ተራ ”ከተረ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም ”ውሃ መክበብ” ወይም ”መገደብ”ማለት ነው። የከተራ በዓል ከጥምቀት በዓል አንድ ቀን ቀድሞ ነው የሚከበረው። የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ-ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውሃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው የእምነቱ ተከታይ በአንድ ላይ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፤ የወንዝ ወይም የምንጭ ውሃም ይገደባል፤ ይከተራል። ይህ በጥምቀት ዋዜማ የሚደረገው ውሃውን የመከተርና የመገደብ ስርዓትም ”ከተራ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
የታሪኩ መነሻ መዝሙር 113 ቁጥር አምስት ላይ በመጽሃፍ ቅዱስ የተጻፈው ነው፡፡ ”እየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መሃል ላይ ሲቆም ባሕር ባሕር አይታ ሸሸች የሚለውን ቃል መነሻ በማድረግ ነው ይህ ክንውን የሚፈጸመው። በዚህ መነሻነት ታቦታቱ ከየማደሪያቸው ወጥተው በውሃ ዳር በተዘጋጀ ቦታ ማክበር ከጀመሩ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውንም በከተራ ዙሪያ የተጻፉ ታሪኮች ያስረዳሉ።
የተጠራቀመው ውሃ በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ሲከበር የሕዝቡ መጠመቂያ ይሆናል። ከተራ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛ (ማይ ሹም)፣ በጎንደር የአፄ ፋሲል መዋኛ፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛ፣ በሸዋ የአፄ ዘርዓያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳ (ጃንሜዳ) በደማቅ ስነ-ስርዓት ይከበራል።
ከጥምቀት ዋዜማ ማለትም በየዓመቱ ጥር ፲(10) ቀን ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲኾን ምዕመናን ውኃውን በመከተር (በመገደብ) ስለሚውሉ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር ፲፩(11) ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ነው፡፡ ይህ ውኃ የሚከተርበት ሥፍራም “ባሕረ ጥምቀት” ወይንም “የታቦት ማደሪያ” ተብሎ ይጠራል፡፡
ሌላው የከተራ ዕለት ካህናቱ ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ላይ አክብረው ወደ ባሕረ ጥምቀት መሄዳቸው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መሄዱን ለመዘከር ነው፡፡ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ባሕረ ጥምቀት ለመሄድ ሲወጣ “ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት፡፡” የሚለው የሚዘመረውም ይኽንን እውነት ለመግለጽ ነው፡፡
በገጠሪቱ ኢትዮጵያም እንዲሁ ጥምቀት እጅግ በሚያስደስት መልኩ ነው የሚከበረው። በገጠር በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጥምቀት የሚከበረው የከተራ ዕለት ታቦቱ ከቤተ ክርስቲያን ወጥቶ ዳገትና ቁልቁለት በበዛበት መንገድ ወደ ወንዝ ያመራል። ወንዝ ከደረሰ በኋላም ቀድሞ በወጣቶች እና በአገር ሽማግሌዎች በተተከለው የታቦቱ ማረፊያ ድንኳን ውስጥ እንደሚገባ እና ሌሊቱንም ካህናት እና ዲያቆናት ልዩ ልዩ ያሬዳዊ ዜማዎችን ሲያዜሙ ያድራሉ።
የአካባቢው ምዕመናን ድግስ ደግሰው ዝክር የሚያደርጉ ሲሆን፣ ማህሌት፣ ኪዳን እና ቅዳሴም በሌሊቱ መርሀ ግብር ይከወናሉ። በነጋ ጊዜም ከአራቱ ወንጌላውያን ስለ ክርስቶስ መጠመቅ ምንባብ ተነቦ ካለቀ በኋላ፣ ጥምቀተ ባህሩ ተባርኮ ካህናቱ ማጥመቅ ይጀምራሉ።
በተጨማሪም በጉዞ ላይ “እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ እየሱስ፣ መጽአ ቃል እምደመና ዘይብል” የሚሉትና ሌሎች መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም በጎንደር በባቱና በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከተራና ጥምቀት በዓላት በዓደባባይ በድምቀት ይከበራሉ። በርካታ ቱሪስቶችም ዕለቶቹን ምክንያት አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ።
በእለቱ ሁሉም ያለውን ፃእዳውን ለብሶ ወደ መጠመቂያው ቦታ ይሄዳል። ያኔ መንፈሳዊ ስርዓቱ ተፈፅሞ ፀበልን ለመጠመቅ የሚደረገው መራኮት በራሱ ትልቅ ስሜትን የሚፈጥር ነው። ሰው የፀበሉ ቅንጣት ፊቱ ላይ ሲያርፍ የሚሰማው ደስታ እልልታው ጭብጨባው ረክቶ ወደየ ዝማሬው ይቀላቀላል።
̋ እኔስ የታቦት ስራ አለብኝ፤ እኛም እንዳንተው ስራ አለብን….̋ ተብሎ የተጀመረው ወጣቶች ቀድመው አካባቢን በማፅዳት በማሸብረቅ የጀመረውን ስራ ታቦታተ ሕጉ ከመንበራቸው ወጥተው ማደሪያቸው እስኪደርሱ ምንጣፍ በማንጠፍ፤ በመጥረግ፤ አካባቢውን ፀጥታ በማስከበር፤ በዝማሬ አድምቀው የሸኙትን መልሰው ለመቀበል ከፀበሉ ሰዓት ጀምሮ ዳግም ምንጣፎቹን በመሸከም ላባቸወን ሲያንጠፈጥፉ የሚውሉበት በዓል ነው በአለ ጥምቀት።
ከእናቶች ደርበብ ያለ የዝማሬ ድምፅ የሕፃናት የመለእክትን ዝማሬ የመሰሉ የመዝሙር ድምፆች፤ የወጣቶች ሽብሸቦና ጭብጨባ ይህ ሁሉ የጥምቀቱ ድምቀት ነው። በከተራና በጥምቀት ወጣቶች ያሸበርቃሉ። የበዓሉ ድምቀት ይሆናሉ፡፡ ይህ ወቅት አየሩ ተስማሚ፤ አካባቢው ሁሉ ማራኪ ስለሚሆን የሚታየው ሁሉ ይወደዳል፤ የፍቅር ስሜት ያጭራል። የወጣቶችም አይንና ልብም ለፍቅር ይዘጋጃል፤ መፋቀር፤ መከጃጀል፤ መተጫጨት ብሎም መጋባት ከከተራ እስከ ጥምቀት ብሎም እስከ ቃና ዘገሊላ እና አስተሪዮ ማርያም ድረስ ባሉ በዓላት የተለመደ የጥር ወር ልዩ መገለጫ ነው፡፡
ከከተራ እስከ ጥምቀት ባሉት ቀናት ሴቶች አሸብርቀው አደባባይ ይገኛሉ፡፡ ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ እንደሚባለው የክት ልብሳቸውን ለብሰው ጌጣጌጦችን ጨምረው አምረውና ደምቀው ከአደባባይ ይሰየማሉ። በዚህ ወቅት እንኳን ያላገባ ብላቴና ይቅርና በእድሜ ለገፉት ጎልማሳና ሽማግሌ ጭምር የኮረዳዎቹ ውበት ልብ የሚያርድ ነው። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ሎሚ መወራወርና መተጫጨት የቆየ ባህል ነው፡፡
በከተማ|ም ጓደኛሞች ተቀጣጥረው የሚገናኙበት፤ አንድ አይነት ልብሳቸውን ለማሳየት የሚወጡበት፤ ፍቅረኛሞች ያለማንም ከልካይ አብረው የሚውሉበት ቀንም ነው ከተራና ጥምቀት። ወጣቶች በተለያየ መልክ የሚያከብሩትን በአለ ከተራና ጥምቀት ከዝማሬው ጀምሮ እስከ ሀርሞኒካው ጭፈራ፤ ከሀርሞኒካው ዳንሰ የባህላዊ ዘፈኖች ድምር ሁሉም ውብ ድምቀቶች ናቸው።
በትንፋሽ የሚነፋው ሀርሞኒካ በአብዛኛው አፍላ ወጣቶች የሚሳተፉበት የጭፈራ አይነት ነው። ሀርሞኒካውን ከሚነፋው ልጅ ሌላ በፉጨትና በጭብጨባ በሚያጅቡት ወጣቶች ይበልጥ ይደምቃል። ደናሾቹ ወንዶችና ሴት ወጣቶቸ ሲሆኑ የራሱ አጨፋፈር ስልት ባለውና የሀርሞኒካውን ድምፅ ተከትሎ በሚደረገው ውዝዋዜ በርካታ ወጣቶች ደስታቸውን የሚገልፁበት የመዝናናት የመደሰት ቀናት ናቸው በአለ ከተራና ጥምቀት ለወጣቱ።
ወንዶች እና ሴቶችን በነጠላ ተሸፍነው ከዚያም ውስጥ ሆነው ይጨፍራሉ። ሌላ የተለየ ነገር ምን እንደሚያደርጉም አይታወቅም። የደከሙት ሲወጡ የሚተኩ ሌሎች ሴቶችም ወንዶችም ወጣቶች ይኖራሉ። ሀርሞኒካ ማለት እንኳን ለዘንድሮው በዓል በሰላም አደረሰን የሚለውን ለመግለጽ ወጣቶች ያደርጉት የነበረ ጭፈራ አይነት መሆኑንም ብዙሀኑ ይስማሙበታል።
በአብዛኛው በአለ ጥምቀት ሀይማኖታዊ ስርአትን የተከተለ በመሆኑ ቀሳውስቱም ይሁኑ ሌሎች የሀይማኖቱ አስተማሪዎች በሚያደርጉት ጫና በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘት ብቻ እንዲኖረው እየተደረገ በመሆኑ የሀርሞኒካ ዝነኝነት አሁን ላይ ተቀዛቅዟል።
በገጠር ጥምቀቱ ተጠምቆ ታቦቱ ወጥቶ ድንኳን እስከሚነቀል ድረስ ባለው ቦታ እዛው በታቦት ማደሪያ አካባቢ ወጣቶች የገና ጨዋታ ይጫወታሉ፣ አዳዲስ ልብስ የለበሱ ልጃገረዶች ዘፈንና ጭፈራ ያካሂዳሉ። በዚህም ከሚጨፍሩ ልጃገረዶች መካከል አንዱ ጉብል ዐይቶ የወደዳትን ሎሚ ይወረውርባታል፤ አልያም አብራው እንድትጨፍር ይጋብዛታል። በገጠር በዚህ መንገድ ተዋውቀው ትዳር የመሠረቱ ብዙ ወጣቶች አሉ።
በድሮው ዘመን አንድ ወንድ አንዲት የሚወዳትን ሴት እንደሚፈልጋት ለማሳወቅ ጥምቀት እስከሚመጣ ዓመት ሙሉ ይጠብቅ እንደነበር ይነገራል። ከቤት ስለማትወጣ ሌላ ቦታ የማያገኛት ከመሆኑም ሌላ፣ ቢያገኛት እንኳን እንደሚፈልጋት መናገር አይችልም ነበር። በዚህም እንደ ጥምቀት ያሉ የአደባባይ በዓላትን መጠበቅ ይኖርበታል።
ወጣቱ መንፈሳዊ ግልጋሎቱ፤ በባህላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ዝማሬ መሳተፉ፤ የአገልግሎት ስራ ላይ መሳተፉ ልቡ የከጀላትን በበአሉ ላይ ማግኘቱ የገጠሩም የከተማውም አከባበር አንድ አይነት መሆኑን ልብ ይለዋል። ደራሲ መላኩ አላምረው ‹ነፍጠኛ ስንኞች› በተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፉ (ገጽ 54) በጥምቀት በዓል ወቅት ድሮ የነበረውን እና አሁን የሚስተዋለውን በማነጻጸር በሚከተሉት ስንኞች ቋጥሮ አስቀምጦታል፤
ባህልን አክብሮ፣ ከእንስት ርቆ፣
በዓመት አንድ ጊዜ ጥምቀትን ጠብቆ፣
ከኮረዳ መሀል ከውብም ውብ መርጦ፣
ልቡ እንደወደዳት በውል አረጋግጦ፣
ሎሚ በመወርወር የሴት ደረት መትቶ፣
ውቢቷ ኮረዳም ደረቷ ሲመታ፣ ልቧ ተደስቶ፣
‘ሚኖርበት ዘመን፣
ሰው ከሰው ተጫጭቶ፣
ሰው ከሰው ተጋብቶ፣
ድሮ ቀረ ድሮ…
ሰው ከውጭ ተምሮ ባህል ተቀይሮ፣
ሎሚም ዋጋው ንሮ አልሆነም ዘንድሮ …!
ያሁኑ ጎረምሳ፣
ኮረዳ ለመቅረብ፣ ጥምቀት አይጠብቀም፣
ያው ዓመቱን ሙሉ ከሴት ጥግ አይርቅም።
የኮረዳም ደረት፣
ለጥምቀቱ ሎሚ አሻፈረኝ አለ፣
ቀድሞ ተገላልጦ አደባባይ ዋለ። በማለት ወደ ባህላችንና ወደ ቀልባችን እንድንመለስ ሸንቆጥ የሚያደርግ ስንኝ ቋጥሯል፡፡ በአለ ጥምቀት በዓለም የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) የተመዘገበ የማይዳሰስ ቅርስ በመሆኑም በየዓመቱ በርካታ የውጪ አገር ቱሪስቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚስብ ነው።
በማህበራዊ ዘርፍም እንደሚስተዋለው ወጣቶች በጋራ ሆነው ከከተራ በፊት ጀምሮ አደባባዮችን ሲያስጌጡ እና መንግዶችን ሲያስውቡ ይታያል። የበዓሉ ዕለትም በርካቶች ተሰባስበው በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ አንድነት እና ፍቅርን የሚያጠናክር ታላቅ በዓል መሆኑ ይታያል። የእየሱስ ክርስቶስን መጠመቅ መሠረት በማድረግ የጥምቀት በዓልን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ፣ ኤርትራ፣ ሩስያ፣ ጆርዳን እና ዩክሬንም በዓሉን በድምቀት ከሚያከብሩ አገራት ውስጥ ይገኙበታል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥር 10/2016