መንግሥትን ከሀገሩ መለየት ያቃተው . . .!

‹‹መንግሥት ሥራውን ይሠራል፤ ሕዝብን ይመራል። ጊዜው ሲያልቅ በየትኛውም መንገድ የሚቀየርበት አጋጣሚ ይፈጠራል። በጣም የሚደንቀኝ ግን በሥልጡን ዓለም የሚኖሩ አንዳንድ ዲያስፖራዎች ይህንን አያውቁም። ወይም ድርጊታቸው በሙሉ ይህን እንደማያውቁ አስመስሏቸዋል። ›› ሲል ተሰማ መንግሥቴ በተደጋጋሚ የሚያበሳጨውን ጉዳይ ተናግሮ በረዥሙ ተነፈሰ።

ዘውዴ መታፈሪያ በበኩሉ፤ ‹‹በእርግጥ ሀገር እና መንግሥት ፍፁም የተለያዩ ናቸው። ሀገር አጠቃላይ ሕዝብን፣ ሉዓላዊነትን፣ ድንበርን የሚያካትት ብቻ አይደለም፤ ሀገር የጋራ ማንነትን፣ ባሕልን፣ የጋራ ኢኮኖሚን እና ሌሎች በቃል ሊገለፁ የማይችሉ ብዙ ጉዳዮችን ዓምቆ የያዘ መገለጫው ብዙ የሆነ ነው። ሀገር የአንድ ሰሞን መንግሥት አይደለም። መንግሥት ሀገርን የሚያስተዳድር ሥርዓት ነው። ሀገር ለዘላለም ሲኖር፤ መንግሥት ግን ለዘላለም አይኖርም። ›› ሲል የሀገር እና የመንግሥትን ልዩነት ተናገረ።

ገብረየስ ገብረማሪያም ከት ብሎ እየሳቀ፤ ‹‹ ባለምጡቅ አዕምሮ ባለቤት ነን ባዮቹ ከመጽሐፍ መደርደሪያ ፊት ለፊት መነፅራቸውን እያስተካከሉ ቁጭ ብለው ሲናገሩ፤ በተደጋጋሚ መንግሥትን አምርረው እንደሚጠሉ ሳይሆን ባለማስተዋል ሀገራቸውን አምርረው እንደሚጠየፉ አልፈው ተርፈው እንድትጠፋ የሚፈልጉ መሆኑን ሲናገሩ ታዝቤአቸዋለሁ። ተከታዮቻቸውም ለምን ይህን ትላላችሁ? ብለው አይጠይቋቸውም። ›› ሲል እርሱም እንደተሰማ አንዳንድ ዲያስፖራዎችን እየታዘበ መቆየቱን ተናገረ።

ዘውዴ እንደለመደው የእነተሰማን ንግግር በጽኑ ለመቃወም አልሞከረም። ነገር ግን ከእነርሱ የሚለይበትን፤ አንዳንድ ዲያስፖራዎችን የሚቃወምበትን እና የሚደግፍበትን እውነተኛ እምነቱን ተናገረ። ‹‹በእርግጥ ሁልጊዜ ነገርን በቅጡ ሳያዩ ፍፁም መጥፎ ጎኑን ብቻ ለማየት ራስን ማዘጋጀት ስህተት ነው። በሌላ ጎን አንድን ውሳኔ መጠራጠር ደግሞ መብት ብቻ ሳይሆን የሚደገፍ ነው። ዲያስፖራው መንግሥት የሚወስደውን እርምጃም ሆነ የሚሠራውን ማንኛውንም ሥራ ፍፁም ደጋፊ መሆን አለበት ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም። መጥፎ ጎኑን ብቻ ሳይሆን ደግ ጎኑንም መመልከት ይገባዋል። ካላችሁ ግን እስማማለሁ።

በእርግጥ ለኢትዮጵያ ወደብ የሕልውናዋ ጉዳይ ነው። ይህንን ተከትሎ በመንግሥት በኩል ለዘለቄታው የወደብ ችግርን ለማቃለል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ። ከሥራዎቹ መካከል ለጊዜው የተሻለ ነው ተብሎ የታመነበትን ከሶማሌ ላንድ ጋር በወንድማማችነት እና በትብብር ወደብ የማግኛ ድርድሮች ስለመካሔዳቸው ሲነገር፤ አንዳንድ ዲያስፖራዎች ‹ሙሉ ለሙሉ ትክክል አይደለም። ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ በኩል ወደብ ማግኘት የለባትም። ከዚህ በኋላ ከንቱ ጥረት ነው፤ ኢትዮጵያ ፍፁም ወደብ ማግኘት አትችልም። › ብለው በየክርክር መድረኩ እና በተለያዩ የማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ መናገራቸውን እቃወማለሁ። በጉዳዩ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው መግለፃቸው ግን ምንም የሚያስከፋ ነገር የለውም። ነገር ግን መንግሥትን እና ሀገርን ባለመለየት የመንግሥትን ሥራ ለመቃወም በሚመስል መልኩ ሀገር ላይ ጉዳት የሚያስከትል ንግግር ማድረግ ፍፁም ተገቢ አይደለም›› ሲል ተናገረ።

ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ በእርግጥ ኢትዮጵያ ያለችበትን ተጨባጭ ችግር የማያውቁ ይኖራሉ። ጅቡቲ ላይ ከአስር በላይ ኃያላን ሀገራት የባሕር ኃይላቸውን እያሠፈሩ ነው። በሆነ አጋጣሚ እርስ በእርስ ቢጋጩ እንኳ የኢትዮጵያ ጉሮሮ ሙሉ ለሙሉ ተዘጋ ማለት ነው። ኢትዮጵያ አንዲት የጅቡቲ ወደብ አማራጭን ብቻ ይዛ መቆየት በዓለም እየታየ ካለው ፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር እጅግ አደገኛ እና አስጊ ነው። ይህንን አስቀድሞ ለመከላከል አማራጭ በሮችን ለማግኘት ማማተር የግድ ነው።

ይህ አሁን መግባባት ላይ የተደረሰበት ከሶማሌ ላንድ ለሃምሳ ዓመት በሊዝ ይዘን የምንጠቀምበት ወደብ ደግሞ በከፍተኛ ጥንቃቄ በጦርነት ሳይሆን፤ የዓለምን ሕግ መሠረት ባደረገ መልኩ በሰጥቶ መቀበል መርሕ በብልሃት በጣም የሚያጓጓ ጥቅምን በማሳየት ለማግኘት መሞከርን ከኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም አንፃር አይቶ ማሞገስ እንጂ በዘይላ እና በበርበራ መሐል ያለችው ሎጋያ የሶማሌ ናት። የሎጋያን አካባቢ ኢትዮጵያ ከያዘች የሶማሌ መንግሥት ይከፋል፤ የሶማሌ ሕዝብ ኢትዮጵያ ላይ ቂም ይይዛል፤ ብሎ መመፃደቅ አገር ወዳድነት አይደለም።

እኛም እያልን ያለነው ይህንኑ ነው። አንተ እንደምትለው አንዳንድ ዲያስፖራዎች የሚሰጡት ሃሳብ ፍፁም ያሳፍራል። ለችግሮች መፍትሔ የሚገኘው ያለፈውን በደንብ በመመርመር እና አሁን ያለውን ሁኔታ በማጥናት መሆን ሲገባው አስቀድሞ ማጥላላት ላይ ሲያተኩሩ ይታያሉ። በጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራ ሲሠራ እነርሱ ግን በተቃራኒው፤ ዓሣ ለመያዝ እንደሚደናበር ዓይነስውር ወይም ዓይኑን በጨርቅ አስሮ ጥንቸል ለመያዝ እንደሚሯሯጥ ጅል በስሜት በደመነፍስ ነገሮችን በአንድ ወገን በማየት አዋቂ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ።

ሀገራቸውን በተመለከተ የሚሰጡት አስተያየት ያስደነግጣል። ከምንም በላይ በጣም ያበሳጨኝ አንድ ተንታኝ ነኝ ባይ “ኢትዮጵያ ፍፁም ወደብ ማግኘት አትችልም።› ሲል የተናገረው የሃሳብ ገበታ ተሳታፊው ፕሮፌሰር እጅግ አሸማቆኛል።” ሲል ተናገረ።

