የግብርና ተኪ ምርቶች ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ

በግብርና ውስጥ በመሠረተ ልማት፣ በምርምርና በቴክኖሎጂ ኢንቨስት በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን ሊተኩ የሚችሉ የሰብል ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባ ይነገራል። ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ላይ ለውጥ በማምጣት መንግሥት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ጥገኝነት ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል። በግብርና ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ በምጣኔ ሀብት ዘርፍ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ እንዳለውም ምሁራን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ተመራማሪ ቶለሳ አለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በሀገር ውስጥ ማምረት አቅምን ያሳድጋል። በሀገር ውስጥ በስፋት የመተካት ሥራ ትኩረት ከተሰጣቸው የግብርና ምርቶች ውስጥ አንዱ ስንዴ ነው። ይህ እንደ ሀገር በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ስንዴ በአብዛኛው የሚመጣው ከውጪ ሀገር ነበር። የቢራ ገብስና ሌሎች የግብርና ውጤቶችም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጪ ነው የሚገቡት። የሀገር ውስጥ አቅሙ እያለ ለሌሎች ሀገራዊ ዓላማ መዋል ያለበት ሀብትም ለእነዚህ ምርቶች ይውል ነበር ሲሉ ያስረዳሉ። ከውጪ የሚመጣውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ትልቅ አቅም መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው፤ ‹‹ራስን ለመቻል እንዲሁም ምርት ከውጪ ለማስገባት የሚወጣው የውጪ ምንዛሬ ለሌሎች ወሳኝ ሥራዎች እንዲውል ያደርጋል›› ይላሉ።

የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ በተለይ በግብርና ምርት ራስን በራስ መቻል ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ከስንዴ ውጪ ባሉት ሁሉም ዘርፎች ሊሠራበት እንደሚገባ ይመክራሉ። እንደ ሀገር በግብርና ምርት ራስን የመቻል ደረጃ ላይ ቢደረስ ለሀገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው በከፍተኛ ደረጃ ሊሰራበት እንደሚገባ ይጠቅሳሉ።

ተማራማሪው እንደሚሉት፤ ራስን ለመቻል፣ ከጥገኝነት ለመላቀቅ ችግርን በራስ አቅም መፍታት ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን በዓለም በተለያዩ ማዕዘናት የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች፤ የዓለም ገበያ የዋጋ ንረት ከፍ እያለ በሚሄድበት ወቅት አቅርቦቱ ላይ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። ራስን ከመቻል የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ ሁሉም ባለድርሻ አካል በተለይ የግብርና ተኪ ምርቶች እንዲስፋፉ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።

የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የግብርና ሜካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ኡጉታ ኡኩኝ፤ እንደ ሀገር በተለይ ከለውጡ ወዲህ ተኪ ምርቶች ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ያነሳሉ። የግብርና ተኪ ምርቶች ላይ እያንዳንዱ ክልል በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራበት መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

ከዋና ዋና ሰብሎች መካከል እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር የመሳሰሉትን በስፋት ማልማት የተለመደ አልነበረም የሚሉት አቶ ኡጉታ፤ በአሁን ወቅት ግን ሀገራዊ ዓላማን ለማሳካት በስፋት እየተተገበረ እንዳለ ያመላክታሉ። በብዛት ለማምረት ትራክተሮች ተሰማርተው የመስኖ አውታሮችና የመሬት ዝግጅት ተደርጎ የሀገርን ገጽታ ሊለውጥ በሚችል መልኩ እየተከናወን መሆኑን ይጠቁማሉ። በተለይ ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደ አቡካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝና ሌሎች የፍራፍሬ ምርቶች በስፋት መልማታቸውን ይጠቅሳሉ።

ተኪ ምርቶችን በስፋት ማምረት አርሶአደሩ ብቻ ሳይሆን ባለሀብቱ ከልማት ባንክ ብድር ወስዶ ግብርናው ላይ መዋዕለ ንዋዩን በማስፍሰስ እየሰራ መሆኑን በማንሳት፤ ተኪ ምርቶችን የሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ከመሸፈን ባሻገር ወደ ውጪ እየላኩ መሆናቸውንም ይገልጻሉ። ይህ በውጪ ምንዛሬ በኩል ይስተዋል የነበረውን ችግር ለመፍታት አንዱ መፍትሄ መሆኑንም ይናገራሉ።

እንደ አቶ ኡጉታ ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም ባለሀብቱ በስፋት የሚሳተፈው የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወደህ ግን ዋና ዋና ሰብሎችን የማምረት ዝንባሌያቸው ጎልቶ እየታየ ነው። በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተርና መሰል ነባር ዝርያ ያላቸውን ምርቶች እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ ነው። ይህ እየናረ ያለውን የገበያ ዋጋ ለማረጋጋት ትልቅ ሚና ይኖረዋል። “ሁሉም አርሶአደሮች እኩል አያመርቱም። ገበያ መር የሆኑ አርሶ አደሮች አሉ። መሬት ኖሮ ምርት በስፋት ማምረት የማይችሉም አሉ” በማለት ባለሀብቱ በዚህ ዘርፍ መሰማራቱ የምግብ ዋስትናን ይበልጥ ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ይገልጻሉ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ባንኬ ሱሜ በበኩላቸው፤ በክልሎች ትልቅ አቅም ያላቸው ወንዞች መጠቀም ቢቻል ለተኪ የሰብል ልማት ትልቅ አቅም መፍጠር እንደሚቻል በመጥቀስ፤ ይህንን ማድረግ ባለመቻሉ ለብዙ ዓመታት አንዳንድ ምርቶች ከውጪ ሲገቡ እንደነበር ያስታውሳሉ። በሀገሪቷ ሰፊ ለም መሬትና ለግብርናው ምቹ የሆነ ሥነ ምህዳር እያለ እንደሀገር ከውጪ ምርት ማስገባት ኪሳራ መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ምርትን ከማስገባት ይልቅ በብዛት መላክ የነበረባት ሀገር ናት የሚሉት አቶ ባንኬ፤ በአሁኑ ወቅት ከውጪ የሚገቡትን ምርቶች ለመተካት እንደ ሀገር በግብርና ሚኒስቴር በሚቀመጡ አቅጣጫዎች እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ያነሳሉ። ከውጪ የሚገባውን ምርት መተካት ማለት ምርት ለማስገባት የሚወጣውን ዶላር መተካት ማለት እንደሆነ በመግለጽ፤ ሙሉ አቅምን ተጠቅሞ ማምረት እንደ ሀገር ራስን በምግብ ለመቻል እንደሚያግዝ ይናገራሉ።

“ዶላር በማውጣት ከውጪ ሰብል ከማስገባት ሰብል አምርቶ ወደ ውጪ በመላክ ዶላር መግዛት ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ነው። እንደ ታዳጊ ሀገር አዋጭ መንገድ ይህ ነው” በማለት ያስረዳሉ። ባለሙያዎቹ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የዋጋ ንረቱ እየጨመረና ጦርነቶችም እየተስፋፉ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየመጡ ነው። ከውጪ የሚገቡ ነገሮች ላይ እጥረት እየተከሰተ በመሆኑ ከዚህ ሁሉ ጫና ለመውጣት በተቻለ መጠን ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ያስፈልጋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥር 15/2016

Recommended For You