* በቀን 40 የቀዶ ህክምናዎች ይሠጣል
ባህር ዳር፡- በቅርቡ በሶስት የምስራቅ አፍሪካ አገራት መሪዎች ተመርቆ ስራ የጀመረው በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሪፈር/ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ መላክ/ ህክምናን በማስቀረት በቀን እስከ 40 የቀዶ ህክምናዎች እየተሰጠበት እንደሚገኝ የሆስፒታሉ አስተዳደር ገለጸ።
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እያያ ምስጋና ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ ከተመረቀ ጀምሮ ከባህር ዳርና አካባቢው ሪፈር ተብለው ወደ አዲስ አበባ ይሄዱ የነበሩ ታካሚዎችን እንግልት አስቀርቷል። ለህብረተሰቡ ሰፊ አገልግሎት በመስጠት በቀን 40 የተለያዩ አይነት መካከለኛ እና ከባድ የቀዶ ህክምናዎች እየተከናወኑበት ይገኛል።
እንደ ዶክተር እያያ ገለጻ፤ የባህር ዳር ከተማ እና ዙሪያ ወረዳዎችን ነዋሪዎች የህክምና አገልግሎት በፈለገ ህይወት ሆስፒታል ብቻ ተወስኖ ስለነበረ ከፍተኛ የአገልግሎት መዳረስ ችግር ነበር። አሁን ግን ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስራ በመጀመሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ፈጣን የህክምና እርዳታ እያገኙ ይገኛል።
በተለይ በተኝቶ ታካሚ አገልግሎት ውስብስብ የቀዶ ህክምናን ጨምሮ ለተለያዩ ህክምናዎች ወደአዲስ አበባ ሪፈር የሚባሉ ሰዎች በመኖሪያ አካባቢያቸው አገልግሎቱን እያገኙ ነው። በሆስፒታሉ ላለው አገልግሎትም 500 ሐኪሞች በስራ ላይ ተሰማርተዋል። ከዚህ ውስጥ 102ቱ በስፔሻሊስት እና ድህረ ስፔሻሊስትነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ናቸው። 201ዱ ደግሞ በስፔሻላይዜሽን ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛል። የተቀሩት ደግሞ ጠቅላላ ሐኪም እና እጩ ሃኪሞች ናቸው።
‹‹የሆስፒታሉ ታካሚዎችን በቀን የማስተናገድ ትልቁ አቅሙ ሁለት ሺ ሰዎች ነው›› የሚሉት ዶክተር እያያ፣ አሁን ግን በቀን ሶስት መቶ ሰዎች ብቻ እየመጡለት መሆኑን ገልጸዋል። በአጠቃላይ ከጥር ጀምሮ 20 ሺ ሰዎችን ማስተናገድ ተችሏል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ሆስፒታሉ አዲስ እንደመሆኑ የበለጠ መተዋወቅ እና የተለያዩ ወረዳዎችን ነዋሪዎች የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ሲቻል በርካታ ታካሚዎችን ማግኘት ይቻላል። ሆስፒታሉ ሲመረቅ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች አገልግሎት ለመስጠት በመሆኑ ሆስፒታሉ በአገልግሎት አሰጣጡ የበለጠ ሲታወቅ የታካሚው ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ መጨመሩ አይቀርም።
በጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና በሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ሞሀመድ/ፋርማጆ/ ህዳር 1 ቀን 2011 በይፋ ተመርቆ ስራ ጀምሯል። እንደ ሆስፒታሉ መረጃ፤ 207 ሚሊዮን ብር የወጣበት ህክምና መስጫው 500 አልጋዎች እና ዘመኑ የሚጠይቃቸው የኩላሊት ፣የልብ እና የተለያዩ ምርመራዎችን የሚያከናውኑ መሳሪያዎች ባለቤት ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ጌትነት ተስፋማርያም