በእለቱ ዘውዴ ከመቼውም ቀን በላይ ከነተሰማ ጋር ተግባብቷል፤ እርሱም በበኩሉ፤ ‹‹አትፍረድባቸው፤ ዋነኛው ችግር አንተ እንደገለጽከው መንግሥት እና ሀገርን የመለየት ስላልቻሉ ነው። አሁን ያለውን መንግሥት የመጥላት ዝንባሌ በአንዳንድ ዲያስፖራዎች ዘንድ ይታያል። ይህ የተለመደ ነው። በፊትም እንዲህ ነበር። ወደፊትም እንዲሁ ይሆናል።›› ሲለው፤ ተሰማ ከተል አድርጎ ‹‹ራስን አድኖ ጠላትን ማጥፋት በሚመስል መልኩ መንግሥት እና መሪን መጥላት፤ ሀገርን ከመንግሥት መነጠል አለመቻል አልፎ ተርፎ የሀገርን ችግር ለማቃለል ወይም ለማስወገድ በሚወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ የሚሠነዘሩ ትችቶች ያስነውራሉ። አንዳንዱ ደግሞ እነርሱን ተከትሎ ይሳሳቃል። ›› አለ።

‹‹የጨው ክምር ሲናድ የሚያውቅ ያለቅሳል፤ የማያውቅ ግን ይልሳል እንደሚባለው፤ አንዳንዱ ዲያስፖራ ደንታ ቢስ ነው። ኢትዮጵያ ላጋጠማት ችግር መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ በሚወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ያሾፋል። ሀገሩን ለሌሎች አሳልፎ ይሰጣል። ለሀገር ጠቃሚ ነገር ሲሠራ አድንቆ እንደመቆም፤ ለሌሎች ተቆርቋሪ ይሆናል። በአንድ የሃሳብ ገበታ ላይ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር መስማማቷን ተከትሎ ግብፅ እያበደች የሶማሌን ጥቅም ለማስከበር ከጎኗ ነኝ እያለች እንደደነፋችው ሁሉ፤ ደንታ ቢስ ዲያስፖራዎችም ለሶማሌ ተቆርቋሪ መሆናቸውን ለማሳየት መሽቀዳደማቸው ከመቅለል መጠቅለልን ያስመኛል።

ቀላል ወይም ፍሬ ቢስ ሆኖ በሕዝብ ግምት ላይ ከመውደቅ መሞት እና በከፈን መጠቅለል ይሻላቸው ነበር። ሀገርን፣ ሕዝብንም ሆነ መንግሥትን አጠቃለው እንደጠላት መቁጠራቸው እና የጠላትን አቋም መውሰዳቸው፤ አልፈው ተርፈው የሌሎች ሀገሮችን አጀንዳ የሚያራምዱ መሆናቸው ሲታሰብ፤ ለኢትዮጵያ ከሚለፋው ሰው እኩል እነርሱም ኢትዮጵያዊ መባላቸው በቁጭት ያንገበግባል። እንደእኔ ሃሳብ ከሆነ እነዚህ ሰዎች በፍፁም ኢትዮጵያዊ መባል የለባቸውም። የሀገሩ ጠላት የሆነ ሰው የሀገሩ ባለቤት እንደሆነ ሰው መጠሪያው ሊሆን አይገባም። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የእነርሱን ንግግር የሚደግፈው ሰው ነው። በድርጊታቸው ማዘን ቢቻል ትክክል አለመሆናቸውን ነግሮ መገሰፅ ሲገባ እያጨበጨቡ መሳቅ አሳፋሪ ነው።›› ሲል የልቡን ተናገረ።

ገብረየስ ትንሽ የተሰማን ሃሳብ ለማለሳለስ የፈለገ በሚመስል መልኩ፤ ‹‹ የመንግሥትንም ሆነ የሕዝብን ስህተት መንቀስ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ይህ ሲሠራ ትክክለኛውን የሕዝብን እና የመንግሥትን ሥራ ክፍተት ከማወቅ ውጤቱንም ከመረዳት የመነጨ መሆን አለበት። በተጨማሪ የሚሰጠው አስተያየት ሀገርን ምን ያህል እንደሚጎዳ መረዳት እና ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። በስሜት መመራት እና ሁኔታዎችን ሳያገናዝቡ እና ከብዙ አቅጣጫዎች ሳይመለከቱ የነገሩን ምንነት፣ ውስጣዊ ግንኙነትን ሳያጤኑ ሃሳብ መሰንዘር፤ አልፎ ተርፎ ከሀገር ፍላጎት በላይ የሌሎች ሀገሮችን በተለይም የኢትዮጵያን ጥቅም የሚቃረኑትን ማስቀደም፤ በሀገር ላይ መጨከን ነው።

በሁሉም ነገር ላይ ቀድሞ ቸኩሎ ከመቃረን ይልቅ እርስ በእርስ መግባባትን የመሰለ ነገር የለም። መደጋገፍ እና ወንድማማችነት ይቀድማል። በደንብ ልብ መባል ያለበት በዚህ ዓለም ብዙ ነገሮች የተወሳሰቡ እና የተመሰቃቀሉ ናቸው። ችግሮች ሲያጋጥሙ ከብዙ አንፃር መመልከት እንጂ፤ በአንድ በኩል ብቻ እያዩ ዕድሎች በሙሉ የተዘጉ መሆናቸውን ማስተጋባት ከንቱነት ነው። በእርግጥም አንዳንዴ ከሀገራቸው በላይ ስለሌላ አገር ተቆርቁረው ደጋግመው መናገራቸው እጅግ ያበሳጫል። ›› ሲል ተናገረ።

ዘውዴም በበኩሉ፤ ‹‹በተደጋጋሚ አንዳንድ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ነገሮችን የሚያዩበት መንገድ ለምን በተደጋጋሚ የተሳሳተ እንደሚሆን ጥያቄ ይሆንብኛል። መኖሪያዋን ትታ መዞሪያዋን እንዳይባሉ ዘላለማዊ መኖሪያቸው መጠሪያቸው ከሆነችው ከኢትዮጵያ በላይ ኢትዮጵያ በምትሠራው ሥራ ሌሎች ተጎጂ እንደሚሆኑ ማስተጋባታቸው አስከፍቶኛል። አልፈው ተርፈው ለሀገራቸው የበለጠ ጠቃሚ የሆነውን ጉዳይ ማየት መለየት እና በጥንቃቄ ነገሮችን ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ሲኖርባቸው፤ ሁልጊዜም የሚያዩት ዋናውን ሳይሆን ተቀፅላውን ነው። በሚሠሩ ሥራዎች ላይም የሚገኘውን መልካም ውጤት ሳይሆን በሥራው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች እና ወደ ፊት ሊያጋጥም ይችላል ብለው የሚያስቡትን በስጋት መልክ ያስቀምጣሉ።

ፍፁም ወደብ ሊኖራት አይችልም ብሎ በመደምደም የተጣደፈ ሃሳብ በመሰንዘር በአጉል ችኮላ ከመናገር አልፈው፤ የኢትዮጵያ ድርጊት ቀጣናውን የሚበጠብጥ እንደሆነ የማስመሰል ዝንባሌ የሚታይባቸው መሆኑ ያሳዝናል። ‹‹በከንቱ ኩራት እየተሰቃዩ ለኢትዮጵያ የሚያስቡ መስለው ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ የሌላ ሀገር ጥቅም የሚያሳስባቸው መሆኑን ማሳየታቸው ያስከፋል።›› አለ።

በመጨረሻ ተሰማ፤ ‹‹ ኢትዮጵያ ዲያስፖራውን ‹መታጠቂያዬን አጥብቁልኝ አጠንክሩኝ› እያለች እየተማፀነች ባለችበት በዚህ ጊዜ፤ መልሚያዋን ያቅዳሉ ለዛም ይሠራሉ ተብሎ ሲታሰብ በተቃራኒው መጥፊያዋን ለማመቻቸት ለሌሎች መሣሪያ ሲሆኑ መመልከት ያሳዝናል። እኔ በበኩሌ አንዳንድ ዲያስፖራዎች እንኳን ሊያለሙን የሚፈፅሙት ድርጊት ሊያጠፋን ፍላጎት ያላቸው ይመስላል። የምታደርገውን ሁሉ የሰውን አገር ሉዓላዊነት ለመድፈር እንዳሰበች፤ የሰውን ግዛት ለመውረር እየተዘጋጀች እንደሆነ የማስመሰል አካሔዳቸው ያበሳጫል።

ኢትዮጵያ ግን ቀድሞም ቢሆን ባላት የዘመናት ታሪክ ወራሪን ድል መንሳት እንጂ፤ አንዴም በታሪኳ ሌሎች ሀገሮችን ወራ የማታውቅ የራሷን መብት ስታከብር የሌላውንም አገር መብት የምታከብር ለዓለም ምሳሌ የሆነች ድንቅ አገር ነች።›› ሲል እርሱም በበኩሉ የሚያምንበትን ተናግሮ ሃሳቡን ጠቀለለ።

ፌኔት ኤሊያስ

አዲስ ዘመን ጥር 16/2016

Recommended For You