አዲስ አበባ፡- በከፍተኛ ደረጃ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆነውና በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳለው የሚታመነው የአዋሽ ተፋሰስ ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል ልዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተገለፀ።የደቡብ ግሎባል ባንክ ለተፈናቃዮችና ችግረኞች የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ብሄራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን እንዳስታወቁት፤ በአሁኑ ወቅት በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ለአደጋ ተጋልጠዋል።በተለይም ደግሞ በድርቅ፣ ጎርፍና እና ተያያዥ ችግሮች የተነሳ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለአደጋ የሚጎዱበት አጋጣሚ በመኖሩ ችግሩን ከወዲሁ ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ምዕራባዊ አዲስ አበባን ጨምሮ እስከ አዋሽ ተፋሰስ ድረስ ለጎርፍ የመጋለጥ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የገለፁት አቶ ዳመና፤ በአሁኑ ወቅትም ቢሆን በአዋሽ ተፋሰስ የስጋት ምልክቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።ቀጣናው በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይ ያለው ትርጉም የላቀ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም መንግስት አደጋው እንዳይከሰት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።በቀጣይ ደግሞ አደጋዎችን ለማቃለል የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም በሰው ሰራሽ ምክንያቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች ውስጥም አብዛኞቹ ወደቀያቸው መመለሳቸው አመል ክተው፤ በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ጣቢያ ያሉት ከአንድ ሚሊዮን እንደማይበልጡ አስገንዝ በዋል። ዜጎች ሙሉ ለሙሉ እስኪቋቋሙ ድረስም ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት 6020 እየተላከ ሲሆን የ40 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የደቡብ ግሎባል ባንከ ለተፈናቃዮችና ችግረኞች ይሰጥ ዘንድ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለብሄራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክቧል። በርክክቡ ወቅት የማርኬቲንግና ብራንድ ዲቨሎፕመንት ዋና ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳኛቸው አስናቀ ‹‹ድጋፉ ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት ጋር የሚያደርገው አንዱ ስራ ሲሆን በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር