የጥምቀትን በዓል ከማክበር ጎን ለጎን ለሰላም ዘብ እንቁም

የጥምቀት በዓል በወርኃ ጥር በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በልዩ ልዩ ይከበራል፡፡ በዓሉ የሚከበርበት ዋና ዓላማም ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በሰው እጅ የተጠመቀበትና ለሰው ልጆች ሁሉ ትህትና እና ፍቅርን ያስተማረበትን ቀን ለማሰብ ነው፡፡ በዓሉን መላ የእምነቱ ተከታዮች በየአብያተ ክርስቲያናት በሚካሄድ በተለያዩ ሥነሥርዓቶች በድምቀት ያከብሩታል፡፡

በዓሉ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በአደባባይ በድምቀት ይከበራል፡፡ በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው ይህ በዓል በዋዜማው የከተራ በዓልን በማክበር ይጀምራል፡፡ በከተራ ዕለት ታቦታት ከየአድባራቱ ወጥተው በቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና በምእመኑ በደማቅ ሥነሥርዓት ታጀበው በውሃ አካላት ዳርቻ በሚዘጋጁላቸው ቦታዎች ያመራሉ፤ በዚያው ያድራሉ፡፡ ታቦታቱ በሚገኙበት የወንዝ ዳርቻዎች የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቶች ይከወናል፡፡

በማግስቱ ጠዋት የጥምቀት በዓል ሥነሥርዓት ይከበራል፡፡ የእምነቱ ተከታዮች ከጥምቀት ሥነሥርዓቱ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ባህላዊ ቀኑን ሲያደምቁት ውለው ታቦታቱ ወደየመጡበት ደብር ይመለሳሉ፡፡ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት ሲከበር የኖረው ይህ በዓል፤ ከሃይማኖታዊው ሥርዓቱ ባሻገር ምእመኑ ማህበራዊ እሴቶቹና መስተጋብሩ የሚያጠናክርበት ነው፡፡ ይህም የጥምቀት በዓል በሁሉም ማህበረሰብ ተጠባቂና ተናፋቂ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ጥምቀት ከሌሎች የአደባባይ በዓላት የተለየ ድባብ ያለው ሲሆን፣ ለእዚህም ልዩ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ከአለባበስ ጀምሮ እስከ ውበት አጠባበቅ ድረስ ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ ድምቅ ፍክት ብሎ የሚታይበት ነው፡፡ ይህም ‹‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› የሚለውን የአበው አባባል እውነትነት ፍንትው አድርጎ ያመለክታል፡፡

ከከተራ ዕለት ጀምሮ በዓሉን ለማክበር አምረው እና ተውበው ከየቤቱ የሚወጡ እናቶች ፣አባቶች፣ወጣቶች እና የበዓሉ ውበትና ድምቀት ይሆናሉ፡፡ ለጥምቀት የክት ልብስ ይለበሳል፤ አዳዲስ ልቦሶች ይገዛሉ፤ ይህን ማድረግ ያልቻለም ያለውን አጥቦና ተኩሶ ይለብሳል፡፡ የዘመኑ ወጣቶች ደግሞ አለባበሱን ከቀደመውም በላይ እያደረጉት መጥተዋል። ጓደኛሞች፣ እህትማማቾች ወንድማማቾች ወዘተ አንድ አይነት የባህል ልብስ በመልበስ ወደ አደባባይ ይወጣሉ፡፡

ጥምቀት ሲነሳ መቼም የማይዘነጋው ጎበዛዝቱ ለቆነጃጅቶች የሚወረውሩት ሎሚ ነው፡፡ የሎሚ ውርወራ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባሕላዊ የመተጫጨት ዘዴ ተደርጎ ይወሰዳል። በተለይ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍሎች በወጣቶች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ ወጣቶች የሚተያዩበትና የሚተጫጩበት በመሆኑ አንድ ጎረምሳ ለወደፊት የትዳር አጋር እንድትሆን ለፈለጋት ኮረዳ ሎሚ በመወርወር የእርሱ እንድትሆን የሚጠይቅበትም ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ተያይተው ተጫጭተው ለትዳር የበቁ ብዙዎቹ ምስክሮችም አሉ፡፡

በዓሉ ለወጣቱ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች በርካታ ትዝታዎችን ጥሎ የሚያልፍ ነው፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ በልዩ ሁኔታ የሚታደሙበት በዓል እንደመሆኑ በዓመቱ ‹አምና ይሄኔ› እየተባለ በትዝታ ጭምር እስከ መታወስም ይደርሳል፡፡ በተለይ በመዲናችን በአዲስ አበባ በጃንሜዳ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ልዩ ትዝታን የሚያጭር እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ። በጃንሜዳ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር የሀርሞኒካ ጨዋታ፣ የተለያዩ ባሕላዊ ጭፈራዎች እና መሰል ሁነቶች ይከወናሉ፡፡

አሁን አሁን የጥምቀት በዓል ቀደም ባሉት ጊዜያት ይከበር ከነበረው የአከባበር “ስታይል” ለየት ባለሁኔታ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ሀገሪቱ ያላት ቱባ ባሕል የሚታይበትም ጭምር እየሆነ ነው፡፡ የበዓሉ ታዳሚዎች በተለያዩ የባሕላዊ አልባሳት ደምቀው በጓደኛነት፣ በቡድን፣ በቤተሰባዊነት፣ በማህበር፣ በአንድነት አንድ አይነት ልብስ በመልበስ ለየት ብለው የሚታዩበት ፤ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚገልጹበት ነው፡፡

የጥቀምት በዓል ፊቱንም ቱሪስቶችን በመሳብም በእጅጉ ይታወቃል፡፡ እንደ ጎንደር ባሉ ቦታዎች በዓሉ በልዩ ሁኔታ በሚከበርባቸው አካባቢዎች በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ አካባቢዎቹ ይተማሉ፡፡ የጥምቀት በዓል የዓለማችን የማይዳሰስ ቅርስ (Intangible world heritage) ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ታኅሣሥ 1 ቀን 2012 ዓ.ም መመዝገቡ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎም የቱሪስቶችን ቀልብ በእጅጉ በመሳብ የሚታወቀው ይህ የጥምቀት በዓል የቱሪስት መስህብነቱ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህ በዓል የኛ ብቻ መሆኑ ቀርቶ ዓለም አቀፍዊ እንደመሆኑ በበዓሉ ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን እየገቡ ይገኛሉ፡፡

የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በውጭ ሀገራት የሚኖሩት የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያ የሚገኙበት እንደመሆኑ ለየት ባለ መልኩ እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ የተደረገላቸው እነዚህ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን አባላት በዓሉን ለማክበር ወደ ሀገራቸው መግባት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም በበዓሉ የሚገኙ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እንዲጨምር እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

በበዓሉ ላይ ለመታደም ሀገር አቋርጠው የመጡ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች በዓሉን በሰላም አክብረው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ለማድረግ መላ ኢትዮጵያውያን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ለእዚህም ከጥንት ጀምሮ የምንታወቅበት ኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነትና መስተንግዶ ባሕላችን በዚህ ጊዜም ጎልቶ መታየት አለበት። እንግዶቻችንን በሰላም ተቀበልን በማስተናገድ በበዓሉ የማይረሳ ትዝታን ይዘው እንዲመለሱ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ባለፉት ዓመታት በስፋት እንደተስተዋለው ለጥምቀት በዓል በድምቀት መከበር አስተዋጽኦ እያደረጉ ካሉት አካላት መካከል ትልቁን ሚና እየተጫወተ ያለው ወጣቱ ነው፡፡ ወጣቱ ከበዓሉ አስቀድሞ የታቦታቱን የማደሪያ ቦታ፣ ታቦታቱ የሚጓዙባቸውን መንገዶች ከማጽዳት አንስቶ፣ ስጋጃ በማንጠፍ፣ ቄጤማ በመጎዝጎዝ እና የበዓሉን ታዳሚዎች በሥርዓት በማስተናገድ ፤ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በዓሉ በሰላም እንዲከበር እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ሚናውን ዘንድሮም አጠናክሮ ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡

ወጣቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ያሳየውን ትህትና እና ፍቅርን በማሰብ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በመላበስ ሰላም ከማስፈን አንጻር ብዙ ሥራዎች መስራት ይጠበቅበታል፡፡ እንደዚህ አይነት የአደባባይ በዓላት በሰላም ተከብረው እስኪጠናቀቁ ድረስ የሁሉንም ሰው ርብርብ ይጠይቃሉ፡፡ የዚህ በዓል በሰላም መከበር የማይጥማቸው እኩይ አላማ ያላቸው አካላት ደግሞ በተገኘው አጋጣሚ ተጠቅመው ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለማራመድ ሊፈልጉ ይችላሉ። ስለሆነም የበዓሉ ታዳሚዎች በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከሚያከናውኑት ተግባር በተጨማሪ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። መልካም በዓል!!

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን ጥር 10/2016

Recommended For You