* 521 ቢሊዮን ብር ከቀረጥ ነጻ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፡– ከቀረጥ ነጻ የገቡ ዕቃዎች ላልተፈቀደና ተገቢ ላልሆነ አካል ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የጉሙሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።2011ን ሳይጨምር ባለፉት 10 ዓመታት 521 ቢሊዮን ብር ከቀረጥ ነጻ የኢንቨስትመንት ፈቃዶች መሰጠቱንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በኮሚሽኑ የጉሙሩክ ህግ ተገዢነት ዘርፍ የጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አሸናፊ ባሳ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ላለፉት 10 ዓመታት ከቀረጥ ነጻ የገቡ ዕቃዎች ላልተፈቀደና ተገቢ ላልሆነ አካል ጥቅም ላይ እየዋለ እንደነበር በርካታ ማሳያዎች አሉ።ከቀረጥ ነጻ ገብተው ከታለመላቸው ዓላማ እየዋሉ ካሉት ዕቃዎች መካከል ተሽከርካሪዎችና የኮንስትራክሽን ዕቃዎች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።የቱሪዝም ዘርፉን ለማበረታታት ተብሎ የተፈቀደውን እድል ተጠቅመው አስገብተው ሌላ ስራ ላይ የሚያውሉ የቱሪዝም ድርጅቶች መኖራቸው ተደርሶባቸዋል።
በተመሳሳይ የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማበረታታት ተብሎ የተፈቀደውን መብት ተጠቅመው የኮንስትራክሽን ዕቃዎችና ማሽነሪዎችን አስገብተው ከታለመለት ዓላማ ውጭ የሚያውሉ መኖራቸውን በህብረተሰቡ ጥቆማ ተደርሶባቸዋል ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ይህም በኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደሩም በላይ ሀገሪቷ ማግኘት የነበረባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አሸናፊ ማብራሪያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ቀደም ባሉ ጊዜያት በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተፈቀዱትን ከቀረጥ ነጻ እድል ማስፈጸም ላይ ብቻ ትኩረት በማድረጉ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩትን መከላከል አልቻለም።በቅርቡ ጉሙሩክ ራሱን ችሎ ኮሚሽን ሆኖ እንደ አዲስ ከተዋቀረ ወዲህ ከቀረጥ ነጻ የተፈቀዱ መብቶች አጠቃቀም ዙሪያ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ አዲስ አሰራር ዘርግቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል። ከቀረጥ ነጻ መብቶች አጠቃቀም ክትትልና ቁጥጥር ቡድኖች በዋና መስሪያ ቤት እና በቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ቡድኖች ተቋቁመዋል፡፡
ቡድኖቹ በማዕከልና በየአካባቢው ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የተፈቀዱ መብቶች መረጃዎች የማደራጀት ስራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ያብራሩት አቶ አሸናፊ ፤ከሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ባለፉት 10 ዓመታት ለማን ምን ያህል ብር የሚገመት ምን አይነት ዕቃ ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ መብት ተሰጠው ? የሚለውን መረጃ የማደራጀት ስራው ሲጠናቀቅ መብቱን ተጠቅሞ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሰው ማን ነው የሚለውን የመለየት ስራ እየተሰራ ነው።ከታለመላቸው ዓላማ ዉጪ ያዋሉት እነ ማን ናቸው? የሚለውን መረጃዎች የማሰባሰብ ስራም እየተሰራ ነው።በወረቀት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ሲጠናቀቁ መሬት ላይ ወርዶ የመለየት ስራም ይሰራል፡፡
ከቀረጥ ነጻ አስገብተው ከታለመላቸው ዓላማ ዉጪ ባዋሉት ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ያብራሩት አቶ አሸናፊ፤ ያስገቡትን ተሽከርካሪ ለሌላ ዓላማ የሚያውሉት ላይ በተያዘበት ቀን ባለው የቀረጥ መጠን 50 በመቶ ቅጣትና ታክስ እንዲከፍሉ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
አቶ አሸናፊ እንደተናገሩት፤ መረጃ አደራጅቶ ያለመያዝ፤ አንዳንድ ኢንቨስተሮች ባስመዘገቡት ቦታ አለመገኘት እንዲሁም ከቀረጥ ነጻ እድልን ያለ አግባብ የተጠቀሙት ላይ ክስ ተመስርቶባቸው አስፈጻሚዎች ከቀረጥ ነጻ እድል ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ በነጻ መለቀቅ እየተወሰደ ላለው እርምጃ ተግዳሮት እየሆነ ነው።ሁሉም ህብረተሰብ ጥቆማ በማድረስ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
መላኩ ኤሮሴ