አዲስ ዘመን ትናንት እንዴትስ አለፈ፤ ትናንትን በዛሬ በአዲስ ዘመን ድሮ ትውስታዎች የአጭር ቀሚስ ቁጥጥር፤ የ40 ዓመቷ ሴት፤ 22 ጠንቋዮች የሳምንቱ አጋጣሚና ሌሎች ጉዳዮችም ተካትተዋል።
የአጭር ቀሚስ ቁጥጥር በሐረር
ሐረር፡- (ኢ-ዜ-አ-) በሐረር ከተማ ውስጥ አጫጭር ቀሚስ እየለበሱ በሚዘዋወሩት ሴቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የሐረር አውራጃ ፖሊስ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ ገለጡ፡፡
በተደረገው ቁጥጥር መሠረት በሐረር ከተማ ውስጥ የሀገርን ባህል የሚያጎድፍ ልብስ ለብሰው የተገኙት 67 ልጃገረዶችና ሴቶች 2ኛ ፖሊስ ጣቢያ እየቀረቡ ዳግመኛ ላለመልበስ መፈረማቸውን ሌተናል ኮሎኔል ኃይለ ሚካኤል አስረድተዋል፡፡ ይኸው አፈጻጸም ለወደፊቱ በየጣቢያው ተላልፎ በሚገባ በሥራ ላይ እንደሚውል ታውቋል፡፡
በዚሁ ይዞታ በከተማው ውስጥ ይታይ የነበረው የአጭር ቀሚስ ለባሾች ቁጥር መቀነሱንና ለወደፊት ጨርሶ እንደሚጠፋ ሌተናል ኮሎኔል ኃይለሚካኤል ገብሬ እምነታቸው መሆኑን ገልጠዋል፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 2 ቀን 1962 ዓ.ም)
የ40 ዓመት ሴት በአንድ ጊዜ ሦስት ልጆች ወለዱ
ሐረር፡- (ኢ.ዜ.አ) ወይዘሮ ፋጡማ ኢብሮ የተባሉ የ40 ዓመት ሴት ሐረር ከተማ በሚገኘው፣ በምሥራቅ አርበኞች ሆስፒታል ውስጥ ባለፈው ዓርብ 3 ሕጻናትን በአንድ ጊዜ መገላገላቸውን የሆስፒታሉ አስተዳደር አቶ ሽፈራው አቢቢ አስታወቁ።
ከሕጻናቱም መካከል መጀመሪያ የተወለደው ወንድ 4 ኪሎ ከሃያ አምስት ግራም ክብደት ሲኖረው፣ ተከትለው የተወለዱት ሌሎች አንድ ወንድና ሴት ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ኪሎ ከ20 ግራም ክብደት እንዳላቸው ተገልጧል።
(አዲስ ዘመን፣ ግንቦት 7 ቀን 1971 ዓ.ም)
22 ጠንቋዮች ራሳቸውን አጋለጡ
ደሴ፡- (ኢ.ዜ.አ) ወሎ ውስጥ፣ በደላንታ ወረዳ የኢላና ትምህርት ቤት መምህራን ከጣርዳት፣ ከደሀናንና ከዝባን የገበሬ ማኅበራት ጋር በመተባበር በመካከላቸው የተሰገሰጉትን 22 አባይ ጠንቋዮች ራሳቸውን አጋልጠው ክቡር ወደ ሆነው የሥራ መስክ እንዲሰማሩ አደረጉ።
እነዚሁ 22 አባይ ጠንቋዮች በተሰጣቸው ትምህርት አምነው ድቤዎችን (ከበሮዎችን)፣ እንዲሁም በእጃቸው ይገኙ የነበሩትን ልዩ ልዩ የጥንቆላ ዕቃዎችንና መጻሕፍት ለገበሬ ማኅበራቱ በራሳቸው ፈቃድ አስረክበዋል። አባይ ጠንቋዮቹ ካስረከቧቸው ዕቃዎች ውስጥ፣ በተለይ ከበሮዎቹ በአካባቢው ለሚቋቋመው የኪነት ቡድን መገልገያ እንዲሆን መሰጠቱ ተገልጧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23 1971ዓ.ም
በከበርቴው ይቀለብ የነበረው ዘንዶ በገበሬው ተገደለ
በኢሉባቦር ክፍለ ሀገር፣ ዱጳ በተባለው ቀበሌ አንድ የቀድሞው የመሬት ከበርቴ ከአንድ ገበሬ ላይ እየወሰደ ይቀልበው የነበረ አንድ ዘንዶ ሰሞኑን በገበሬው ተገደለ፡፡
ነጋሽ ተመመ የተባለው የቀድሞው የመሬት ከበርቴ ከገበሬው በግ እየነጠቀ ቆሎ ተብሎ በተሰየመ እንጨት ሥር እያደረ ዘንዶውን ይቀልብ የነበረ መሆኑን ተገልጧል፡፡
ዘንዶው ሰሞኑን ነጋሽ ተመመ በሌለበት እንደልማዱ ወደ እንጨቱ ሲመጣ በአካባቢው የተሠማሩትን፣ የገበሬውን ከብቶች በማግኘቱ ከመካከለቻው አንዷን በግ ሲይዛት ደርሶ ገበሬው በጦርና በመጥረቢያ ጨፍጭፎ ገድሎታል፡፡
ዘንዶው ቁመቱ ስምንት ሜትር፣ ጎኑ 60 ሳንቲ ሜትር ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ቆዳው በኤግዚቢትነት በአካባቢው የገበሬ ማኅበር ጽ/ቤት የሚገኝ መሆኑን የዳሪሙ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 23 ቀን 1979ዓ.ም
ተቆጣጣሪ በመምሰል ያጭበረበረው ተቀጣ
ደሴ፡- (ኢዜአ) በደሴ ከተማ ውስጥ ምንም አይነት ሥልጣን ሳይኖረው የአሥር አለቃ ነኝ በማለት ከገጠር ወደ ከተማ የሚገባውንና የሚወጣውን እህል፣ ስኳርና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በመፈተሽ ሲያወናብድ የተገኘው ዓሊ መሐመድ በ3 ወር እስራት እንዲቀጣ የ04-01-01 ቀበሌ ማኅበር የፍርድ ሸንጎ ከትናንት በስቲያ ወስኖበታል።
በተከሳሹ ላይ የእስራት ቅጣት ሊወሰንበት የቻለው ባልተሰጠው ሥልጣን በመንገድ ላይ እየጠበቀ ስኳርና ሸቀጥ ጭነው ወደ ገጠር የሚወጡትንና እህል ጭነው ወደ ከተማ የሚገቡትን መኪናዎች እያስቆመ በመፈተሽ የተመቸውን ጥቅም በመቀበል ሲለቅ ያልተመቸውን ደግሞ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በማቅረብ አወናብዶ ለማስቀጣት ሞክሮ እንደነበር በማረጋገጡ ነው፡፡
( አዲስ ዘመን፣ የካቲት 19 ቀን 1969ዓ.ም)
ፖሊስ ጣቢያ
ግንቦት 14 ቀን ከጠዋት 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ሲሆን ሰፈሩ ቄራ ሰፈር የሆነ ገብረጻድቅ ተስፋዬ የሚባል ሰው ያንድ እግር ጫማ፣ 2 የቆዳ ገንባሌ ይዞ ሲሔድ በእቴጌ መነን መንገድ ተገኝቶ በጥርጣሬ ኪዳኔ ይማም በሚባል ፖሊስ ተይዞ መጥቶ ዋቢውን እስኪያቀርብ ታስሯል፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 5 ቀን 1936 ዓ.ም)
ግንቦት 14 ቀን ከቀኑ 4 ሰዓት ሲሆን የሰሜን ምሽግ ገፈርሣ የሚጠብቁት የጦር ሚኒስቴር ወታደሮች ኃይለማሪያም ዘለቀና ማሞ ወልደጻድቅ የሚባሉት ሌቦች ሌሊት ሁለት ሆነው 7 ሰዓት ላይ የምሽጉን ቆርቆሮ ሰርቀው ሲሔዱ ሮምታ ብንተኩስ ተሁለቱ አንዱን ሌባ ገደልነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ሰኔ 5 ቀን 1936 ዓ.ም)
የሳምንቱ አጋጣሚ
እሁድ እለት አምባሳደር ቡና ቤት ቁጭ ብለን ሻይ ስንጠጣ አንድ የምናውቀው ሰው በመጠጥ ኃይል ተሸንፎ መዝጊያውን የከፈተ መስሎት ከመስተዋት ጋር ሲታገል በማየታችን በጣም አስቆናል፡፡
ሺመክት አለሙ
አዲስ ከተማ
……………
አንድ መጽሔትና ጋዜጣ ሻጭ ልጅ ለአንድ የውጭ ዜጋ ታይም መጽሔት ለመሸጥ በሚያሳየው ጊዜ የውጭ ሰው ሐውማች ብሎ ሲጠይቀው ልጁ ጣቱን እያሳየ ዋን ብር ዋን ስሙኒ ብሎ መለሰለት፡፡
(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 2 ቀን 1968 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጥር 7/2016