.የአገር ውስጥ ቱሪዝም በስፋት እየተሰራ አለመሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ:- ከቱሪዝም ዘርፉ የሚያ ገኘው 50 በመቶ የሚሆነው ገቢ የጉዞ ወኪሎቹ ባዘጋጁት ፓኬጅ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ በስፋት እየተሰራ አይደለም፡፡
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች የብቃት ማረጋገጥና ደረጃዎች ምደባ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፋሲል እንዳለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት ፤ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪስት መዳረሻ ተፈላጊ ከሆኑ 10 ሀገራት ውስጥ ለመመደቧ ምስጢር የጉዞ ወኪሎች ጥረት ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ ዘርፉን በማሳደግ በኩል የማይተካ ሚና እንዳላቸው ያሳያል።
“በየዓመቱ 48 በመቶ የቱሪዝም እድገት ሊያሳይ የቻለውም የጉዞ ወኪሎቹ እና የማህበራቱ የማስተዋወቅ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው” ያሉት አቶ ፋሲል፤ አሁን የቱሪስት ፍሰቱ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሆኗል ብለዋል። ቱሪዝም ከግብርናው ዘርፍ ቀጥሎ የውጪ ምንዛሪ ማስገኛም መሆኑን የጠቀሱት አቶ ፋሲል፣ ለዚህ ደግሞ የጉዞ ወኪሎች አጋዥነታ ቸው አጠያያቂ አይደለም ብለዋል።
የአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ በስፋት እየተሰራ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ ፋሲል፣ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው መንግስት መሆኑን ገልጸዋል። መንግስት የጉዞ ወኪሎችና ማህበራትን ያደራጀ ሥራ እየተሰራ አይደለም ብለዋል። የጉዞ ወኪሎች አሁን ላይ ባለ መረጃ 650 የደረሱ ሲሆን፤ ቱሪዝሙን በማሳደግ ዙሪያ ትልቅ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በዋናነት ሥራቸው የውጪ አገር ቱሪስቶችን ማስጎብኘት ላይ ስለሆነ የቱሪዝም አቅሙን እያጎለበቱ መሆ ኑን አመልክተዋል።
የአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ እንዲሰሩ አጋዥ ኃይል ስላልነበረ አሁን የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ብቻ የሚመለከት ዳይሬክቶሬት እየተቋቋመ መሆኑን አቶ ፋሲል አመልክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሃጅ ሙሃጅር ጅማ በበኩላቸው ፣የአገር ውስጥ ቱሪዝም ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ አገሩን የሚያውቅ ብቻ ሳይሆን ከአገሩ ይልቅ ሌሎች አገራትን ለማወቅ የሚናፍቅ ትውልድ እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
እርሳቸው እንደገለጹት፤ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይም ሆነ የውጪ ጉዞዎች ላይ እንደ እስልምና ሥራዎች ተሰርተዋል ማለት አያስደፍርም። ታሪካዊ ቦታዎችን የማስተዋወቁ ሁኔታ በሃይማኖት ብቻ የተገደበ መሆኑም ሌላው ችግር ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የአገሩ አምባሳደር ሆኖ እንዳይሰራና ቱሪዝሙን እንዳያሳድገው አድርጓል።
የቆሮንጦስ አስጎብኝና የጉዞ ወኪል ሥራ አስኪያጅ መምህር ቢንያም ቢያድግልኝ በበኩላቸው፣ ቱሪዝም በበቂ ደረጃ እየተሰራ ነው ማለት እንደማይቻል ጠቅሰው፣በተለይም በአገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ በበቂ ሁኔታ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦና ኃላፊነት ወስዶ እየተሰራ አይደለም ብለዋል፡፡
የጳጉሜን አስጎብኚ እና የጉዞ ወኪል ሸር ኩባንያ የኦፕሬሽን ማኔጀር አቶ ሲሳይ ጌታቸው እንደገለጹት፣ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር ውስጥ ቱሪዝም ትልቅ ስፍራ ያላቸውና የገቢ ምንጭ የሚሆኑ ሃይማኖታዊ ቅርሶች በአገር ውስጥ አሉ ፡፡ ሆኖም ይህንኑ ሀብት በማሳወቁ ላይ የጉዞ ማህበራት የማይተካ ሚና አላቸው። ሆኖም የቱሪዝም ዘርፉ ተቀናጅቶ ስለማይሠራ ባለቤት አልባ ሥራዎች እየበዙ፤ ተናጠላዊ ሥራዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ያስረዳሉ። ይህ ደግሞ አዳዲስ መዳረሻዎች እንዳይተዋወቁ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው