በንጉሱ ከልብ የተወደደው ቢትወደድ

በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት በተለይ ከአድዋ ድል በኋላ የአገሪቷን የውጭ ጉዳይ እንዲያስፋፉ ባለሙሉ ሥልጣን ሆነው የተሾሙ ሰው ነበሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ከሹመቱ በተጨማሪ የቢትወደድነት ማዕረግ የተሰጣቸው በንጉሱ የተወደዱ ሰውም ነበሩ። በዚህ ኃላፊነት ሥራቸው ንጉሠ ነገሥቱን ወክለው የውጭ አደራዳሪዎችን ያነጋግራሉ፣ ከኃያላን መንግሥታትም ጋር ይጻጻፋሉ። ከአማርኛ ሌላ በጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሠለጠኑ ስለነበሩ ለዚህ ሥራ ብቃት የነበራቸው ሰው ነበር።

ቢትወደድ አልፍሬድ ኢልግ ይባላሉ። በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ኑሮውን ኢትዮጵያ ውስጥ የመሠረቱ፤ የስዊትዘርላንድ ዜጋ ነበሩ። ኢልግ በምሕንድስና ሙያው ባቡር እና የቧንቧ ውሀ ለአገራችን ካስተዋወቋቸው ብዙ ዘመናዊ የሥልጣኔ መስመሮች ሁለቱ ሲሆኑ በንጉሠ ነገሥቱ ፊት ታላቅ ታማኝነትን በማፍራቱ የዘውድ አማካሪ እና የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ እስከ መምራትም የበቁ ሰው ነበሩ።

ቢትወደድ ኢልግ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ሚና ከተጫወቱ አውሮፓውያን መካከል በሀገሪቱ ባሳለፏቸው ሃያ ሰባት ዓመታት እና ባስቀመጧቸው የልማት አሻራዎቹ የታሪክ ሥፍራው በጣም የጎላ ነበር።

ኢልግ በ ስዊትዘርላንድ፣ ፍራውንፌልድ በሚባል ከ ዙሪክ ከተማ በሰሜን-ምሥራቅ አቅጣጫ በሚገኝ ሥፍራ በ መጋቢት ወር በ1846 ዓ.ም ተወልዶ በስድሳ ሁለት ዓመቱ የገና ዕለት ( ታሕሣሥ 29 ቀን) ፲፱፻፰ 1908 ዓ.ም ዙሪክ ላይ በልብ ሕመም ምክንያት አረፈ።

ኢልግና ኢትዮጵያ

ታዋቂው የታሪክ ምሁር ሪቻርድ ፓንክኸርስት ዳግማዊ ምኒልክ ገና በልጅነታቸው የ ዓፄ ተዎድሮስ እስረኛ በነበሩ ጊዜ ቴዎድሮስ አጠገባቸው የነበሩትን አውሮፓዊ ወንጌላውያን መድፍና መሣሪያዎች እንዲሠሩላቸው ማግባባታቸውን ልብ አድርገው ነበርና የሸዋ ንጉሥ ሲሆኑ በ ኤደን ላይ የነበረ አንድ የስዊትዘርላንድ ዜጋ ነጋዴ ምሕንድስና የሚያውቁ አውሮፓውያን ባለሙያዎችን እንዲፈልግላቸው ጠይቀውት ነበር ይላል።

ኢልግ እና ሁለት የአገሩ ሰዎች በ ፲፰፻፸ 1870 ዓ.ም አካባቢ ጉዞዋቸውን ወደ ኢትዮጵያ አምርተው ሸዋ ሲገቡ ንጉሥ ምኒልክ መጫሚያ እንዲሠራላቸው ያዙትና ሠርቶ ባበረከተላቸውም መጫሚያ እጅግ እንደተደሰቱ ይነገራል። በሌላ ዘገባ ደግሞ ንጉሡ ኢልግን ጠመንጃ እንዲሠራላቸው አዘዙት።

ኢልግ ጠመንጃ ለመሥራት ሙያ እንደሌላቸውና ከውጭ የሚመጣ መሣሪያ እሱ ከሚሠራው እጅግ የላቀ እንደሚሆን ቢያስረዱም፤ ምኒልክ ኃሳባቸውን የማይለውጡ ሆኑ። ከዛም እንደተጠየቁት የሙከራውን ውጤት ሲያሳይዋቸው ንጉሡ ተደስተው ይሄንኑ ጠመንጃ በግምጃ ቤታቸው የክብር ቦታ ሰጡት ብለው አዘዙ። ከዛ በኋላ በምሕንድስና ሥራ በደሞዝተኝነት ቀጥረውት በየወሩ ሰባት ወይም ስምንት ፓውንድ በጠገራ ብር ይከፈላቸው እንደነበር ፓንክኸርስት ዘግቧል።

ኢልግ የሰሩት ድልድይ

ኢልግ ከሠሯቸው አንዱ አዋሽ ወንዝ ላይ የቆመው ድልድይ ነው። ስለዚህ ድልድይ ሥራ ኢልግ ሲጽፉ፤ የመጀመሪያው የድልድይ ሥራ እንደነበረና የድልድዩ ቋሚዎች በሰው ሸክም አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር ተጉዘው እንደመጡ ይተርክና ሥራውን በሐሩር እና በዶፍ እንዲሁም በማታ የዱር አራዊትን በመቋቋም እራሳቸው ድንጋይ እየጠረቡ፣ ምስማር፣ ችንካር እና ብሎን እያቀለጡ እየቀጠቀጡ እንደሠሩት ይናገራሉ።

ባቡር በኢትዮጵያ

ምኒልክ በሸዋ ንጉሥ ከሆኑ በኋላ ሐዲድ አዘርግተው ባቡር ለማስገባት አሰቡ። ይህም ሀሳባቸው እንዲፈቀድላቸው የበላያቸውን ንጉሠ ነገሥቱን አጤ ዮሐንስን ፈቃድ ጠየቁ። በአጤ ዮሐንስ አካባቢ የነበሩ መኳንንቶች መክረው ምኒልክ ከግዛታቸው ከሸዋ ውጭ ሐዲድ ለመዘርጋት እንደማይችሉ ተነገራቸው። በሳቸው መቸኮልና መጓጓት ምክንያት አልፍሬድ ኢልግ በሥራና በሀሳብ ተጠምደው እንደነበር ወዲያውም ለ ጃንሆይ ምኒልክ የሞዴል ባቡር ተጎታች ጋሪዎችን እየጎተቱ በሐዲድ ላይ ሲሄድ የሚያሳይ ሠርቶ ሲያሳያቸው በጣም እንደተደሰቱ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፋቸው ዘግበዋል።

ከ ዓፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ ምኒልክ የንጉሠ ነግሥትነትን ዘውድ በ ጥቅምት ወር ጭነው ወዲያው በ ኅዳር ወር ላይ የምድር ባቡርን ሥራ አንቀሳቅሰዋል። ለዚህም ኢልግ ከማንኛውም ኩባንያ ጋር ተዋውለው ሐዲዱን ለማሠራት የሚችልበትን ፈቃድና የሚዋዋልበትን የውል ዓይነት መጋቢት 1፩ ቀን 1886 ፲፰፻፹፮ ዓ.ም አስጽፈው በማህተማቸው አትመው ሰጡት። ኢልግም ፓሪስ ከተማ ላይ ቢሮ ከፍተው ለሥራው የሚያስፈልገውን መዋእለ ነዋይ፤ ሥራውን የሚኮናተሩ ድርጅቶችን እና ሌላም ጥናቶችን ማቀናበር ጀመሩ።

የዚህ የምድር ባቡር መሥመር ከ ጂቡቲ ወደብ ተነስቶ አዲስ አበባ ድረስ 784 ፯፻፹፬ ኪሎ ሜትር ሲሆን ሥራው በ 1890፲፰፻፺ ዓ.ም ተጀምሮ ከሀያ ዓመታት በኋላ በ 1910 ዓ.ም ተገባደደ። መቸም የኃሳቡ ጠንሳሽ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክም ሆኑ ሕልማቸውን ዕውን በማድረግ ብዙ አስተዋጽዖ ያስመዘገበው ኢልግም ፍጻሜውን ባያዩትም በኢትዮጵያ የምድር ባቡርን ስናስብ የእነዚህ የሁለቱ ሰዎች ትዝታ በታሪክ ተመዝግቦ ይኖራል።

ፖስታ

ዳግማዊ ምኒልክ በመንግሥታቸው ስርዓትን ለማስገባት፤ ኢትዮጵያ ከ አውሮፓ “ክርስቲያን ሕዝብ” ጋር እንዲለማመድ እና በዋናነት ግን በ1885 ፲፰፻፹፭ ዓ.ም ለ አድዋ ጦርነት መንስዔ የሆነውን የውጫሌ ውል ካፈረሱ በኋላ እንደልባቸው ከውጭው ዓለም ጋር ያለ ኢጣልያ ጣልቃ ገብነት መገናኛ መንገድ አስበው የፖስታ ስርዓትን ሲመሠርቱ በጊዜው የፖስታ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት በ ስዊስ ከተማ በርን ላይ ነበር።

ንጉሠ ነገሥቱ የፖስታ ድርጅት ከተቋቋመ በኋላ ወደ ውጭ አገር ከጻፏቸው ደብዳቤዎች አንዱ ሐምሌ 13 ቀን 1887 ዓ/ም ኢልግ ወደ አገሩ ሄዶ በነበረበት ጊዜ ለሱ የጻፉት ይጠቀሳል። የኢልግ መልስ ምን እንደነበር ባናውቅም፣ ምኒልክ ግን የቱን ያህል ናፍቀውት እንደነበር እንገነዘባለን።

የእንጦጦው ቤተ መንግሥት ግንባታ

የእንጦጦ ቤተ መንግሥት የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ዋና ከተማቸውን ከ አንኮበር ወደ እንጦጦ ሲያዛውሩ መጀመሪያ የሠፈሩት በድንኳን ነበር። ወዲያ መሐንዲሳቸው አልፍሬድ ኢልግ አዲስ ቤተ መንግሥት እንዲያሠራላቸው በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት፣ አሁን ድረስ ቆሞ በቤተ ቅርሳ ቅርስነት የሚያገለግለውን ሕንጻ አሠራላቸው።

ቤተ መንግሥቱ ከአንኮበሩ ቤተ መንግሥት ያነሰ እና በዚያ ጊዜ የነበሩትን ቤተ መንግሥቶች ያህል ስፋት የለውም በሚል በጊዜው ነቀፋ ተሰንዝሮበት ነበር። ሆኖም ምኒልክ የ ንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን እስከጨበጡ ጊዜ ድረስ ተገልግለውበታል። አንዳንዴም ወደ ሰሜን ሲጓዙ ወይም እንጦጦ ማርያምን ሊሳለሙ ሲሄዱ ያርፉበት እንደነበር ይታወቃል። እሳቸውም ከሞቱ በኋላ እቴጌ ጣይቱ እስከ ዕድሜያቸው መጨረሻ ድረስ በግዞት ኖረውበታል።

አዲስ አበባም የሚገኘው “ታላቁ” ወይም “የምኒልክ ቤተ መንግሥት” በ 1890 ፲፰፻፺ ዓ/ም ላይ መታነጽ ሲጀምር ኢልግ በምሕንድስናው ሥራ ላይ ብዙ ተሳትፎ እንደነበረው ተጽፏል። በጊዜው ከተማዋን ትጎበኝ የነበረች፣ ወይዘሮ ፒስ የምትባል እንግሊዛዊት “(በቤተ መንግሥቱ) ብዙ (የስዊስ ባሕር ምስል እና የዊሊያም ቴል ጸሎት ቤት) ስዊሳዊ ተጽእኖዎች እንደተገነዘበች መፃፏን ሪቻርድ ፓንክኸርስት በፅሁፋቸው ገልፀውታል።

ንፁህ የቧንቧ ውሃ ለቤተመንግስቱ

ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ ስለዚህ ሥራ በሰፊው ሲያጫውቱን ሥራው በ1886 ፲፰፻፹፮ ዓ/ም እንደተጀመረና ለቧንቧ መግዣ ሰባት ሺ ማርያ ጠሬዛ ብር እንደሰጡ፤ ውሃው ከእንጦጦ ኪዳነ ምኅረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተጠልፎ ከቤተ መንግሥቱ እንደገባ ይነግሩናል። የቤተ መንግሥቱ የቧንቧ ውሃ ከተገጠመ በኋላ ምኒልክ አዲስ አበባ ከተማ በሙሉ እንዲዳረስ የውሃ ቧንቧ አስገዝተው ቧንቧው ከ ጂቡቲ እስከ ድሬዳዋ በምድር ባቡር፣ እስከ አዲስ አበባ ደግሞ በሰው ሸክም እንዲመጣ አዘዙ። ሆኖም እሳቸው ያሠሩት የቧንቧ ውሃ እምብዛም ሳይስፋፋ እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ ቆየ።

ሆኖም በዘመኑ የምኒልክ እንግዳ ሆኖ ኢትዮጵያን የጎበኘው አሜሪካዊው ዊሊያም ኤሊስ በምኒልክ አዳራሽ “ለኔ ክብር በተዘጋጀ ሰባት ሺ ሰዎች በተጋበዙበት ግብር ላይ፣ ጠጅ የሚባለውን መጠጥ በግብር ቤቱ ዙሪያውን በተገጠመ ቧንቧ የፈለገው ሰው እየተነሳ ከቧንቧው ይቀዳል።” ሲል ተናግሯል።

አጼ ሚኒሊክ በቢትወደድ ኢልግ የተነሡት ፎቶግራፍ ዳግማዊ ምኒልክ ኢልግን የውጭ ዜጋም ቢሆን እንኳ ያከብሩትና ያምኑትም ነበር። ትውልድ አገሩ ስዊስ የቅኝ ግዛት ምኞት የሌላትና ትንሽ፣ የ ባሕር ወደብ የለሽ እና ከሌላ አውሮፓዊ ኃያል መንግሥታት ጋር ያልተሻረከች መሆኗም የኢልግን ታማኘት ሳያጠናክረው አልቀረም።

ኢልግም በበኩሉ “እንደ አባቴ እወዳቸዋለሁ” ያላቸውን ምኒልክን ለሀያ ዓመታት በታማኝነት አገልግሏል። ኢልግ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ ትግራይ እና ዝዋይ የመሳሰሉ ቦታዎች ተጉዟል። እንዲሁም ወደ ጣልያን አገር ተጉዞ ከሚንስትሮቻቸው ጋር ከተወያየ በኋላ ሲመለስ ኢጣልያ ኢትዮጵያ ን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ሀሳብ እንዳላት ዳግማዊ ምኒልክን አስጠንቅቋቸዋል።

ከጦርነቱም በኋላ የ አድዋ ድልም ያስከተለውን የድርድር (diplomacy) መስፋፋት እንዲያስተዳድር እና የአገሪቷን የውጭ ጉዳይ እንዲይስፋፋ ባለሙሉ ሥልጣን አደረጉት። ንጉሠ ነገሥቱ ኢልግን ሲሾሙት አብረውም የ ቢትወደድን ማዕረግ ሰጡት። በዚህ ኃላፊነት ሥራው ንጉሠ ነገሥቱን ወክሎ የውጭ አደራዳሪዎችን ያነጋግራል፣ ከኃያላን መንግሥታትም ጋር ይጻጻፋል። ሰውዬው ከ አማርኛ ሌላ በጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣልያንኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሠለጠነ ስለነበር ለዚህ ሥራ ብቃት የነበረው ሰው ነበር።

ከንጉሠ ነገሥቱም ሌላ ከብዙ ኢትዮጵያውያን መሳፍንት፣ መኳንንትና ሹማምንትም ጋር ይጻጻፍ እንደነበር ተዘግቧል። ከነኚህም መሃል እቴጌ ጣይቱ፣ የ ጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ የ ሐረርጌው ገዥ ልዑል ራስ መኮንን፣ የ ጅማው አባ ጅፋር እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ይገኙበታል።

ከ አድዋ ድል በኋላ በ ኢጣልያ እና ኢትዮጵያ መሃል ጥቅምት ፲፮ 16 ቀን 1889 ፲፰፻፹፱ የተፈረመውን የዕርቅ ውል፤ ከ ብሪታንያ እና ከ ፈረንሳይ መንግሥታት ጋር በ መጋቢት ወር የተፈረሙትን ውሎች

እንዲሁም ከጀርመን መንግሥት እና ከኦቶማን ግዛት መንግሥት ጋር የተፈረሙ ውሎችን በማዘጋጀትም ሆነ እስከ ማዋዋል ድረስ ኢልግ ሙሉ ተሳትፎ እንደነበረው ታሪክ ይዘግባል።

ወደ መጨረሻው ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱም ጤናቸው እየደከመ መጣ። በቤተ መንግሥቱም እሱን የሚመቀኙት ሰዎች በዙ። ከሁሉም ግን የካቲት ወር 1897 ፲፰፻፺፯ ዓ/ም የ ጀርመን ልዑካንን የመራው ፍሬድሪክ ሮሰን የተባለው ጀርመናዊ በ ኢትዮጵያ መንግሥት እና በ ጀርመን መንግሥት መሃል ብዙ ውሎችን ከተፈራረመ በኋላ በቤተ መንግሥቱ የኢልግ ተሰሚነት እየመነመነ ሄዶ በ ፲፱፻ ዓ/ም ሥራውን ለቆ ወደትውልድ አገሩ ተመለሰ።

ወደአገሩ ከተመለሰ በኋላ በእሪ በከንቱ ሠፈር ያለው መኖሪያ ቤቱ የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት (የአሁኑ ዳግማዊ ምኒልክ) በ 1901 ፲፱፻፩ ዓ/ም ተከፈተበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን ትምህርት ቤቱ አሁን አራት ኪሎ ወዳለበት ሥፍራ ተዛወረ። አልፍሬድ ኢልግም በተወለደ በስድሳ ሁለት ዓመቱ የ ገና ዕለት

(ታሕሣሥ ፳፱ 29 ቀን) 1908 ዓ/ም ዙሪክ ላይ በልብ ሕመም ምክንያት አረፈ።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን  ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You