ሎሚ ለሽታ ጥምቀት ለትውስታ

“እነሆ ጥምቀት ደረሰ፤

ነጭ እና መብሩቅን እየለበሰ”

ብለን ገና መጣ መጣ ከማለታችን በጊዜ የተሳፈረው ጥምቀት፤ እንደ ታክሲ ቆሞ አይጠብቅምና ትዝታውን ብቻ ጥሎልን እብስ አለ። ለመሆኑ ጥምቀት እንዴትስ አለፈ? መቼም የዋዛ አይደለምና ጥሎብን የማያልፈው የትዝታ መዓት የለም። በሀገራችን ኢትዮጵያ፤ በቅድስቷ ምድር የማይከበር በዓል የለም። አንዱን ከአንዱ ማስበለጥ ባይቻልም እንደ ጥምቀት ያለ ደማቅ ክብረ በዓል ለማግኘት ግን ያዳግታል። አብዛኛዎቹ በዓላት በገጠርና ከተማ አሊያም እንደየአካባቢው፤ የአከባበር ሥርዓትና ድምቀታቸው ይለያያል። በጥምቀት ምድር ግን በመላው ኢትዮጵያ ከገጠር እስከ ከተማ አቧራው ይጨሳል።

ጭፈራው … ድለቃው … ዳቦና ጠላው፤ ብቻ ምኑ ቅጡ … ከወዲያ መንፈሳዊ የአምልኮ ሥርዓቱ፤ ከወዲህ ደግሞ የባሕል ድግሱ፤ ላይና ታቹ በአጀብ የተሞላ ነው። “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለው ፉከራዊ አባባል ውስጣዊ ወኔውን እየቀሰቀሰው በአንድ እግሩ ቆሞ ጥምቀትን ፍለጋ የማይወጣ የለም። ጥምቀትም በእኩልነት ያምናል፤ ምንም ባይኖረን ካላቸው እኩል በደስታና ፌሽታ እናከብራለን። “ደም ካልፈሰሰ፤ ደም ካላየሁ” አይልም። በእለተ ጥምቀት እንዲሁ ዝም ብለን ወደ አደባባይ ብንወጣ፤ በባዶ ኪስ ወጥተን በገንዘብ ሊተመን የማይችል ደስታና እርካታ ሸምተን እንገባለን። ምክንያቱም ጥምቀት የነብስ እንጂ የሥጋ ብቻ አይደለም።

የበዓሉን ደስታ የምናገኘው በአደባባይ ተሰባስበን በኅብረት ያለንን ስሜት በማዋጣት እንጂ፤ ስላለን ብቻ በተናጠል የምንሸምተው ባለመሆኑ ነው። ከምንም በላይ ኅብራዊ የመንፈስ ትስስርን ይሻል። ቢኖርም ባይኖርም ጥምቀት አያስጨንቅም። ትዝታም ሳይጥል አያልፍም። አብዛኛዎቻችን የጥምቀቱን ቀሚስና ጃኖ አውልቀን ካስቀመጥን ቀናት ተቆጥረው ሳምንት ለማስቆጠር ሁለት ያህል ቀናት ቢቀሩትም፤ የሞቀው ውሃ ግን ገና አልቀዘቀዘም። በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ዛሬም ድረስ ዘልቋል።

በጥምቀት ምድር፤ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እያለ ባለው ሁሉ አጊጦ፤ አምሮ እንዲሁም አሸብርቆ የሚወጣው ሰው ብቻ አይደለም። ጥበብም ልክ እንደ ሰው ሁሉ በኪነ ጥበባት ድግስ ደመቅ ብላ፤ ከወትሮው በተለየ እምር ትላለች። የሚያብለጨልጨውንም የውብ ቀሚሷን ጥለት አዘቅዝቃ፤ እንደ ማለዳ ጀንበር ትወጣለች። ለጥምቀት የማይነሳ ብዕር የለም። ከያለበት ተጠራርቶ የማይሰባሰብ የሙዚቃ መሣሪያም እንዲሁ። ባለቅኔው ይቀኛል። አዝማሪው ያንጎራጉራል። ተወዛዋዡም ይወዛወዛል። ሠዓሊው በሥዕሉ፤ የቅርጽ ንድፍ ጥበበኛውም በቅርጻ ቅርጹ፤ ሁሉም ያለውን ይዞ ወደ አደባባይ ይወጣል።

በዓሉ የአንዲት ቀን ብቻ ባለመሆኑ የአክባሪው የተዝናኖት ፍላጎት መጠኑ የገዘፈ፤ ዳርቻውም የሰፋ ይሆናል። ይህን ፍላጎት ተከትሎም በየስፍራው የሚቀርቡ የኪነ ጥበብ ሥራዎች የበዓሉ ዋነኛ ድምቀት ናቸው። በጥምቀት ብዙ ትዝትና ትውስታዎች “አሉኝ” ብንል፤ የትዝታዎቻችን ጥፍጥና ከእነዚሁ የጥበብ ጓዳዎች የራቀ አይደለም። ከሚከወኑ መንፈሳዊ ሥርዓቶች በተጨማሪ የክብረ በዓሉን ውበት የምንለካው፤ ተገኝተን ከተቋደስናቸው ኪናዊ የባሕልና የጥበብ ትርዒት አንጻር ነው። የጥምቀት ውበቱ ከምኑ ላይ ይሆን? ስንልም፤ ከአልባሳት፣ ከሚበላና ከሚጠጣው ብቻ እንዳልሆነ እንገነዘባለንና።

በጥምቀት የሚታዩ ባህላዊና ኪናዊ ቱርፋቶች ሁሉ ይማርካሉ። በዚህ ጊዜ የማይከውን ምንስ አለ፤ ውበት ከውበት ይለካል። ፍቅር በፍቅር ይታጨዳል። ከሁሉም ለመብለጥ ሁሉም አሸብርቆ ይመጣል። የቆነጃጅቱ አለባበስና የጸጉር አሠራር የወንዱም እንዲሁ ማራኪ እይታን ያጎናጽፋል። የጎበዙ የከዘራ አያያዝ ወንድነቱን ይናገራል። ሸንቀጥ እያለ ከውስጡ የጀግንነትን መንፈስ ለመላበስ ይታገላል። ጀግንነቱ ቢኖርም ባይኖርም፤ መስሎ መታየቱ ግን ግድ ነው። ምክንያቱም ከብዙዎች መሐል በዓይኑ አይቶ የወደዳትንና የተመኛትን፤ የሕይወቱ አጋር ልትሆን የምትችለዋን ሴት በዚህ ሁሉ አማሎ የራሱ ማድረግ አለበት። ልክ እንደ እርሱው አይቶ የሚመኛትም ብዙ ነውና `ሳይቃጠል በቅጠል` ነው ነገሩ። በተባረከው እለት የርሷ የሆነውን ልበ ሙሉ የምትጠብቀዋም ሴት አትጠፋም። ሴቶቹም፤ ከሁሉም ሴቶች በላይ ቆንጆና ውብ ሆኖ ለመታየት ከጌጣ ጌጡ እስከ አልባሳቱ ባለው ሁሉ ይጠበቡበታል። በዓይኑ እያየ በልቡ ሲከጅላት የነበረው ጎበዝም እንዲህ ሲል ይጫወትላታል፤

አሞራው በሰማይ ሲያይሽ ዋለ፤

የአንገትሽን ንቅሳት ውበትሽን እያለ።

እንግዲህ አሞራው እርሱ እራሱ መሆኑ ነው። ልቧን አሸፍቶ ለመዝረፍ ሲል አስቀድሞ ቅኔውን በግጥምና በዜማ መዝረፍ የወጉ ነው። ጥምቀትን በጣፋጭ ትዝታ ከሚያስናፍቁን ነገሮች አንደኛው ሙዚቃ ስለመሆኑ ክርክር የለም። በጥምቀት ኪነ ጥበብን በጥበብ፤ ጠቢባኑን በትውስታ ዓይነ ሕሊና አሻግረን መመልከታችን አይቀርም። በሙዚቃ ሥራዎቻቸው የልብ ትርታችንን ቀስቅሰው ጥምቀት በደረሰ ቁጥር ትዝ፣ ትውስ የሚሉን በርካታ ድምፃውያንና ሥራዎቻቸው ከፊታችን ድቅን ይላሉ።

“ሎሚ ብወረውር ፤

ደረቱን መታሁት።

አወይ ኩላሊቱን

ልቡን ባገኘሁት”

ስትል በቻቺ እስክስታ ድምፃዊቷ የወጉን አድርሳ ነበር። የዘንድሮን ጥምቀት ግን በዚህ ታዘብኩት። በዕለተ ጥምቀቱ ይህን መሳጭ ውብ ባሕል ለመመልከት ላይ ታች ብልም፤ ሎሚው ይሁን ልብ ጠፍቶ ይህን ግን ለማየት ሳልታደል ቀረሁ። አልፎ አልፎ ከአንዳንዶቹ እጅ ላይ የሚታይ ቢሆንም ነገረ ግን፤ ‘ሎሚ ለሽታ’ እያለ ከአፍንጫው ስር ሽታውን መማግ የመረጠ ይመስላል። ይሁና … ብለን ወደ ሙዚቃው ስናልፍ፤ በጥምቀት ሰሞን የምንወደውንና ትውስታችን ያረፈበትን ሙዚቃ አለማድመጥ፤ ውስጣዊ ድባባችንን ቀዝቀዝ ከማድረጉም በላይ ቅር ቅር ያሰኘናል። ለአብነትም ይሁኔ በላይ፤

እዮ ዘገሊላ ዕለት

እቴ ዘገሊላ ዕለት

ነይልኝ በኔ ሞት

ለአስተርዮ ማርያም (2 ጊዜ)

እመጣለሁ እኔም።

በጥምቀት የወደዳት ቆንጆ ድንገት ከዓይኑ ሽው ብትል የፍቅሩን ቀጠሮ በአስተርዮ ማርያም ይሁን ይላል። ወትሮም የምናዳምጣቸው ሙዚቃዎች፤ ጥምቀት በመጣና በሄደ ቁጥር የትዝታና ትውስታን ድፍድፍ ጥለውብን፤ ዳግም የማይመለሱ እስኪመስለን ይናፍቁናል። ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ጎንደርና ኢትዮጵያ”፤ ሰማኸኝ በለው “ደቦት እንሥራ”፤ አቦነሽ አድነው “ባላገሩ” አዲስ አበባንና የዘንድሮውን ጥምቀት አዋደው፤ እኛንም ለትዝታና ናፍቆት ከዳረጉን ሙዚቃዎች መካከል ነበሩ።

ለጥምቀት የሚሆን ግሩም የዜማ ገጸ በረከት ይዞልን የመጣ ድምፃዊም ነበር። ከዚህ ቀደም “ኧረ ጉዴ ኧረ ጉዴ፤ ይህ መወደድ ያኮራል እንዴ” በሚለው ሥራው አድናቆትን ለማትረፍ የቻለው ሚኪያስ ንጉሤ (ሚኪ ላላ) ከሦስት ሳምንታት በፊት ደግሞ ‘ኩንስንሷ’ እያለ የሚገልጻትን ሸጋ ልጃገረድ “ቆየን ካየን” እያለ በነጠላ ዜማ አድማጩን ከነስሜቱ ቁጭ ብድግ አስደርጎበታል። “እንዲህ አይነት ሙዚቃ ካየን እኛም ቆየን” ያሉ ብዙ ናቸው። እነዚህን ጨምሮ በርካታ ሙዚቃዎች የዘንድሮውን ጥምቀትን ሞቅ ደመቅ አድርገውልናል።

ከፀደይ መልስ ውሃ ጠምቶት ላንቃው በደረቀው በጥር ወር፤ የጥምቀት ሰሞን ላይ፤ ሰማይ ሳይጠቁር ደመናም ሳናይ ቅኔ ይዘንባል። በዚያ ሰሞን ቅኔን ለባለቅኔው የሚተውለት የለም። ገበሬውም በጓሮና በመስኩ ሁሉ ቅኔን ዝረፍ ዝረፍ ያሰኘዋል። ባለውለታውን የሚረሳ አይደለምናም የሕይወቱ መሠረት የሆነውን በሬውንም እንዲህ ሲል በቅኔ ዜማ ያዜምለታል፤

አለኝ አንድ በሬ እንደኔው የከፋው

የሆዴን ብነግረው የጉንጩን ሳር ተፋው!

በሬ እንደ አንተ የሚሆን የሚሽከረከር፤

ጎኔ እንደ አንተ የሚሆን የሚሽከረከር

እንዝርትም አይገኝ ከፈታይ መንደር።

በሬ አንተን የጠላ ጎኔ አንተን የጠላ፤

የገና የጥምቀት ይለምናል ጠላ።

ይሄ ገበሬ “ጎኔ” እያለ የሚጠራው የሚያርስለትን በሬውን ነው። ቃሉን ቅኔ አልብሶ በሬው የእርሱ ማረፊያ ጎኑ ስለመሆኑ ይነግረናል። ለበሬው የሚገባውን ነፍጎ ለጠላውማ በገና በጥምቀቱ ምንም ተስፋ እንደሌለው ጭምር እቅጩን ይነግረዋል። በክረምቱና በዝናቡ ወቅት መሥራት የነበረበትን ለዘነጋ ሰነፍ ዓመቱን ሙሉ በዓል ብሎ ነገር የለውም። የሰው እጅ እንዳየ ጾሙን ውሎ ጾሙን ያድራል። ጥምቀትን ሌላ ምን ያስናፍቃል፤ ስንል የወጣቶቹ ጨዋታ ነው። በየጎዳናውና መንደሩ በሠፈርም ሆነ በአጋጣሚ በአንድ ተሰባስበው በባሕል ጭፈራ፤ እንዲሁም፣ ልዩ ልዩ ጨዋታ ያደምቁታል።

በወሎ፣ ላሊበላ፤ በላስታና ሰቆጣ እስክስታ ይንቀጠቀጣል። በዜማ በቅኔው አንዱ ከአንዱ ብሽሽቁ ሁሉ ተናፋቂ ነው። ውስጣዊ ስሜታቸውን ያንጸባርቁበታል። አድናቆትን፣ ፍቅርን፣ ውዳሴን አንዳንዴም ቅኔ አዘል ተረብን የመሰለ ነገር እናስተውልባቸዋለን። እንኳንስ የሀገሩን ሕዝቦች ቀርቶ፤ ከባሕር ማዶ ሳይቀር በአንዲት ጥላ ስር ባሰባሰበው የጥምቀት በዓል፤ በዕለቱ መስቀል አደባባይ የተለየ ነበር። በብሔር ብሔረሰቦች የባህል ጭፈራ ደምቆ፤ ኪነ ጥበብ አንድነት፤ አንድነትም የውበት ጌጣችን መሆኑን ያሳየ ትርዒት ነው።

ጃንሜዳም የተዋበውን የሽሮሜዳ ቀሚሷን ለብሳ ነበር። ዘንድሮም ይህን ከመሳሰሉት ትውፊቶቻችን ጋር ከወዲህና ወዲያ `ጢው ጢው` የሚለው የሃርሞኒካ፤ የሙዚቃ መሣሪያ ድምፅ ትዝታ ጣይ ድምቀት ነበር። ምናልባትም ከአዋቂው ይልቅ በሕጻናቱ እጅ ላይ በዛ ብሎ ይታይ ነበር። ከሀርሞኒካው ባሻገር በተወሰኑ ስፍራዎች በየአጥሩ ተከልለው ያሉትን ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎቻችንን ይዘን ብንወጣ ከምንም በላይ ለሙዚቃችን ዳግም ትንሳኤ ይሆን ነበር።

በጥምቀት ምድር የኢትዮጵያን አፈር ለመርገጥ የሚመኝ ብዙ ነው። ጥቁር ቢሆን ነጭ፤ ከምዕራብ ቢሆን ከሩቅ ምሥራቅ ያየ የሰማው ሁሉ ናፍቆ መምጣቱ የማይቀር ነው። በጥምቀት ሰሞን፤ የጥበብ አብዮት ተቀስቅሶ ጥበባት ለማበባቸው አንድም ከዚሁ ነው። የባሕላዊ ጭፈራ ቤቶች ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልተው ይፈሳሉ። የአዝማሪዎች ቅላጼ እየተስረቀረቀ፤ ግጥምና ዜማው ይዥጎደጎዳል።

ከወዲህ ጥግ ጭብጨባ፤ ከወዲያ ጥግ ተቀበል ነው። እስክስታው አወራረዱ ፉከራና ሽለላው እንዲሁ በደስታ አስክሮ፤ ሲለዩት በትዝታና ናፍቆት የሚንጥ ስለመሆኑ ይረዱታልና ዓመት ዓመት እየጠበቁ ለዚሁ የሚመጡም ብዙ ናቸው። እነዚህ እንግዶች እንደ ሌላው ዓመት በገፍ ሆነው ባይታዩም ዘንድሮም በሀበሻ ቀሚስና በጃኖ ሱሪ ሲምነሸነሹ ነበሩ። ብዙ ትርዒቶችን ብመለከትም አንዲቷ ግን፤ ግርምትን ጭራብኝ ነበር።

እሁድ ከሰዓት፤ ከደጃች ውቤ መንደር አለፍ ብሎ፤ ከአንደኛው ጎዳና ዳር ካለ መዝናኛ ሥፍራ፤ በርከት ያሉ ወጣቶች ተሰባስበው በጭፈራ አቧራውን ያጨሱታል። ድንገት በዚያ ሲያልፉ የነበሩ አራት ነጮች ይህን ይመለከቱና ቀልባቸውን ቢስበው ጊዜ መጥተው ወጣቶቹን ተቀላቀሉ። ከአራቱ ሁለቱ ወንዶችና አንደኛዋ ሴት በጭፈራው ለመንቀጥቀጥ ሲውተረተሩ፤ አንደኛዋ ሴት ግን በዚያና በዚህ እየተሽከረከረች በያዘችው የቪዲዮ ካሜራ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በስልኳ እያፈራረቀች ትቀርጽ ጀመር። በጭፈራ ላይ ያሉትን፤ ወጣቶቹ በፍቅር ተቀብለው ከመሐል በማስገባት እስክስታ በየአይነቱ ያስወርዷቸዋል። ድንገት መብራቱ ጠፋና ሲያንባርቅ የነበረው ግዙፍ ቴፕ ጸጥ እረጭ አለ።

መብራቱ ቢሄድ ቅኔውን ማን ዘርፎ፤ ማን ሊቀኘው ነው፤ ያለው ወጣት ወዲያው በድምፁ ማስጨፈሩን ቀጠለ። እዚህ ጋር ነበር ግርምቱ፤ እንግዳ ነው ያሉት ፈረንጅ ከልጁ ድምፅ አስታኮ ድምጹን በማስገባት፤ ቅኔውን ይዘርፍ ጀመረ። ባሕላዊ ሙዚቃዎችን እያቀያየረ ያስጨፍራል። በአንዳንዱ ቃላት ቢሰናከልም ጭፈራና ሙዚቃ አያያዙን ከሰውነት እንቅስቃሴው ጋር ላየውማ፤ አንድ የፒያሳ ‘ጨላጣ’ ነው የሚመስለው። ነገሩ ሁሉንም ሳያስገርም አልቀረም። ከጎኔ የነበረው ልጅ መወዛወዙን አቁሞ ፈዞ እየተመለከተው “ይሄስ ምኑ ፈረንጅ ነው፤ የጎጃም እረኛ ነው እንጂ” አለ።

በመሐል ቀድሞ ሲያስጨፍር የነበረው ወጣት፤ እጁን ወደ ኪሱ ሰዶ ድፍኗን የሁለት መቶ ብር ኖት አውጥቶ እፈረንጁ ግንባር ላይ ለጠፈለት። ሌላ ሁለት ልጆችም ሀምሳና መቶ ደገሙት። ለካስ ኢትዮጵያ ሀገሩ ብቻም ሳትሆን ቤቱም ጭምር የሆነች ቤተኛ ኖሯል። ኋላ ላይ ከድካሙ የተነሳ ትንፋሽ አጥሮት እያለከለከ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለአስር ዓመታት ያህል እንደኖረና ሁሉንም ነገር በደንብ እንደሚያውቅ በመናገር፤ ልጆቹ በሸለሙት ብር ላይ ስድስት ያህል ባለ ሁለት መቶ ኖቶችን ጨምሮ ለወጣቶቹ ሰጠና ሦስቱን እንግዶቹን ይዞ ተሰናብቶ ሄደ።

በጥምቀት ጥበብ ከባሕላዊ ትውፊቶቻችን ጋር ብቻም እንዳልሆነች መቸም እንዳልዘነጋነው ተስፋ አደርጋለሁ። ኪነ ጥበብ በሁሉም ሥፍራ፤ በየትኛውም ጊዜና ቦታ እፁብ የማጣፈጫ ቅመም ነውና። ከጥምቀተ ባሕር እስከ ልዩ ልዩ ጎዳናዎች ድረስ የነበረው መንፈሳዊ የሆነው የክብረ በዓሉ ሥነ ሥርዓት፤ በኪነ ጥበባዊ መዓዛ እንዳወደ ነበር። ወረቡ፣ ሽብሸባው፣ ለነብስ ሲሳይ የሆኑት ዝማሬዎች በበገናና መለከቱ፤ እንዲሁም በመሰንቆና ክራሩ ተዋሕደው ውብ ድባብን ሲያጎናጽፉት ነበር።

ዕጣን ዕጣን ሸተተኝ መሬቱ፤

አባቴ ሚካኤል ያደረበቱ።

በስተመጨረሻዋ ስንኝ ውስጥ “አባቴ ሚካኤል” የምትለዋን እንደየታቦታቱ ስም በመቀያየር በተመሳሳይ ዜማ ቅኔው ይወርዳል። የከርሞውን እየናፈቅን ለዛሬው የትዝታ ማኅደር የሆነን የዘንድሮውን የጥምቀት በዓላችንን ብናይ፤ ብዙ የትዝታ ስንቅ የሚቋጥርልን ነበር። ግን በአንዴ ከሁሉ ተገኝቶ ሁሉን ለማየት አይቻልምና ያየሁ የተሰማኝን ይቺን ታህሏን ካልኳችሁ፤ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና፤

ከርሞ እንገናኝ በዓመት፤

ከርሞ እንገናኝ በአመት፤

አንተም ደህና ብትሆን፤

እኛም ባንሞት።

መባባሉ ወትሮም ልማዳችን ነውና እኔም የወጉን አድርሼ አበቃሁ።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ጥር 16/2016

Recommended For You