የምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ መምህርት የነበረችው ወጣቷ ቆንጆ ከአንድ ሰው ጋር ተዋወቀች። ትውውቃቸው አድጎና ጎልብቶ ለቁም ነገር በቃ። እነዚህ አቶ ዘመኑ ሰናይና ወይዘሮ የሺ ወርቁ የተባሉ ጥንዶች በትዳር ተጣምረው በልጅ ሲባረኩ መጀመሪያ እቅፋቸው ውስጥ የገባችው የዛሬዋ የሴቶች አምድ እንግዳችን ወይዘሮ ሳራ ዘመኑ ናት።
ወይዘሮ ሳራ ዘመኑ ዛሬ ለሆነችው ሁሉ የወላጆቻ እጅ እንዳለበት ትመሰክራለች። ወላጅነትን ከወላጆቿ ተምራ በጥሩ የልጅ አስተዳደግ ሁለት ልጆቿን አሳድጋ ለቁም ነገር ያበቃችው ይች ሴት፤ ከሕይወት ልምዷና ከስራ ገጠመኞቿ የተቀዱ ማንም ማንበብና መፃፍ የሚችል ሰው አንብቦ ሊረዳው የሚችለው ጤናማ የልጆች አስተዳደግን የተመለከተ መፅሀፍ ፅፋ ለአንባቢዎች አቅርባለች።
እንግዳችን ወይዘሮ ሳራ ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በናዝሬት ትምህርት ቤት። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በምስራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማረች። አስራ ሁለተኛ ክፍልን ተፈትና ጉዞ ወደ አሜሪካ ሀገር ሆነ። አሜሪካን ሀገር የነርሲንግ የትምህርት ዘርፍ ተማራ የተዋጣላት ባለሙያ ሆነች።
ከ25 ዓመታት በፊት የነርስነት ትምህርቷን ጨርሳ ነበር ወደ ስራ የገባችው። በነርሲንግ የተለያዩ ሕክምና ተቋማት ላይ የሰራች ሲሆነ አሁን ላይ በኮሚኒቲ ኮሌጅ ውስጥ ነርሲንግ ታስተምራለች። ቨርጂኒያ ኮሚኒቲ ኮሌጅ ውስጥ መምህርት፤ በሆስፒታል ሀኪም በመሆን የሀበሻ ኮሚኒቲ ውስጥ የተለያዩ ስራዎች ትሰራለች።
ባለትዳርና የሁለት ልጆቸ እናት የሆነችው ወይዘሮ ሳራ ዘመኑ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ትዳር ውስጥ መቆየቷን ትናገራለች። በትዳሯ ስኬታማ ልጆቿንም በስርዓት አሳድጋ የመጀመሪያ ልጇ የሕክምና ትምህርት ቤት (ሜዲካል እስኩል) የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ስትሆን ወንዱ ልጇም በዚህ ዓመት በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተመራቂ ተማሪ መሆኑን ትናገራለች።
እንደ ወይዘሮ ሳራ ገለፃ በውጭ ሀገር ሆኖ ልጅ ወልዶ ማሳደግ እጅግ ከባድ እንደሆነ ብዙዎች ያወራሉ። የትም ሀገር ቢሆን ማሕበረሰብ የራሱ የሆነ ስርዓትና ስነ ምግባር አለው። ይህ ማለት ሰው የሀገሩን ማንነት ሳይለቅ ራሱን ሆኖ በስርዓት ማሳደግ ሲሞክር ምንም አይነት ማስመሰል ስለማይቻል ልጆች በራሳቸው የሚተማመኑ የባሕል ግጭት የማይኖርባቸው ልጆች ይሆናሉ።
ወላጅነት ራስን መሆን ነው። ከባሕል ከወግ ከትናንት ማንነት ከራስ አስተዳደግም ጭምር በተቀመረ ልምድ ግብረ ገብንና ስርዓትን ማሳወቅ ልጆችን አታድርጉ የሚባሉትን ነገር በምክንያት ማስረዳት ተገቢ መሆኑን ነው ወይዘሮ ሳራ የምትናገረው።
እንደ ወይዘሮ ሳራ በራሱ የሚተማመን ልጅ ለማሳደግ ሁልጊዜ የምናደርገው ነገር አንድ አይነት የማይቀያየር መሆን አለበት። ይህም ማለት ሕግ ካወጣን ሁልጊዜ በዚያ ሕግ መመራት አለብን፤ አይሆንም ብለን የወሰነውን ነገር አይሆንም ነው። በተቻለ መጠን እናት እና አባት አንድ አይነት አቋም መያዝ አለባቸው። እናም ለልጆቻችን (consistency) ተከታታይነት ያለው አካሄድ መጠቀም በጣም አስፈላጊ ነው። እነሱም የሚፈልጉት ይህንኑ ነው።
ቤታችን ውስጥ ሕግ ያስፈልገናል። ልጆቹ የሚመሩበት በእኛ የወጣ እና ልጆቹ የሚከተሉት ሕግ:: ይኼ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ይኼ ለልጆች ውስጣዊ ደህንነት ይሰጣቸዋል። ራሳቸውን መምራት ስለማይችሉ ሕግ በእርግጥም ያስፈልጋቸዋል። ያ ሕግ ዛሬ የሚሰራ ነገ የሚሻር መሆን የለበትም፤ ልጆቹን ግራ ያገባቸዋል። ይህ በራስ መተማመናቸው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ታዲያ በዚህ ሕግ ላይ የተመሰረተ ጥሩ ግንኙነት ያስፈልገናል፤ ሕጉን ማከብራቸውን መከታተል ያስፈልጋል። ከእኛ ፍቃድ ውጪ ያንን ሕግ መሻር እንደማይቻል ማወቅ አለባቸው ትለናለች።
ስለእነሱ፤ ስለማንነታቸው ስንናገር አዎንታዊ (postive) መሆን አለበት:: ይህ ታዲያ ከውልደታቸው ከዳይፐር ቅያሬ ሰዓት ይጀመራል፤ የምንላቸውን ይሆናሉ፤ የምንላቸውን ነገር ልባቸው ውስጥ ይፅፋሉ፤ ያትማሉ፤ ምክንያቱም እኛ ነን ቅርባቸው። ከማንም በላይ የሚያምኑት የሚወዱት እኛን ነው። ለእራሳቸዉ ያላቸው አመለካከት፤ ራሳቸውን የሚያዩበትን መነፅር ጥሩ እንዲሆን፤ የምንመራቸውን ነገር አስበን በጣም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት በራስ መተማመናቸው እንዲጎለብት መሰረት ነው። ሌላም የውጪ ሰው አሉታዊ ነገር እንዲላቸው መፍቀድ የለብንም። አንድ ሰው የተናገረውን ዉስጣቸው ይዘው ራሳቸውን በዚያ መነፅር ሊያዩ ይችላሉ። ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን።
ልጆች ትችት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም፤ ለትችት አልደረሱም። ልጆችን ከተቸናቸው ያን ትችት ወይም ተቃርኖ በመፍራት መስራት የሚፈልጉትን ወይም መስራት ያለባቸውን አይሰሩም። ይልቁንስ መምራት፤ ትክክል የሆነውን እና ያልሆነውን ማስተማር፤ ማበረታታት፤ ትጋታቸውን ማድነቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህ ለልጆች በራስ መተማመን ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ ትልቁ ሀይል የወላጅ ነዉ። ልጆች እራሳቸውን የሚያዩበትን መነፅር መሰረቱን መጣል እና መቅረፅ ያስፈልጋል።
ይህም በተመሳሳይ መልኩ ከልጅነት መጀመር አለበት። በተለይ በልጅነት እድሜያቸው ሁሉንም እንፈልጋለን ለሚሉ ልጆች ሁለት ወይም ሶስት ነገር መርጦ የቱን ትፈልጋለህ (ትፈልጊያለሽ) ብሎ ማስመረጥ፤ ልብስ መግዛት ሊሆን ይችላል፤ ማድረግ የሚፈልጉት ነገር ሊሆን ይችላል፤ የቤት ውስጥ ስራ ማገዝ ሊሆን ይችላል፤ በሁሉም ሁኔታ ከማዘዝ ይልቅ ምርጫ እንዲኖራቸው ማስተማር፤ ይህ “እራሴ መምረጥ እችላለሁ” የሚል ስሜት ያጎለብትላቸዋል፤ በራስ መተማመናቸው ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል በማለት ታብራራለች።
̋በእኛ ቤት የተለያዩ አይነት የልጅ አሰተዳደጎችን ተከትለናል። ሁለታችን የተማርን ነን። ተሰደን መሄዳችንን ባንረሳውም የመጣንበት ሀገር ባሕል ማንነት ነግረን ሳይሆን ኖረን አሳይተናቸዋል። ከሄድንበት ሀገር ሰው አስተሳሰብ ጋር አስታርቀን እየኖርን ልጆችን ማሳደግ ችለናል። የኛ ባሕል የሚያሳፍር ያልሆነ የሚደብቅ ሳይሆን ተኮርቶበት አደባባይ የሚወጣ መሆኑን ነው ነግረን ያሳደግናቸው። ̋
ልጆቻችንን ሁሌ መመረቅ አንረሳም። አንደበታችን ምርቃት ብቻ ይሁን:: ከአፋችን አትረባም አንተስ አንቺስ እያልን የምንረግመው ከኛ ይራቅ:: ቃል ኃይል አለው:: ልጆች ከልጅነታቸው ለሌሎች ሰዎች እንዴት ክብርና ትህትና ማሳየት እንዳለባቸው የሚያሳይ ጥሩ ልምምድ ነው። ስለዚህ እኛ ልጆቻችንን በምርቃት ነው ያሳደግነው ምርቃቱም ሰርቷል ትላለች።
ልጆች የሰጠናቸውን የሰሙትን እጥፍ አድርገው መልሰው ይሰጡናል:: ስለዚህ እንዲመለስልን የምንፈልገውን ብቻ እንስጣቸው:: ያ ማለት በመልካም ስነምግባር ለማስተማር ከፈለግን መልካም እሴቶችን እየነገርንም እየኖርንም እናሳያቸው ብላለች።
በሕይወት ልምዷም ሆነ ከወላጆቿ ያገኘችውን የልጅ አስተዳደግ ሁሉም ይማርበት ዘንድ ̋ ጤናማ የልጆች አስተዳደግ ̋ የሚል ልጆችን እንደየ እድሜያቸው በአግባቡ በጥበብ ማሳደግ የሚል ሀሳብን የያዘ መፅሃፍ አበርክታለች። ልጆች ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ ወላጆች የሚያደርጉት ነገር ነው መጨረሻ ላይ ሰው ሲሆኑ የሚመራቸው የሚል ሀሳብ ያላት ወይዘሮ ሳራ ሰው ሁሉ የልጅነት ስርዓት ውጤት በመሆኑ ነገን ብሩህ ለማድረግ ትውልድ ላይ መስራት አማራጭ የማይኖረው መሆኑን ታስረዳለች።
ዓለምን ውብ አድርጎ ለመስራት በልጆቼ በኩል መሄድ ይገባል የምትለው ወይዘሮ ሳራ፤ ለልጆች የምትመች ዓለምን ለመፍጠር የራሴን ኃላፊነት መወጣት የሁሉም ማሕበረሰብ ደርሻ ነው በማለት ትገልጻለች። ህጻናት ከኛ አብራክ የወጡ እና ተመሳሳይ የሆኑ ቢመስለንም፣ ወላጆችም በአንድ አይነት የአስተዳደግ ዘዴ ለማሳደግ ብንሞክርም ልጆች የተለያየ ማንነትን ያዩ ናቸው የምትለው ሳራ፤ ልጆች ላይ የምናስተውለውን ልዩነት ሳንሰብራቸው ደግፈን እና አጎልብተን ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባናል ትላለች።
ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልጆች ትምህርት ተምረው እኛ በምንፈልገው መስክ ብቻ እንዲያድጉ ነው የምናደርጋቸው። ነገር ግን ልጆች ስሌላው የሕይወት ክፍል ሳያውቁ ያድጋሉ ያ ደግሞ ልጆች አድገው ከሕይወት ጋር በሚኖራቸው ግብግብ የስነልቦና ቀውስ ይፈጠርባቸዋል። ልጆቻችን ስናሳድግ አንዳንዴ እድሜያቸው የሚደርሱበት ኃላፊነት ምን ማለት እንደሆነ እንዴት እንደሚወጡት እየነገርናቸው ማሳደግ ይገባናል ትላለች። ልጆቻችን በሚሰማሩበት ቦታ ሁሉ እኩል አስተዋጽኦ እንዳላቸውም መንገር ያስፈልጋል። ሁላችንም ዓለም ያለን ሰዎች የራሳችን ተሰጥኦና ዝንባሌ አለን። በመሆኑም ልጆች ያላቸውን ተሰጥኦ እንዲያጎለብቱት በማድረግ በማንነታቸው ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ ማድረግ የወላጆች ኃላፊነት ነው።
ሁሉም ሰው በእኩል የኑሮ ደረጃ ላይ ባይኖርም፤ አንድ አይነት አስተሳሰብ ባያራምድም ልጁ መጥፎ እንዲሆንበት የሚፈልግ የለምና ወላጅነትን በጥበብ በማድረግ፤ የተፃፉ ልምዶችን በማንበብ፤ የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ ነገ ሀገርን እንደሀገር ለማስቀጠል የሚበቁ ብቁ ዜጎች ለማፍራት የእያንዳንዳችን ድርሻ የላቀ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባናል ትላለች።
በመጨረሻም ሕፃናት አይምሮ ብሩህ እና ፈጣን እንዲሆን ከምንመግባቸው ምግብ ባልተናነሰ መልኩ ሌሎች ማነቃቅያዎችን እና እንክብካቤዎችን ይፈልጋል ትለናለች። ሁሉም ሕፃናት ሲወለዱ ጂኒየስ የመሆን ብቃት ይዘው ነው የሚወለዱት። ሆኖም እያንዳንዱ የጭንቅላት ህዋስ ባለው ብቃት (potential) ልክ ካልተነቃቃ በልጁ አይምሮ ውስጥ ያሉት የነርቭ ግንኙነቶች (synapse) እየተወገዱ ወይም እየደከሙ ይሄዳሉ።
እነዚህ የነርቭ ግንኙነቶች (synapse) በጊዜ ከተነቃቁ ግን እያደጉ እየበለፀጉ ይሄዳሉ። በዚህም ሕፃኑ ባለ ብሩህ አይምሮ ባለቤት ይሆናል። በጣም የሚገርመው የልጆች አይምሮ አንድ አዋቂ ከሚያስበው እና ከሚያመላልሰው ሃሳብ በላይ ማስተናገድ እና ማከናወን ይችላል።
ለምሳሌ አዋቂ ከሆነ በኋላ የተለያዩ ቋንቋዎች መልመድ በጣም ይከብደናል ሕፃናት ግን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መልመድ መስማት ብሎም መናገር ይችላሉ። ስለዚህ ይሄንን ብሩህ አይምሮ ደሞ ማነቃቃት፣ መቅረፅ፣ ማዘጋጀት እና መስመር ማስያዝ የወላጆች እና የአሳዳጊዎች ኃላፊነት ነው።
ወላጆች አንድ ማስተዋል ያለባችሁ ነገር ልጆቻችሁ ሁሉ ሳይንቲስት ፓይለት ዶክተር ወይም ኢንጅነር መሆን አይጠበቅባቸውም። ምርጥ አርቲስት ምርጥ ሰዓሊ ወይም ምርጥ ባለሙያ መሆን በራሱ ትልቅ ስኬት ነው። በመሆኑመ ልጆቻችሁን ከሌሎች ልጆች ጋር ማነፃፀር የለባችሁም ከዛ ይልቅ የራሳቸውን ታለንት ወይም ተሰጦ እንዲከተሉ እና መንገድ እንዳይስቱ ብቻ መርዳት ያስፈልጋል ትላለች። ከወይዘሮ ሳራ በአብዛኛው ምክርና ትምህርትን ያዘለ ውይይታችንን በዚህ መልኩ አብቅተናል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥር 7/2016