የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ስፍራ ሰጥታ ከምታከብራቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ የጥምቀት በዓል ነው። በዓሉ መከበር የሚጀምረው ጥር 10 ነው። ጥር 10 ከተራ ሲሆን፣ ጥር 11 ደግሞ ዋናው የጥምቀት በዓል ነው። በከተራ ወደ 40 ሺህ የሚሆኑ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በጥምቀተ ባሕር ያድራሉ። ጥር 11 ቀን ደግሞ ከጥምቀተ ባሕር ወደ መንበረ ክብራቸው ይመለሳሉ።
ታቦታቱ ከማደሪያቸው ሲወጡም ሆነ ወደ ማደሪያቸው ሲመለሱ በሕዝበ ክርስቲያኑ ይታጀባሉ። በዚህ የጥምቀት በዓል ላይ በዋናነት የሚታደሙት የእምነቱ ተከታዮች ቢሆኑም ከእምነቱ ውጭ የሆኑ አንዳንድ የሌላ እምነት ተከታዮች አጋር በመሆንና በመሳተፍ ጭምር ይታደማሉ።
ጥምቀት ከተለያዩ ዓለም ሀገራት ጭምር የሚታደሙበት በዓል መሆኑም ይታወቃል። ከመንፈሳዊ ይዘቱ በተጨማሪ ሰዎች ማኅበራዊ ኩነቶችንም በማከናወን አብሮነታቸውን ያጠናክሩበታል። የጥምቀት በዓልን መነሻና ሥርዓት፤ እንዲሁም ለሰው ልጆች ሰላም፣ አብሮነትና አንድነት ያለውን አበርክቶ ከሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ መልስ እንዲሰጡን ከመልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ ፈንታሁን ጋር ቆይታ አድርገናል።
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ ፈንታሁን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ደብረ ታቦር እየሱስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው የተወለዱት። ዘመናዊ ትምህርት ተወልደው ባደጉበት አካባቢ በሚገኙ ዕድገት ፈለግ፣ ጻዲቁ ዮሐንስ፣ አሸዋ ሜዳ ትምህርት ቤቶች በመከታተል እስከ 10ኛ ክፍል ተምረዋል። በጎንደር ፖሊ ቴክኒክ የሙያ ማሰሠልጠኛ በቱሪዝም ዘርፍ በደረጃ ሦስት (በሌቭል ስሪ) ተመርቀዋል። ወደ መንፈሳዊው (የቤተ ክርስቲያን ትምህርት) በማዘንበል ዜማ፣ ቅኔ፣ ወደ ሰሜን ጎንደር በማቅናትም፤ አራቱ ጉባኤያት የሚባሉትን ትርጓሜ መጻሕፍት ጭምር ተምረዋል።
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ በመንፈሳዊ ትምህርትና አገልግሎት ከቆዩ በኋላ ነው ወደ ሥራ የገቡት። ከ2006 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ደብረ ታቦር እየሱስ ቤተ ክርስቲያንን በማስተዳደር አገልግለዋል። ከ2011 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር ጀምሮ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ኤዲቶሪያል ቦርድ አርትዖት ክፍል ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ሀገረ ስብከት በየረር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የአራት ጉባኤያት የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር ናቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣም በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከመልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ ፈንታሁን ጋር ያደረገውን ቆይታ ታነቡ ዘንድ ይጋብዛል። መልክም ንባብ።
አዲስ ዘመን ፤ የጥምቀት በዓል መነሻና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ይግለጹልን?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ የጥምቀት በዓል መሠረቱ እየሱስ ክርስቶስ ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ተነሥቶ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመውረድ ወይንም በመሄድ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ። ይህን ቀን ለማሰብም ታቦታት ጥር ዐሥር ቀን ከማደሪያቸው ወጥተው በባሕረ ጥምቀት ያድራሉ። በእየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት የሚያምኑ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን የሚያከብሩት ለመጽደቅ ነው። በዓሉ የአደባባይ በመሆኑ ከእምነቱ ውጭ ያሉት በመዝናኛነት ሊወስዱት ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፤ ጥምቀት ከተራና ማግሥት አለው። የዚህ ምሳሌ ምንድን ነው? ወይንም ምንን ያሳያል?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ ከተራ ማለት ከበበ ማለት ነው። በዓለ ጥምቀትን ለማክበር ውኃ ያስፈልጋል። የሚመረጠው ወንዝ ነው። ወንዝ ከሌለ ግን ክብ ቅርጽ ባለው ነገር ውስጥ ውኃ ይዘጋጃል። በከተራ ከማደሪያቸው የሚወጡ ታቦታት በወንዝ ወይንም በተዘጋጀ የውኃ አካባቢ ያድራሉ። ይህም ክርስቶስ ከገሊላ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ የመውረዱ ምሳሌ ነው። እያንዳንዱ ቤተ መቅደስ የሚመሰለው በገሊላ ነው።
ታቦታቱ የሚያድሩባቸው ሁሉ በዮርዳኖስ ነው የሚመሰሉት። ማኅሌቱ፣ ቅዳሴው አጠቃላይ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ስለሚከናወን ማደሪያዎቹ እንደ ቤተ ክርስቲያን ነው የሚቆጠሩት። ጥር 11 ቀን ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት በስተቀር ሁሉም ታቦታት ወደ መንበረ ክብራቸው ማደሪያቸው ይመለሳሉ። የቅዱስ ሚካኤል ታቦት የሚቀረው በዓሉ በ12 በመሆኑ ነው።
በዓሉም ቃና ዘገሊላ በመባል ይታወቃል። ጥር ወር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትልልቅ በዓላት የሚከበሩበት በመሆኑ እንደየአካባቢው የታቦታት ንግሥ ሥርዓት ይከናወናል። ለምሳሌ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ጥር 21 ቀን ይከበራል። በተለይም በጎንደር አማኙ ሎዛ ማርያም ብሎ የሚጠራት ቤተ ክርስቲያን ጥር 21 ትልቅ ክብረ በዓል በመሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱም በዚያው ልክ ከፍ ያለ ነው።
ቅዱስ ሚካኤል የራሱ የሆነ ክብረ በዓል ስላለው ለብቻው በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ሲባል ነው ከሌሎቹ ወደ ኋላ የሚቀረው። ይህም የሆነው በጥንት ሊቃውንት በመወሰኑ ነው። በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በካሌንደር ዝግ ሆኖ ይከበር ነበር። በዓፄ ገብረ መስቀል ዘመን በነበረው ሥርዓት ታቦታት፣ ጥር 11 ቀን ከመንበራቸው ወጥተው በዕለቱ ተመልሰው ይገቡ ነበር። በቅዱስ ላልይበላ ዘመን ደግሞ በከተራ ጥምቀተ ባሕር አድረው በማግሥቱ ነበር የሚመለሱት። በዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ደግሞ ታቦታት ሁሉም አካባቢ በረከት ያግኝ ወይንም እንዲባርኩ በሚል ታቦታት በሄዱበት እንዳይመለሱ የሚል ሥርዓት ተሠራ።
በተለያየ ጊዜ የተለያየ ሥርዓት ቢወጣም ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ለማከናወን አንድ ቀን በቂ እንዳልሆነ ግንዛቤ በመያዙ፣ የአማኙም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ፣ በታሪክ ሂደት ሁለት ቀን ሊሆን ችሏል። የታቦታቱ ተምሳሌት ለሚለውም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታቦት የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም ያለ ነው። ታቦትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተቀበለው ደግሞ ነብዩ ሙሴ ሲሆን ታቦት የተቀበለባት ቦታ ደብረ ሲና ትባላለች።
ነብዩ ሙሴ ታቦቱን ለመቀበል 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሟል። ታቦት ከመንበሩ ከማደሪያው ወጥቶ ጥምቀተ ባሕር የሚያድረው ለባዕለ ጥምቀት ብቻ ነው። ነገር ግን ሀገር አደጋ ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ ሊወጣ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። ለአብነትም ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያ በኃይል በወረረበት ጊዜ አባቶቻችን የአራዳ ጊዮርጊስን ታቦት ይዘው ነበር ዐድዋ የዘመቱት።
አዲስ ዘመን፤ የጥምቀት በዓልን በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ነው የሚታደመው። የዓደባባይ በዓል የተባለው ለዚህ ነው ወይንስ ሌላ ምክንያት አለው?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ መስከረም 17 ቀን የሚከበረው መስቀልና ባዕለ ጥምቀት የአደባባይ በዓላት ናቸው። ጥምቀት የአደባባይ በዓል የተባለው ታቦታት ከመንበረ ማደሪያቸው ወጥተው በባሕረ ጥምቀት በማደራቸው ነው። አደባባይ ስፋትን ያሳያል። በጥንት ጊዜ በአደባባይ ነጋሪት ይጎሰማል፣ የሀገር መሪ ዐዋጅ ያስነግራል፣ ልዩ ሀገራዊ መልእክትም ሆነ ብሔራዊ በዓላትም በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበሩት በዓደባባይ ነው። ሌላው ብዙ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሳተፍበት በመሆኑ ከአደባባይ ውጭ በአሉን ማክበር አይቻልም።
በዓሉ በዚህ ሁኔታ እንዲከበር ደግሞ ቅዱስ ያሬድ መሠረት ነው። የቅዱስ ያሬድ ዜማ ባይኖር፣ ሥርዓተ ማኅሌቱ፣ ጸናጽሉ፣ መቋሚያው እንዲሁም የአለባበስ ሥርዓቱ፣ ካባው፣ አናት ላይ የሚጠመጠመው ሻሽና ሌሎችም ለበዓሉ ደምቀት የሆኑ ነገሮች ባይኖሩ በዓሉ ደማቅ አይሆንም ነበር። በተጨማሪም የቅዱስ ያሬድን ትምህርት የተማሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የድጓ፣ የአቋቋም፣ የቅኔ፣ የዝማሬ፣ የቅዳሴ፣ የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ያደርጋሉ። ከእምነቱ ተከታይ ውጭ ያሉትን ከሚስቡት ነገሮች አንዱ የሊቃውንቱ ሽብሸባ፣ በአንድ አይነት አልባሳት የሚደምቁት የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ በእያንዳንዱ አጥቢያ የሚገኙ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መዘምራን እና መዘምራት፣ ምእመኑም ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ የሚያደረጉት እጀባ ሁሉ ለበዓሉ ድምቀት ይሰጠዋል።
አዲስ ዘመን፤ በዕለተ ጥምቀት የሃማኖት አባቶች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ከሚጠቀሙት አልባሳት በተጨማሪ ግዴታ የሆነ የአለባበስ ሥርዓት ካለ ከነምክንያቱ ቢያስረዱን?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ ሰው የሌለውን እንዲለብስ አይገደደም። ግን ደግሞ አልባሳቱ ነጭ ቢሆኑ ይመረጣል። ጥምቀት የደስታ፣ የፍቅርና የአንድነት ነው። ነጭ ደግሞ የእነዚህ መልካም ነገሮች መገለጫ ነው። ነጭ በመጽሐፍ ቅዱስ የደስታ፣ የድል ምልክት ነው። በዓለ ጥምቀት የቅድስት ሥላሴ አንድነት፣ ሦስትነት የተገለጠበት፣ የእየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ትሕትና፣ የመጥምቁ ዮሐንስ ልዕልና የተገለጸበት፣ ዮርዳኖስ የተቀደሰበት፣ የእዳ ደብዳቤ የተቀደደበት፣ መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል ወርዶ በእየሱስ ክርስቶስ ራስ ላይ ሲቀመጥ የታየበት ነው። እነዚህ ሁሉ የደስታ መገለጫዎች ናቸው።
በዓለማዊውም ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የሚል አባባል አለ። ይህም በዓለ ጥምቀቱ ንጹሕና ጸዐዳ በሆነ ሁኔታ መከበር እንዳለበት ያስገነዝባል። በዓለ ጥምቀት በአለባበስ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊውም ጭምር ጠንካራ መሆንን እንደሚገባ የሚያስገነዝብ በዓል ነው። ታቦት ከመንበረ ማደሪያው ወጥቶ ከመንፈሳዊ ነገር ውጭ ሌላ ነገር ሊታሰብ አይገባም።
አዲስ ዘመን፤ በዓሉ መንፈሳዊ ቢሆንም ማኅበራዊ ዕሴትም አለው። አንድነቱና ልዩነቱ እንዴት ይገለጻል?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ በቤተ ክርስቲያን ልዩነት የሚባል ነገር የለም። ክርስቶስ ሰው የሆነው የተጣለውን ዓለም አንድ ለማድረግ ነው። ማኅበራዊ ወይንም ማኅበር አንድነትን ነው የሚያሳየው። የኢትዮጵያ ባህል ከሃይማኖቱ የሚቃረን አይደለም። በተለይ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ባህላቸው ከቤተ ክርስቲያን የወጣ አይደለም።
በበዓለ ጥምቀት የሚዘፈነው ዘፈን ማወደስ ስለሆነ እንደ ኃጢአት አይታይም። የዘፈናቸው ግጥም ከመንፈሳዊ ጋር የተያያዘ ነው። ለምሳሌ
‹‹ ሴቶች ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ፤ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ፤ አንድ እንጀራ ሳልይዝ ስወጣ ከቤቴ… ››
የሚሉት አንዱ ሲሆን፣ በሌላኛው ወገን ደግሞ አሞራው በሰማይ ሲያይህ ዋለ፣ አሞራው በሰማይ ሲያይህ ዋለ… እነዚህ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው። መንፈሳዊ ይዘታቸውን የለቀቁ አይደሉም። በተለይ የገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል መንፈሳዊና ባህላዊ ዕሴቶችን ጠብቆ በማቆየት በኩል ይጠቀሳሉ።
ጥምቀት መተጫጫ ተድርጎም በማኅበረሰቡ የሚነገረው፤ ጥምቀት ላይ ብዙ ሕዝብ የሚታደምበት በመሆኑ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። አንድ ወንድ በበዓለ ጥምቀት ላይ አይቷት ለትዳር የፈቀዳትን ልጅ አካባቢዋን፣ ቤተሰቧን አጥንቶ ለወደ ፊት ለማመቻቸት እንጂ በዕለቱ የሚያደርገው ነገር የለም። አሁንም የገጠሩን ነው የማነሣው። ባህሉ በሚፈቅደው መሠረት ሽማግሌ ወደ ቤተሰቧ ልኮ ነው ጋብቻው ሕጋዊ የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፤ አንዳንድ ሀገሮችም የጥምቀት በዓልን ያከብራሉ። የኢትዮጵያ ግን በተለየ ሁኔታ ይታያል፤ ምክንያቱ ምንድን ነው?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 451 ዓመተ ምሕረት ድረስ የክርስትና ሃይማኖት አንድ ነው የነበረው። ሁለትም፣ ሦስትም አልነበረም። ከ451 በኋላ ነው ኦርቶዶክስና ካቶሊክ በሚል የተለየው። ከ1520 ዓመተ ምሕረት በኋላ ደግሞ ጀርመናዊው ሉተር ከካቶሊክ አፈንግጦ ወጣ። ስለዚህ ተለያየ። ስለዚህ የኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት የጥንቱን ይዘው ቀጠሉ። የጥንቱን ይዘው የቀጠሉት ጥምቀትን ያከብራሉ።
እነዚህም የግብጽ፣ የአርመን፣ የሶርያ፣ ሕንድ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን እና የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያን የሚባሉት ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ሮማኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ጆርጂያ፣ ሀገሮች በዓለ ጥምቅትን ያከብራሉ።
የኢትዮጵያ ግን ከእነዚህ ሁሉ ይለያል። ቅዱሳት በዓላት በደመቀ ሥርዓት እንዲከበሩ ያደረገው ቅዱስ ያሬድ ነው። ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ሲደርስ በዜማው አገልግሎቱን ሰፊ አደረገው። ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥባት ሀገር በዓለም ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 24 ሰዓት ነው አገልግሎት የምትሰጠው። በሌላው ዓለም እንዲህ ያለ አገልግሎት የለም። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ባለቤቱ መንፈስ ቅዱስ የገለጸለት ቅዱስ ያሬድ ነው። ቅዱስ ያሬድ ባይኖር ኖሮ አሁን ባለው መልኩ የጥምቀት በዓልን ማክበር አይቻልም ነበር። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ልዩ የሚያደርጋት ሥርዓተ ማኅሌት ስላለው ነው።
አዲስ ዘመን፤ እንደ ጥምቀት ያሉ በዓላት፣ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ያላቸው አበርክቶ እንዴት ይገለጻል?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ ማኅበራዊ ኑሮ ለመኖር መጀመሪያ ሰላም ያስፈልጋል። ሰላም ወደ ፍቅር ያመጣል። ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ደስታን መነጣጠል አይቻልም። የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አጠቃላይ ይዘቱ ሁሉ መንፈሳዊ ነው። መንፈሳዊ ከሆነ ደግሞ ከሥጋዊ ነገር የራቀ ነው። ለምሳሌ ፀብ፣ ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ምቀኝነት፣ አድመኝነት፣ ሌብነት፣ ተንኮል ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወት ቦታ የላቸውም። በዓለ ጥምቀት የማይተዋወቁትን በማስተዋወቅ፣ የተራራቁትን በማቀራረብ፣ የተጣሉ ቢኖሩ እንዲታረቁ በማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው። አብሮ መጫወት፣ መብላት መጠጣቱም ልዩነትን ያርቃል። አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም የሚባለው ለዚህ ነው። ሰው አብሮ የሚሆንበት ቀን ደግሞ በዓለ ጥምቀት ነው። ስለዚህ በዚህ ወቅት ማኅበራዊ ትስስሩ የበለጠ ይጠናከራል። በሃይማኖታዊ ሥርዓቱም ቢሆን የእግዚአብሔር ቃል ነው የሚነገረው።
የተበደለ እንዲካስ፣ የተጣላ እንዲታረቅ፣ ሀገር ሰላም እንድትሆን ነው የሚጸለየው። መንፈሳዊ ነገር ሁሌም ጤና ነው። የሰውን አእምሮ ጤናማ የሚያደርገው ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በበዓለ ጥምቀቱ ታቦታት ጥንድ ድርብ በለበሱ ቀሳውስት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በብዙ ሕዝብ ታጅበው ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ሲሄዱ፣ ሲመለሱም ያለ እንከን መሆኑ በራሱ ሰላም ነው። በዓሉን ሊያከብር የወጣ ሰው ችግር ሊፈጥር ቀርቶ የጠፋ ዕቃ ቢያገኝ እንኳን ለባለቤቱ ነው መመለስ የሚጠበቅበት።
ከዚህ ውጭ ችግር የሚፈጥሩ ቢኖሩ በዓሉ በሰላም እንዲከበር የማይፈልጉ፣ ኢትዮጵያም ሰላም እንድትሆን ፍላጎት የሌላቸው ናቸው። ማኅበራዊ ዕሴቱ ከኢትዮጵያም አልፎ ዓለምን የሚያስተሳስር ነው ማለት ይቻላል። በዓለ ጥምቀትን ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በርካታ ሰዎች ይመጣሉ። እንዲህ ዓለም በአድናቆት የሚያየውንና በበዓሉ ላይ ለመታደም በየዓመቱ ጓጉቶ የሚመጣ እያለ እኛ ለምንድን ነው እንቅፋት ለመሆን የምንሞክረው ? እንዲህ ማድረግ አግባብ አይደለም።
አዲስ ዘመን፤ በዓለ ጥምቀቱን የሰላም እና የፀጥታ ስጋት አድርጎ የማየቱ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ነው። ይህ በሃይማኖቱም ሆነ በአማኙ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖር ስለሚችል እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ለሀገር አንድነት ስጋት የሚፈጥር ነገር ነው። ከላይ ያነሣናቸውን በዓሉ ከመንፈሳዊ ይዘት ባለፈ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕሴቶች ያለውን መልካም የሆነ ፋይዳዎች የሚንድ ነው። በዓላት የደስታ፣ የፍቅርና የሰላም ምንጭ እንጂ የስጋት ምልክት መሆን የለባቸውም። አንዳንዴ ለሀገር ሰላምና ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነት ሲባል በጥንቃቄ የሚያዙ ነገሮች አሉ። ፀረ ኦርቶዶክስና ኢትዮጵያ የሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን የሚያሳዩ አንዳንድ ምልክቶች አሉ። በትክክል የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኝ ከሆነ የተቀመጠን እንቅፋት ያነሣል እንጂ እንቅፋት አይሆንም። ነገር ግን መስሎ፣ ሰርጎ በመግባት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳታገኝ፣ ወደ ልማት ፊቷን እንዳታዞር፣ የሀገሪቱም ፖለቲካ እንዳይረጋጋ ህዝቧም በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ የሚያደርጉ በውስጥም በውጭም አሉ። ፈታኞቹ ግን በሀገር ውስጥ ያሉት ናቸው።
በተለይ ደግሞ ከመንግሥት አቅምም በላይ የሆኑት ማኅበራዊ ድረ ገጾች (ሶሻል ሚዲያዎች) በአካባቢ ላይ ያልተፈጠረን እንደተፈጠረ አድርጎ በማቅረብ፣ ችግር የመፍጠራቸው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው። በተለይም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ቤተ ክርስቲያን የምታከብራቸውን ቅዱሳት በዓላት ላይ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን በዓላትን ስታከበር የሌላ እምነት ተከታዮች የሆኑ ከጎኗ ሆነው የሚተባበሩ መኖራቸው አይዘነጋም። እነዚህ ሊመሰገኑ ይገባል። ሁሉም እንዲህ ነው መሆን ያለበት። ኦርቶዶክስም ለሌላው እምነት ቀናኢ ናት።
ችግር የሚፈጥሩ አካላት ሥርዓት እንዲይዙ የሚያደርገው ሕግ ነው። ሕግ ተፈጻሚነት ሊኖረው ይገባል። ሕጉን በማስፈጸም መንግሥት ድርሻውን የሚወስድ ቢሆንም ለሰላም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘብ መቆም አለበት። በተለይ ደግሞ በዓለ ጥምቀቱ በሰላም እንዲከበር የማድረጉ ኃላፊነት የሁላችንም ነው። በመላ ሀገሪቱ ከ40 ሺህ በላይ ታቦታት ናቸው ከመንበረ ማደሪያቸው ወጥተው በባሕረ ጥምቀቱ የሚያድሩት። ለዚህ የፀጥታ ኃይል በመመደብ ብቻ ስጋቶችን ማስቀረት አይቻልም። መገንዘብ የሚገባን ነገር ሰላምን በማወክና በማደፍረስ የሚያስጨንቁት ጥቂቶች ናቸው። አንድነቱና መተባበሩ ካለ እነዚህን ጥቂቶች መከላከልና መቋቋም ይቻላል።
አዲስ ዘመን፤ ጥምቀት የሰላም በዓል ነውና ሰለሀገራችን ሰላም ጥቂት ቢሉን ?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ በጣም በርካሽ ዋጋ ሲበዛም ደግሞ በነፃ የምናገኘው ውኃ ነው። ሰላም ንጹሕ ውኃ ነው። እንቅልፍ ነው። ሰላም ቅዱስ ተግባር ነው። ሰላም የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ጸሎት ነው። ትምህርትም ይሰጣል። አዎ አሁን ላይ ሀገራችን ችግር አለ። ግን ችግሩ እንዴት ይፈታ ነው ዋናው ነገር መሆን ያለበት። በሀገራችን ብሂል ዕርቅ ደም ያደርቅ ይባላል። ተቀራርቦ መነጋገር ነው የሚያስፈልገው። ለዚህም ሦስት ነገሮች አሉ። እንደ ሃይማኖት ሰማያዊ፣ እንደ ዜግነት ኢትዮጵያዊ፣ እንደ ሰው ዓለም ዐቀፋዊ ናቸው። የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በእነዚህ ነው።
እዚህ ላይ የምሁራን ዕውቀት መፍትሔ ማምጣት መቻል አለበት። ለዚህ ሁሉ ቅንነትና እውነት ያስፈልጋሉ። እግዚአብሔር ልቦናቸው ቅን ለሆነ ለእስራኤል እጅግ ቸር ነው ይላል። ጠማማ ልብ ከ እግዚአብሔር ያርቃል። ሰው ከ እግዚአብሔር ጋር ነው መኖር ያለበት። ሰው ሰውን መውደድ ነው ያለበት። በሰዎች መካከል የሐሳብ ልዩነት አለ። አንድ እንዲሆንም አይጠበቅም። የሐሳብ ልዩነት ዕውቀትን የሚያፈልቅ እንጂ የሚያለያይ መሆን የለበትም። በሀገራችን የተፈጠረው አለመረጋጋት፣ ጦርነት፣ ድርቅ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም የሚስተዋለው ፈተና እጅግ ያሳስባል። ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ደግሞ ዋናው ተግዳሮት ዘረኝነት ነው። ሆኖም ግን ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ማበጀት ይቻላል። ዋናው መሆን ያለበት ያለመሰልቸት መወያየት፣ መነጋገር ነው።
የችግሩን መንስኤ ከሥር መሠረቱ አውጥቶ መመርመር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያውያንን እያጣላ ያለው የቋንቋ ችግር ነው ? የቋንቋ ቅዱስም፣ እርኩስም የለውም። ቋንቋ አያጣላም። ጎሣም ቢሆን አያጣላም። ምክንያቱም ሰው ዘሩን ወይንም ጎሳውን መርጦ ስለማይወለድ። አንዱ የሌላውን ቋንቋ መናገር ቢችል ይመረጣል እንጂ አያጠላም። የሚገባው ለግጭት መንስኤ የሆነውን መለየት ነው። ብዙ ሀገሮች ችግሮቻቸውን የፈቱት በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ነው።
አዲስ ዘመን፤ የሐሳብ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ፣ ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግም መንግሥት ጥረት እያደረገ ይገኛል። የመንግሥትን ጥረት በማገዝ በኩል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምን ይጠበቃል?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ መንግሥት ብቻውን መፍትሔ ሊያመጣ ስለማይችል ምክክሩ አሳታፊ መሆን አለበት። ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ሁሉ መሳተፍ ይኖርባቸዋል። የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ጸሎቷ ስለሰላም፣ ስለሀገር ነው። ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም ጭምር ነው የምትጸልየው።
አዲስ ዘመን፤ ጥምቀት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ የባህልና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል። መመዝገቡ ያለውን ጠቀሜታ እንዴት ይገልጡታል ?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ ዩኔስኮ ትልቅ ተቋም ነው። በዚህ ድርጅት ጥምቀት መመዝገቡ ፋይዳው ብዙ ነው። አንድን ነገር ዓለም ሲያውቀው ከፍ እያለ ነው የሚሄደው። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ስሟ ሲነሣ ለሁላችንም ትልቅ ክብር ነው። በዚህ የጥምቀት ወቅት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ይመጣል። ቱሪስት በመምጣቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በማጓጓዝ፣ ባለሆቴሎች በሚሰጡት አገልግሎት አትራፊ ይሆናሉ። አነስተኛ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ሳይቀሩ ይጠቀማሉ።
ዕውቅናው ጸንቶ እንዲቆይና ዘላቂ እንዲሆን በዓለ ጥምቀት ሥርዓቱ ተጠብቆ እንዲከበር ሁላችንም ድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል። ከውጭ ሀገራት የሚመጡ የመገናኛ ብዙኃን መልካሙን ገጽታውን ትተው በበዓለ ጥምቀት ሰው ተደበደበ፣ ሞተ በሚሉት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የኢትዮጵያን ስም እንዳያጠፉ ማድረግ የምንችለው እኛ ነን።
አዲስ ዘመን፤ እስከ አሁን ከተነጋገርነው ውጭ ያልተነሣ ነገር ካለ፣ እንዲሁም ተጨማሪ መልእክትም ካለዎት?
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ በቅድሚያ ለሁሉም የእምነቱ ተከታዮች እንኳን ለበዓለ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ። በዓሉ በሰላምና በደስታ እንዲከበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ውጭ የሆኑ ወገኖችም እንደ እስከ አሁኑ ተባባሪ እንዲሆኑ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፤ መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ ፈንታሁን ለቃለ መጠይቅ ስለተባበሩን እናመሰግናለን።
መልአከ ታቦር ኃይለ እየሱስ፤ እኔም በዓለ ጥምቀትን በተመለከተ ሐሳብ እንድሰጥ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግስቱ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም