ለሕክምናው አስተዋፅኦ ያደረገ ፕሮግራም

 የሰዎችን ጤና አደጋ ውስጥ ከሚከቱ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል አንዱ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ቀዶ ሕክምና አለማድረግ ነው። በዋናነት ደግሞ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ከኢንፌክሽን የጸዱ አለመሆን፣ በተደራጁ የሕክምና ግብአቶችና የቀዶ ሕክምና ባለሞያዎች አለመሟላትና የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጣቸውን የደህንነት ቼክ ሊስቶች ተከትሎ ቀዶ ሕክምና አለማድረግ ህመምተኞችን ለኢንፌክሽን ከማጋለጥ በዘለለ ለተወሳሰቡ የጤና ችግሮች ሲያጋልጣቸው ይስተዋላል። ይህ ችግር ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ገና በማደግ ላይ ባሉ ሌሎች ሀገራት በስፋት ይታያል። ይህንኑ ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ “ላይፍ ቦክስ″ የተሰኘ ምግባረ ሰናይ ድርጅት አንድ ፕሮግራም ይዞ ብቅ ብሏል።

ዶክተር አሰፋ ተስፋዬ በሙያቸው ሀኪም ሲሆኑ በሕብረተሰብ ጤና የማስተርስ ዲግሪ አላቸው። በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የክሊኒካል አስተዳደርና ጥራት ክፍል ኃላፊ ናቸው። ላይፍ ቦክስ በተሰኘው ድርጅት ውስጥ ደግሞ ‹‹ክሊን ከት›› የተሰኘው ፕሮግራም ክሊኒካል መሪ ሆነው ይሰራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ‹‹ላይፍ ቦክስ›› ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ደህንነቱ የተጠበቀ ቀዶ ሕክምና ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። ደህንነቱ የተጠበቀ ቀዶ ሕክምና እንዲኖር የዓለም ጤና ድርጅት የደህንነት ቼክ ሊስት መሳሪያ የፈጠሩ ሰዎች የመሰረቱት ድርጅትም ነው። በተለይ ‹‹ላይፍ ቦክስ›› ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ክሊን ከት›› የተባለውን ፕሮጀክት ሀሳቡን ከመጠንሰስ ጀምሮ እ.ኤ.አ በ2016 ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ ይታወቃል። በጊዜው ፕሮጀክቱ በሙከራ ደረጃ በአምስት ሆስፒታሎች ላይ ተግባራዊ ተደርጓል። ከነዚህ ሆስፒሎች ውስጥ ደግሞ ቀዳሚው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነው።

በመቀጠልም፣ ጥቁር አንበሳን ጨምሮ በምኒልክ፣ ቅዱስ ጴጥሮስና በአዲስ አበባ አጎራባች በሚገኘው ፍቼ ሆስፒታሎች ተግባራዊ ሆኗል። በተጨማሪም ፕሮግራሙ በአብዛኛው በአዲስ አበባ በሚገኙ ሌሎች ሰባት ሆስፒታሎች ውስጥ ተግባራዊ ተደርጓል። ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙት እንደነ ሕይወት ፋና፣ አደሬ፣ ወልቂጤና ሌሎች ሆስፒታሎችም የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ባጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ36 በላይ በሚሆኑ ሆስፒታሎች ውስጥ ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሆኗል። ይህ ሲባል ኢትዮጵያ የፕሮግራሙ መነሻ ሆነች እንጂ በውጪ ከሰባት ሀገራት በላይ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ከነዚህ ውስጥ ላይቤሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ቦሊቪያ፣ ማላዊ፣ ሕንድና ኮትዲቯር ይጠቀሳሉ። ፕሮግራሙን የማስፋት ስራም በአሁኑ ጊዜ በደምብ እየተሰራ ይገኛል።

‹‹ክሊን ከት›› ፕሮግራም ላይፍ ቦክስ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ዋና ምሰሶ ተደርጎ የሚወሰደው ትልቁ ፕሮጀክት ነው። ሆኖም ከዚህ ፕሮግራም ውጪ ሌሎችም በላይፍ ቦክስ የሚከናወኑ ስራዎች አሉ። የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2008 የደህንነት ቼክሊስትን ለዓለም ሲያስተዋውቅ ላይፍ ቦክስን የመሰረቱ ሰዎች የደህንነት ቼክሊስቱን በማበልፀግ ሂደት ተሳትፎ ነበራቸው። ይህን የደህንነት ቼክሊስት መሳሪያ እንዴት በሁሉም ሀገራት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ከሚል መነሻም ነው እንዲበለፅግ የተደረገው። ከዛ በኋላ ደግሞ ይህን የደህንነት ቼክሊስት በተለይ አቅማቸው ደከም ባሉ ሀገራት ውስጥ እንዴት ማድረስ ይቻላል የሚል ውይይት ነበር። ከዚህ ሂደት በኋላ ነው ክሊን ከት ፕሮግራም ኢትዮጵያን ጨምሮ በላይቤሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ቦሊቪያ፣ ማላዊ፣ ሕንድና ኮትዲቯር ተግባራዊ መሆን የተጀመረው።

ዶክተር አሰፋ እንደሚያብራሩት የላይፍ ቦክስ ትልቁ ተልእኮ ደህንነቱ የተጠበቀ ቀዶ ሕክምና እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህን ተልዕኮ ለማሳካት በርካታ ባለሞያዎች እንዲሰለጥኑ ሙከራ ተደርጓል። በዚህም ከ14ሺህ በላይ የሚሆኑ የሕክምና ሙያተኞች፣ የቀዶ ሀኪሞች፣ የሰመመን ባለሙያዎችና በቀዶ ሕክምና ክፍሎች ውስጥ የሚሰሩ ነርሶች ስልጠና ወስደዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ በሆኑ ሀገራት ከ35ሺህ በላይ የሚሆን /pulsoksym­etry/ በቀዶ ሕክምና ወቅት በታካሚው ደም ውስጥ ምን ያህል የኦክስጂን መጠን እንዳለ የሚለካ መሳሪያ በነፃ እንዲሰራጭ ተደርጓል። ይህም ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና እንዲኖር በማስቻል ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከ180 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕሙማንም የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

በዚሁ ክሊን ከት ፕሮግራም አማካኝነት የቀዶ ሕክምና ኢንፌክሽን አደጋን በ34 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡ ፡ በተለይ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ያሉ ስድስት የኢንፌክሽን ቅድመ መከላከል እርምጃዎች፤ ማለትም የእጅ ንፅህናን መጠበቅ፣ የቀዶ ሕክምና ክፍል ጨርቆች ንፅህና፣ የቀዶ ሕክምና መሳሪያዎች ፅዳት፣ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ለታካሚዎች የሚሰጡ መድሃኒቶች ደህንነትና አሰጣጥ እና ሌሎችም የህሙማንን ጤና ከማሻሻልና በኢንፌክሽን ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን የጤና እክል በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ለማየት ተችሏል።

የቀዶ ሕክምና ደህንነት ቼክሊስት እንደ ሀገር በሁሉም ጤና ተቋማት ውስጥ ከቀዶ ሕክምና በፊት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ የሚታይ እንዲሆን ተደርጓል። ጤና ሚንስቴርም የቀዶ ሕክምና ደህንነት ቼክሊስት አጠቃቀም ያለበትን ደረጃ በየወሩ ይከታተላል። ከላይፍ ቦክስ ውጪ ያሉ አጋር ድርጅቶች በሚሰሯቸው ስራዎች ደህንነቱ የተጠበቀ ቀዶ ሕክምና እንዲኖርና በማድረግና ደህንነቱ ካልተጠበቀ ቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ የሚመጡ ኢንፌክሽኖችን በመቀነስ ረገድ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ዶክተር አሰፋ እንደሚገልፁት ክሊን ከትን የመሰሉ ፕሮግራሞች ከዓለም ጋር የሚያቀራርቡ ናቸው። ለአብነትም የዓለም ጤና ድርጅት የደህንነት ቼክ ሊስት ሲበለፅግና በኢትዮጵያ በሚተዋወቅበት ጊዜ በብዙ የሕክምና ባለሙያዎች ዘንድ እንደ ተጨማሪ ስራ ተደርጎ ነበር የሚወሰደው። ይሁንና ዛሬ ይህ የደህንነት ቼክ ሊስት ከቀዶ ሕክምና በፊት በሁሉም ጤና ተቋማት ውስጥ እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ የሚታይ ነው። ይህም በተለይ ሕሙማን ለከፋ የጤና ችግርና ለአላስፈላጊ ኢንፌክሽኖች እንዳይጋለጡ ከመከላከል አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ እያበረከተም ይገኛል።

በርካታ ታካሚዎችም ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንደማያገኙ ይታወቃል። የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትም ውስን ነው። የቀዶ ሕክምና እድል ቢገኝም ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። አደጋውም የዛኑ ያህል ከፍ ያለ ነው። እንደ ሀገርም ከቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ በርካታ ችግሮች መኖራቸው ሲነገር ይሰማል። ከዚህ በተቃራኒ ባደጉት ሀገራት የቀዶ ሕክምና ደህንነት ቼክ ሊስት በአግባቡ ስራ ላይ ይውላል፤ ግዴታም ነው። በኖርዝ ካሮላይና ላይ በተሰራ ጥናት በርካታ ሆስፒታሎች በጥናቱ ተሳትፈው የቀዶ ሕክምና ደህንነት ቼክ ሊስት በአግባቡ ተግባራዊ ያደረጉ ሆስፒታሎች የቀዶ ሕክምና ቦታ ኢንፌክሽኖችንና በዚህ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸው ተረጋግጧል። ይህን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንደ ላይፍ ቦክስ አይነት ድርጅቶች ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ከቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር በርካታ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ የሕክምና ባለሙያዎች የሚወስዷቸው ስልጠናዎች አንዳንድ ጊዜ ልክ አይደሉም። የቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዴት መስራት እንዳለባቸው ቀጥተኛ የሆነ ትምህርት አይሰጣቸውም። ከዚህ አንፃር የላይፍ ቦክስ አንዱ ምሰሶ የጋራ ስራና ኮሚዩኒኬሽን ነው። ይህ ማለት በቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚሰራ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ፣ የሰመመን ባለሙያ፣ ነርሶች፣ የፅዳት ባለሙዎች እንደ ቡድን መስራት አለባቸው። እንዲህ አይነት ትምህርቶች በመደበኛው ትምህርት ላይ እምብዛም አይታዩም። ይህን ሁኔታ ለመቀየር ላይፍ ቦክስ ይዞት የመጣው የጋራ ስራና ኮሚዩኒኬሽን ስልጠና ትልቅ ውጤት አምጥቷል።

ከዚህ ውጪ ግን ከቀዶ ሕክምና መስጫ ተቋማት መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ሰፊ ችግር እንዳለ ይታወቃል። ለምሳሌ የቀዶ ሕክምና መስጫ ክፍሎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ላይሰሩ፤ ወይም የሚፈለገውን ግብአት ላያሟሉ ይችላሉ። ከዚህ አኳያ ላይፍ ቦክስ በጣም ቀላል የሚመስል ነገር ግን ደግሞ ለቀዶ ሕክምና በጣም አስፈላጊ የሆኑ የpulsoksymetry መሳሪያዎችን በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ለሆኑ ሀገራት በነፃ አሰራጭቷል። አሁን ደግሞ ባደጉት ሀገራት እንደቀላል የሚታይ፤ ነገር ግን፣ እንደ ሀገር በበርካታ ጤና ተቋማት ውስጥ የማይገኘውን capnography የተሰኘ መሳሪያ ከነስልጠናው በነፃ እየተሰጠ ይገኛል። ይህም ከቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር በመቅረፍ ረገድ ትልቅ ውጤት እያመጣ ነው።

በተጨማሪም በላይፍ ቦክስ የሚሰሩ የፕሮሰስ ዲዛይን ስራዎችም አሉ። ማለትም የቀዶ ሕክምና ፍሰቱ ምን መምሰል እንዳለበት፣ ታካሚዎች እንዴት አድርገው መግባት እንዳለባቸው፣ በየትኛው መንገድ ነው ቅድመ ሁኔታዎች ከተሰሩ በኋላ የቀዶ ሕክምና መሳሪያዎች ሊወጡ የሚችሉት የሚሉና ሌሎችም ሰፋ ያሉ የዲዛይን ስራዎችን ይሰራል። ለምሳሌ የካቲት 12 እና አለርት ሆስፒታሎችን መውሰድ ቢቻል የቀዶ ሕክምና መሳሪያዎች የሚጓጉዙባቸውን ነገሮች እንደላይፍ ቦክስ ዲዛይን ተደርገው ፖሊሲ የተደረጉባቸው አሉ።

የባዮ ሜዲካል ባለሙያዎች ምንም እንኳን ስልጠና ወስደው እንደ ሀገር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢመረቁም ተግባራዊ የሆነ እውቀትና መፍትሄ መስጠት ላይ ክፍተት እንዳለባቸው በማየት ላይፍ ቦክስ ለባዮ ሜዲካል ባለሙያዎች ጠንካራ ስልጠናዎችን ሰጥቷል። ለዚህ መነሻ የሆነውም ቀዶ ሕክምና የሚሰራባቸው እቃዎች ማፅጃ ማሽኖች ብልሽት ማጋጠም ነው። እነዚህን መሳሪያዎች ለመጠገንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት እዲሰጡ ተደርጓል።

ዶክተር አሰፋ እንደሚሉት በቀዶ ሕክምና ደህንነት ዙሪያ የሚሰራው ስራ በላይፍ ቦክስ ብቻ የሚሰራና የሚቀጥል አይደለም። በላይፍ ቦክስ በኩል የሚመጡ ሀሳቦችም የፕሮጀክት ሀሳብ ብቻ ሆነው መቅረት የለባቸውም። ፕሮጀክቶቹ እንደ ሀገር ለቀዶ ሕክምና ደረጃ ሆነው መቅረብ የሚገባቸውና ለሁሉም ጤና ተቋማት ተደራሽ መሆን ያለባቸው ናቸው። በቀጣይም በርካታ ታካሚዎችን ለመርዳትና ሕክምና ባለሙያዎችንም ለማብቃት አሁን ያለው ከአጋር ድርጀቶችና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ያለው ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

 አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You