
አዲስ አበባ:- ትውፊቱ ተጠብቆ የቆየው የጥምቀት በዓል ለሕዝቡ ሰላምና ፍቅር መጎልበት ባለው አስተዋፅዖ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ይዘቱ ሳይበረዝ ከነሙሉ ክብሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ እንደሚገባ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓል በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ትናንት ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያቀረቡት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያነት ጠብቃ የጥምቀትን ትውፊታዊ ሥርዓት ለትውልድ ስታስተላልፍ ቆይታለች፡፡ በዚህም በዓሉ ከኢትዮጵያ አልፎ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) እውቅና አግኝቶ በመመዝገብ የዓለም ሕዝብ ሀብት መሆን ችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ እለቱ በማኅበረሰቡ መሐከል ምንም አይነት የልዩነት ድንበር እንዳይታዩ የሚያደርግ የበረከት በዓል እንደመሆኑ ለሕዝቡ ሰላምና ፍቅር መጎልበት ታላቅ አስተዋፅዖ አለው።
ጥምቀት ወሰን የለሽ የፍቅር በዓል በመሆኑ እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ገልጸዋል። ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱ ሳይበረዝ ተጠብቆ ለትውልድ መተላለፍ እንዳለበትም ተናግረዋል።
በዓሉ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በሰዎች መካከል ወሰን የለሽ ፍቅር የሚታይበት በመሆኑ መንከባከብና መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። “በአደባባይ ላይ የሚከበሩ ታላላቅ በዓላትን በሚገባ ጠብቀን እና ተንከባክበን በመያዝ ጎብኝዎችን በመሳብ ታላቅ የኢኮኖሚ አቅም ልናደርጋቸው ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል።
መንግሥት እንደ ጥምቀት ያሉ የማኅበረሰብ ሀብቶች ጎልብተው እንዲዘልቁ አቅዶ እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊና የአዲስ አበባ ከንቲባ ተወካይ ሂሩት ካሣው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዓሉ በኢትዮጵያ የሚናፈቅና የሚወደድ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሰላምና የፍቅር መሠረት የሆነው አምላክ እንዲሰማ የተነገረበት ቀን ነው በማለት፣ ይኸውም የሰው ልጆች በይቅርታና በፍቅር እንዲኖሩ እርስበርሳቸው እንዲዋደዱ፣ እንዲደጋገፉና እንዲተሳሰቡ ዳግመኛም ወደ ጥፋት እንዳይሄዱ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

“በአዲስ አስተሳሰብና እይታ አሻግረን የምንመለከተውን በጎ ነገር ለማግኘት እንድንተጋ፣ እንድንተጋገዝና የበጎነትን ሥራ እንድናከናውን በተግባር ትምህርት የተገኘበት ነው” ብለዋል። ይህ ከሆነ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የቀደምት አባቶችን ትውፊት ተረክበው፣ ተንከባክበውና ጠብቀው ከነሙሉ ክብሩ ለቀጣዪ ትውልድ ማሸጋገር እንዳለባቸውም አስታውቀዋል።
ጥምቀትን በመሰሉ ሃይማኖታዊም ሆኑ ባሕላዊ ሁነቶች በሚከበሩ ጊዜ በሀገራችን ልዩ ልዩ ክፍሎች በጋራና በመከባበር የማክበር ባሕላዊ ትውፊታችን እንደተጠበቀ ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ፣ ፈጣሪ ያለፍቅር አይገኝምና ፍቅርን በማስቀደም አንዱ ለአንዱ ዘብ በመቆም የፍቅርን መልካም መዓዛ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጥምቅት በዓል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንትና ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ በርካታ ምዕመናንና የውጭ ሀገራት ዜጎች በተገኙበት በጃንሜዳ ተከብሯል።
የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት ከዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ወካይ የማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወቃል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም