የጃንሜዳው የአልሞሪካ ጠቢብ ጋሽ አበራ ሞላ

ከተራና ጥምቀት ለአርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ )ልዩ ትዝታዎች አሉት። በከታራና በጥምቀት በዓላት በጃንሜዳ ተገኝቶ አልሞሪካ መጫወትና ታዳሚውን ማዝናናት የሰርክ ሥራው ነበር።

አልሞሪካ ሲጫወት ልብ ይመስጣል። ምንም እንኳ አልሞሪካ ከተጫወተ ከአራት ያላነሱ አስርት ዓመታትን ቢያሳልፍም፤ ዛሬም ምቱን ጠብቆ ትንፋሹን በስሱ እና በወፍራሙ ወደ ውስጥ እያስገባ እና እያስወጣ በዝግታ ከንፈሩን እና ምላሱን እያንቀሳቀሰ ሲጫወት የሚወጣው ድምፅ በአልሞሪካ ብቻ እየተጫወተ ነው ብሎ ለማመን ይከብዳል። በሳክስፎን ተቀናብሮ የሚሰማ ለስላሳ ሙዚቃ ያህል ትዝታ ውስጥ ከቶ ያስተክዛል፤ ስሜትን ቀስቅሶ መንፈስን ያድሳል።

ጋሽ አበራ (አርቲስት ስለሺ ደምሴ) ጃንሜዳ አካባቢ ተወልዶ በማደጉ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ ጥምቀት እና አልሞሪካ በልቡ ውስጥ በደማቁ የታተመበት ኢትዮጵያዊ ነው። አብሮ አደጎቹም እንደሚናገሩለት፤ ቀድሞም ቢሆን አልሞሪካ ሲጫወት የሚፈጥረው የደስታ ስሜት ብረሩ ብረሩ ያሰኝ ነበር። ነገር ግን ጋሽ አበራ ከአርባ ዓመት በፊት ከሀገሩ ሲወጣ ከጃንሜዳ ፣ ከአልሞሪካ ጨዋታ እና ከአካባቢው ሰው ራቀ።

ጋሽ አበራ ከሀገር ከወጣ በኋላ ጃንሜዳ የአልሞሪካ አጨዋወትም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተቀነባበረ የሙዚቃ ምት ተጠንቶ የሚቀርብበት ሳይሆን፤ እንዲሁ ከንፈር ላይ አልሞሪካውን ወደ ግራ እና ወደ ቀኝ እያንቀሳቀሱ አየር በመሳብ እና በማስወጣት ብቻ ላይ በመመርኮዙ እየተበላሸ እና ለዛ እያጣ ተወዳጅነቱን እያጣ መምጣቱን ይናገራል።

ጋሽ አበራ ስለጥምቀት

‹‹ጥምቀት ለእኔ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች በጣም ትልቅ ክብረ በዓል ነው። ነገር ግን በአጋጣሚ እኔ የተወለድኩት እና ያደግኩት በጃንሜዳ አካባቢ በመሆኑ፤ እኔ እና የአካባቢው ማህበረሰብ ለበዓሉ ከፍ ያለ ቦታ አለን። ›› ይላል።

ጋሽ አበራ የከተራና የጥምቀት በዓልን በእርሱ በኩል እንዴት ያሳልፍ እንደነበር ሲናገር፤ ከጓደኞቹ ጋር እንደ ማንኛውም የበዓሉ አክባሪ ከከተራ ጀምሮ ታቦታቱን ከቤተ ክርስቲያን አውጥተው ጃንሜዳ ድረስ ይሸኛሉ። ታቦታቱ ሲያድሩ እነርሱ እዛው ያመሻሻሉ። በነጋታው የሚሸኙ ታቦቶች ሲሸኙ፤ ጋሽ አበራ ከጓደኞቹ ጋር እርሱም እየተጫወተ ታቦታቱን ይሸኛል። ሁሉም ታቦቶች አይሸኙም ሚካኤል ይቀራል። ታቦቱ እዛው አድሮ ጋሽ አበራ ከአባቱ ጋር የካ ሚካኤልን ሸኝቶ ከሰዓት ከቤተሰብ ጋር ያሳልፍ ነበር።

ጋሽ አበራ የእነርሱን መንደር ሰው ለየት የሚያደርገው ምን እንደሆነ ሲያብራራ፤ ‹‹የእኛን ለየት የሚያደርገው ምክንያት ክብረ በዓሉ በሚከናወንበት ጊዜ ከየአካባቢው ሰዎች ተሰባስበው ታቦታት ይዘው ወደ ጃንሜዳ ይመጣሉ። ከከተራ ቀን ጀምሮ ታቦታቱ እስኪደርሱ የሚጠብቀው ሰውም ሆነ ታቦታቱ ከደረሱ በኋላ በበዓሉ አክባሪዎች የተለያዩ ጨዋታዎች ይከናወናሉ። ሃይማኖታዊ ወረብ እና ሽብሻቦውም አለ። ያንን እየተመለከትን በዓሉን የምናከብረው ለሶስት ቀናት ነው። ያለምንም መዛነፍ በየዓመቱ ለሶስት ቀናት በቅርብ በሰፈር ውስጥ በብዙ ሰው በዓሉን ማክበርም ሆነ ሲከበር ማየት እጅግ አስደሳች ነው። ›› ይላል።

ጋሽ አበራ፤ ጥምቀት ለጃንሜዳ ልጅ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊ እና ለውጭ ሀገር ዜጎች ሳይቀር የሚያስደስት መሆኑን ደግሞ መካድ እንደማይቻል በማስታወስ፤ በተለይ የተለያየ ብሔር ያላቸው ሰዎች ወደ ጃንሜዳ በመምጣት በሜዳው ላይ በተለያዩ ቦታዎች ክብ ሰርተው ሲጨፍሩ አንዱ አማርኛ ፣ ሌላው ጉራጌኛ፣ ሌላኛው ኦሮምኛ ሌላ የራሱን ባህል ጠብቆ ሲጨፍር፤ ግማሹ ዱላ ይዞ ሆ እያሉ መመልከት ያዝናናው እንደነበር ያስታውሳል።

‹‹ያደግነው የጋሞ፣ የኦሮምኛ፣ የትግሬኛ፣ የወላይተኛ እና ሌላ ሌላውም የየባህሉን ሲጨፍሩ እያንን ነው። የጃንሜዳ ሳር ተረግጦ አቧራ ሆኖ እስከሚቦን ያለማንም ከልካይ ጭፈራው ይደምቃል። ›› የሚለው ጋሽ አበራ፤ ያንን ማየት ብቻ ሳይሆን ማስታወስ ራሱ እንደሚያስደስተው ይናገራል።

‹‹በዚህ ዓመትም ሆነ በቀጣይ ዓመት በሕይወት እስካለን ድረስ ወደፊትም ጥምቀት ማክበራችንን እንቀጥላለን። አንደኛዋ ልጄ ውጭ ናት። ከሁለቱ ልጆቼ እና ከባለቤቴ እንዲሁም ከቅርብ ቤተሰቦቼ ጋር በመሔድ ከህብረተሰቡ ጋር በመገናኘት በዓሉን እናከብራለን። ቤታችን ለሚካኤልም ቅርብ በመሆኑ በሚካኤል ቀንም በዓሉን ማክበራችንን እንቀጥላለን። ›› በማለት የእዚህ ዓመትም ሆነ የቀጣዮቹን ዓመታት የጥምቀት በዓል አከባበሩንም በተመለከተ ይናገራሉ።

የጥምቀት ትዝታ

አዲስ አበባ ቸሬ ሰፈር ስድስት ኪሎ አካባቢ ጃንሜዳ አቅራቢያ የተወለደው ጋሽ አበራ ሞላ (አርቲስት ስለሺ ደምሴ)፤ በውጭ ሲኖርም የጥምቀት በዓል ለእርሱ እጅግ ልዩ በመሆኑ በትዝታ ይሰቃይ ነበር። እንኳን ከሀገሩ ርቆ ለዓመታት ጥምቀትን ሳያከብር መቆየት ቀርቶ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ሲከታተል፤ ጥምቀት እስከሚደርስ የበዓሉን ቀን የሚጠብቀው በጉጉት ነበር።

ጋሽ አበራ ለአርባ ዓመታት አካባቢ ከሀገሩ ውጭ ሲኖር በዓሉ ሲከበር እንዴት እንደነበር፤ በበዓሉ ላይ የሚከናወኑት ድርጊቶች፣ የአካባቢው ሕብረተሰብ ግንኙነቱ፣ ድግሱ፣ ቤት ውስጥ ምን እንደሚደረግ፣ ከቤት ውጭ ምን እንደሚካሔድ ፣ የነበረው ማህበራዊ ግንኙነት ሁኔታው ሁሉ ትዝ እያለው ያሰላስል እንደነበር ይገልፃል።

‹‹ ሀገር ውስጥ ሆነን በዓሉ በመጣ ቁጥር ያለፉት ጊዜያት እንዴት እንደነበሩ ትዝ ይሉናል። ትናንትናም ሆነ ዛሬ በዓሉን ስናከብር ዕለቱን እየተደሰትን ያለፈውን እያስታወስን ነው። በዚህ መልኩ በዓሉን ማክበር የተለመደ ነው። ከሀገር ውጭ ሆኖ ሲታሰብ ግን የሚገርም ነው። በተመሳሳይ መልኩ ለማክበር ያዳግታል። ›› የሚለው ጋሽ አበራ፤ በርግጥ ውጭ ቢሆንም እንደ አቅም የሚከበርበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራል።

‹‹እኔ አሜሪካን ስኖር በበዓሉ ወቅት ኢትዮጵያ የነበረውን የጥምቀት አከባበር በቪዲዮ እና በፎቶ እናይ ነበር። ዘር ከልጓም ይስባል እንደሚባለው ሁሉ የትም ቢኬድ የበዓሉ ትዝታ አይለቅም። ስለዚህ በየትኛውም መንገድ በዓሉን ለማክበር ጥረት ይደርጋል። ›› በማለት የሚገልጸው ጋሽ አበራ፤ አሜሪካን በገባበት ጊዜ ብዙም ቤተክርስቲያን እንዳልነበር እና በዓሉንም ለማክበር ይቸገሩ እንደነበር ያስታውሳል።

ቀደም ሲል አሜሪካ ከመሄዱ በፊት፤ አሁን እንዳለው ዓይነት ማህበራዊ ልዩነት እንዳልተፈጠረ እና አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖረው ሰው ከሁሉም ጋር የሚኖር ብሔር ሳይለይ የተዋለደ፤ የሃይማኖት ልዩነት ሳይቀር የማይገድበው እንደነበር በማስታወስ፤ በቤተሰብ ደረጃ ቀርቶ በሰፈር እና በአካባቢም ብሔር እና ሌሎች አሁን እያለያዩን ያሉ ጉዳዮች እንደማይነሱ ያስታውሳል።

‹‹ማንም ማንንም ብሔሩን ጠይቆ አያውቅም። በሃዘንም በደስታም በማንኛውም ጊዜ በጋራ የሚኖር፤ የሚተሳሰብ፤ የአንዱ ቤተሰብ የሌላው ቤተሰብ እንደሆነ ታስቦ ብሔሩ ሳይጠየቅ የሚጎበኝበት እና አንዱ ሌላውን እንዴት ነህ? እያለ ቤቱ ድረስ ሔዶ የሚጠይቅበት መልካም ምኞቱን የሚገልፅበት ጊዜ ነበር። ›› ይላል።

ጥምቀት በአሜሪካ

እንደጋሽ አበራ ገለፃ፤ በጣም በውስን ከተሞች ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድ እና ቨርጂኒያ ላይ ኢትዮጵያውያኖች በብዛት ነበሩ። በብዛት ባሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ ጥቂት ቤተክርስቲያኖች ነበሩ። በዛ ጊዜ በአሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ እንደ አሁኑ የሰፋ ባለመሆኑ በቅርብ ርቀት በድምቀት ለማክበር ያስቸግር ነበር። ነገር ግን ልክ ኢትዮጵያ እንደሚከበረው በስፋት ብዙ ሰው ተሳትፎበት ባይከበርም፤ ኢትዮጵያውያኖች በግል ቦታ ተከራይተው ያከብሩ ነበር። ኒዮዎርክም ቤተክርስቲያን ነበር፤ እናም ኢትዮጵያውያን ለበዓሉ በተከራዩት ቦታ ላይ ወይም በየቤተክርስቲያኑ ከሩቅም ቢሆን ተሰባስበው እየተገናኙ ሲያከብሩ ቆይተዋል። ይህ ከአርባ ዓመት በፊት ነው።

አሁን በአሜሪካ ብዙ ቤተክርስቲያናት በየከተሞቹ አሉ። ከጊዜ ብዛት የኢትዮጵያውያን ቁጥር እያደገ እና እየሠፋ ቤተክርስቲያንም ብዙ በመሆኑ የአሁኑ አከባበር በጣም የተለየ ነው። አሁን እንደውም ጥምቀትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በዓላት ያከብራሉ። ከኢትዮጵያ የሚለየው ምናልባት የቀኑ እና በመጠኑም ቢሆን የሰዎች ቁጥር ማነስ ብቻ ነው።

የጋሽ አበራ ዕንባ ፈሶ አይቀርም

ፅዳት እና ውበት ላይ መሥራት ከጀመረ ሃያ አራት ዓመት አካባቢ መቆጠሩን በማስታወስ፤ እርሱ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ይህንን ሃሳብ ይዞ ሥራ ሲጀምር ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ አስር ዓመት አካባቢ ሆኖት እንደነበር ይገልፃል።

ሥራውን ከሌሎች ጋር ተባብሮ ሲጀምር፤ ከተማው በተለይ ፒያሳ እና መርካቶ በጣም ቆሽሸው የሚያሳፍር ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ያስታውሳል።

የፅዳት ሃሳቡን ሲያቀርብ ግን ብዙ ተማሪዎች እና የየአካባቢው ማህበረሰብን ድጋፍ አገኘ። ከፅዳቱ ጎን ለጎን በትምህርት ቤት አካባቢ ብቻ ሳይሆን ከትምህርት ቤት ውጪም በየጎዳና እና በየቤቱ ሰዎች አካባቢያቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ እንዲሁም የሚያገኙትን ጤና እና ሀብት በተመለከተ ለማሳወቅ ዕቅድ ቀርጾ በ27 ትምህርት ቤቶች ላይ ሥራ ጀመረ።

ከሰኞ እስከ ዓርብ የአካባቢ እንክብካቤ ላይ በማተኮር 18ሺህ ተማሪዎች ከሳይንስ እና ስፖርት እንዲሁም ከተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች ጋር በማስተሳሰር ዕውቀት እንዲጨብጡ እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሠራ። አካባቢን ጠብቆ እንዴት በፅዳት መኖር እንደሚቻል በተግባር እንዲያሳዩ ሁኔታዎችን አመቻቸ። ችግኞች እንዲተከሉ እና ዛፎች በስፋት እንዲኖሩ ከሌሎች ጋር ለዓመታት እንደደከመ ይገልፃል።

የአረንጓዴ ልማትም ሆነ ቆሻሻን በማስወገድ ከተማን የማፅዳት ሃሳብን ሲያመነጭ ብዙዎች እንደደገፉት ይናገራል። ‹‹በየቦታውም የጋሽ አበራ እምባ ፈሶ አይቀርም›› በሚል ወጣቱ በቁጭት አካባቢውን ለማጽዳት ተነሳስቶ እንደነበር ያስታውሳል።

‹‹እኛ ሀገር ያለው ትልቁ ችግር ግላዊ አመለካከት ነው። ማለት ሁሉንም የራሴ ነው ማለት ይታያል። ይህ ምንም ፋይዳ የለውም፤ እንደውም ሁሉንም ነገር ያሳጣል። ማህበረሰቡ ጋር አንድ ላይ ሆኖ መሥራት አንዱ ለሌላው ያለውን ዕውቀት እንዲያካፍል ማድረግ ይሻላል።›› የሚለው ጋሽ አበራ፤ በጋራ የመሥራት በጋራ የመገናኘት ፣ የሲቪል ማህበረሰቡን አስተባብሮ የጋራ አቅም እና ችሎታ እንዲኖር የማድረግ ሁኔታዎች የሉም ይህ ነገር መስተካከል አለበት ሲል ተናግሯል።

ብዙ ነገር የሚመጣው ከመንግሥት ነው። መንግሥት ያመጣውን መንግሥት ይመልሰዋል። ከመንግሥት ባሻገር ግን ማህበረሰቡ ራሱ የሚሠራበት ሁኔታ ቢኖር መልካም ነው የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል።

‹‹ሥራውን በጀመርንበት ሰሞን በወቅቱ በእኔ አነሳሽነት በአንድ ግለሰብ ይህንን ሁሉ ማድረግ ከተቻለ የሲቪል ማህበረሰብ ደግሞ ተሰባስቦ ራሱን ቢችል ብዙ ሊሠራ ይችላል።›› በሚል በነበረ ተነሳሽነት ከግለኝነት ወደ ማህበራዊ ተሳትፎ ቢያድግ ጉልበቱ፣ አቅሙ እና ዕውቀቱ ተጨማምሮ ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል በማመን የሲቪል ማህበረሰብን ይዞ ለመሥራት ሙከራ አድርገው እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን በወቅቱ በመንግሥት በኩል የነበሩ ሰዎች ፈሩ። ምክንያታቸው ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ሲሰባሰብ አመፅ ሊመጣ ይቻላል የሚል ስጋት በመኖሩ ሳይሳካ መቅረቱን ያስታውሳሉ።

‹‹በርግጥም ቀድሞም ቢሆን ተማሪን ይዘን ‹ሆ› ብለን መጣን እያልን ስናፀዳ እና ዛፍ ስንተክል ወጣቱ እንደ አንበጣ ጋራውን ወሮ ዛፍ ሲተክል ሁኔታው በጣም ያስፈራቸው ነበር። ካደረ ከዋለ አመፅ ያመጣል የሚል ስጋት ስላደረባቸው የዛን ጊዜ የነበሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ‹ማን ናችሁና› ብለው አስፈራሩን። ስለዚህ የሲቪል ማህበረሰብን ትተን የግለሰቦች ተሳትፎን አስቀጠልን። ›› ይላሉ።

የጃንሜዳው የአልሞሪካ ጠቢብ…

ወደ ውስጥ እና ወደ ውጭ በማስገባት እና በማስወጣት ብቻ ስለሚጫወቱ መሳጭ አይደለም። ›› የሚለው ጋሽ አበራ ዜማዎች ተቀናጅተው እና ተቀናብረው የሚፈለገውን ሙዚቃ እየተጫወቱ አይደሉም። ነገር ግን ትንሽ የሚያውቅ ሰው ቢያሰለጥናቸው አልሞሪካ ተወዳጅ የሙዚቃ መሳሪያ መሆኑን ጋሽ አበራ ይናገራል።

እነሱ ከአርባ ዓመት በፊት አልሞሪካ ሲጫወቱ ብዙ ሰው በተመስጦ ያዳምጣቸው እንደነበር በማስታወስ፤ በአልሞሪካው የኦሮምኛ፣ የወላይተኛ የተለያየ ዓይነት ሙዚቃ ሲጫወቱ ግማሹ በደስታ ተከትሎ ያጨበጭብ እና ይደሰት እንደነበር ይናገራል። አሁን ግን በተቃራኒው በአልሞሪካ መሞዘቅ እየቀረ መሆኑን ያመለክታል። ምክንያቱን ሲያብራራ ‹‹ሁሉም ነገር ሥርዓት ሲኖረው ጥሩ ነው። ወዙን እና ለዛውን ካጣ እንዲሁም ሰዎች ሲሰሙ ምንም ዓይነት ነገር ካላገኙ፤ ምቱ ተቀነባብሮ ሰው አብሮ ሊመሰጥ እና ሊጫወት የሚችል ካልሆነ እንደውም አልፎ ተርፎ ልቅ የሆኑ ማህበረሰቡን የማያስደስቱ ነገሮች ካሉ ተቀባይነቱን ይጠፋል። ይህ እንዳይሆን ሥርዓት እና መልክ አስይዞ በየሠፈሩ የሙዚቃ ማህበር በማቋቋም አልሞሪካ እንዲያንሰራራ ማድረግ ይቻላል። ›› ብሏል።

ጋሽ አበራ አያይዞም፤ ‹‹የሥነ ጽሑፍ የተውኔት መለማመጃ ቢኖር፤ ወጣቱ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። የሚያሳዝነው ወጣቱ ምንም የተዘጋጀለት ነገር የለም። ጊዜውን በከንቱ አልባሌ ነገሮች ላይ የሚያውልበት ሁኔታ ይበዛል። ቁም ነገርን የማያይበት ይበዛል። ስለዚህ አሁን ላይ አንዱ ሌላውን ይሰድባል፤ አንዱ ሌላውን ያሽሟጥጣል። ይሄ ሁሉ ሁኔታ ሆን ተብሎ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተሠራ ሥራ ነው። ስለዚህ ይሄንን እየፈረሰ ያለ ቤት ለመገንባት፤ ያለውን አቅም ማጎልበት ፣ ለወጣቶች ሰፊ ዕድል መፍጠር እና ጉልበታቸውን መጠቀም ይገባል። ይህንን ለማድረግ አሁንም መልክ አስይዞ ወደፊት መቀጠል ይቻላል።›› ሲል ሃሳቡን ገልጿል።

የጋሽ አበራ መልዕክት

ጋሽ አበራ ‹‹አሁን ያጣነው ብዙ ነገር አለ። ›› ይላል። ይህንኑ ሲያስረዳ አብሮነትን በመጥቀስ፤ ‹‹ አብሮነትን ለምን አጣን ስንል ባለፈው ተጎድተናል ተጠቅመናል እያልን ስንነታረክ ነው። ›› በማለት ምክንያት የሚለውን ያስረዳል። በዚህ ምንም ጥቅም እንዳልተገኘ በመጠቆም፤ ከጉዳት በስተቀር የመጣ ምንም ነገር የለም። ይሄ ጉዳት ደግሞ በግል ብቻ ሳይሆን በሀገር ላይም እየተንፀባረቀ መሆኑን ያብራራል።

ጋሽ አበራ መፍትሔ የሚለውን ሲጠቁም ‹‹ያየነውን ክፋት እና መጥፎ ነገር ትተን ጥሩ የምንሆነው እንዴት ነው? ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ያለፈውም ሆነ የአሁኑ በደል እና አስከፊ ነገርን የፈጠረው እከሌ ላይ ነው በመባባል ማላከክ አያዋጣም። ችግሩ ሁላችንም ላይ ነው። መከራው የሚያንኳኳው የሁሉም ቤት ነው። የችግሩም ባለቤቶች እኛው ራሳችን ነን። በራሳችን የመጣውን ችግር ራሳችን መፍታት አለብን። ግዴታውም ያለብን ተምረንም መለወጥ ያለብን እኛው ራሳችን ነን። ›› ይላል።

ችግሩ ካልተፈታ የሚመጣው አስከፊ ነገር ገደብ ሊኖረው እንደማይችል በማሳሰብ፤ ሕዝብ ይህንን አይቷል እና ተረድቶ ከእንግዲህ ለራሱ ሲል ራሱን ማስተካከል እና በኢትዮጵያዊነት ፀንቶ መኖር እንደሚገባ አርቲስት ስለሺ ይናገራል። አሁን ሁሉም ነገር ፈር ከመልቀቁ በፊት አብሮነትንና አንድነትን በማጠናከር አንድ መሆን እንደሚያስፈልግ መልዕክቱን አስተላልፏል።

አሁንም ግለሰቦች ጊዜያዊ ባለቤትነት እየተሰጣቸው አካባቢያቸውን እንዲያለሙ እና እንዲያፀዱ፤ እንዲጠብቁ እና እንዲያሳምሩ እየተደረገ እየተሠራበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁኔታውን በማስተካከል መስመር የማስያዝ እና ህብረተሰቡ በይበልጥ እንዲሳተፍ ባለቤቱም ራሱ እንዲሆን ሥራዎችን እየሠሩ መሆኑንም ይናገራል።

ሽልማቶች

ጋሽ አበራ ከሌሎች ጋር የሠራውን እና ያገኘውን ሽልማት በዝርዝር ሲያስረዳ፤ ‹‹አዲስ አበባ ላይ ፅዳቱንም ችግኝ ተከላውንም የጀመርነው እኛ ነን። ጎንደር እና ጎጃም ደረስን፤ ደቡብ ኦሮሚያ እና ሌሎችም ብዙ አካባቢዎችን አለማን። ስለዚህ ሥራችን በአፍሪካ ትልቅ ምሳሌ ሆኖ የተባበሩት መንግሥታት ሽልማትን አገኘን። በተባበሩት መንግሥታት ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ በጀመርንበት ቦታ አሸናፊ ሆነን ተሸለምን። ›› በማለት የመጀመሪያውን ሽልማት ያስታውሳል።

ቀጥሎ በእንግሊዝ ሀገር በለንደን ፓርላማ ውስጥ በዛፍ ተከላ እና በፅዳት ከአፍሪካ ኢትዮጵያ አንደኛ፣ ሁለተኛ ሩዋንዳ፣ ሶስተኛ ዑጋንዳ መሆናቸው እና ይህ ውጤት በእነርሱ የመጣ መሆኑ ተጠቅሶ የወርቅ ሽልማት ማግኘታቸውንም ያብራራል። ሌሎችም የተለያዩ ሽልማቶችን መኖራቸውን የሚናገረው ጋሽ አበራ፤ ዓለም አቀፍ የጤና ሽልማት ማግኘታቸውንም ያስታውሳል።

ዛሬ የታየው ከእንጦጦ ጀምሮ ሾላን ይዞ ዙሪያውን በዝቋላ እና የረርን ይዞ ወደ ላይ መናገሻ ድረስ ያለው ጫካ ሕዝቡን፣ ተማሪውን እና የመንግሥት ሠራተኛውን፣ የሃይማኖት መሪዎችን በሙሉ በየዓመቱ በማስተባበር በተተከለ ችግኝ የተገኘ ጫካ መሆኑንም ይገልፃል።

‹‹አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን መቀሌ አካባቢም ትልቅ ሥራ ተሠርቷል። ድሬዳዋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ሥራዎች ተሠርተዋል። የተሠሩት ሥራዎች ትልቅ ለውጥ እና ውጤት አምጥተዋል። ውጤቱ ላይ በመመስረት አሁን ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለመሥራት ተነሳስተናል። ያው የተሻለ ነገር ደግሞ ይዘን እንመጣለን ብለን እናስባለን። ›› ብለዋል።

ጋሽ አበራ በአልሞሪካ ላይ

‹‹በፊት በብዛት ሰዎች አልሞሪካ ይጫወታሉ። አሁን ግን ብዙዎቹ ሙዚቃዎቹን በደንብ አጥንተው ሳይሆን አፍን ግራና ቀኝ በማወዛወዝ እና ትንፋሽን

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You