የሀገር ባለውለታው አንጋፋው ዲፕሎማት

አንድ አንጋፋ ጋዜጠኛ የልብ ወዳጄ፤”ከአፍሪካ መዲናነት እስከ ዓለም መድረክ”በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ ጥር 24 ድረስ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ የዲፕሊማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ ተመልክቶ ደወለልኝ። ለእይታ በቀረቡ ታሪካዊ ፎቶ ግራፎችና ሰነዶች መገረሙንና መደነቁን ነግሮኝ ሲያበቃ፤ ስለ ዕንቁው አምባሳደር ከተማ ይፍሩ በዚሁ ጋዜጣ”ነጻ ሀሳብ”ላይ ያስነበብሁትን መጣጥፍ ተመልክቶ ኖሮ ምነው ቀዩን እንቁ ዘነጋኸው አለኝ።

ወዳጄ የዓለማቀፍ ግንኙነት ተማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቤተኛም ነውና፤ አመጣጡን ብጠረጥረም፤ ከእሱ ይምጣ ብዬ ደግሞ የምን ቀይ እንቁ አመጣህ ስለው፤ አሁን ማን ይሙት ጠፍቶህ ነው አለኝ፤ እኔም ካወቅሁት ለምን እጠይቅሀለሁ አልሁት፤ የዲፕሎማሲያችን የውሃ ልክና ምልክት፤ ዛሬ የተባበሩት መንግስታት ዓለምን ቁጭ ብድግ የሚያደርግበትን የጸጥታው ምክር ቤት ሀሳብ አፍላቂ፤ ጉምቱው ዲፕሎማት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ ጠፍተውህ ነው አለኝ።

መልስ አልሰጠሁትም። ያው ስለ ዕንቁው አምባሳደር ካስነበብኸን አይቀር በነካ ብዕርህ ስለእሳቸውም አንድ በለን አለኝ። እሽ ከሽ ይበልጣል ብዬ እርስዎ አዝዘውኝ እምቢ አልል ብዬ ባይሆን ፈቃድዎ ከሆነ ርዕሱን እንዲህ ላሻሽለው። “የጸጥታው ም/ቤት አባት ቀይ እንቁ ዲፕሎማት፤” በሚል። ቃል በገባሁት መሠረት እነሆ ወዳጄ ፣ እነሆ አንባቢዎች።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ (1904- 1967)፣ ለፈጸሙት በጎ ተግባር የ2013 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ልዩ ተሸላሚ ነበሩ። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተከናወነው 9ኛው የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ላይ እንደተገለጸው፣ ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ለአገራቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎትን ሰጥተዋል:: ከተጠቀሱት አገልግሎቶቻቸው አንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሉ ከተመሠረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር የተያያዘ ነው:: በዚያን ጊዜ የ34 ዓመት ዕድሜ የነበራቸው አክሊሉ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር አንድ ላይ ሆነው ወደ ሳንፍራንሲስኮ አቅንተው ነበር::

ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ በዚህ ጉባኤ ላይ የጸጥታው ምክር ቤትን (ሴኩሪቲ ካውንስል) የሚመለከት”አንድ አገር ጥቃት ሊደርስብን ይችላል ብሎ ቅሬታ ቢያቀርብ ሴኩሪቲ ካውንስል መሰብሰብ አለበት”ሲሉ አንድ ሐሳብ ያቀርባሉ:: ይህ ሀሳብ ግን በአሜሪካውያኑ ተቀባይነት አልነበረውም:: “…በምን ማስረጃ አውቀን ነው አገሮቹ ችግር ውስጥ ናቸው የምንለው” ሲሉ አሜሪካውያኑ የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባሉ። እሳቸው ግን ጣሊያን በ1929 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችውን ግፍና ለመንግሥታቱ ማኅበር ለሊግ ኦፍ ኔሽን አቤቱታዋን ባቀረበች ጊዜም ሰሚ አጥታ እንደነበር ታሪክን በማጣቀስ አስረዱ:: ሐሳቡ ተቀባይነት አገኘ:: ታሪክ የሚናገረውም የጸጥታው ምክር ቤት (ሴኩሪቲ ካውንስል) መሰብሰብ የጀመረው ከዚያ በኋላ ነበር::

በዚህና በሌሎች ተግባሮቻቸው ለክብር የበቁት ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉን ልዩ ሽልማትን ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የተቀበሉት የወንድማቸው ልጅ ናቸው:: ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የ1967 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም. ከገደላቸው 60 ሹማምንት አንዱ ነበሩ ይለናል በእለቱ የቀረበው ሀተታ ዘ አበርክቶ:: ስራቸው ከመቃብር በላይ ነውና እያነሳሳን እንዘክራቸዋለን።

ክቡር ጸሀፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ለጋሲዮን የፕሬስ አታሼ በመሆን ስራ ጀምረው በአገር ውስጥ በልዩ ልዩ መሥሪያ ቤቶች በሚነስትርነትና በመጨረሻም ለ13 ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለሀገራቸው ነጻነት፣ አንድነት፣ እድገትና ብልጽና ለ39 ዓመታት ያገለገሉ አስተዋይ መሪ ነበሩ:: ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በምሥራቅ ሸዋ አስተዳደር በአድአ ወረዳ ልዩ ስሙ ደምቢ በሚባል ሥፍራ ከአለቃ ሀብተወልድ ካብቴነህና ከወይዘሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም. ተወለዱ ይሉናል ጸሐፊውና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ደረጀ መላኩ።

ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የአማርኛ ትምህርት በአዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ራጉኤል ቤተክርስቲያን፣ ዘመናዊ ትምህርት ደግሞ በዳግማዊ ምኒሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲማሩ ከቆዩ በኋላ በ1917 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ግብጽ ሀገር ተልከው በሊሴ አሌክሳን ድሪ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለው በ1923 የፈረንሳይን ባኩሎሪያ በማዕረግ ተመረቁ:: ከእዚያም ወደ ፈረንሳይ አገር ሄደው በሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ከ1923- 1928 ዓ.ም. ድረስ ሲማሩ ቆይተው በመጨረሻ በሕግ ትምህርት ሊሳንስ (ኤል ኤል ቢ) አገኙ:: በተጨማሪም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በፐብሊክ ሎው እና በኢኮኖሚክስ ዲፕሎማ ዶክትሬት፣ እንዲሁም በንግድና በፖለቲካ ሳይንስ ሰርተፊኬት ተቀብለዋል::

ክቡርነታቸው በሊሴ አሌክሳንደሪ በትምህርት ላይ በነበሩበት ጊዜ በግብጽ የኮፕቲክ ፓትሪያርክ በአቡነ ዮሐንስ ለትምህርት የተወሰዱት የኢትዮጵያ ተማሪዎች ችግር ላይ ስለወደቁ በጊዜው የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን አንደራሴ ከነበሩትና ከግብጽ ባለሥልጣኖች ጋር በመነጋገር ችግሩ እንዲፈታ አድርገዋል:: ፈረንሳይ ሀገር ሶርቦን ዩንቨርሲቲ በትምህርት ላይ እንዳሉ ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በመወረሯ በሊግ ኦፍ ኔሽን የኢትዮጵያ ዴሊጌሽን ዋና ጸሃፊ፣ ከዚያም በፓሪስ በኢትዮጵያ ሌጋሲዮን የፕሬስ አታሼ፣ ከ1928-1929 ዓ.ም. ደግሞ አንደኛ ጸሐፊና ከ1929 ዓ.ም.-1933 ዓ.ም. ጉዳይ ፈጻሚ በመሆን ሲሰሩ ኢጣሊያኖች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ይፈጽሙት የነበረውን ግፍ ለመላው ዓለም በማሳወቅ በአደረጉት ትግል ኢትዮጵያ የአውሮፓውያንን ድጋፍ እንድታገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል::

ኢትዮጵያ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላም ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው፣ ከ1935 እስከ 1952 ዓ.ም. በጽህፈት ሚኒስቴር ም/ሚኒስቴር፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስቴር እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው አገልግለዋል:: ከ1953 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1966 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትርና የጽህፈት ሚኒስትር ሆነው ከመስራታቸው በላይ በተደራቢነት በ1958 ዓ.ም. የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሚኒስትር ነበሩ::

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ለሀገራቸው ነጻነትና አንድነት ገና በትምህርት ቤት ሳሉና በዚያም በተከታታይ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ካደረጉት ትግል በተጨማሪ ለእደገቷና ለብልጽግናዋ የፈጸሟቸው ተግባራት በርካታ ቢሆኑም ለአብነት ያህል ጥቂቱ ከዚህ ቀጥሎ በአጭሩ ተመልክቷል:: እንግሊዞች ቀደም ብለው ይዘዋት የነበረውን ጋምቤላን፣ ፈረንሳዮች ጅቡቲ ጠረፍ አጠገብ ያለችውን ውሃ ያለባትንና ስትራቴጂክ የሆነችውን አፋምቦን እና እንግሊዞች ኦጋዴን ለቀድሞው ብሪትሽ ሶማሌ ላንድ የግጦሽ መሬት ብለው የያዙትን ሪዘርቭድ ኤሪያን እንዲሁም ለማስተዳደር ችሎታ የላችሁም ብለው የያዙትን የምድር ባቡር አስለቅቀዋል:: ኢጣሊያኖች ሲወጡ ከእንግሊዞች ጋር የነበረውን ስምምነት የእንግሊዞችን የበላይነት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ የኢትዮጵያን መብት በሚያስከብር መልክ እንዲለወጥ የሀገሪቱ ወሰን ክልል (በሶማሊያና በሱዳን በኩል ያለው ሲቀር) ሌላው በሰላም ውሳኔ እንዲያገኝ አድርገዋል::

ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የአንድ ሀገር አስተዳደርና እድገት ሊጎለብት የሚችለው የተጠናከሩ ድርጅቶች ሲኖሩት መሆኑን በመገንዘብ ለእነዚህ መሰረት የሆነው ሕገ መንግስት ተሻሽሎ እንደገና እንዲወጣ፣ ከዚያም የፍትሐ ብሔርና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች፣ የጠቅላይ ሚኒስትርና የሚኒስትሮች ስልጣንና ተግባር የሚወስን ሕግ፣ የዳኞች ሹመትና በፍርድ አሰጣጥ ነጻነት ሕግ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ሕግ፣ የመንግስት ሰራተኞች የጡረታ ሕግ፣ አገር አገዛዝ ደንብ፣ የውትድርና አገልግሎት ሕግ፣ ሌሎችም የአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሥራ ሂደት የሚያፋጥኑና ሥነ ሥርዓት የሚያስይዙ ሕጎች እንዲወጡ አድርገዋል::

በልማቱም መስክ የሁለተኛውና የሶስተኛው አምስት ዓመት ፕላን እንዲዘጋጅ፣ የሕብረተሰቡ የስራ ፍላጎት ከፍ እንዲልና የስራ ፈቱ ቁጥር እንዲቀንስ በሰጡት አመራርና በአደረጉት አስተዋጽኦ በመንግስትና በግል ክፍለ ኢኮኖሚ ይገኝ የነበረው ምርት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በማሳደግና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በማርካት ረገድ የታየው ኢትዮጵያ አስተማማኝ አቅጣጫ እንደያዘች የሚያመለክት ነበር::

የዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሀገር ውስጥ መቋቋም የኢኮኖሚ ጥቅምና ለአገር ክብር እንደሚያስገኝ እንዲቋቋምና ቻርተሩ እንዲፈረም ጽ/ ቤቱም አዲስ አበባ እንዲሆን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጽ/ቤትም አዲስ አበባ እንዲመሰረት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ መስኮች በአገር ውስጥ አመራር በመስጠት በሚያካሂዱት የኃላፊነት ሥራ ብቻ ሳይወሰኑ በአያሌ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ እየተገኙ ታሪካዊና መሠረታዊ የሆኑ ተግባራት አከናውነዋል::

ለአብነት ያህል፡-

ሀ/ ፓሪስ በተደረገው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ የሰላም ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ከሌሎች መንግስታት ጋር በእኩልነት ተካፋይ እንድትሆን ባደረጉት ጥረት በአፍሪካ ውስጥ በቅኝ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ አገሮች ነጻነታቸውን እንዲያገኙ፣ ኢጣልያ በቅኝ ግዛት የያዘቻቸውን ሀገሮች እንድትለቅና ለኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ዶላር የጦር ካሳ እንድትከፍል እንዲሁም ኢትዮጵ ውስጥ የሚገኘውን የጠላት ንብረት ኢትዮጵያ እንድትወስድ አስወስነዋል::

ለ/ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር በአሜሪካን ሀገር በሳንፍራንሲስኮ ከተማ በ1937 ሲረቀቅ ኢትዮጵያ የመንግስታት ማህበር መስራች ሀገር እንድትሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገው፣ይኸው በመሳካቱ ቻርተሩን በሚያዘጋጀው ጉባኤ ላይ ተካፍለው በመጨረሻ ቻርተሩን በኢትዮጵያ መንግስት ስም ፈርመዋል::

ሐ/ ከ1937-1945 አራቱ ታላላቅ መንግስታት የኤርትራን ጉዳይ ለመመርመር በአደረጉት ጉባኤና ከእዚያም በኋላ ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ በታየበት ጊዜ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ጋር እንድትቀላቀል ተከራክረው በማሳመን አዎንታዊ የሆነ ውጤት አስ ገኝተዋል::

መ/ የስዊስ ካናል ችግር በደረሰ ጊዜ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች መሪ በመሆን በለንደን ጉባኤ ላይ ከተካፈሉ በኋላ ወደ ፕሬዚዳንት ናስር (የግብጽ መሪ የነበሩ ናቸው::) ከተላኩት አምስት ሀገሮች መልዕክተኞች አንዱ ሆነው ተመርተዋል::

ሠ/ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አሥራ አምስተኛ ዓመቱን እስከ አከበረበት ድረስ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች መሪ በመሆን በስብሰባው ላይ እየተገኙ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኮሌክቲቭ ሴኩሪቲና በተባበሩት መንግስታት ላይ ያላቸውን ጽኑ እምነት ግንዛቤ እንዲገኝ አድርገዋል::

ረ/ የአፍሪካ ነጻ መንግስታት አራት ብቻ በነበሩበት ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት በ1948 ዓ.ም. በአደረገው ጠቅላላ ጉባኤ በአንድ ድምጽ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ጉባኤውን መርተዋል:: በዚያን ጊዜ አንድ አፍሪካዊ ለዚህ ኃላፊነት ሲመረጥ እርሳቸው በታሪክ የመጀመሪያው ነበሩ::

ሰ/ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ውስጥ ባደረጋቸው የመሪዎች ስብሰባ ላይ አዘውትረው ተካፍለዋል። በተለይም ከግንቦት 14-17 ቀን 1955 ዓ.ም. በተደረገው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት የጎሳ ጉዳይ አንስተው ባሰሙት ንግግር”የሶማሊያ ዜጎች በኢትዮጵያ፣ በፈረንሳይና በእንግሊዝ ግዛት ስር ይገኛሉ:: ኢትዮጵያ ያለ ሶማሊያ ሕዝብ ፈቃድ የሶማሊያን መሬት ነጥቃ ወስዳለች::” በማለታቸው ክቡር ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ የቀረበው ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ታሪኳ የታወቀና ነጻነቷን ከሶስት ሺህ ዘመን አንስቶ የሕንድ ውቅያኖስን የሚያካብብ ለመሆኑ ታሪክ እንዲመሰክርላት በታሪክ ውስጥ የሶማሊያ መንግስት የሚባል እንደሌለ በአደባባይ ሞግተዋል።

በ1942 ዓ.ም. ስለቅኝ ሀገሮች ጉዳይ ተከፍቶ በነበረው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን መንግስት በመወከል በመገኘትም፤ ሶማሊያ በተቻለ ፍጥነት ነጻነቷን ማግኘት አለባት በማለት እንደተከራከሩ፣ የአገር ጥያቄ ማንሳት የሚቻል ከሆነ ኢትዮጵያ ታሪኳ የሚፈቅድላትና የጂኦግራፊ አቀማመጥ ሁኔታዋ በሚመሰክርላት መሰረት ሶማሊያ ራስዋን ከኢትዮጵያ ግዛት እንደ አንዷ አድርጋ እንደምትጠይቅ፤ ሆኖም ኢትዮጵያ ከመሬቷ አንዲት ጋት እንደማትሰጥ ይህንንም አይነት ፈለግ አንደማትከተል አስረድተዋል።

በማናቸውም ሀገር ጉዳይ ውስጥ ማንም ጣልቃ እንዳይገባ፣ ጠቅላላ ወሰን እንዲከበር፣ አለመግባባቶች በሰላም መንገድ እንዲያልቁ፣ ለአፍሪካ አንድነት ጥረት እንዲደረግ ኢትዮጵያ አጥብቃ ስለምትጠይቅ የሶማሊያ መንግስትም በዚህ ዓላማ ተመርቶ እንዲሰራ ያላቸውን ምኞት በመግለጽ ሰፊ መልስ ሰጥተዋል::

ሻሎም ! አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥር 9/2016

Recommended For You