አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ የሂሳብ ኦዲት ቦርድ አገሪቱን እስከ በ 2012 ዓ.ም ድረስ አለም አቀፍ ደረጃውን ወደ ጠበቀ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓት ለማስገባት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል በቂ ድጋፍ ከመንግስት አለማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በአለም ባንክና በሌሎች አለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የተጠናውን ጥናት መሰረት በማድረግ አገሪቱን ካለችበት የተበላሸ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓት ለማውጣትና አለማቀፍ ደረጃውን ወደጠበቀ ስርዓት ለማሸጋገር የተያዘው እቅድ ተፈፃሚ እየሆነ አይደለም።ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት መንግስት በቂ ድጋፍና ትኩረት መስጠት ያለመቻሉ ሲሆን ቦርዱ የተወሳሰበ ችግር ያለበት በመሆኑም በቀረው አንድ አመት ጊዜ ውስጥም እቅዱን ለማሳካት አዳጋች አድርጎበታል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የፋይናንስ ሪፖርት ጥናት የኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት አለም አቀፍ ደረጃውን ያልጠበቀ መሆኑና የሚላኩ ሪፖርቶችም ተዓማኒነት የጎደላቸው መሆኑን ተረጋግጧል።
በዚህም መሰረት መንግስት የተሰጠውን ምክረሃሳብ ተቀብሎ የፋይናንስ አዋጅ ከማውጣት ጀምሮ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓቱን የሚቆጣጠር ቦርድ እስከማቋቋም ድረስ የተለየዩ ስራዎች ሰርቷል።አሰራሩን ሊያዘምን የሚያስችል ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ ወደአለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ለመሸጋገር እቅድ ተነድፏል።ይሁንና ቦርዱ ከተቋቋመ በኋላ ስራውን ለማከናወን የሚያስችል ድጋፍ አላደ ረገም፤ በተለይም በሰው ሃይል ረገድ ቦርዱ ያለበትን ክፍተት ለመሙላት የተደረገ ጥረት የለም።
«መንግስት አዋጁን ከማውጣትና ቦርዱን ከማቋቋም ባለፈ የጉዳዩን አስፈላጊነት በሚገባ አልተረዳውም፤ በቂ ድጋፍም እያደረገለት አይደለም» ያሉት አቶ ጋሼ ፣ እስከዛሬ ድረስም ቦርዱ ብቻውን ሲታገል እንደነበር አመልክተዋል።በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ከተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ በየጊዜው መለዋወጣቸውና በአራት አመታት ጊዜ ውስጥም አመራሮቹ የተሰበሰቡት ሶስት ጊዜ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ፋይናንስ ሪፖርት አቅራቢ ድርጅቶች ስርዓቱ መዘመን ያለውን አገራዊ ፋይዳ በአግባቡ ያልተገነዘቡት መሆናቸው፤ አንዳንዶቹም ከግል ጥቅማቸው የተነሳ በነበረው ኋላቀር አሰራር እንዲቀጥል ስለሚሹ ተባባሪ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት ተቋሙን ለአራተኛ ጊዜ የማደራጀት ስራ ቢሰራም ካለበት ዘርፈ ብዙ ችግር የተነሳ የተያዘውን እቅድ ከግብ ለማድረስ አዳጋች እንደሚሆንበት ተናግረዋል።በተለይም መንግስት በቂ ትኩረት ያለመስጠቱ ተቋሙ ራሱ ቀጣይነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ « የተሟላ ግልፅና በቀላሉ ሊረዱት የሚችል የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ ስርዓት ለህዝብ ተጠቃሚነት» በሚል ርዕስ ትናንት በጌትፋም ሆቴል የግማሽ ቀን አውደ ጥናት አዘጋጅቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
ማህሌት አብዱል