ተወልዶ፤ እያደገና አድጎ በመጣባቸው ዘመናት ሁሉ አዲስ ዘመን ያለ አንዳች መታከት በትጋት እያለፈ ዛሬን ደርሷል። ዛሬ ላይም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ በሄደባቸው መንገዶች ሁሉ ያሳረፋቸውን አሻራዎች በ”አዲስ ዘመን ድሮ” ዳግም ያስታውሰናል። “ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው″ ስለተባለው የከፋዎች የጥምቀት በዓል አከባበር፤ በአንደኛው የሀገራችን ክፍል፤ የወለደቻትን ሕጻን ልጇን ከነህይወቷ ስለቀበረችው እናት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለአክሱም ሀውልት ስለሚደረገው አቀባበል ከቅርብ እሩቅ ትውስታ ተካቷል። “ከርስዎ ለርስዎ” የመፍትሔ ጠብታዎች፤ እንዲሁም “አባቴ ካወጉኝ” ከምትል ከአንዲት ወግ ቢጤ ገጠመኝ ጋር ለዛሬው ትውስታ ይሁኑ ብለናል።
በከፋ የጥምቀት በዓል በድምቀት ካልተከበረ ድኅነት ይወረሳል የሚለው ጎጂ ልማድ እየቀነሰ ነው ተባለ
በደቡብ ክልል፣ በከፋ ዞን “የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ ካልተከበረ ድህነት ይወረሳል” በሚል አጉል ልማድ በዓሉን ለማክበር ሲባል ለልብስና ለተለያዩ ጌጣጌጥ መግዣ የሚወጡ ወጪዎችን ለመቀነስ የተካሄደው እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑን የዞኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
….
እያንዳንዱ አርሶ አደር ገንዘብ ባይኖረው ለበዓሉ በሬውን እስከመሸጥ ይደርሳል ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ በአቅም ማነስ ይህን መፈጸም ያልቻሉ አባወራዎች ትዳራቸውን እስከማፍረስ የሚገደዱበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ጥር 12 ቀን 1994 ዓ.ም)
የወለደቻትን ሕጻን ቀብራለች የተባለች ተያዘች
በቤንች ማጂ፣ ቤንች ወረዳ፣ ቃሽ በተባለው ቀበሌ የወለደቻትን ህጻን ከነህይወቷ ቀብራለች ያላትን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ግለሰቧ ደግሞ ያለፍላጎቷ ተደፍራ የወለደች በመሆኗ በብስጭት መቅበሯን ገለጸች፡፡
የዞኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወታደር ናካ ባንዚኬስ ከትናንት በስቲያ እንደተናገሩት፤ የሦስት ልጆች እናት የሆነችው የሠላሳ ዓመቷ ወይዘሮ ጥር 4 ቀን 1994 ዓ.ም፣ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የወለደቻትን ህጻን ከነህይወቷ የቀበረችው በጓሮዋ ነበር፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ ባደረጉት ጥቆማ ግለሰቧ በሦስተኛው ቀን ተይዛ ስትጠየቅ በጓሮዋ እንደቀበረቻት በመናገሯ የሕጻኗ አስክሬን እንዲወጣ ተደርጎ ለምርመራ ወደ ሚዛን ተፈሪ ሆስፒታል መላኩን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ግለሰቧ ድርጊቱን ለምን እንደፈጸመች ተጠይቃ ሦስት ልጆቿን የወለደችለት ባለቤቷ ከሦስት ዓመታት በፊት በሞት ከተለያት ወዲህ በከፍተኛ ችግር ላይ መውደቋ ሳያንሳት አንድ ግለሰብ ገበያ ውላ ስትመለስ አስገድዶ በመድፈር እንዳስረገዛት ገልጻለች፡፡
ግለሰቡ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ክስ ቢመሰርትም ምንም ፍትሕ ለማግኘት ባለመቻሌ ህጻኗን በብስጭት ለመቅበር ተገድጃለሁ በማለት ተናግራለች፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ጥር 12 ቀን 1994ዐ ዓ.ም)
በደቡብ ወሎ የአክሱም ሐውልት አቀባበል ኮሚቴ ተቋቋመ
የአክሱም ሐውልት ወደ ሀገሩ ሲመለስ አቀባበሉን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በደቡብ ወሎ አስተባባሪ ኮሚቴ መቋቋሙን የዞኑ ማስታወቂያ ጽህፈት ቤት ገለጸ። የሐውልቱ መመለስ በተለያዩ ጊዜያት አላግባብ ውጪ ሀገር የሄዱትን ቅርሶቻችንን ለማስመለስ አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶች ባህልና ስፖርት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እሸቱ ተስፋዬ የኮሚቴው አባላት የሐውልቱን መመለስና በአሉን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ስለሚደረገው ዝግጅት ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ድጋፍ እንዲሰጥ ማንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
(አዲስ ዘመን፣ ጥር 13 ቀን 1997ዓ.ም)
ማይክ ታይሰን ካሜራ ሰብሮ ሊከሰስ ነው
የዓለም ከባድ ሚዛን ቦክሰኛው ማይክ ታይሰን ሰሞኑን ባለቤቱ ሮቢን ጊሸንስ ፊልም ወደምትሠራበት፣ ወደ ካናዳ ቫንኮቨር በሄደበት ወቅት ጋዜጠኞች ፊልም አንስተው ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ሲሞክሩ የካሜራውን ጫፍ ጠምዝዞ ማስተካከያውን በመስበሩ ካናዳ ቴሌቪዥን ጣቢያ ክስ ሳይመሰርትበት እንደማይቀር ተገምቷል፡፡
በዚህም ወቅት ክብደቱ ከታይሰን 31 ኪሎ ግራም ዝቅ ያለው ፊልም አንሺው ማይክ ቲሞብሬስ በታይሰን እንቅስቃሴ ተደናግጦ ካሜራውን እንደያዘ እግሬ አውጪኝ ብሏል፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ጥር 12 ቀን 1997 ዓ.ም)
ከእርስዎ ለርስዎ
*ጸጉሬ ባፈገፈገ ቁጥር የደመና ግላጭ ጸሐይን መቋቋም አቅቶኛል። ምን ይሻለኛል?
_ የአንበሳ ጎፍር ለጥፍበት እንዳልልህ ወደ ኬንያ መሻገር ሊኖርብህ ነው። የእኛዎቹ እንደሆን በአደንና በስደት አልቀዋል።
*የከተማችን ወጣቶች እንደ ኦሳማ ቢላደን ለመምሰል ጺማቸውን ማሣደግ ከጀመሩ ሰነባበቱ። እነዚህ ወጣቶች መጨረሻቸው ምን ይሆን?
ከታዛቢዎች አንዱ (ከክብረ መንግሥት)
_ ይሄስ ግድ የለም ችግሩ “ቢላዋ ይዘን ለአደን” እንውጣ ያሉ እንደሆን ነው። ለፖሊስ ሹክ በል።
*የቤቴ መክፈቻ ቁልፍ እየጠፋ አስቸግሮኛልና እባክህን መላ በለኝ።
_ በጊዜ መግባት ልመድ፤ በጨለማ የጠፋ አይገኝምና።
*”ካንተ ጋር ካልሆነ ምግብ አይበላልኝም” የምትል ጓደኛህ ለሥራ ጉዳይ ለሳምንት ወጣ ብለህ ብትለያት ምን ታደርጋለህ?
ዘነበ ሀ/ዮሐንስ (ከሸዋሮቢት)
_ ምስሌ የተቀረጸበትን ቪዲዮ ፊልም መተው፤ ወይንም በሕልሟ መመላለስ።
*ጠጥቼ ሞቅ ሲለኝ ሙዚቃ አደምጣለሁ። ወዲያው እንባዬ ይመጣል፤ ለምን ይሆን?
ጌታሁን (ከአርሲ አሣሣ)
_ ያለገደብ የጠጣኸው ሞልቶ እየፈሰሰ።
(አዲስ ዘመን፣ ጥር 12 ቀን 1994 ዓ.ም)
“አባቴ ካወጉኝ”
የአባቴ ጓደኛ ጡረተኛው አባባ ሙላት እንደወትሯቸው ልብስ ሰፊው አባቴ ጋር መጥተው ሲጨዋወቱ ውለው አንድ ሙሉ ልብስ አስቀድደው ሣምንት መጥተው ሊወስዱ ቀጠሮ አስይዘው ሄዱ። ቀጠሮ በተያዘበት ቀን ልብሱ አልቆላቸው ቢጠበቁ አባባ ሙላት ቀሩ። ቀርተውም ሳይቀሩ በቀጠሮው ማግስት መጥተው መጫወት ጀመሩ።
“አባቴ ሙላት ልብስዎ እኮ አልቋል! ውሰዱት እንጂ!” ቢሏቸው “አሁንማ ምኑን ወሰድኩት?” አሉ።
“ምነው? ምን አጋጠመህ?” ቢሏቸው
“አይ! የቆረጥኩት ሎተሪ ሳይወጣልኝ ስለቀረ ነው! መውሰድ ያልቻልኩት” ብለው በሱቁ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አስቀው በረጅም ጊዜ ክፍያ ሙሉ ልብሱን ወሰዱ።
( አዲስ ዘመን፣ ጥር 14 ቀን 1994 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 14/2016