባለመቀላቀላቸው ምክንያት እነርሱም ሆኑ ሌሎች ስለ ሥጋ ደዌ በቂ ግንዛቤ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል ይላሉ።
ሌላው ቀኑን ማክበር ያለው ፋይዳ ችግሩን አስመልክቶ መንግሥት ጋ ያለውን ክፍተት ለማመልከት የሚያግዝ ሲሆን፤ እ.አ.አ “በ2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥጋ ደዌ ታማሚዎችን የማግለሉ እና መድሎ የማድረጉን ደረጃ ወደ ዜሮ እናደርሳለን። የሚለውን የዓለም የጤና ድርጅት እቅድ ታሳቢ በማድረግ፤ እቅዱን እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዓለም ለማሳካት ይረዳ ዘንድ ምክክሮች ለማድረግ ያግዛል። አሁን እየታየ ያለውን ቁጥር ለመቀነስም የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲነሱ፣ ብሎም ተግባራዊ እንዲሆኑ ያግዛል ይላሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁን ላይ በስጋ ደዌ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ፤ እንዲሁም ቁጥሩን ለመቀነስ ታማሚዎቹ በብዛት የት አካባቢ እንዳሉ ጥናት በማድረግ በሽታውን መቆጣጠር እንደሚገባ የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁን ያለው ቁጥር ለወደ ፊት ያሰጋልና ችግሩ ሳይባባስ በቁጥጥር ሥር መዋል እንዳለበትም ይናገራሉ።
የሥጋ ደዌ ተማሚዎች በሁለት መንገድ ይገለላሉ። አንደኛው ራሳቸውን በራሳቸው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ማህበረሰቡ ይተላለፍብኛል በሚል ስጋት ያገላቸዋል። ወደ ሕብረተሰቡ ያለምንም ፍራቻ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ ብሔራዊ ማህበሩ እየሠራበት ይገኛል። አቅማቸውን ለማብቃት ባሉት 80 ቅርንጫፍ ማህበራት አማካኝነት አቅማቸውን የማጎልበት ሥራም ይሠራል። እንዲሁም ራሳቸውን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ወፍጮ በመገንባት ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል። እንዲሁም በቡና ማሸግ እና መቁላት ሥራ ላይ ተሠማርተው በኢኮኖሚ ራሳቸውን ብሎም ቤተሰቦቻቸውን እንዲደገፉ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አቶ ዐቢይ ይናገራሉ።
ብሔራዊ ማህበሩ ከመንግሥት ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር በመረከብ ለስጋ ደዌ ታማሚዎች የሚሆን ማዕከል ገንብቷል። ማዕከሉ ያለ ውጭ ሀገራት እርዳታ ተረጂዎችን ይደግፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ የሥጋ ደዌ ታማሚዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ነድፎ መሥራት እንደሚገባም ያስረዳሉ።
የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የተጎጂዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም። የሁለም ጉዳይ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት እንደሚገባቸው አቶ ዐቢይ ይናገራሉ። በቀጣይም የግንዛቤ ሥራዎችን ለመሥራት የታቀደ ሲሆን፤ በተለይም መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ብዙ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ሕብረተሰቡም ታማሚዎችን ከማግለል ይልቅ ለተጠቃሚነታቸው እገዛ ማድረግ እንደሚኖርበት አስረድተዋል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥር 16/2016