መቼም በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ ነውና ነገሩ ፤“ገና እንዴት አለፈ?” ይለናል የ1964ቱን የገና በዓል አከባበርን ለዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ሲተርክልን ∙ ∙ ∙ የበዓሉን ድምቀት ከነ ዶሮና ጠጁ ከትረካው ጋር በምናብ ትውስታ እያጣጣምን።
ከበዓሉ መንደር ወጣ ስንል ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገኙት ቤቶች በሙሉ አንድ አይነት ቀለም እንዲቀቡ ትዕዛዝ ወጥቷል። ውሻ ሰውን ነከሰ ማለቱ ቀርቶ፤ ውሻውን ነክሶ የተከሰሰው ግለሰብ ለፍርድ ቀርቧል። ከዚህ ላይ የጳውሎስ ኞኞን ደብዳቤ ጣል በማድረግ ሁሉም ከየፈርጁ ተሰናድተዋል።
ገና እንዴት አለፈ ?
ከእስክንድሪያ በመጣው ፍሬምናጦስ ምስክርነት ከ3ሺህ 133 ዓመተ ምሕረት ጀምሮ መከበር የጀመረውና በራሳችን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29 የሚውለው በዓለ ልደት በቀደምም አንድ አክሎ አልፏል።
….
በነብይ ከጌታ ዘንድ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች። ስሙንም አማኑኤል ይሉታል” የተባለው ይፈፀም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል ከሚለው የቅዱስ መጽሐፍ አገላለጽ የምንረዳው ይህንኑ ነው። ታስቧል፤ ይታሰባል።
ይህንን ክንውን ዞሮ መመልከቱ ደግ ነበር። ሆኖም “ደም በፈሰሰበት ዓውደ ዓመት ከቤት አትውጡ” የሚለው የአያቴና የእናቴ ልማድ በድምጽ ብልጫ አሸነፈ። ያም ሆነ ይህ፣ ገና እንዴት አለፈ?
“በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” የተባለለትን የድሮ ዘመን በትዝታነቱ ትተን ዛሬ ላይ እናተኩራለን። በዋዜማው የተለያዩ ትላልቅ ሆቴሎች፤ ሌሎችም እንዳቅማቸው ሙዚቃና ቡፌ ደግሰዋል። የዚያን ቀንም እንደወትሮው ብዙ ወጣቶች ድምፅ ማጉያ ጨብጠው ዕውቅ ድምፃውያንን ለመምሰል ሲውተረተሩ ተስተውሏል። ለየት ያለ ዝግጅት ካቀረቡት መሐል አንጋፋው ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አንዱ ነው። በዚያ የመገኘት ዕድሉ ገጥሞን ነበር። ከሁለት ሰዓት ያነሰ በፈጀው በዚሁ ድግስ ሶሎ ኮንሰርት፣ ያሬዳዊ ዝማሬ፣ የአማርኛ ግጥሞች፣ ባሕላዊ ሙዚቃ እና ፖፕ ሙዚቃዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይም የኅብረት ዝማሬዎች በአብዛኛው የልደትን በዓል የሚያመለክቱ፤ የበዓሉንም ትልቅነት የሚያበስሩ ነበሩ።
….
ይህንን በዚሁ አጠናቀን ስንወጣ በፆም የከረሙት የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ በተለይም የኦርቶዶክስ አማኞች ሌሊቱን ሙሉ በየቤተክርስቲያኑ በምሥጋና ያነጉ ሲሆን፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ቡራኬ ሰጥተዋል።
….
በ24 ሰዓት አገልግሎቱ የታወቀውና በእንግሊዝ ግዙፍ የዜና ማሰራጫ የሆነው ቢ-ቢ-ሲ “ኢትዮጵያን በትኩረት” በሚል ርዕስ ስለ ገና በዓል ሰፋ ያለ ዝግጅቱን በማለዳ ሞገድ አስደምጧል።
የገናን በዓል ካጀቡት ሌሎች አስገራሚ ትዕይንቶች መሐል አንዱ የጋዝ ሰልፍ ነበር። ከአራት ኪሎ ቶታል እስከ ቱሪስት ሆቴል የነበረው ወረፋ በወቅቱ አጠያይቋል። ከየቤቱ ሰው የቀረ አይመስልም። ምኒልክ አደባባይ ሞቢል ደርሰን አቶ ደረጀ ዓለማየሁ እንዳጫወቱን ከሆነ የጋዝ እጥረት የለም። በእርግጥ አንዳንድ ቦታዎች ስላለቀና ዓመት በዓልም ስለሆነ ግፊያው አይሎ ሊሆን ይችላል። .
ሌላው ያነጋገረ ጉዳይ ደን ነው። በዚህ ዓመት ጥድ አልተረፈም። “አንድ ዛፍ ከመቁረጥህ በፊት ሁለት ችግኞችን ትከል” ያለው የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት የመስቀል አደባባይን ንግድ አለማየቱም ደግ ነገር ነው። ለማንኛውም መምሰል አይከለከልም፤ ግን 4 በመቶ ቀርቶታል የተባለውን የሀገራችን የደን ይዞታ ወደ ነበረበት ከመመለስ ጨርሶ ማጥፋቱ ይቀላል ተባለ እንዴ?
መቼም በዓል ተተርኮ አያልቅም፤ ግን በዘንድሮው ገና የራሱ ዜማም በማትረፍ በይበልጥ ሳይደምቅ አልቀረም። በአምባሰል ሙዚቃና ቪዲዮ መደብር አሳታሚነት ገበያ ላይ የዋለው የመስፍን አበበ ካሴት እንዲህ ብሏል።
ብሩህ ሰማይ፤ ብሩህ ዕለት
መልካም በዓል፤ መልካም ልደት
ላከበረው የደስታ ቀን ይሁንለት
(አዲስ ዘመን ጥር 1 ቀን 1987 ዓ.ም)
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት ቤቶች ተመሳሳይ ቀለም እንዲቀቡ ትእዛዝ ተላለፈ
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙት መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድና የሌላም ዓይነት ተግባር ማከናወኛ መደብሮች ከዚህ ወር ጀምሮ ለአካባቢው የሚስማማ ቀለም እንዲቀቡ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ክፍሎች ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት ክቡር ሚኒስትር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ ናቸው።
……
የሚቀቡትም ቀለም አልባሌ ሳይሆን በየዓይነቱና በጥራቱ የተሻለ መሆን አለበት። የቀለሙንም ዓይነት በየክፍሉ የሚገኙ ማዘጋጃ ቤቶች ሊሰጡ ይችላሉ ሲል የማዘጋጃ ቤቱ የማስታወቂያና የሕዝብ ኅብረት ማስፋፊያ ክፍል በተለይ ለአዲስ ዘመን ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ በአየርና በከፍተኛ ሥፍራ ሆነው ሲያዩት አብዛኛውን ቤት ጣራው የቆሸሸ፤ ቀለሙ የዛገ ሆኖ ይታያል። ስለዚህ እንደ ባለቤቱ መራጭነት አረንጓዴ ወይም በቀይ ቡናማ ቀለም መቀባት አለበት የሚል ማሳሰቢያ ክቡር ከንቲባው መልዕክት ውስጥ ይገኛል። ያረጀውም ጣሪያ እንዲለወጥ የክፍሉ ባለሥልጣኖች በጥብቅ ታዝዘዋል።
(አዲስ ዘመን መስከረም 7 ቀን 1964ዓ.ም)
ሰው ውሻ ነክሶ ተቀጣ
ኒውተን ዲስተር የሚባል አንድ የሚዙሪ ተወላጅ ሹሺ የሚባል የጎረቤቱን ሰዎች የውሻ ቡችላ ነክሶ ተከሶ በውሻዋ ላይ ስለፈጸመው የነከሣ ወንጀል 3 መቶ ብር ተቀጥቷል።
በንክሻ ወንጀል ክሱን የመሠረተችው ሉሉ የምትባለዋ የውሻዋ ባለቤት፤ ለፍርድ ቤቱ ስታስረዳ፤ ፎስተር ለብዙ ጊዜ ጨዋ ጎረቤታችን ነበር፤ ከውሻዋም ጋር ይዋደዳሉ። ከጊዜ በኋላ የመጣበት የውሻ መንከስ ጠባይ ለእኛም ስለሚተርፍ ሠፈሩን ለቅቆ ይውጣልኝ በማለት አመለከተች።
(አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 1964 ዓ.ም)
አንድ ጥያቄ አለኝ
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*ጅብ የሚጮኸው ወደ መሬት አጎንብሶ ነው፤ ቀና ብሎ የጮኸ እንደሆን ሰማዩ ይሰነጠቃል የሚሉት እውነት ነው?
ፍሥሐ ማን ዱባለ (ከካራቆሬ)
-ውሸት ነው። እንኳን ሰማይ ሊሰነጥቅ ግድግዳም አይበሳ።
ወይዘሪት ሰብለ ካሣ
-እምይ ብዙ ሰው እንደ ድመት ጭራውን የሚቆላው የሚፈልጋት ጣፊያ እስኪጣልለት ድረስ ነው። ከዚያ በኋላ ይረሳዋልና እስከማይለወጥበት ጊዜ ድረስ ብቻ ማመን ነው።
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 26 ቀን 1963 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2016