የሚያነብ ትውልድ ሀገር ማጎልበት ላይ የዝሆንን ድርሻ ይወስዳል

አርሲ ካፈራቻቸው ውድ ልጆቿ መካከል አንዷ ናት። አርሲ ውስጥ በምትገኝ አቦምሳ በምትባል ትንሽዬ ከተማ ውስጥ ነበር የተወለደችው። መምህራን ከሆኑ ወላጆች የተወለደችው የዛሬ እንግዳችን በልጅነቷ የአስተማሪ ልጅ አርአያ መሆን አለበት በሚል መርህ ጎበዝ በመሆን ከፊት መስመር ተሰላፊ ነበረች።

ማክዳ ሁሴን አርሺ ትባላለች። በሙያዋ ነርስ ናት። ባለትዳርና የሶስት ሴት ልጆች እናት ስትሆን የልጆች መጽሀፍ ትጽፋለች። ኑሮዋን ያደረገችው በአሜሪካ የቨርጂኒያ ግዛት ነው። ሀገር ወዳድ የሆኑ እና ብቁ ዜጎችን ማፍራት የሚቻለው ልጆች ላይ በመስራት ነው የሚል ሀሳብ አላት። በንባብ የዳበረ አዕምሮ ትልቅ ዋጋ አለው የሚለው ሀሳብም በእጅጉ አትኩሮት የምትሰጠው ጉዳይ ነው። በቅርቡም ‹‹the world needs a uniquely happy you ›› መጽሀፍ የጻፈች ሲሆን ይህ መጽሀፍ ወደ አማርኛ ‹‹ የዓለም መብራቶች ›› በሚል ተተርጉሟል ። በዛሬው የሴቶች ገጻችን ስለጻፈችው የልጆች መጽሀፍ ፣ ስለልጆች አስተዳደግ እና የህይወት ልምዷን እንድታጋራን እንግዳችን አድርገናታል ።

አባቷ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ፤ እናቷ ደግሞ የሒሳብ መምህር ናቸው። የማክዳ ወላጆች መምህራን በመሆናቸው በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ስራቸውን ሲያከናውኑ ማክዳም ከእህትና ወንድሞቿ ጋር አብራ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተዘዋውራ ኖራለች። በአርሲ ክፍለ ሀገር ሳጉሬ የምትባል ከተማ ፣ በናዝሬት ከተማ ኑሯቸውን አድረገዋል። ማክዳም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በሀላባ ከጨረሰች በኋላም ወደ አዲስ አበባ መጡ። ማክዳ የጽሁፍ ዝንባሌዋ ከልጅነቷ ጀምሮ የነበረ ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተለያዩ ጽሁፎችን ትጽፋለች። ይህን የመጻፍ ዝንባሌዋን የተመለከቱት አባቷም ወደፊት የስነ-ጽሁፍ ሰው ልትሆን እንደምትችል ይነግሯት ነበር። የመጻፍ ክህሎቷም ጥሩ በመሆኑ በትምህርት ቤት ውስጥ ካሉ የቋንቋ መምህራኖቿ ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበራት ።

ማክዳ ወንድምና እህቶች የወላጆቻቸውን ፈለግ በመከተል ወደ መምህርነት ሙያ ሲያቀኑ ማክዳ ወደ ጤናው ዘርፍ የገባቸው ከሌላ አንድ እህቷ ጋር ነበር ። የነርሲንግ ትምህርት (አዋላጅ ነርስ )ለመማር ምክንያት የሆናት አጋጣሚ በልጅነቷ የምታስታውሰው ነበር ። በአሰላ ከተማ ውስጥ የሷ መኖሪያ እና የአሰላ ሆስፒታል ቅርብ ለቅርብ ናቸው። እናም በአሰላ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ነጭ ጋወናቸውና የልብሳቸው ጸዓዳነት ነርስ መሆንን እንድትመኝ አደረጋት። ማክዳም የምትፈልገውን ነገር አገኘች። የመሰናዶ ትምህርቷን ስትጨርስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የነርሲንግ ትምህርት ክፍልን ተቀላቀለች። ‹‹ አባቴ እንደሚለው በጊዜው ወደ ቋንቋ እና ወደ ስነ-ጽሁፍ ባደላም። ነገር ግን ይበልጥ መማር የምፈልገው ነርሲንግ ነበር ›› የምተለው ማክዳ ዩኒቨርሲቲ በነበረችበት ወቅትም የጽሁፍ ዝንባሌዋን አልተወችውም ።

ትምህርቷን ስትጨርስ በዚያው በጎንደር ከተማና ፣ ባደገችበት የሳጉሬ ጤና ጣቢያ ሰርታለች ። ከዛ በመቀጠል በመካከለኛው ምስራቅ ዱባይ የሰራች ሲሆን አሁን ወደ አሜሪካን ሀገር ተጉዛ ኑሮዋን በቨርጂኒያ በማድረግ በነርሲንግ ሙያ እያገለገለች ትገኛለች ። የነርሲንግ ሙያ ለማክዳ ከእናትነት ቀጥሎ ልገልጸው ቃላት ያጣሁለት ሙያ ነው ትላለች። ‹‹ የነርሲንግ ሙያ ማለት ሰው አንቺ ጋር የሚመጣው በደከመበት ባቃተው ሰዓት ነው ። ያ ደግሞ ትልቅ ኃላፊነት ነው። ››

ማክዳና ቤተሰቦቿ በተለያዩ ቦታ ተዘዋውረው ይኑሩ እንጂ የማክዳ እናት ግን ከሀገር ወጥቶ መኖርን የምትደግፍ አልነበረችም። ሁሉም ሰው በሀገሩ ሰርቶ መለወጥና ማደግ ይችላል የሚል አቋም ነበራት። ነገር ግን ማክዳ በስራ እና በትዳር ህይወቷ አጋጣሚ ከሀገር ወጥታ ስትኖር ከ13 አመት በላይ ሆኗታል። ማክዳ በስራዋ ነርስ ስትሆን የምትኖርበት ሀገር የስራ ባህል እና የኑሮ ሁኔታ ከልጆች ጋር በቂ ጊዜ ለማሳለፍ ምቹ አለመሆኑን ታነሳለች ። በመሆኑም ከቤታቸው ውጪ በስራ አለም የተሰማሩ ሴቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቤት መሆን ፣ አልያም ደግሞ ልጆቻቸውን ቤት ትተው ስራ ለመስራት የቱን መምረጥ እንዳለባቸው ሲወዛገቡ አስተውላለች። አንድ በስራ አለም ላይ ያለች ሴት የልጆች እናት ስትሆን የሚደርስባትን ውጥረትም በራሷ እንደተመለከተችው ትናገራለች ።

ማክዳ (The world needs a uniquely happy you ) የአማርኛ ትርጉሙ ‹‹ የዓለም መብራቶች ›› በሚል በቅርቡ ለንባብ ያበቃችውን የልጆች መጽሀፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆናት አጋጣሚ ሶስተኛ ልጇን ወልዳ በቤት ውስጥ አራስ በነበረች ጊዜ ከወሊድ በኋላ ያለው ድካም ልጅን መንከባከብ ይህ ሁሉ ተጨምሮ ደግሞ በወሊድ እረፍት ምክንያት ትታ የመጣችውን ስራ እንኳን በአራስ ቤት ውስጥ ሆና ለመስራት የተገደደችበት ወቅት ነበር። ታዲያ ይህን መጽሀፍ ስትጽፍ ልጇን ለማጥባት በምትነሳበት ወቅት ልጇ ተኝታ ከዚያም ድጋሚ ከእንቅልፏ እስከምትነሳ ድረስ መጽሀፏን መጻፍ ጀመረች ።

ማንኛዋም ሴት ኑሮዋና ፍላጎቷን ባማከለ መልኩ የምትፈልገውን ነገር ደስ እያላት ልታደርገው ይገባል። አንዲት ሴት በአሁን ሰዓት ስራም ሰርታ ገንዘብ ለማምጣት ቤት ውስጥ እናት ለመሆን ፣ ሚስት ለመሆን እነዚህ ሁሉ ሀላፊነቶች አሉባት ። የምትለው ማክዳ ይህን ሁሉ ለማድረግ በነበራት ውጥረት ውስጥ ያስተዋለችውን ነገር ጤናማ እናት ሆኖ ለመኖር እና ጥሩ ዜጋ ለማፍራት ማድረግ የምችለውን መገደብ ያስፈልጋል ። ‹‹ ልጆቿን ቤት ውስጥ ቁጭ ብላ ማሳደግ የምትፈልግ እናት ብትኖር ደስ እያላት እንድታደርገው ፣ ልጆችም ወልዳ ስራ መስራት ግድ የሚላት የህይወት መስመር ላይ የምትገኝ እናትም ደስ አያላት እንድትሰራው ትመክራለች።

መጽሀፉ ልጆችን በምን መልኩ ማሳደግ እንደሚገባ ፍላጎታቸውን እና ዝንባሌያቸውን እያየን በሚፈልጉት መልኩ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ እንዴት መንገድ መምራት ይገባል የሚለውን ያካትታል ። ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልጆች ትምህርት ተምረው እኛ በምንፈልገው መስክ ብቻ እንዲያድጉ ነው የምናደርጋቸው። ነገር ግን ልጆች ስሌላው የህይወት ክፍል ሳያውቁ ያድጋሉ ያ ደግሞ ልጆች አድገው ከህይወት ጋር በሚኖራቸው ግብግብ የስነልቦና ቀውስ ይፈጠርባቸዋል። ስለዚህም ትላለች ማክዳ ልጆቻችንን ስናሳድግ እንደየ እድሜያቸው የሚደርሱበትን ሀላፊነት ምንማለት እንደሆነ እንዴት እንደሚወጡት እየነገርናቸው ማሳደግ ይገባናል ትላለች። ልጆቻችን በሚሰማሩበት ቦታ ሁሉ እኩል አስተዋጽኦ እንዳላቸው መንገር ያስፈልጋል።

በመጽሀፉ ላይ ከሰባት የሚበልጡ የተለያየ ሙያላይ የተሰማሩ ገጸ-ባህሪያት ይገኛሉ ። ልጆች ያላቸውን ዝንባሌ ከልጅነታቸው ጀምሮ በማየት በልጅነታቸው ፈልገው የሚያደርጉትን ነገር በማጎልበት አድገውም በልጅነታቸው የሚፈልጉትን ነገር ሆነውት ማሳየት ነው ። ከዚያም እነዚህ ጓደኛማቾች አድገው በሙያቸው በማንነታቸው ሳናናቁ ተዋደውና ተከባብረው ዘልቋል ጓደኝነታቸው አንድነትን ለመሳየት በመጽሀፉ ላይ ተሞክሯል።

ከሀገር ከወጣች 13 ዓመት የሆናት ማክዳ በየእለት ተዕለት ኑሮዋ በአብዛኛው ማለት በሚቻል የምትጠቀመው እንግሊዘኛ ቋንቋን ነው። በመሆኑም መጽሀፏን በእንግሊዘኛ ቋንቋ እሷ ስትጽፈውና ስታዘጋጀው ወደ ሶስት ወር ገደማ የፈጀባት ሲሆን ዘጠኝ ወር ለሚሆን ጊዜ ደግሞ የአርትኦት ስራው ሲሰራ ቆይቶ ለንባብ ሊበቃ ችሏል። ለልጆች የሚያነቡት በመሆኑ በጥንቃቄ ዝግጅት ተደርጎበታል።

መጽሀፉ ልጆችን በምን መልኩ ማሳደግ እንደሚገባ ፍላጎታቸውን እና ዝንባሌያቸውን እያየን በሚፈልጉት መልኩ ራሳቸውን እንዲያሳድጉ እንዴት መንገድ ማሳየት ይገባል የሚለውን ያካትታል። መጽሀፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ ጥሩ ተቀባይነትንም አግኝቷል። ‹‹ እኔ ነኝ እንዴ የጻፍኩት እስከምል ድረስ በጣም ጥሩ ተቀባይነትን አግኝቻለሁ። በተለይ ደግሞ በዚያ ሀገር የሚኖሩ እናቶች ወደውታል ›› ህብረተሰቡ ሴቶች ላይ ጫን ይላል የምትለው ማክዳ ሴቶች መሆን የሚፈልጉትን የሚያበረታታ ስለሆነ ራሳቸውን በገጸ-ባህሪያቱ ውስጥ እንዳገኙትም ነግረዋታል። በቤታቸው ፣ በቤተ-መጽሀፍቶች በትምህርትቤቶች ውስጥ እንዲሁ እንዲቀመጥ መርጠውታል ። ስትል ያለውን ተቀባይነት በደስታ ትገልጻለች ። ማክዳ በህይወቷ የሚገጥሟት ፈተናዎች ወይንም አሉታዊ ነገሮችን ማንሳት ባትፈልግም መጽሀፏን በምትጽፍበት ወቅት ግን ጊዜ ያጥራት እንደነበር ትናገራለች ።

መጽሀፉ በአንባቢያን ዘንድ ተቀባይነትን ከማግኘት ባሻገር ሶስት ሽልማቶችን እንዲሁ አሸንፏል። (the world needs a uniquely happy you ) የእንግሊዘኛ ርዕሱ ሲሆን ‹‹ የዓለም መብራቶች ›› የአማርኛ ትርጉሙ ነው። ማክዳ ‹‹ የተሸለምኳቸው ሽልማቶችም ይበልጥ እንድጽፍ ያበረታቱኛል ›› ትላለች ። ( mama`s choice award ) ( በእናቶች ምርጫ አዋርድ ) የመጀመሪያ ሽልማት ሲሆን በሴቶች የሚመራ ድርጅት ሆኖ ላለፉት ሀያ አመታት ለቤተሰብ የሚሆኑ ስነ-ጽሁፎችን እየመረጠ ሽልማት ይሰጣል። የማክዳ መጽሀፍም የጎልድ ሲል አዋርድ ለማሸነፍ ችላለች ። ሁለተኛው ሽልማት ደግሞ (royal dragon fly book award )ስቶሪ ሞንስተርስ በሚል ዘርፍ አሸንፋለች ። ሶስተኛው ሽልማት ደግሞ በምርጥ ተነባቢ መጽሀፍ ሽልማት ተበርክቶላታል።

መጽሀፏን ጽፋ ለንባብ እንዳበቃችም በእውቁ የአማዞን ገበያ ላይ ለሽያጭ መቅረብ ችሏል ። በአማዞን ላይ እጅግ በጣም የታዋቂ ሰዎች መጽሀፍት ይገኛሉ። ማክዳም መጽሀፋን እዚህ ላ ለማስቀመጥና በአለምቀፍ ደረጃ ያሉ ወላጆች ጋር እናቶ፡ች ጋር እንዲደርስ በማሰብ ለአማዞን ብቁ ነው ለመባል የሚያስችሉ መመዘኛዎችን ካለፈች በኋላ መጽሀፏን ለማስቀመጥ ችላለች።

በመጽሀፉ ላይ የተካተቱት ገጸ-ባህሪያት የተለያየ አለም ላይ ያሉ ባህሎችን የሚወክሉ በመሆናቸው በራሳችን ቋንቋ ልጆቻችን ስለሌላው ዓለም ታሪክና ባህል ፣ ቴክኖሎጂን እንዲያውቁ ማድረግ እንችላለን በማለት ወደ አማርኛ ቋንቋ ተተርጉሟል። ከዚህም ባሻገር በሀገራችን ያለው የልጆች መጽሀፍ በቁጥር አናሳ በመሆኑ ሌሎችን ከመውቀስ ይልቅ የመፍትሄ አካል መሆንን መርጣለች ። የልጆች መጽሀፍትን የሚጽፉ ደራሲያን መጽሀፎቻቸውን ልጆችን በሚጋብዝ መልኩ እንዲያዘጋጁት ስትልም ሀሳቧን ታካፍላለች ።

በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተቀባይነትን ያገኘው መጽሀፍም ‹‹ የዓለም መብራቶች ›› በሚል ወደ አማርኛ ተተርጎሟል። መጽሀፉን ጋዜጠኛ አንተነህ ከበደ የተረጎመው ሲሆን \አርትኦት ስራውን ደግሞ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ሰርተውታል። በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይም አንድ ሜትር ከ30 ቁመት እና አንድ ሜትር ስፋት ያለውን አማርኛውንም እንግሊዘኛውንም መጽሀፍ በጋራ የያዘ ሲሆን ለልጆች በሚስብ መልኩ እንዲታያቸው ታስቦ የተዘጋጀ ነው። መጽሀፉ ልጆችን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ህጻናት ሊወዱት በሚችል መልኩ በቀለማት ያሸበረቀ ሆኖ የተዘጋጀ ነበር። ህጻናት የማንበብ ፍቅራቸው እንዲዳብር መጽኀፍን ደስባላቸው እና ደስተኛ በሆኑበት ጊዜ ብንሰጣቸው መጽሀፍን ደስ ከሚለው ስሜት ጋር ያያይዙታል በማለት ከመጽሀፍ ጋር ያላቸው ቁርኝት እንዲዳብርም ጭምር የታለመ ነበር ።

ማክዳ ለሚያነብ ሰው በሮች ሁሉ ክፍት ናቸው የሚል ሀሳብ አላት። በእስልምና እምነትም ቢሆን ነብዩ መሀመድ የተባሉት የመጀመሪያው ትእዛዝ አንብብ ነው ስትል ትገልጻለች ‹‹ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ሲባል አባባል ብቻ አይደለም ሙሉ ሰው ስለሚያደርግ ነው። ›› ትላለች ማክዳ በምትኖርበት ሀገር እና ተወልዳ ባደገችባት ኢትዮጵያ ንባብን የተመለከተ ሰፊ ልዩነት ስለመኖሩ ታነሳለች። መጽሀፎች በተለያዩ ቦታዎች በቀላሉ ይገኛሉ። በኛ ሀገር ግን ማንበብ ወደ ጎን የተተወ ይመስላል ስትል የታዘበችውን ትገልጻለች። ‹‹ ልጆች ማንበብን እንዲወዱ እና ባህላቸው እንዲያደርጉት ወላጆች አብረዋቸው ሊያነቡ ይገባል። ምክንያቱም ህጻናት የምንናገረውን ሳይሆን የምናደርገውን ነው የሚመለከቱት›› ትላለለች። ልጆች የሚያድጉበት መንገድ እና ሳይንስ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀያየረ ነው የምትለው ማክዳ ልጆቿን ለማሳደግ የምትኖርበትን ሀገር የልጅ አስተዳደግ ባህል መማር ማወቅ እና ልጆቿን በዛ መንገድ ከራሷ አስተዳደግና ባህል ጋር አጣምራ ታሳድጋለች ። ባለንበት ዘመን የተለያዩ ባለሙያዎች ባጠኑት ጥናት ሰዎች ህጻናት በእናታቸው ማህጸን ሳሉ ከአባት ወር ጀምሮ ድምጽን ይሰማሉ የሚል ነው። ማክዳም ልጆቿ መጽሀፍ ማንበብን ለምዳቸው እንዲያደርጉ ከእርግዝና ጊዜዋ ጀምሮ ይህንን ታደርግ እንደነበር ታስታውሳለች።

በቅድሚያ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተጽፎ መጽሀፍ ወደ አማርኛ የተተረጎመው የማክዳ መጽሀፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለአንባቢያን ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል። በትግርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋ የትርጉም ስራው ያለቀ ሲሆን በሶማልኛ ፣ በአፋርኛ እና ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም ለሚፈልጉ ሰዎች ማክዳ ጥሪዋን ታቀርባለች ።

‹‹ ለመስራት የደከምኩባቸው በቃኝ ያልኩባቸው ጊዜያት ነበሩ ነገር ግን በስራዬ የሚያግዘኝ የትዳር አጋር ተሰጥቶኛል ›› የምትለው ማክዳ እናቶች የምናበረክተው ነገር ሁላችንም ጋር አለ ‹‹ የውሀ ጠብታም ብትሆን ዛሬ ላይ የምናደርገው ነገር ነገ ለልጆቻችን ስለሚጠቅም ዝም አትበሉ የሚያነብ ትውልድ ሀገር ማጎልበት ላይ የዝሆንን ድርሻ ይወስዳል። ›› የምትለው ማክዳ ማንበብ በአዕምሮ እድገት ላይ በቤተሰብ ፍቅር ላይ ፣ በሀገር ሰላም መሆን ላይ ትልቅ ድርሻ አለው። ስትል ትገልጻለች ። ስለዚህም ልጆቻችን እንዲያነቡ በማድረግ ነገም እንዳንወቅሳቸው እኛም እንዳናለቅስ የሚያነብ ዜጋ እንድንፈጥር አብረን እንስራ የሚል መልእክቷን ታስተላልፋለች።

ማክዳ ከትዳር አጋሯ ዶክተር ኢስማኤል ኢድሪስ ዩሱፍ በትዳር 20 አመት ቆይተዋል። ሶስት ሴት ልጆችንም አፍርተዋል። በእነዚህ ጊዜያት ዘመም ስል ቀና እያደረገ በህይወቴ ትልቅ ድርሻ አለውና ክብር ይገባዋል ትላለች። በሀገር ውስጥ የነበረውን የመጽሀፍ ምርቃት ያማረ እንዲሆን የተባበሯትን ፣ መጽሀፉን በጥንቃቄ በማተም ፓክ ፐርፌክት ፓኬጂንግ እና ፕሪንቲንግ እንዲሁ አመስግናለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2016

Recommended For You