ብሔራዊ ጥቅም በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት ለሀገርና ለሕዝብ ሲባል የሚከፈል ዋጋ ነው:: ዋጋው መስዋዕትነትንም የሚጨምር ነው:: ሀገር እና ሕዝብም የሚጸኑትና ከአሰቡትም ደረጃ መድረስ የሚችሉት ብሔራዊ ጥቅም ሲከበር ነው:: ብሔራዊ የጥቅሙን የማያስከብር ሀገር ሉአላዊነቱን ማስጠበቅ አይችልም:: ህልውናውም አደጋ ላይ የወደቀ ነው::
ሀገራት እንደነባራዊ ሁኔታቸውና በየወቅቱ እንደሚያጋጥማቸው ችግር የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳን ይቀርጻሉ:: ይህን ብሔራዊ አጀንዳ ምንነትና አስፈላጊነት በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ መረጃ ይሰጣሉ፤ በሕዝቡ ዘንድ ቅቡል እንዲሆን ተግባቦት ይፈጥራሉ:: ይህ ሲሆን ወጣት አዛውንቱ፤ ሴት ወንዱ ያለምንን የቀለም፤ የብሄር፤ የኃይማኖት ሌሎች ልነቶች ሳይገድቡት ከብሔራዊ ጥቅሙ ጎን ይቆማል:: መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት ይከፍላል:: እኛስ ?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሉአላዊነቱ ቀናኢ ነው:: በየዘመናቱም ከውስጥና ከውጭ የተቃጡ ሉአላዊነትንና የግዛት አንድነትን የሚፈታተኑ ተግባራትን በጽኑ ታግሎ ሀገሪቱን ከነሙሉ ክብሯ ለአሁኑ ትውልድ አስረክቧል::
ኢትዮጵያውያን በሀገራችን ህልውና ለመጣ ቀልድ አናውቅም:: ቤቴ፤ ዕርስቴ፤ ሚስትና ልጆቼ ሳንል ሀገራችንን አስቀድመን እራሳችንን ለመስዋዕትነት እናቀርባለን:: በደምና አጥንታችንም ሉአላዊነትታችን እናስከብራለን፤ ነጻነታችንንም እናረጋግጣለን:: አልፎ ተርፎም በኮርያ፤ በኮንጎ፤ በላይቤሪያ፤ በሶማሊያ፤ በሩዋንዳና ብሩንዲ እንዲሁም በሱዳን በመዝመት በግጭትና በጦርነት ውስጥ የገቡ ሀገራትን እናረጋጋለን፤ ወደ ሰላማቸው እንመልሳለን::
በአጠቃላይ በእናት ሀገራችን ለመጣብን ጨርቄን ማቄን ሳንል ህይወታችንን እንሰጣለን፤ አጥንታችንን እንከሰክሳለን፤ ደማችን እናፈሳለን:: እምቢ ለሀገሬ በማለት ብሔራዊ ጥቅማችንን እናስከብራለን:: ሆኖም አሁን አሁን የሚታዩ ዝንባሌዎች ይህንን ኢትዮጵያዊ ማንነት የሚገዳደሩና እየዋሉ፤ እያደሩ ከሄዱ የሀገርን የሕዝብ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉና ብሎም ሀገርንም የሚያፈርሱ ይሆናሉ:: ሰሞኑን ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ በተመለከተ የተሰሙ አንዳንድ ድምጾች አስደንጋጭ ናቸው:: አንዳንዶቹ አስተያየቶች ከአንድ ኢትዮጵያዊ ሊደመጡ የማይገባና ዜግነትንም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው ::
የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆንም ከስነ ልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጎታል:: የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ እንዲል ከማድረጉም ባሻገር በኢኮኖሚ ረገድም ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል:: ለበርካታ መሰረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶችን ይውል የነበረውን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል:: ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለኪራይና ለመጓጓዣ ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል::
በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነትም ረገድ የኢትዮጵያ ሚና አሽቆልቁሏል:: ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ በዓለም እጅግ ተፈላጊ ከሆኑትና የሃያላን ሀገራትንም ቀልብ የሚስብ በመሆኑ እድገቷን የማይፈልጉ አካላት በተቀነባበረ ሴራ ከቀይ ባሕር እስኪያርቋት ድረስ ገናና እና በሁሉም ዘንድ ተፈላጊ ሆና ቆይታለች:: ሆኖም ሀገሪቱ ወደብ አልባ ከሆነች ጀምሮ ተፈላጊነቷ አሽቆልቁሏል::
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሰረት የሌላቸው ናቸው:: የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል:: በአጠቃላይም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሸፍናል::
ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም:: ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በባሕር በር የተከበበች ሀገር ነች:: ከላይ እንደጠቀስኩት በሴራ እና በተሳሳተ ትርክት ከቀይ ባሕር እንድትርቅ ከመደረጓ በስተቀር በአፈጣጠሯ ለቀይ ባሕር የቀረበ ነው:: በሶስተኛ ደረጃ በታሪክም በቀይ ባሕር ላይ ለዘመናት የበላይ ሆና መቆየቷን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ያሏት ሀገር ነች::
ስለዚህም ኢትዮጵያ በግፍ ከይዞታዋ እንድትነቀል ከመደረጓ ውጪ ባለቤትነቷን የሚከለክላት አንዳችም ዓለም አቀፍ ሕግ የለም:: ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነችበትም ሆነ ከቀይ ባሕር እንድትወገድ የተደረገበት አካሄድ ምንም አይነት ሕጋዊ መሰረት የሌለው ነው:: ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትወገድና ወደብ አልባ እንድትሆን የተደረገው በ1900፤ 1902 እና 1908 ከቅኝ ገዢዎች በተደረጉ ውሎች አማካኝነት ነው:: እነዚህ ውሎች ደግሞ በተባበሩት መንግስታት መመስረቻ ቻርተር ሕጋዊነታቸውን አጥተዋል::
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲቋቋም ካወጣቸው ድጋጌዎች አንዱ ሀገራት የቅኝ ግዛት ውሎችን የመቀበል ግዴታ እንደሌለባቸው የሚደነግገው አንቀጽ አንዱ ሲሆን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር ካለመሆኗም ባሻገር በቅኝ ገዢዎች የተረቀቁትን የ1900፤ 1902 እና 1908 ውሎችን የመቀበል ግዴታም የለባትም::
ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ ከሆነችባቸው ውሎች መካከል የቅኝ ግዛት ውሎች ተጠቃሾች ናቸው:: ከአጼ ሚኒሊክ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከቅኝ ገዢዎች ጋር ያደረገቻቸው ስምምነቶች የባሕር በሯን አሳጥተዋታል:: የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በባህሪያቸው ቅኝ ሲገዙ የነበሩ ኃይሎች በአስገዳጅ መልኩ ቀኝ ገዢዎች ላይ የፈጸሙት ደባ ነው:: ስለዚህም ውል ከማለት ይልቅ በጉልበተኛና በደካማ መካከል የተፈጸመ አስገዳጅ ስምምነት ነው ማለት ይቻላል:: እነዚህ ውሎች የቅኝ ገዢዎችን እንጂ የተገዢዎችን ሙሉ ፈቃደኝነት የያዙ አይደሉም::
ስለዚህም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው የ1900፤ የ1902 እና የ1908 ውሎች ገዢ ውሎች አይደሉም፤ ስለዚህም ተፈጻሚነት አይኖራቸውም:: እነዚህ ውሎች በተባበሩት መንግስታት ማቋቋሚያ ቻርተር ላይም ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው በግልጽ ተደንግጓል:: እነዚህንና ሌሎች አጋዥ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመንተራስ ኢትዮጵያ ዛሬ ፊቷን ወደ ባሕር በር አድርጋለች::
በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ለውጥ ከመጣ ጀምሮ በትኩረት ከሰራባቸውና ለውጥ ካመጣባቸው ጉዳዮች አንዱ የባሕር በር ጥያቄ ነው:: መንግስት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል:: ለ27 ዓመታት ያህል ፈርሶ የቆየውን የባሕር ኃይል እንደገና በማደራጀት ኢትዮጵያ እንደገና የባሕር ኃይል እንዲኖራት አድርጓል::
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ከ33 ዓመታት በኋላ የባሕር በር የምታገኝበት አማራጭ ተገኝቷል:: ሰላማዊ አማራጭን ሲከተል የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን ከሶማሌ ላንድ ጋር የባሕር በር የሚገኝበትን መግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding) ተፈራርሟል::
ይህ ሲሆን ታዲያ በርካታ ዜጎች ተደስተዋል:: የኢትጵያን መበልጸግ የሚሹ ወገኖችም በሁኔታው በጣም ተገርመዋል፤ አድናቆታቸውንም ገልጸዋል:: ሆኖም ሶማሌ ሪፑብሊክ፤ ግብጽና አረብ ሊግ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል:: የሶማሊያ ሪፐብሊክ የሚጠበቅ ሲሆን ግብጽና አረብ ሊግ ግን በማይመለከታቸው ጉዳይ መግባታቸው አሰገራሚ ነው:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከግብጽና አረብ ሊግ እኩል የኢትዮጵያና የሶማሊ ላንድ የባሕር በር ስምምነትን እኩል ሲቃወሙ መስማት በእጅጉ ያሳምማል፤ ወዴት ነው እየሄድን ያለነው የሚለውን ጥያቄም ያጭራል::
በዚሁ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት‹‹ የአንዳንድ ሀገራት ተቃውሞ የሚጠበቅ ነው፤ የሚገርመው ግን ኢትዮጵያዊ የሆኑና የእኛ ያልናቸው ሰዎች የበለጠ ሲጮሁ መስማታችን ያስገርማል›› ብለዋል:: የእሳቸውም ንግግር ከላይ ያልነውን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው::
ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳያቸው ቢለያዩም በብሔራዊ ጥቅምና በህልውና ጉዳይ ተለያይተው አያውቁም:: የባሕር በር ጉዳይ ደግሞ የህልውና ጉዳይ ጭምር ነው:: ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት “የህልውና ጉዳይ ነው” ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው:: እንደዚህ ከሆነ ደግሞ በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣ አስተያየት ወይም ነቀፌታ መስጠት ሌሎችን ያስደስት እንደሆነ እንጂ እንደ ሀገር የሚሰጠው ጥቅም የለም፤ እንደውም በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ላይ ተለያይቶ መገኘት ለጠላቶች በር ይከፍት እንደሆን እንጂ አንድነትን አያመጣም::
ሁኔታውን የበለጠ የሚያገዝፈው ደግሞ ይህንን የልዩነት አስተያየት የሚሰጡት ተማሩ፤ አወቁ የምንላቸው ሰዎች ሆነው መገኘታቸው ነው:: ከእነዚህ ሰዎች በሳል አመራርን፤ አብሮነትን፤ ሀገራዊ ጥቅምንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያጎሉ ሃሳቦችና ምሁራዊ ትንታኔዎች መቅረብ ሲገባቸው በአንጻሩ በወደብና የባህር በር እጦት የሚንገላታውን ዜጋ የበለጠ ወደ ጨለማው የሚወስዱ አስተሳቦችን ማስረጽ ከአንድ ከተማረ ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም::
የኢትዮጵያን ማደግ በማይፈልጉ ኃይላት ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እንድትወገድ ተደርጓል:: ለዘመናትም ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ምንም ድርሻ እንዳልነበራት ሆን ተብሎ በተሰራጨው ትርክት ኢትዮጵያና ቀይ ባሕር ተቆራርጠው ኖረዋል:: ከሕዝቡ ልብ ውስጥ ቀይ ባሕርን ማውጣት ባይቻልም ስለቀይ ባሕር ማሰብና ማውራት እንደ ሀጢያት ሲቆጠር ቆይቷል:: ባለፉት 30 ዓመታት ስለ ወደብና ባሕር በር ማውራትም ሆነ የኢትዮጵያን የባለቤትነት መብት መጠይቅ እንደነውር ከማስቆጠሩም በላይ ጸብ አጫሪ አስብሎም በነገረኛነት ያስፈርጅ ነበር::
ዛሬ ዕድሉ ሲከፈት ሁኔታውን መደገፍና አለፍ ብሎም ምሁራዊ አስተዋጽኦ ማበርከት ሲገባ ተቃዋሚ መስሎ መገኘት አግባብ አይደለም:: ጭራሹኑም አንዳንድ ምሁራን በፖለቲከኝነት እፈረጃለሁ በሚል ስጋት በወደብና በባሕር በር ዙርያ እንኳን መረጃ ለመስጠት ፍላጎት ሲያጡ ይታያል:: ጋዜጠኞች ለአንዳንድ ምሁራን ስልክ ደውለው መረጃ በባሕር በር ጉዳይ ስጡኝ በሚሉበት ጊዜ የሚያጋጥማቸው ተግዳሮት ‹‹ይህንን ብናገር በፖለቲከኝነት እፈረጃለሁ፤ የገዢው ፓርቲ አባል እባላሁ ወዘተ››የሚል ፍራቻ ነው:: ሆኖም የባሕር በርም ሆነ የወደብ ጉዳይ ከአንድ መንግስት ወይም ፓርቲ ህልውና ጋር በፍጹም ሊተሳሰር የማይችልና ሀገርና ዜጎች እስካሉ ድረስ የሚዘልቅ ነው:: ስለሆነም እራስን ለወቅታዊ ፍራቻ እያስገዙ መሄድና በምን ይሉኛል ስሜት ታጥሮ መጓዝ ከአንድ ምሁር የሚጠበቅ አይደለም::
ምሁራን ሕዝብ እና ሀገርን አስቀድመው የሚንቀሳቀሱ እውነት ፈላጊዎች ናቸው:: ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም እውነተኛ ሃሳብ እስከያዙ ድረስ ‹‹እገሌ እንዲህ ይለኛል፤ በእዚህ እፈረጃለሁ›› በሚል ስጋት ከምሁራዊ ደረጃቸው ሊወርዱ አይገባም:: የዛሬ ምሁራን ትላንት በሕዝብ ሀብትና ገንዘብ የተማሩ ናቸው:: ስለዚህም ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ሃሳብ ላይ መሳተፍና የሕዝብን ጥቅም ማረጋገጥ አለባቸው:: በዚህም ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መረጃ የመስጠት የሞራል ግዴታ አለባቸው:: ጊዜ አይቶ መረጃ መስጠት እና መንፈግ የምሁራን ባህሪ አይደለም::
ይህ ችግር የምሁራን ብቻ አይደለም:: ይበልጡኑ የመንግስት ኃላፊዎችን የሚመለከት ነው:: የመነግስት ኃላፊዎች በወቅቱ መረጃ መስጠት ግዴታ እንዳለባቸው እየታወቀ ብዙዎቹ ዳተኛ ሆነው ይገኛሉ:: መንግስት ኃላፊዎች የሕዝብና የሀገር ጥቅምን የሚያስከብሩና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያረጋግጡ መረጃዎችን ጭምር ለመስጠት የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ሲሉ መስማት የተለመደ ነው:: ሆኖም ብሔራዊ ጥቅም ለአንድ ለተወሰነ የመንግስት መሪ ወይም ሕዝብ የሚተው ሳይሆን ሁሉም በሙያው፤ በእውቀቱ፤ በገንዘቡ፤ በፍላጎቱ ወዘተ ሊደግፈው የሚገባና መስዋዕትነትም የሚጠይቅ ከሆነ ይህንኑ መክፈል የሚጠይቅ ነው::
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ጥር 9/2016