አዲስ አበባ፡– የህብረት ስራ ማህበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገታቸውና ውጤታማነታቸው እየጨመረ መሆኑን የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው ዓለም አቀፍ የህብረት ስራ ቀንን ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች በሀረር ከተማ ያከብራል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ዓለም አቀፉን የህብረት ስራ ቀን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት፣ የህብረት ስራ ማህበራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ ውጤታማነታቸውም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ማህበራቱ የአባላቶቻቸው ቁጥር በፈጣን ሁኔታ እያደገ ከመሆኑም በላይ ህብረተሰቡ ህብረት ስራ ማህበራት በትክክልም ይጠቅሙኛል፣ችግሬንም ይፈቱልኛል፣ማህበራዊና ቁሳዊ ችግሬንም ያስወግዳሉ የሚለውን አስተሳሰብ መያዙ ለእድገታቸው መጨመር እንደ ምክንያት እንደሚጠቀስ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩልም በህብረት ስራ ማህበር መደራጀት ከህብረተሰቡ ከራሱ ገፊ ሆኖ እየመጣ እንዳለ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በ2005 ዓ.ም ከ 30ሺ እስከ 40 ሺ የነበሩት ማህበራት ዛሬ ወደ 88ሺ ደርሰዋል፤ ከቁጥራቸው ባሻገርም የካፒታል አቅማቸው በዛው ልክ እድገትን እያሳየ ነው፤ ይህ ደግሞ በኢኮኖሚው ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ እያለ መምጣቱን የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በከተሞች አካባቢ የሚታየው የኑሮ ውድነት ሰው ሰራሽ የሆነና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው መሆኑን የሚያሳየው የህብረት ስራ ማህበራት ላይ ምንም ጭማሪ አለመታየቱ ነው፤ በአንጻሩ በአሁኑ ወቅት ማህበራቱ በቂ ምርት አለን ብለው ወደ ገበያው እየተቀላቀሉ ሲመጡ ምንም አዲስ ነገር ሳይመጠ አንዳንድ ሸቀጦች በከፍተኛ ሁኔታ የዋጋ መረጋጋት እየታየባቸው ነው።
«ህብረት ስራ ማህበራት ለፍትሀዊና ለዘላቂ ሰላም» በሚል መሪ ቃል በአገራችን ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓልም ባለፉት አመታት በዘርፉ ውጤታማ ስራን የሰሩትን ለማበረታታ ሌሎችም የእነሱን ፈለግ እንዲከተሉ ለማድረግና በዘርፉ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትን የእውቅና ሽልማት ለመስጠት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን አባላት፣ ከ 24 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያፈሩ ከ 88 ሺ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት ፣388 የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች እና 3 የህብረት ስራ ፌዴሬሽኖች ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
እፀገነት አክሊሉ