
አዲስ አበባ፡- በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ የሚገኙ ባህላዊ ዕሴቶች ሀገር ጸንታ እንድትቆም ምክንያት ሆነዋል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።
‹‹ቤተሰብን መመስረት ሀገርን መገንባት ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ አንድ ሺህ ጥንዶች የተዳሩበት ሁለተኛው የሺህ ጋብቻ ካርኒቫልና ኤክስፖ ትናንት ተካሂዷል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንደገለጹት፤ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች ሀገር እስከዛሬ ጸንታ እንድትቆም ምክንያት ናቸው፡፡ ከነዚህ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች መካከል ጋብቻ አንዱ ነው፡፡
ማህበረሰብ ያለቤተሰብ ሊቆም አይችልም፤ ትዳር ቤተሰብንና ሀገርን ለማስተዳደር የሚያስችል ኃላፊነት የሚገኝበት በመሆኑ ጥንካሬን መጎናጸፍ የሚቻልበት ነው ብለዋል፡፡
ጋብቻ ቤተሰብንና የሀገራዊ ኃላፊነት ለመቀበል የሚያስችል የሽግግር ጊዜ ነው ያሉት አቶ ቀጄላ፤ ጋብቻ የሀገርንና የማህበረሰብ መሰረት ለማጽናት ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።
እንደ አቶ ቀጄላ ገለጻ፤ በተለይ እንዲህ በጀማ የሚደረግ ጋብቻ ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጎልበት እንዲሁም ባህልን ለማስተዋወቅ ድርሻ አለው፡፡
አቶ ቀጄላ አክለውም፤ በየግል የሚወጣ የተጋነነ ወጪ በመቀነስ ብሎም በቱሪዝም ዘርፍ ገቢ በማስገኘት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
መርሀ- ግብሩ ባህልን ከማጠናከር ጎን ለጎን የቋንቋ እድገትና የተለያዩ እውቀትና ልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚቻልበት እንደሆነም ነው አቶ ቀጄላ የገለጹት፡፡
በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትዳር ለመመስረት የሚቸገሩ ዜጎች ይኖራሉ ያሉት አቶ ቀጄላ፤ የሺህ ጋብቻ መርሀ- ግብር ይህንን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እንደ አቶ ቀጄላ ገለጻ፤ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት በቅንጅታዊ አሰራር ተጠቃሚ ለመሆንና የጋራ ግብ ለማሳካት ያግዛል፡፡ የሺህ ጋብቻ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ከሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ አንድ ሺህ ጥንዶች በባህላዊ አልባሣት፣ ጌጣጌጦች፣ በባህላዊ ጨዋታዎች፤ ጭፈራዎችና የተለያዩ ትዕይንቶች ደምቀው በጀማ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል።
መርሀ ግብሩ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ለመመዝገብ የሚችልበት ሁኔታ ለመፍጠር ከሁለት ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ድፎ ዳቦና ከ10 ሺህ በላይ ሲኒዎች በያዘ ረከቦት ቡና የማፍላት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በተጨማሪም ከ20 ሜትር በላይ ኬክና አንድ ሺህ ሴቶች ቡና የሚያፈሉበት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም