– ከ2005 ጀምሮ ያስመዘገበችው 7ሺ540 ምልክቶችን ነው
አዲስ አበባ፡– አገሪቱ የንግድ ምልክት ምዝገባ በማካሄድ ረገድ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኗን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።በአገሪቱ ውስጥ ከተመዘገቡ ከ18ሺ200 የንግድ ምልክቶች ውስጥ 59 ከመቶ በውጭ አገራት የተያዘ መሆኑንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ቦጋለ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ አገሪቱ የንግድ ምልክት ምዝገባ በማካሄድና ጥበቃ እንዲደረግለትም የምታደርገው ጥረት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።
የንግድ ምልክት አሰጣጥ 1978 ዓ.ም ጀምሮ በንግድ ሚኒስቴር ሥር የነበረ ሲሆን፤ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ስር በአዲስ መልክ የንግድ ምልክት ምዝገባ ተካሂዷል። እስካሁን ባለው የንግድ ምዝገባ ሂደትም 18ሺ200 የንግድ ምልክቶች ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን፤ 7ሺ540 ምልክቶች የአገር ውስጥ ሲሆኑ 59 ከመቶ ወይንም 10ሺ699 የንግድ ምልክቶች በውጭ አገር የተመዘገቡ ናቸው።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ የንግድ ስያሜ መያዝና የንግድ ምልክትን መያዝ ልዩነትን አለመረዳት ጭምር እንደሚስተዋል ገልፀዋል። በግንዛቤ ደረጃ በጎላ መልኩ የተሠራበት አይደለም። በመሆኑም እስካሁን ባለው ሂደት የውጭ ንግድ ምልክት ምዝገባ የላቀ ነው። ይሁንና ከባለፈው ዓመት ጀምሮ መሻሻሎች መኖራቸውን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪም የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት በሐዋሳ፣ ጅማ እና ባህርዳር ከተሞች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት በመምጣት የንግድ ምልክት ያለማስመዝገባቸው በአገሪቱ ምጣኔ ሃብት ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርና በዓለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት አስቸጋሪ የሚሆን ነው። በነፃ ገበያ ውድድር ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ሚና ያሳድራል። በተጨማሪም ተቋሙ በክህሎት የዳበረ ባለሙያና ለሥራው በቂ ትኩረት ማነስ ችግሩን አባብሶታል።
የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ ሁለቱን ብቻ የፈረመ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ትዕግስት፤ አልፎ አልፎ ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸውን ተቋማት የንግድ ምልክት የመጠቀም አዝማሚያ መኖሩን ገልፀዋል። ይሁንና ይህ የራስን ምርትና የንግድ ምልክት የኢትዮጵያ ምርቶች ጎልተው እንዳይወጡና በዓለም ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ተፅዕኖ ያሳድራል።
በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ይግባኝ ሰሚ የሆኑት ወይዘሪት እየሩሳሌም ተፈሪ በበኩላቸው፤ ከባለቤትነትና ከንግድ ምልክት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎች መኖራቸውን ጠቁመው በዚህ ዓመት ብቻ 60 መዝገቦች ላይ አቤቱታ ቀርቦ ለ46 ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ቀሪዎቹ እስከ ሐምሌ 14 ድረስ በቀጠሮ ላይ ናቸው። በዚህ ውስጥም የውጭ ተቋማት ቅሬታ መኖሩን አብራርተዋል።
ከኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት በተገኘው መረጃ፤ የንግድ ምልክት አንድ ድርጅት የሚሰጠው አገልግሎት ከሌላው የሚለይበት ምልክት ሲሆን፤ አንድ የንግድ ምልክት ከወጣ በኋላ እስከ ሰባት ዓመት መጠቀም ይቻላል። ከዚህን በኋላ በሦስት ወራት ውስጥ ያለቅጣት፣በቅጣት ደግሞ በስድስት ወራት በአጠቃላይ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የንግድ ምልክቱ መታደስ አለበት። በተጨማሪም አንድን የንግድ ምልክቶች እስከ ሦስት ዓመት ምንም ሳይሠራበት የተቀመጠ ከሆነ ውድቅ ይደረጋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር