የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እያደቀቀ ያለው ኮንትሮባንድ

የሕገ ወጥ ንግድ ወይም የኮንትሮባንድ ዜናዎች የመንግሥትም ሆኑ የግል ብዙኃን መገናኛዎች የየዕለት የዜና ማሟሻ ከሆኑ ሰነባበቱ። ወርቅ፣ ቡና፣ ሳፋየር፣ የውጭ ምንዛሬ፣ የቅባት እህል፣ ጫት፣ መጠጥ፣ እህልና ጥራጥሬ፣ የቁም እንስሳት፣ ዓሣ፣ ነዳጅ፣ ወዘተረፈ ምን አለፋችሁ ወደ ውጭ በኮንትሮባንድ የማይወጣም ሆነ የማይገባ ነገር የለም ማለት ይቻላል። የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ የውጭ ምንዛሬ፣ ብረት፣ የጦር መሣሪያ፣ የእጅ ስልኮች፣ ጨርቃጨርቅ፣ የተለያዩ ሸቀጦች፣ ትንባሆ፣ መድኃኒት፣ ወዘተረፈ በተለያየ መንገድ በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ይገባሉ።

ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ከመሠረቱ እንደ ምስጥ እየበላውና እየቦረቦረው ነው። ሕጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ እያስወጣ፤ ፋብሪካዎች በሕገ ወጥ መንገድ ከሚገቡ ምርቶች ጋር መወዳደር ስላልቻሉ እየተዘጉ ስለሆነ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እየተሰናበቱ ይገኛል። የጨርቃጨርቅና የብረት ፋብሪካዎች ለሕገ ወጥ ንግዱ ቀድመው መሰዊያው ቀርበው እየተሰዉ ነው። በውጭ ምንዛሬ እጦት፤ በጦርነትና በጸጥታ ችግር አሳሩን እየበላ ባለ ኢኮኖሚ በአናቱ ሕገ ወጥ ንግድ ተጨምሮ ክፉኛ እየደቆሰው ይገኛል። ይህ ትናንት የተጀመረ ሳይሆን ባለፉት አመታት እንደ አዲስ እየገነገነ የመጣ ሕገ ወጥነት ነው።

በየዓመቱ ከአራት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እንደሚሸሽ በተባበሩት መንግሥታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ መረጃ ያሳያል። ይህም ከሀገሪቷ የሚወጡት ምርቶች ሊያስገኙት ይችሉ ከነበረው ገቢ ጋር ተዳምሮ ሀገሪቷ የምታጣው የውጭ ምንዛሬ ቀላል እንደማይሆን ያሳያል። በተጨማሪ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የኮንትሮባንድ መስፋፋት ለትይዩ የውጭ ምንዛሬ ገበያው ማደግ አንድ ምክንያት ሲሆን የብር ዋጋ እንዲዳከም አድርጓል።

በአሁኑ ሰዓት 1 ዶላር እስከ 56 ብር( የዕለቱ የባንኮች ምንዛሪ ዋጋ) ድረስ ለመመንዘሩ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ፍላጎቶቻቸውን ከውጭ ሀገራት በሚያስገቡት ምርቶች ለሚያሟሉ ሀገራት፤ የውጭ ምንዛሬ ያለው አስፈላጊነት ከምንም በላይ ነው። በተለይም መሠረተ ልማት ግንባታ ለማካሔድና ወሳኝ የሆኑ የካፒታል ዕቃዎችን ለማስገባት እንዲሁም ዕዳዎችን ለመክፈል የውጭ ምንዛሬ አስፈላጊነቱን ከፍ ያደርገዋል።

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገሪቷ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ መጠን መጨመር የመንግሥት ዋነኛ ግብ ቢሆንም ላለፉት አሥርት ዓመታት ማሳካት ግን አልተቻለም። ለአብነት የማዕድን ዘርፉን መጥቀስ ይቻላል። ከ650 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ገቢ ያስገኘው የማዕድን ዘርፍ በ2011 በጀት ዓመት ወደ 44 ሚሊዮን ዶላር መውረዱ በማዕድን ሚኒስቴር ይፋ መደረጉ ይታወሳል። ከትግራይ ክልል በባህላዊ መንገድ ተመርቶ ይቀርብ የነበረ ወርቅ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ያስታውሷል።

ለገቢው መቀነስ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ሲሆን ችግሩ በየጊዜው እየተባባሰ ነው። በአንድ ወቅት የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ ወደ ሱማሌ ክልል ጉብኝት ባደረገ ወቅት በየቀኑ ከ1 ሺህ 600 በላይ የቁም እንስሳት በሕገወጥ መንገድ በሱማሌ ክልል በኩል ከሀገር እንደሚወጣ አስታውቆ ነበር። በተጨማሪም ዋሴ ብርሃኑ (ዶ/ር) የተባሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ባደረጉት ጥናት ኬንያ ድንበር አካባቢ ባሉ አንዳንድ ከተሞች ወደ ውጭ የሚላኩ ከብቶች 70 በመቶ የሚሆኑት በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እንደሚወጡ፤ የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ ከ2011 ዓ.ም በነበሩ አምስት ዓመታት ውስጥ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በመንግሥት መያዛቸውን አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አውስታለች።

በሕገወጥ የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረውና የኢኮኖሚኒስት መጽሔት አካል በሆነው ዘ ኢኮኖሚስት ኢንጀሊጀንስ ዩኒት የተሰኘው ተቋም በኩል ከሦስት አመት በፊት የተካሄደ ጉባዔ ላይ በረዳት ፕሮፌሰር ፈንታ ማንደፍሮ በቀረበ ጥናት፤ በኢትዮጵያ በሁሉም የንግድ መስኮች ከሚታየው እንቅስቃሴ 40 በመቶው በሕገወጥ ንግድ መስክ የሚመደብ ነው ሲሉ መግለጻቸው አይዘነጋም። በተለይም በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት መስክ፣ በመድኃኒትና በትንባሆ ምርቶች ላይ የሚታየው ሕገወጥ የሀገር ውስጥ ንግድ ከፍተኛ ደረጃ የያዘ ነው።

ከዚህም ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ የ48 በመቶ የሀገር ውስጥ ሕገወጥ ንግድ ድርሻ እንደያዘ ሲገለጽ፣ ትንባሆ የ45 በመቶ እንዲሁም የመድኃኒት ዘርፉ 30 በመቶ የሕገወጥ ንግድ የተስፋፋበት እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ አቅርበዋል። በጥናቱ መሠረት የአምስት ዓመታት ዋጋው እንደተሰላ አብራርተው፣ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2017/18 ባለው ጊዜ ውስጥ የ18 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሕገወጥ የገቢ ንግድ እንደተመዘገበ ግምታዊ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩ ገልጸዋል። መንግሥት በበኩሉ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ብቻ የዘጠኝ ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቱን፣ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2016 በነበረው ጊዜ ውስጥም ከ17 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መታጣቱ እንደሚገመት ረዳት ፕሮፌሰር ፈንታ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ለመጣው የሕገወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አስተዋጽኦ አድርገዋል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በመደበኛውና በኢመደበኛው ንግድ መስክ የተሰማሩ ነጋዴዎች ትክክለኛውን ምርት ከተጭበረበረውና ሕገወጥ ከሆነው በመቀላቀል የሚፈጽሙት ማጭበርበር አንደኛው ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት መንስዔ እንደሆነ አብራርተዋል።

ከዚህ ባሻገር በደኅንነትና በፀጥታ ሠራተኞች ብሎም፣ በጉምሩክ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች ከለላ እየተሰጣቸው በወታደራዊ አጀብ ጭምር ታግዘው የሚገቡ የሕገወጥ ምርቶችም በሀገሪቱ እየተስፋፋ ለመጣው የሕገወጥ ንግድና እንቅስቃሴ ወቀሳ ከሚቀርብባቸው መካከል እንደሚመደቡ ተጠቅሷል። ይህ ሁሉ አሁንም ድረስ መሠረታዊ ችግር ሆኖ ከሚገኘው የሙስና ተግባር ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን ከምንጊዜውም ይልቅ ተጋላጭ እያደረጋት እንደመጣ ረዳት ፕሮፌሰር ፈንታ ገልጸዋል።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንደተናሩት፣ በሕገወጥ ንግድ አማካይነት ከኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ከሚጓዙት ሸቀጦች ውስጥ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ የቁም እንስሳት፣ ወርቅ፣ ሳፋየርና ሌሎችም በገፍ እየወጡ ነው። በመሆኑም የድንበር ንግድን በሕጋዊ መንገድ ለማካሄድ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ስምምነት ማድረግ አንዱ መፍትሔ እንደሆነ፣ የንግድ ሸቀጦችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን በዲጂታል መንገድ መከታተል የሚቻልበት የኤሌክትሮኒክ ሥርዓት መዘርጋት ከጠቀሷቸው ውስጥ ይገኙበታል።

ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተግሪቲ የተሰኘው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ግልጽነት ተቋም ከሚያወጣቸው መረጃዎች እንደሚታየው፣ እ.ኤ.አ. ከ2005 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ1.2 ቢሊዮን እስከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር በሕገወጥ ንግድ ብሎም በተጭበረበረ የንግድ ሰነድ አማካይነት ወደ ውጭ ሲሸሽባት ቆይቷል። ይህ አኃዝ በአሁኑ ወቅት ከዚህም በላይ እየጨመረ እንደሚመጣ ይታመናል። የተጠቀሰው አኃዝ በየዓመቱ የኢኮኖሚዋን 2.2 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ሲገለጽ፣ የዓለም ባንክና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተለያየ ወቅት በተጭበረበሩ የንግድ ሥራዎች፣ ስምምነቶችና ሰነዶች በተለይም ገቢና ወጪን በማዛባት (ወጪን በማናርና ገቢን በማሳነስ) የሚፈጸሙ የንግድ ወንጀሎች እየተበራከቱ እንደመጡ በተለያየ ጊዜ ያወጧቸው ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

በኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች የሚካሄዱ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳውና ችግሩም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑ በዚያ ሰሞን በተካሄደ ውይይት እንደገና ተገልጿል። ከሕገወጥ ንግድና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ሀገሪቱን ኢንዱስትሪ አልባ ወደ ማድረግ እያሸጋገረ መሆኑን ጭምር የሚያመለክት ነው። በውይይት መድረኩ ተናጋሪ ከነበሩ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ስምምነት ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ ከገቢና ወጪ ንግድ ጋር የተያዘው ሕገወጥ ንግድ አሳሳቢ የሚባል መሆኑን ጠቁመዋል።

የችግሩን ግዝፈት ለማመልከት ምሳሌ ያደረጉት የቁም ከብት የወጪ ንግድን ነው። ሁለት ሚሊዮን የሚሆን የቀንድ ከብት በሕጋዊ መንገድ ኤክስፖርት ከተደረገ 20 ሚሊዮን የሚሆነው በሕገወጥ መንገድ እንደሚሄድ ጥናቶች የሚያመለክቱ መሆኑን ገልጸዋል። ከቀንድ ከብት ሌላ የጥራጥሬ ምርቶችም በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እየወጡ ሲሆን፣ በገቢ ምርቶች ረገድም አብዛኞቹ የኢንዱስትሪ ምርቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር እንደሚገቡ፣ በዚህም ሳቢያ የሀገር ውስጥ አምራቾች እየተጎዱ እንደሆ ነ አቶ ሙሴ ጠቁመዋል ።

በመሆኑም ችግሩ አሳሳቢና ፈጣን መፍትሔ የሚያሻው መሆኑን አስረድተዋል። በመድረኩ ሌላ ተናጋሪ የነበሩት የማክሮ ኢኮኖሚው ባለሙያው አቶ አሚን አብደላ በበኩላቸው ሕገወጥ ንግድ የተለያዩ መገለጫዎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሀገሪቷ በሕገወጥ መንገድ በሚደረጉ ንግዶችና በገንዘብ ዝውውር ያጣችው የሀብት መጠን ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 70 ቢሊዮን ዶላር በደረሰኝ ማጭበርበር እንደምታጣ ጥናቶች ያመላክታሉ ያሉት አቶ አሚን ይህም ከገቢና ወጪ ንግድ ሒደት ጋር ተያይዞ ዋጋን አሳንሶና ከፍ አድርጎ በማቅረብ በሚፈጸም ማጭበርበርና ገንዘብን በሕገወጥ መንገድ ከሀገር በማሸሽ (በካፒታል ፍላይት) የሚታጣ እንደሆነ አመልክተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን የሳይበር (የበይነመረብ) ግብይትን በመጠቀም መንግሥት የማያውቃቸው ንግዶች እየተካሄዱ መሆኑን የተናገሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ተደማምረው በአሁኑ ወቅት የሕገወጥ ንግዱ በሕጋዊ መንገድ ከሚካሄደው እየበለጠ መሄዱን ጠቁመዋል።

በተለይ በኮንትሮባንድ የሚገባውና የሚወጣው ብዛት ያለው ሲሆን በአንፃሩ ተያዘ የሚባለው ግን አነስተኛ መሆኑንም አስረድተዋል። የኮንትሮባንድ ንግድን የሚመለከት ጥናት ለማድረግ በተንቀሳቀሱበት ወቅት ቁጥጥሩ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር፣ ሦስት አራት ሸሚዝ ደርበው ለማለፍ በሚሞክሩት ላይ የሚበረታ መሆኑን እንዳስተዋሉ ተናግረዋል። በኮንቴነር የሚተላለፈውን ዋናውን የኮንትሮባንድ ንግድ ትኩረት እንዳላገኘና የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ሥራው ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናና ኮሜሳ ውስጥ ብትገባ የሀገር ውሰጥ ኢንዱስትሪዎች ይጎዳሉ የሚል ሥጋት እንደነበራቸው መለስ ብለው ያስታወሱት አቶ አሚን፣ አሁን ግን ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ አልባ ሊያደርጋት የሚችለው ትልቁ ሥጋት ኮንትሮባንድ እንደሆነ በመግለጽ የችግሩን አሳሳቢነት አመላክተዋል። የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ በሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጋር መወዳደር አቅቷቸው እየተዘጉ መሆኑን ያስረዱት አቶ አሚን ኮንትሮባንድ በሁሉም ዘርፍ እየተስፋፋ መሄዱ በግልጽ እየታየ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኮንትሮባንድ ከኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና ከመሳሰሉት አልፎ ወሳኝ የሚባሉ መድኃኒቶች ሳይቀር በኮንትሮባንድ እየገቡ መሆኑ ችግሩን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ እያደረገው እንደሆነ፣ ጉዳቱም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ማዳረስ እየተሸጋገረ መሆኑን አመልክተዋል። አሁን ላይ በሕጋዊ መንገድ ከሚላከው የወጪ ንግድ ምርት ይልቅ በተለይ በአንዳንድ ዘርፍ ላይ በሕገወጥ መንገድ የሚገባው እየባሰ መምጣቱ ትልቅ ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ አሚን፣ ይህም ሰዎች ሕጋዊ ሥነ ሥርዓትን ከመከተል ወደ ሕገወጥነት እያመዘኑ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ የሚያመርተው የሀገር ውስጥ አምራች በኮንትሮባንድ በሚገባውና በተሻለ ጥራትና በዝቅተኛ ዋጋ መሀል ከተማ ላይ እየተሸጠ በሚገኘው ምርት እየተንኮታኮተ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የሀገር ውስጥ አምራች ጉዳት ውስጥ እየወደቀ ከሆነ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይም እያረፈ ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም ማለት እንደሆነ፣ በዚህ ሒደት መንግሥት ከፍተኛ የሚባል የታክስ ገቢ እያጣ መሆኑን ባለሙያው በማብራሪያቸው አመልክተዋል።

የሕገወጥ መንገድ እንቅስቃሴ ሌላው መገለጫ ገንዘብ ከሀገር ማሸሽ (ካፒታል ፍላይት) እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አሚን የኢትዮጵያ ካፒታል ፍላይት ከአፍሪካ ከፍተኛው የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል። ለዚህም በባንክና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ልዩነት አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ሌላው ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት በዕቃዎች ላይ የሚጣሉ ከፍተኛ የታሪፍ ጫናዎች እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ይህ ጫና ሕገወጥና ኢሞራላዊ ነጋዴዎችን ወደ ኮንትሮባንድ ንግድ እንዲገቡ የሚገፋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ሙሴ በበኩላቸው ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት በዋነኝነት የሚጠቀሰው በድንበሮች አካባቢ ያለው የማኔጅመንት ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹እውነት ለመናገር በጣም በሙስና የተዘፈቀ የጠረፍ አካባቢ አስተዳደር ነው ያለን። ይህ ትልቅ ችግር ነው፤›› በማለት ይህንን መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሻሎም ! አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥር 16/2016

Recommended For You